በኢትዮጵያ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በኤች አይ ቪ ኤድስ ተይዘው ነገር ግን ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩን ሳያውቁ እንደሚኖሩ የፌዴራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ669 ሺህ በላይ ሰዎች በኤች አይ ቪ ቫይረስ እንደተያዙ የፌዴራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዳንኤል በትረ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ኤች አይ ቪ በደማቸው እንዳለ ተመርምረው እራሳቸውን በማወቅ መድኃኒት እየወሰዱ ያሉ ሰዎች ቁጥር 483 ሺህ ብቻ መሆኑን ዳንኤል ገልፀው የተቀሩት ከ186 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በምርመራ እራሳቸውን ሳያውቁ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት በህብረተሰቡ በኩል ለኤች አይ ቪ የተሰጠው ትኩረት በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ ከፍተኛ የሚባል መዘናጋት ከመፈጠሩ ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ ተመርምሮ እራሱን ለማወቅ ወደ ምርመራ ቦታ መሄድ በመዘንጋቱ እንደሆነ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡
በተለይም ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ወዲህ በስፋት በመንገድ ዳር እና በጤና ተቋማት ይደረጉ የነበሩ የምርመራ ሥራዎች በመቆማቸው ችግሩ እንዲባባስ ሊያደረገው እንደሚችልም ስጋታቸውን ዳንኤል ገልጸዋል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ በስፋት ይሰጡ የነበሩ የኤች አይ ቪ ምርመራዎች በኮቪድ-19 ምክንያት በመቆማቸው እና የህብረተሰቡ ራስን የማወቅ ተሳትፎ በመቀነሱ ስርጭቱን የከፋ እንዳያደርገው ያሰጋል ይላሉ ዳንኤል፡፡ በመሆኑም ትኩረቱ ለኮቪድ-19 ብቻ ከሆነ የሌሎች በሽታዎች ገዳይነት እንደሚጨምር አስተያየታቸውን ያስቀመጡ ሲሆን የምርመራ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠልና ጎን ለጎን በትኩረት መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ቫይረሱ በደማቸው እንዳለ ሳያውቁ ከቫይረሱ ጋር አብረው የሚኖሩ ሰዎች በስፋት እንደመኖራቸው መጠን የመመርመር ባህልን ካላሳደግን ስርጭቱ ውስጥ ለውስጥ ሊቀጣጠል የሚችልበት እድል እየሰፋ ስለሚሄድ ከወዲሁ ሊገታ እንደሚገባ ዳንኤል አስታውቀዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ይላሉ ዳንኤል እንደ አገር ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡
ችግሩን የባሰ አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ በኤች አይ ቪ ከሚጠቁ ሰዎች ውስጥ ከ15 እስከ 24 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙ መሆኑ እንደሆነ ዳንኤል ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ወዲህ አብዛኛዎቹ የጤና ተቋማት ትኩረታቸውን ወደ ኮቪድ-19 ስላዞሩ በአንጻሩ ሌሎች የቅድመ መከላከልና መደበኛ የህክምና አገልግሎቶች እንዲዘነጉ ማድረጉን የገለጹት ዳንኤል፣ ኤች አይ ቪን ከመከላከል፣ ምርመራ ማድረግና መደበኛ የመድኃኒት አጠቃቀም ላይ ክፍተት መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
ኤች አይ ቪ በደማቸው ውስጥ ያለ ሰዎች መድኃኒቱን መውሰድ ካቆሙ አይደለም በኮቪድ-19 በሌሎች በሽታዎችም የመጠቃትና መቋቋም አቅማቸው ይፈተናል፤ ስለሆነም ኤች አይ ቪ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግና መድኃኒቱን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባቸው ዳንኤል አሳስበዋል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ከዚሀ በፊት የነበረው መዘናጋት በአገራችን ያስከፈለውን ዋጋ ዛሬ ላይ ተደግሞ ላለማየት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በኮቪድ-19 መከሰት መዘናጋቱ እንዳይበረታ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሮች፣ ክልሎች፣ ባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶች ከዚህ በፊት ይወጡት የነበረውን ኃላፊነታቸውን ሳይዘነጉ እንዲከውኑ ለማስቻል መመሪያ ተዘጋጅቶ መሰራጨቱን ዳንኤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች ተዘጋጅቶ የተላከው መመሪያ በዋናነት ኤች አይ ቪ በደማቸው ላለባቸው ሰዎች የሚሰጠው መደበኛ የመድኃኒት ስርጭት እንዳይሰተጓጎል እና ሌሎች የሚደረጉ ድጋፎችና የእንክብካቤ ሥራዎች እንዳይቋረጡ የሚያጠናክር ነው ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ በቀን 31፣ በዓመት 12 ሺህ ሰዎች በኤች አይ ቪ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በቀን 61 ሲሆን፣ በዓመት 23 ሺህ ሰዎች መሆናቸውንም ጽሕፈት ቤቱ ጨምሮ አስታውቋል።
አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት በአሁኑ ሰዓት ከመንግሥት የጤና ተቋማት በየሦስት ወሩ እየተመላለሱ የኤች አይ ቪ መድኃኒት የሚወስዱ ሰዎች በአገር አቀፍ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ በመፍራት ወደ ጤና ተቋማት መሔድ ማቆማቸውን አረጋግጣለች፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 83 ግንቦት 29 2012



