በምሥራቅ አፍሪካ ኮቪድ-19 ከመከሰቱ በፊት 28 ሚሊዮን ዜጎች ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል

0
1157

በምሥራቅ አፍሪካ በኢጋድ አባል አገራት ውስጥ ኮቪድ-19 ከመከሰቱ በፊት 28 ሚሊዮን ሰዎች ለምግብ ዋስትና ችግር ተጋልጠው እንደነበር ኢጋድ አስታወቀ።
በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል አገሮች ውስጥ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት 28 ሚሊዮን ሰዎች ለምግብ ዋስትና ችግር ተጋልጠው እንደነበረ ኢጋድ ግንቦት 27/2012 ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።

በቀጠናው የተመዘገበው ቁጥር በዓለም ላይ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች 20 በመቶ ያህል እንደሚሸፍን ተገልጿል።
ኢጋድ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ቀደም ሲል የከፋ የምግብ ዋስትና የነበረበትን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ይበልጥ እንደሚፈትነው ተገልጿል። ወረርሽኙ በሚያስከትለው ጫና ‹ምን ያህል ሰዎችን ለምግብ ዋስትና ችግር ተጋላጭ ይሆናሉ› በሚል በተሠራው ትንበያ፣ 25 ሚሊዮን ሰዎች የፈረንጆቹ 2020 ከመገባደዱ በፊት ለከፋ የምግብ እጥረት ይጋለጣሉ ተብሎ እንደሚገመትም በመግለጫው ተጠቁሟል።

የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ፣ ግጭትና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ችግሩን እንደሚያባብሱት የጠቆመው ኢጋድ፤ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል።
የዓለም የምግብ ቀውስን በተመለከተ ይፋ በተደረገው ሪፖርት መሰረት፣ ኮቪድ-19 ወረርሽን የሚቀጥል ከሆነ ችግሩ ይበልጥ ሊከፋ እንደሚችልም በመግለጫው ተመላክቷል።

በቀጠናው በምግብ ዋስትና ላይ በርካታ ስጋቶች እንደሚያጋጥም የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገልፀዋል።ወርቅነህ አክለውም አሁን ላይ ቀጠናው አስከፊ በሆኑ የአየር ንብረት ክስተቶች እና እጅግ አስከፊ በሆነ የበርሃ አንበጣ ወረራ ውስጥ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የሚከሰቱ ተደራራቢ ቀውሶች የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠናን ለከፋ የምግብ እጥረት ሊዳርጉ እንደሚችሉ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ስጋታቸውን ገልጸዋል። ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብና የልማት አጋሮች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር የ2020 የዓለም የምግብ ቀውስ እና የኢጋድ የምግብ ቀውስ ሪፖርት ግንቦት 27/2012 በዙም መተግበሪያ አማካኝነት በተካሄደ ስብስባ ይፋ ሆኗል። በሪፖርቱ ላይ እንደተገለጸው እ.አ.አ 2019 በዓለም ላይ 135 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል ነበር። ከነዚህም መካከል 73 ሚሊዮን ወይንም ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአፍሪካ አገራት እንደሆነ በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ እስያ፣ ላቲን አሜሪካና ካሪቢያን አገራት የሚገኙ እንደነበሩ ተመላክቷል።

በዓለም ላይ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ካለባቸው 10 አገራት መካከል ሦስቱ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና የሚገኙ ሲሆኑ፣ እነርሱም ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን መሆናቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል። ለምግብ እጥረት መፈጠር ዋነኛ መንስኤዎች ግጭቶች መፈጠር፣ የአየር ንብረት ለውጥና የኢኮኖሚ አደጋዎች መሆናቸው ተጠቁሟል።

በሪፖርቱ እ.ኤ.አ በ2019 በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና 27 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ እጥረት ገጥሟቸው እንደነበር ተገልጿል። ከእነዚህም አብዛኛውን ድርሻ የሚይዙት ኢትዮጵያና ሱዳን እንደሆኑና በቅደም ተከተል 8 ሚሊዮን እና 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች ለምግብ እጥረት መዳረጋቸው ሪፖርቱ ላይ ተመላክቷል።
እ.አ.አ በ2016 በቀጣናው ከነበረው 23 ነጥብ 6 ሚሊዮን አሃዝ አንጻር የምግብ እጥረት የገጠማቸው ሰዎች ቁጥር መጨመሩንም ተገልጿል። ኢትዮጵያ እ.አ.አ 2016 ከነበረው 9 ነጥብ 7 ሚሊዮን የምግብ እጥረት የገጠማቸው ዜጎች አሀዝ አንጻር መቀነሱንና በሱዳን ደግሞ እየጨመረ መምጣቱን ሪፖርቱ ያትታል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በቀጣናው ያደረሰው ጉዳት ከግምት ሳይገባ በምሥራቅ አፍሪካ በአሁኑ ወቅት ከ24 እስከ 25 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ እጥረት ሊገጥማቸው እንደሚችል ተጠቁሟል። ጅቡቲና ኤርትራ የምግብ እጥረትን አስመልክቶ የቅርብ ጊዜ ቁጥራዊ መረጃ ባለማቅረባቸው በሪፖርቱ አለመካተታቸው ተጠቅሷል።

በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተው የበረሃ አንበጣና የጎርፍ አደጋ የምግብ እጥረት የሚያጋጥማቸውን ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምረው እንደሚችልም ነው ተመላክቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 83 ግንቦት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here