የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚረዳ የድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሸከርካሪዎች ተርሚናል ግንባታ በአፋር ክልል ኤሊደአር ወረዳ ዲችኦቶ ከተማ ተጀምሯል።
ግንባታውን ያስጀመሩት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ የተርሚናሉ ግንባታ ድንበር ተሻጋሪ አሸከርካሪዎችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ህብረተሰቡን የበሽታው ተጋላጭነት ለመቀነስ የላቀ ሚና እንደሚኖረው ነው የጠቆሙት።
በቀን ከአንድ ሺህ በላይ ድንበር ተሻጋሪ ተሸከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም የሚኖረውና ግንባታው በአንድ ወር ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ይጠበቃል ተብሏል።
የተሽከርካሪዎች ማቆያና በሂደትም ለሾፌሮች የመታጠቢያ፣ ማረፊያ፣ ምግብ፣ ጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎቶችን የሚሰጥ ነው ብለዋል።
በምሰራቅ አፍሪካ ደረጃውን የጠበቀ ተርሚናሉ ለማድረግ የሚስፋፋ መሆኑን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትር ደኤታ አቶ አወል ወግሪስ በበኩላቸው ክልሉ በጋላፊ በኩል የሀገሪቱ ከ90 በመቶ በላይ ወጪና ገቢ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበትና በቀን እስከ 2ሺህ ተሽከርካሪዎች የሚተላላፉበት ትራንስፖርት ኮሪደር መሆኑን ገልጸው በጂቡቲ ካለው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋትጋር ተያይዞ አሸከርካሪዎች የሚኖራቸው ቆይታ በተራዘመ ቁጥር ለአላስፈላጊ ወጪ ከመጋለጥ በላይ ለተያያዥ የጤና እክል እያደረጋቸው በመሆኑ የተርሚናሉ ግንባታ ይህን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
200 ሚሊዮን ብር ያህል ወጪ የሚደረግበት ተርሚናል በ16 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012



