ሕግ ቢኖርም ብልሃቱን ማጥበቅ ያዋጣል

0
571

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

በተለያየ የሥራ አጋጣሚ በአንድም በሌላም በኩል ዕውቅና እና ዝና ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት ዕድሉ ነበረኝ። እነኚህ ሴቶች ሰብሰብ ብለው በተገናኙበት አጋጣሚ ሴቶችን የተመለከተ ጉዳይ ሲነሳ፤ ሕግጋት መጥበቅ እንዳለባቸው፣ ቅድሚያ ለሴቶች በስፋት መሰጠት እንዳለበት፣ ጥቃት እንዲቆም ምን ይደረግ ወዘተ እያሉ ይነጋገራሉ።
ንግግራቸው ሲጠቃለል፤ ወንዶች ማድረግ ስለሌለባቸው እንዲሁም መንግሥት ሊያደርግ ስለሚገባው ነገር ነው የሚሆነው። ለሴቶች የሚተላለፈው መልዕክት በጣም ትንሽ ነው። ልብ ብላችሁ ከሆነ! የሴቶች ቀንን ሰብሰብ ብለው የሚያስቡትና የሚያከብሩት እነማን ናቸው? ሴቶች። የሚመካከሩት ስለምንድን ነው? «የሴቶች ጥቃት እንዴት ይቁም!» እያሉ። መሰባሰቡ ከፍቶ አይደለም፤ ግን ጠብ የሚል መፍትሄ የሚቀርብበት አለመሆኑ ያበሳጫል።
ታድያ እነዛ ሴቶች፤ «እርሷስ ምን ታደርግ?» በሚለው ላይ ብዙ አስተያየት ሲሰጡ አይሰማም። አስተያየት ካላቸውም ከ«በርትታ ትማር» እና «ራሷን ትጠብቅ» የዘለለ አይደለም። ገና ብዙ ግንዛቤን በሚፈልግ ማኅበረሰብ ውስጥ ይህም ሆነ በመንግሥት የሚደረግ የሕግ ማሻሻያ ብቻውን ያለውን ችግር ሊቀርፍ አይችልም።
ተፈጥሮ ባታደላም፤ ግን ለሁሉም ሰው ለእያንዳንዱ የተለያየ የተፈጥሮ ፀጋ ትሰጣለች። ሴት ልጅም /በአብዛኛው/ የራሷ የሆነ በተፈጥሮ የታደለችው ጸጋ አለ፤ ይህም ብልሃቷ ነው። ብዙ ታሪኮችም ሆኑ አፈ-ታሪኮች የሴቶችን ብልሃት በየዘመኑ አሳይተውናል። እናም! በርትቶ ከመማርና ራስን ከመጠበቅ ባለፈ፤ ብልህ ትሁን የሚል ሐሳብም ሊያክሉ ይገባል።
«ሕግ ጥፋት ከተፈጸመ በኋላ ነው የሚደርሰው» ይባላል። በእርግጥ አንዱ ላይ ተግባራዊ የሆነ ሕግ ሌላውን የሚያስተምር እንደሚሆንና፤ በጊዜ ሒደትም ጥፋት እየቀነሰ እንደሚሄድ ይታወቃል። ለዚህም የሴቶችን መብት የሚያስከብር፤ በደል አድራጊዎቹንም ደኅና አድርጎ የሚቀጣ ሕግ እንዲኖሩ ሁላችንም እንፈልጋለን።
ያ እስኪሆንስ? ከአስከፊ ጥቃት ያመለጡ ሴቶች የሉም? በውሳኔያቸው ሊደርስባቸው ከሚችል ፈተና የተረፉስ አይገኙም? መንገድ ላይ የሚለክፏቸውን ጎረምሶች ማሸነፍና ዝም ማሰኘት የቻሉስ? በብልሃት አስከፊ ጊዜያትን የተሻገሩ ሴቶች የሉም? አሉ። የእነዚህ ሴቶች ታሪክ መነገር አለበት። አንዲት ሴት ትንሽ ከሚመስለው ለከፋ ጀምሮ የትኛውም ጥቃት ሲቃጣባት፤ ቀድማ ወደ ሐሳቧ «በሕግ እፋረዳለሁ!» ብላ አይደለም የምታስበው፤ ሊደርስባተ ካለው ችግር ግን በብልሃት ልታመልጥ ትችላለች።
እናም አብሯት ያለውን ብልሃቷን እንድትጠቀም፤ ችግር ቢፈጠር እንኳ እንዴት ማምለጥ እንደምትችል ማወቅ አለባት። በተፈጥሮ የታደለችውን ጥበብ ባላት አቅም ሁሉ እንድትጠቀምም መንገሩ ያስፈልጋል። ይህ በሁሉም መንገድ ላይሠራ ይችላል፤ ግን ለሰው ልጆች ሁሉ የተሻለ ዘመን መጥቶ ጥቃት የሚቀንስበት አልያም የማይኖርበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ብልሃቱን መያዙ ያዋጣል።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here