ባለስልጣኑ በ25 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የ15 መንገዶች ግንባታ ስምምነት ተፈራረመ

0
867

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከ25 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግባቸው 15 መንገዶች ግንባታ ለማከናወን ከተለያዩ ተቋራጮች ጋር ስምምነት መፈራረሙን አስታቀ።
መንገዶቹ 1 ሺ 22 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ሲሆኑ፣ አንድ ከባድ የመንገድ ጥገናና አንድ የጠጠር መንገድን ጨምሮ ቀሪዎቹ በአስፋልት ደረጃ የሚገነቡ ናቸው ተብሏል።
መንገዶቹን ሰርቶ ለማጠናቀቅም እንደየመንገዱ ሁኔታ ከአንድ አመት እስከ አራት አመት ጊዜን የሚወስዱ መሆናቸው ተገልጿል ።
የመንገዱ ወጪም ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን፣ ፕሮጀክቱን ከፈረሙ 11 ተቋራጮች መካከልም ሰባቱ ሀገር በቀል ተቋራጮች ናቸውም ነው የተባለው ።
መንገዶቹ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙና በጠጠር ደረጃ የነበሩ ከመሆናቸውም ባለፈ ለተለያዩ እንቅስቃሴዎች ምቹ ያልነበሩና ለዘመናትም የህዝብ ጥያቄ ሆነው የቆዩ መሆናቸው ተነግሯል ።
መንገዱ ሲጠናቀቅም በአካባቢው ማህበረሰብ ኑሮና ኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ የተገለፀ ሲሆን፣ እንደ ሀገርም የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳለጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ የራሱን ጉልህ ሚና ይጫወታል ተብሏል።
መንገዶቹ ከዚህ በፊት በጠጠር መንገድ ደረጃ የነበሩ ሲሆን፣ ካላቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበርዊ ጠቀሜታ አንፃር ታይቶ በአሁኑ ወቅት በአስፋልት ደረጃ እንዲገነቡ ታቅዶ የውል ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በተጨማሪም ቀደም ሲል ከተፈርሙ መንገዶች መካከል በውላቸው መሰረት የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ 20 ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ እንዲሽጋገሩ መደረጋቸውን ተመላክቷል። እንዲሁም 21 የመንገድ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ መደረጋቸው ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here