6 አዳዲስ የመስኖ ግድብ ግንባታዎችን ሊጀምሩ ነው

0
503

መንግሥት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንፎርሜሽን እቅድ ዘመን አዳዲስ የሚጀመሩ ፕሮጀክቶች አይኖሩም ብሎ የነበረ ቢሆንም፣ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስቴር ስድስት አዳዲስ የመስኖ ግድብ ግንባታዎችን ለመጀመር እንደተዘጋጀ ታወቀ።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶችን አትጀምርም ተብሎ በጠቅላይ ሚንስትሩ ጭምር ቢገለፅም የወንዝ አገናኞች (‹ሪቨር ኮሊደሮስ›) ለማልማት በሚል ከመንግሥት በጀት ተፈቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ይገነባሉ የተባሉት ስድስቱ አዳዲስ ግድቦች በአጠቃላይ ከ44 ሺሕ ሄክታር በላይ መሬትን በመስኖ ያለማሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ግድቦቹ ያላቸው ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ በደንብ ተጠንቶ የቦታ መረጣ እንደተደረገም ታውቋል።
ከሚገነቡት ስድስት ግድቦች መካከል አራቱ ማለትም ካዛ፣ ጉደር፣ ጨልቸልና ብላቴ ግድቦች ዋና ግድቦች ሲሆኑ የተቀሩት ሁለቱ የርብና ወልመል ግድቦች ደግሞ ከዋናው ግድብ የመጥለፊያ ግድቦች እንደሚሆኑ ታውቋል። እነዚህን ግድቦች ለመገንባት የሚያስፈልገው የቦታ ዝግጅት ከክልል መንግሥታት ጋር በመነጋገር እንደተዘጋጀም ሚንስቴሩ አስታውቋል። ከአዲሶቹ ግድቦች ሦስቱ በኦሮሚያ ሲገነቡ ቀሪ ሦስቱ በአማራ፣ ትግራይና ደቡብ ክልል እንደሚገነቡም ታውቋል።
በሚኒስቴሩ የመስኖና ተፋሰስ ዳይሬክተር ሰለሞን ቸሬ እንደተናገሩት አዲስ የሚገነቡት የመስኖ ግድቦች የጥናትና የዲዛይን ሥራቸው ከተጠናቀቀ ረዘም ያለ ጊዜን አስቆጥረዋል። ፕሮጀክቶቹ መሠረታዊ የሚባል ለውጥ ስለማያስፈልጋቸው መስተካከል ያለባቸውን ጥቃቅን ጉዳዮች የግድቦቹ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ ማድረግ ይቻላልም ብለዋል።
ሚኒስቴሩ አዲስ ለሚገነቡት ግድቦች ግንባታና ለወጣቶች የመስኖ እርሻ ልማት የሚሆን ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር መድቦ ወደ ተግባር ለመግባት ሒደት ላይ እንዳለም ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የመስኖ ግድቦቹ ከተሠሩ በኋላ በመስኖ የሚለማው መሬት ባለመዘጋጀቱ የተነሳ ግድቦቹ ያለአገልግሎት ለረዥም ጊዜ ይቆያሉ ያሉት ሰለሞን ከግድቦቹ እኩል የመስኖ አውታሮቹ ግንባታም ሊታሰብበት እንደሚገባ ሙያዊ አስተያየታቸውን ያክላሉ።
ከዚህ ቀደም የተጀመሩ የመስኖ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክቶች ከሞላ ጎደል እየተጠናቀቁ ነው የሚለው ሚንስትሩ በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው የዘገየው የመገጭ ግድብን አስመልክቶ፤ በመጀመርያ ዲዛይኑ ሲሠራ የግድቡ ውኃ የማስወጫ ቦታ ላይ መሬቱ ውኃውን የመሸከም አቅም አለው ተብሎ ቢታሰብም ቦታው ተቆፍሮ ሲታይ ግን የመሸከም አቅም እንዳሌለው በመታወቁ የዲዛይን ለውጥ በማድረግ በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ እንዳለ አሳውቋል። አሁን ላይ ግንባታው 55 በመቶ ደርሷል የተባለ ሲሆን በ2013 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ በመገንባት ላይ ያለው የተንዳሆ የመስኖ ግድብ መጓተት የተከተለው የግድቡ ውኃ የሚተኛበት ቦታ ላይ የሚኖሩት የአካባቢው ማኅበረሰብ የክልሉ መንግሥት ተለዋጭ ቦታ ባለመስጠቱ የተነሳ እንደሆነ የሚገልጹት ሰለሞን አሁን ላይ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመወያየት መፍትሔ ለመስጠት እየተሞከረ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም መስሪያ ቤቱ ግንባታቸው በተጠናቀቁ እና ገና በመገንባት ላይ ባሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ 12 ሺሕ የተማሩ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመስኖ እርሻ ልማት ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛል። በ50 ሄክታር ላይ 12 የተማሩ ወጣቶች እና 100 በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠኑ እንዲሁም የጉልበት ሠራተኞች ተሰማርተው ያለማሉ የሚል የ100 ቀናት እቅድን ማውታቱ ይታወሳል። ለዚህም 12 የመስኖና ሌሎች መሠረተ ልማቶች የተሟሉላቸውና የመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ያሉ ቦታዎች ተመርጠዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here