የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪ ቢልለኔ ሥዩም ለጋዜጠኞች በላኩት መልዕክት ‘ወይዘሮ’ ወይም ‘ወይዘሪት’ የሚለው ቅድመ ቅጥያ ከሥማቸው በፊት አስፈላጊ አለመሆኑን መግለጻቸው ያላስደሰታቸው ግለሰቦች የማኅበራዊ አውታሮች መወያያ አድርገዋቸው ነበር። ቤተልሔም ነጋሽ ይህንን ተንተርሰው ባቀረቡልን መጣጥፍ፥ የመረጡትን መሆን የግለሰቦች ምርጫ ሲሆን፣ ምርጫቸውን ማክበር ደግሞ የሌሎች ግዴታ ነው በማለት ጽፈዋል።
ባለፉት ሳምንታት የነበረውን “የወይዘሮ”፣ “ወይዘሪት” ውዝግብ ተከትሎ አንድ ወዳጄ በፌስቡክ የውስጥ መልዕክት መላኪያ አንድ ጥያቄ ላከልኝ። ጥያቄው ‘የፕሬስ ሴክሪታሪዋን ወይዘሪት ወይም ወይዘሮ መባል ባለመፈለግ ለጋዜጠኞች “አትቸገሩ፣ ዝም ብላችሁ በስሜ ብቻ ጥሩኝ” ማለታቸውን በሚመለከት ምን ታስቢለሽ? እንደ አንዲት ኢትዮጵያዊ ሴት እንዲህ ማለትስ ትችላለች ወይ?’ የሚል ነበር። የወዳጄ ጥያቄ በየማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛው የነበረውን የልክ “ነች”፣ “አይደለችም” ክርክር አንድ ጎን የሚሳይ ነው። ይህን ያህል አጀንዳ ጠፋ ወይ እስኪባል በሁሉም ዋና ዋና የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ወሬው ይኸው ነበር።
ላይ ላዩን ሲታይ ጉዳዩ እንደሚታሰበው ቀላልና የሥም ጥሪ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ምናልባት በአደባባይ፣ በሕዝቡ በተለይ ለመረጃ ቅርብ በሆነው ማኅበረሰብ ዘንድ አዲስ ቢመስልም ጨርሶ አዲስ ጉዳይ አይደለም። በበኩሌ የሴት መብትና ጉዳይ ይመለከተኛል በምንለው ሴቶች ዘንድ ጉዳዩ ከመታወቅ አልፎ ውይይት የተደረገበት፣ ምናልባትም የተሻለ አቻ ቃል በማጣት ‘እንስታዊነት’ የሚባለው ፌሚኒዝም አቀንቃኝ በምንባለው ዘንድ ቢስተካከሉ ብለን ከምናስባቸው ጉዳዮች እንደ አንድ ሊወሰድ የሚችል ነው። በወንዶች የሥም ጥሪ ላይ የጋብቻ ሁኔታቸው ተለይቶ እንዲጠራ በማይጠየቅበት ሁኔታ ሴቶች ያገቡ ወይም ያላገቡ መሆናቸውን የሚያሳይ ቅጥል ከሥማቸው በፊት ቀድሞ መጠሪያ እንዲሆናቸው ለምን ይገደዳሉ? ከእኩልነት አንፃርስ አንዱ ፆታ እንዲያደርግ የማይጠየቀውን ሌላው እንዲያደርግ ማስገደድ ትክክል ነው ወይ? የሚለው ቢያንስ እርስ በርሳችን ያነሳነው፣ ከዚያም አልፎ ‘ሴታዊት’ የተሰኘችው ተቋም ሁለቱን ያጣመረ፣ ለሁለቱም የሚሆን “ወይዝ “ የሚል ቃል እንጠቀም ብላ እስከማቅረብ ደርሳ እንደደነበር በአካባቢው ያለን እናውቃለን።
ይህ ጉዳይ ርዕስ ሆኖ ሲነሳ በዋናነት መታወቅ ያለበት ወይም መረሳት የሌለበት ሌላው ጉዳይ ማኅበረሰቡ ለትዳር የሚሰጠው አክብሮት ያላገቡ ሴቶችን ያልተሟሉ ወይም ምንም በሥራና በሙያ የላቁ ቢሆኑ የሆነ ጉድለት ያለባቸው እንደሆኑ አድርጎ የማየት አባዜ በስፋት ያለ መሆኑ ነው። ከሥም ጥሪው በስተጀርባ ያለውም የሴቶችን የትዳር ሁኔታ ለማወቅ የመፈለግ በዚያም ላይ ተመሥርቶ ደረጃ የማውጣት፣ ቦታ የመደልደል ሲቀጥልም ፍርድ የማኖር አዝማሚያ ነው።
በአጠቃላይ ሲታይም ሴቶችን የፈለጉትን እንዲሆኑ መተው – ለማኅበረሰባችን የማይቻል ይመስላል። ከመጽሐፍ ቅዱስ እስከ ቁርዓን እና ከሰባኪ እስከ ሃይማኖት አስተማሪና “ተርጓሚ” እንዲሁም ራሱን “ዐቃቤ ባሕል” አድርጎ እስከሾመ አውቃለሁ ባይ ሴቶች ‘እንዲህ ነው መሆን ያለባቸው’፣ ‘አይ! እንዲያ ነው’ በሚል መሥመር አሥምሮ ከመሥመሩ ወዲያ እንዲቆዩለት የሚወተውት ብዙ ነው። እንዳለመታደል ሆኖ በብዙዎች ሃይማኖትና እምነት ዘንድ ለሴቶች የሚሰጠው ሥፍራ የአናሳነት፣ የተገዥነት፣ በወንድ ጥላ ሥር የመዋል ነው። በሴቶች መብቶች ተሟጋቾች በተለይም በእንስታዊነት ዘንድ ሃይማኖት የወንዶችን የበላይነት ለማስቀጠል እንደ አንድ መሣሪያ በማገልገል ላይ ያለ እንደሆነ ይጠቀሳል።
“የእኔ አውቅልሽ” ፖለቲካ
ማኅበረሰባችን የግለሰብ ነጻነትን የማያከብር፣ ሰዎች እንዲህ ነው መሆን ያለባቸው አልያም ‘እንዲህ ቢሆኑ፣ እንዲያ ቢያስቡ፣ እንዲህ ቢያደርጉ ይሻላል’ በሚለው ላይ ጠንካራ አቋም ያለው ነው ለማለት ይቻላል። የፖለቲካ ምኅዳሩን በመግባባት ሳይሆን በጥላቻና በመከፋፈል ላይ የተመሠረተ የሚያደርገውም ይኸው ‘የእኔ አውቅልሃለሁ፣ እኔ ልወስንልህ’ አባዜ እና ከእኔ ሐሳብ ወዲያ ላሳር፣ የሌላው ሐሳብ ሁሉ አልባሌ ነው የሚል በሽታ ነው። ይህ ለአጠቃላዩ ማኅበረሰብ ከሞላ ጎደል ቢሠራም፣ በሴቶች ላይ እጅግ ይበረታል። ከአለባበስ እስከ ፀጉር ቁርጥና የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ከምዕራባውያን ተውሶ፣ እነሱን መጥቀስ እንደ አዋቂነት ተቆጥሮ ሳለ የሴቶች እኩልነት ሲባል የምዕራባውያን፣ በሥሜ ጥሩኝ ሲባል ባሕል አፍራሽ የሚል ቅጥያ ይለጠፋል።
በጎዳና ሲሔዱ ከመጎንተል እስከ ልጆች የማሳደጉን፣ በውጪም በቤትም ያለውን ሥራ የመሥራቱንና የመምራቱን ኃላፊነት እስከመስጠት፥ ሴቶች ለወንዶች መገልገያና ረዳት አድርገው የተፈጠሩ፣ የጋራ መገልገያ የሆኑ የሚያስመስሉ ብዙ የመብት ጥሰቶችና ሸክሞችን በሴቶች ትከሻ ላይ አድርጎ የመኖር ልማዶች ማኅበረሰባችን ተክኖበታል። ያንን ልማድ የሚነኩ የሚመስሉ፣ የአባዊ ስርዓቱን ምሰሦ ገፋ የሚያደርጉ ሐሳቦች ሲመጡ ድንጋጤ ይፈጠራል።
ዛሬ “ወይዘሮ/ሪት” አትበሉኝ ያሉ፣ ነገ ትዳር አያስፈልገኝም ቢሉስ? ትንሽ ቆይተው ባል ቤት ውስጥ ሚስቱን ሥራ ማገዝ አለበት ቢሉስ? የሚል ሐሳብ ሊመጣ ይችላል። በአጠቃላይ ወንዶች በማኅበረሰቡ የላይኛውን ቦታና አብዛኛውን ኃይል/ሥልጣን እንደመያዛቸው ያንን ሥልጣን መነጠቅን ወይም ማጋራትን ላይፈልጉ ይችላሉ።
ሴቶችን ለመጨቆን የመፈለግ፣ አጥር አጥሮ ለማስቀመጥ የመሞከር፣ ከአለባበስ እስከ የሕይወት ምርጫ በፈቀድንላችሁ ብቻ ዋሉ ከዚህ አትለፉ የማለት አዝማሚያ ቦታን ላለማስለቀቅ የሚደረግ፣ ከላይ የገለጽነው ድንጋጤ እንዳይመጣ የመከላከል ዘመቻ ነው። የዚህ ዘመቻ አጋፋሪ ቡድን ሴት እናት ናት፣ ሚስት ናት፣ ባሏን ሠርታ ታብላ፣ ቤት ውላ ልጅ ታሳድግ፣ የተፈጠረችው ለዚህ ዓላማ ነው፤ በአጠቃላይ ያለልጅና ትዳር ባዶ ናት ይላል።
በሴቶች ሕይወት ላይ በእነሱ ፋንታ ለመወሰን በመጣሩ በኩል የብዙኃን መገናኛው አጋፋሪነት ሳይረሳ በዚህ ቡድን ራሳችን ሴቶችም አለንበት። ለሴቶች መብት እንቆረቆራለን፣ ፌሚኒስት ነን የምንለው በበኩላችን ሴት ትዳሬ፣ ቤቴ፣ ልጆቼ ብላ ቤት ብትውል፣ ብቻዋን የቤቱን ኃላፊነት ብትሸከም፣ ቀንበሯ ይከብደናል። ዞረን ብናየው ‘ፌሚኒዝም’ ክልከላ፣ ገደብና አድልዎን መቃወም የሆነውን ያህል የፈለጉትን የመሆን “ምርጫ” አቀንቃኝም ጭምር ነው። ስለዚህ ለሁለቱም ወገኖች የምንለው ሴቶች የሚፈልጉትን እንዲሆኑ ለራሳቸው በተለይ ለግለሰቦቹ እንተወው፣ የመረጡትን ሲሆኑ ምርጫቸውን ማክበርም ሥልጣኔ፣ የእነሱንም መብት መረጋገጥ መፈለግ መሆኑን ልንረዳ ይገባል።
ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011