በማንኛውም ሁኔታ የግብርና እንቅስቃሴ መቋረጥ አይኖርበትም

0
1246

በኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ምክንያት እንዲሁም በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ላይ አደጋ በጣለውና አሁንም ስጋቱ ባልቀነሰው የበረሃ አንበጣ መንጋ ሰበብ የምሥራቅ አፍሪካ የምግብ ዋስትና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። በአዘቦቱም ዜጎቿን በቅጡ መመገብ ያልሆነላት አፍሪካ፣ በዚህ ጊዜ ደግሞ የበለጠና ከባደ ፈተና ተጋርጦባታል። ወደፊትም የባሰው እንዳይመጣ ስጋት አለ። ይህንን ከምግብ አቅርቦት ጋር የተገናኘ ስጋት ከሚያጋሩና ያለውን ተስፋና ሊደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ ከሚያመላክቱ ተቋማት መካከል ደግሞ አንዱ ነው፣ የዓለም ምግብ ድርጅት።

ዴቪድ ፒሪ (ፒኤችዲ) በዓለም የምግብ ድርጅት የምሥራቅ አፍሪካ አስተባባሪ እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት እና የአፍሪካ የተባበሩት መንግሥታት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካይ ናቸው። ከአሁን የሥራ ኃላፊነታቸው በፊት የዓለም የድርጅቱ የደቡብ አፍሪካ አስተባባሪ እንዲሁም የዚምባቡዌ፣ ስዋዚላንድ እና ቦትስዋና ተወካይ የነበሩት ሲሆን፣ ድርጅቱን የተቀላቀሉት በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1991 ነበር።

ወቅታዊ የዓለም እንዲሁም አፍሪካ ብሎም የኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በተያያዘ፣ ያለውን ስጋትና ቀጣዩ እርምጃ ምን መሆን አለበት በሚሉ ሐሳቦች ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የአዲስ ማለዳ ጋዜጣ እህት መጽሔት ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው ባልደረባ አሸናፊ እንዳለ ከዴቪድ ፒሪ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።

የበረሃ አንበጣ በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ከተንሰራፋ ዓመት እየተጠጋ ነው። በተለይ በኢትዮጵያ ግብርና ላይ ደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የዓለም ምግብ ድርጅት ግምገማ ምን ያሳያል?
የአንበጣ መንጋው በሶማሊያ፣ ከዛ ተሸግሮ ወደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን ከዛም ተመልሶ ወደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ መመለሱን በቅርበት መከታተል ችለናል። ሁኔታው አሁንም በጣም አሳሳቢ ነው። በምሥራቅ አፍሪካ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲሁም ከበረሃ አንበጣ መንጋ መከሰት በፊትም በነበሩ ድርቅና ግጭቶች ሳቢያ፣ 28 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች የምግብ ርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር።

ኹነቶችን ነጣጥሎ መመልከት በጣም ከባድ ነው፣ ምክንያቱም በተመሳሳይ ጊዜ የሚከሰቱ ብዙ ቀውሶች አሉ። ይህም ታድያ በመደበኛው የምግብ ዋስታና የሌላቸውና በቀን አንድ ጊዜ ወይም ከዛ በታች ምግብ ከሚያገኙ 133 ሚሊዮን ሰዎች በተጨማሪ ነው።

እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኬንያ በዚህ የበረሃ አንበጣ በእጅጉ ተጎድተዋል። በሺሕዎች የሚቆጠሩ የሰብል ማሳዎች ተጎድተዋል። ይኸው የበረሃ አንበጣ በተመሳሳይ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሲዳን፣ ታንዛንያ እና ኡጋንዳንም ክፉኛ ጎድቷል። በኢትዮጵያም በተለይ ደቡብ እና ምሥራቅ ክፍሉ በዚህ የአንበጣ መሄድና መምጣት እንደተጎዳ እናውቃለን።

በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አስከፊ ነው። በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ዝናብ ሲያገኙ፣ አርሶ አደሮችም ሰብል ማምረት የሚጀምሩበት ጊዜ ነው። ይህ ማለት ሁኔታው አንበጣው የበለጠ ምግብ የሚያገኝበትና የሚራባበት ጊዜ ነው ማለት ነው። ይህም ከአሁን ጀምሮ ቁጥጥር ሊደረግበት ካልተቻለ፣ የአንበጣ መንጋው መጠን አሁን ካለበት በ200 እጥፍ ሊጨምር ይችላል።

የምሥራቅ አፍሪካ አገራት የበረሃ አንበጣ በግብርና ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ ለመከላከል፣ የአንበጣውን መራባትና ስርጭትም ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅምና የትብብር ኃይል አላቸው ብለው ያምናሉ?
አዎን! የዓለም የምግብ ድርጅትን ጨምሮ በተባባሪዎች ድጋፍ አቅሙ ይኖራቸዋል። እዚህ ላይ ልብ በል! ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በ25 ዓመታት ውስጥ የበረሃ አንበጣ አልነበረባቸውም። ኬንያም ውስጥ ቢሆን ባለፉት 70 ዓመታት በዚህ መጠን የበረሃ አንበጣ አላገኛትም። እርግጥ ነው፣ አገራቱ አቅማቸውን አጥተዋል። አሁን እንደገና ማሠልጠን ይኖርብናል።

ድርጅታችን እነዚህን አገራት በኬሚካል መርጫ፣ ጸረ ተባይ መድኃኒት፣ ለርጭት የሚያገለግሉ አውሮፕላኖችና ለእነዚሁ አስፈላጊ የሚሆን ነዳጅ ሳይቀር ማቅረብ ይኖርበታል። ለምሳሌ ከአምስት በላይ አውሮፕላኖች ለኢትዮጵያ መንግሥት ሰጥተናል። ይህንንም በምሥራቅ አፍሪካ ክልል፣ በጠቅላላው ሁሉንም አገራት ለማገዛ እንዲያስችለን እያደረግነው ያለነው ተግባር ነው።

ኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲሁም የበረሃ አንበጣው በዚህ የሚቀጥል ከሆነ፣ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ሕዝባቸውን ሊመግቡ የሚችሉበት የምግብ ክምችት አላቸው ብለው ያስባሉ? በቂ የምግብ ክምችትስ አለ ብለው ያምናሉ?
ኮቪድ 19 የምግብ ክምችትን ከዚህም በላይ ያወሳስበዋል። በምሥራቅ አፍሪካ፣ እንኳን አሁን በኮሮና ወረርሽኝ ሰሞን፣ አስቀድሞም ከ135 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የምግብ ዋስትና ያስፈልጋቸው ነበር። አሁን ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተንሰፋራበት ወቅት ደግሞ የከፋ ነው የሚሆነው። ፋኦ እና አፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ የግብርና ሚኒስትሮች ጠርተው ስብሰባ አድርገው ነበር።

በዛም የደረስንበት ስምምነት አለ። ይህም በቫይረሱ ምክንያት ባለው መዘጋጋትና የእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥም ቢሆን የግብርና ምርትን መቀጠል ወሳኝ እንደሆነ ነው። ገበሬዎች መሬታቸውን እንዲያርሱ እንዲሁም ነጋዴዎችም ምርቶችን ይዘው ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድም አለባቸው። በአገራት መካከል ባሉ ድንበሮች መተላለፊያዎችም ለእንቅስቃሴ ክፍት መሆን አለባቸው፣ ቢያንስ ለሰብል ምርት የሚያገለግሉ ግብዓቶችን እና ምግቦችን ለማንቀሳቀስ እንዲቻል።

አገራት ወረርሽኙን መቆጣጠር እንዳለባቸው ግልጽ ነው፣ ግን ደግሞ ሰዎች በረሃብ ምክንያትም መሞት የለባቸውም። ኹለቱንም ማድረግ አለብን። አርሶ አደሮች የእርሻ ሥራቸውን ሲቀጥሉ መንግሥት ደግሞ ቢያንስ ለድንገተኛ አደጋ የሚሆኑ እህል ማከማቻዎችን በተገቢ ስፍራዎች ማሰናዳት ይኖርበታል። አሁን ላይ በቂ የሆነ ተቀማጭ እህል ላይኖር ይችላል። ይሁንና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ፣ ሁሉም ዜጎቻቸውን መመገብ ይኖርባቸዋል።

ኢትዮጵያ በማኅበራዊ ዘርፍ ፕሮግራሞች ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ምግብ እያቀረቡ ካሉ አገራት መካከል በመሆኗ በጣም ደስተኛ ነኝ። ሩዋንዳ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ እና ሌሎች አገራትም በተመሳሳይ ጉዳት ለደረሰባቸው ምግብ በማድረስ ጥሩ እየሠሩ ነው። ወረርሽኙ ከዚህ እየባሰ የሚሄድ ከሆነ፣ የበለጠ ተጎጂ የሚሆኑት ቀድሞ በቀን አንዴ እንኳ መብላት የማይችሉ የነበሩ ሰዎች ናቸው።

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ በተለያዩ አጋጣሚዎች በርካታ የተፈጥሮ ፈተናዎችን አስተናግዷል። ውስጣዊም ሆነ ውጪአዊ በርካታ ችግሮችን መጥቀስ ይቻላል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአንጻሩ የግብርና ምርት በየዓመቱ ስድስት በመቶ ያድጋል ብሏል። እያደገ ካለው ሕዝብ ብዛትም አንጻር ኢትዮጵያ በቂ አልፎም ትርፍ ምርት ይኖራታል በሚለው ይስማማሉ?
የኢትዮጵያ መንግሥት ያለው ቁርጠኝነት ባለፉት ዐስርት ዓመታት የታየውን የግብርና ዘርፍ እድገት አሳይቷል። ባለፉት ኹለት ዓመታት በኢትዮጵያ የምግብ እርዳት የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ከ13 ሚሊዮን ወደ ስምንት ሚሊዮን ወርዷል። ይህ የምግብ ዋስትና ስጋት መቀነስ የለውጡ አንድ አካል ነው። እንዲህ ያለ ለውጥ ሊመጣ የቻለውም መንግሥት የግብርና ምርትን ለማሳደግ ባሳየው ጥረት የተነሳ ነው።

ያ በቂ ነው?
አይደለም። በተለይም ከአየር ጸባይ ለውጥ፣ ውስጣዊ ችግሮችና ከአየር ትንበያ ጋር በተገናኘ ያሉትን ለውጦች ስናይ ነገሩ ከባድ ነው የሚሆነው። በቂ ዝናብ በሌለበት ሳይቀር ብዙ ሰብል ማምረት የሚቻልበት መንገድ ያስፈልገናል።

የመስኖ ልማት እዚህ ላይ ነው ወሳኝ የሚሆነው። ምክንያቱም ምንም ዝናብ ባይኖርና ድርቅ ቢሆን፣ ገበሬዎች ሰብል ማምረት አለባቸው። በኢትዮጵያ የውሃ ቁጥጥርና መስኖ ልማትን ለማሻሻል በመንግሥት የተደረገ በርካታ ጥረት አለ፣ ይህ ደስ የሚያሰኝ ነው። ይህ ምንም እንኳ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ አሁንም ጠንክሮ መቀጠል ያለበት ጥረት ነው። ግብርና በዝናብ ላይ ካለው ጥገኝነት ሊገላግለው የሚችለው የመስኖ ልማት ነው።

በአፍሪካ ግብርናን በገንዘብ መደገፍ ላይ ችግር ነበር። በአፍሪካ የግብርና ዘርፍ ላይ ከሚደረግ ኢንቨስትመንት ይልቅ፣ በችግር ሰዓት ዓለማቀፍ እርዳታ ሰጪ ተቋማት ከፍተኛ ድጋፍ ይደረጋሉ። ግን ለምን ይሆን እነዚህ ተቋማት ከችግሩ አስቀድመው ግብርናውን በገንዘብ ለመደገፍ ያልቻሉት?
ድርጅታችን የዓለም የምግብ ድርጅት ቅድመ መከላከልን ይደግፋል። የአፍሪካን ግብርና በገንዘብ ማገዝ ጠቃሚ መሆኑም እሙን ነው። ይህ ሲሆን ሰዎች ችግር ላይ በሆኑ ቁጥር ምግብ ከማቅረብ ይልቅ የራሳቸውን ምግብ እንዲያዘጋጁ (አርሰው እንዲበሉ) ማድረግ ይቻላል። ነገር ግን ያደጉ አገራት ለግብርና የሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ በኹለት የተከፈለ ነው። ይህም አንደኛው የአደጋ ጊዜ ፈንድ ሲሆን ሌላው የልማት ፈንድ ነው።

የልማት ፈንድ በጠቅላላው ሌላው ጉዳይ ላይ የሚውል ሲሆን፣ የአደጋ ጊዜው ችግር ሲከሰት ሕይወትን ለማዳን ወጪ የሚደረግ ነው። ይህም ጠቃሚ ነው። ድርጅታችን የሚመክረው በጥቅሉ ሰዎች በመንግሥት በሚቀርብላቸው ግብዓት እንዲሁም ከዓለማቀፉ ማኅበረሰብ የሚገኘውን ድጋፍ በመጠቀም አብቅለው ለራሳቸው ምግብ እንዲያዘጋጁና ችግር እስኪከሰት እንዳይጠብቁ ነው።

በአፍሪካ የተሟላና ሁለገብ የግብርና ልማት ፕሮግራም በኩል የአፍሪካ አገራት ከብሔራዊ በጀታቸው ውስጥ 10 በመቶውን ለግብርና እንዲያደርጉ ይጠበቃል። በጠቅላላ በአፍሪካ ካሉ አገራት ግን ይህን ተግባራዊ ያደረጉ ስምንት አገራት ብቻ ናቸው። ከእነዚህም ኢትዮጵያ አንዷ ናት።

አሁን ያለው የምግብ ችግር ምን ያህል ድጋፍ ነው የሚያስፈልገው፣ እስከ አሁንስ ምን ያህል ድጋፍ ተገኝቷል?
በማንኛውም እንዲህ ያለ ቀውስ ሰዓት እንደሚገኘው ሁሉ ከዓለማቀፉ ማኅበረሰብ፣ በጠቅላላ ከሚያስፈልገው ውስጥ 40 በመቶው ይገኛል የሚል ግምት አለን። ከበረሃ አንበጣ መንጋ ጋር በተገናኘም በርካታ ተቋማት እና አገራት ለግሰዋል። የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ሥራም ከሚያስፈልገው ሀብት 80 በመቶ መሰብሰብ ችለናል። አሁን በምሥራቅ አፍሪካ በአንበጣ መንጋው የተጎዱ አገራትን ማገዝ እንችላለን።

አሁን በኮቪድ 19 ምክንያት ግን ችግራችን ተወሳስቧል። ይህም የሆነው አንበጣውን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚያስፈልገውን ግብዓት ሁሉ ከውጪ የምናስገባ በመሆኑ ነው። የባሰ ደግሞ በወረርሽኙ ምክንያት አገራት ድንበራቸውን በመዝጋታቸውና እንቅስቃሴ በመገደቡ፣ ግብዓቶችን የማምጣት ሂደቱን አዘግይቶታል። አሁን ግብዓት ማግኘትም ሆነ እነዚህኑ ምርቶቹን በአካል ሄዶ ለመገበያየት ከባድ ሆኗል፣ በወረርሽኙ ምክንያት አካላዊ መራራቅ የግድ ስለሆነ።

የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ጠቅላላ የሚጠይቀው ወጪ ምን ያህል ነው?
ለአሁን 140 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው። ይህ ግን በቀጣይ 10 ቀናት ውስጥ ሊጨምር ይችላል። ነገር ግን የግል ዘርፉ እንዲሁም የአገራቱ መንግሥታት ጥረቱን እየደገፉ በመሆኑ ደስተኛ ነን።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተጽእኖ ለመቀነስ ለአፍሪካ አገራት የምታቀርቡት የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ይኖር ይሆን?
በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት በየቤቱ የምግብ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል። በዚህ ሁኔታ የተለየ የማኅበራዊ ጥበቃ አሠራር ወሳኝ ነው። ይህም ገንዘብ ማስተላለፍ፣ ቀጥተኛ የሆነ የምግብ ስርጭት ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል። ይህ አጣዳፊ ጉዳይ ነው። የምግብ እጥረቱ ከዚህ ከተባባሰ፣ ለጤና ዘርፍ መሻሻል የሚደረገው ጥረትም ሊሳካ አይችልም።

በመጀመሪያ ደረጃ ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ አባላት ገንዘብ እና ምግብ መቅረብ ይኖርበታል። ኹለተኛ የግብርና ምርት በምንም መልኩ መታጎል የለበትም። የምግብ ሰንሰለቱ እንቅስቃሴው ሳይገታ መቆየት አለበት። አርሶ አደሮች ማምረት ላይ እንዲቀጥሉም የግብርና ግብዓቶችን ማቅረቡ መቀጠል አለበት። አርሶ አደሮች በተመሳሳይ ትራንስፖርት እንዲሁም የምርት ማስቀመጫ ያስፈልጋቸዋል።

በሦስተኛ ደረጃ በአገራት መካከል የምግብ እና የግብዓት ትስስር ክፍት ሆኖ መቆየት ያስፈልገዋል። ከውጪ የሚገባ ምግብ እንዲሁም ግብዓት ላይ ጥገኛ የሆኑ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት አሉ። ድንበሮች ለምግብ እንዲሁም ለግብርና ምርት ግብዓቶች ክፍት መሆናቸውን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው።

የተመጣጠኑ ምግቦች በዚህ የምግብ ትስስር ውስጥ ሊገኙ ይገባል፣ በተለይ ኮቪድ 19ን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የሚያግዙ ናቸው። በሔክታር የሚታረስ ምርት ወይም ምርታማነት መጠንም በተጨባጭ መጨመር አለበት። ይህ ወረርሽኝ ልንገምት ክምንችለው ጊዜ በላይ ሊቆይ ይችላል። ሆኖም የምግቡን ዘርፍ ሊነካው አይገባም።

እንዲህ ያለ ችግር የሚከሰትበት ጊዜ፣ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ኢኮኖሚ በመሠረተ ልማት፣ በግብርና አልፎም የአካባቢውን የምግብ ክምችት በማቆየት ረገድ የክልል ትብብር ይኖራል ብለው ያስባሉ?
በምሥራቅ አፍሪካ የምጣኔ ሀብት ትብብሮች አሉ። የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ እንዲሁም ኢጋድ ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህም ለአባል አገራቱ ፖለቲካዊ እንዲሁም ሙያዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲሠሩ ድጋፍ ለማድረግ እየተጉ ነው። የዓለም የምግብ ድርጅትም ከአገራዊ የምግብ ክምችት በተጓዳኝ ክልላዊውንም ይደግፋል።

ሆኖም ክልላዊ (በምሥራቅ አፍሪካ) የምግብ ክምችት እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም ወይም በጣም ጥቂት ነው። ይህ የሆነው ምንአልባት ጎረቤቶቻቸውን ወይም በዙሪያቸው ያሉትን ስለማያምኑ ሊሆን ይችላል። በድምሩ ይህ እያንዳንዳቸው አገራቱ በየራሳቸው የሚወስኑት ሉዓላዊ የሆነ ውሳኔ ነው።

ምንአልባት ይህ የሆነው ተቋማዊ አሠራር ባለመኖሩ ምክንያት ይሆን?
ተቋማዊ አሠራሮች አሉ። ለምሳሌ ኢጋድ የድርቅና አደጋ መከላከልና ድጋፍ የሚባል ክፍል አለው። የአየር ጸባይ ትንበያ መተግበሪያ ማእከልም እንደዛው። የአርብቶ አደርና የእንስሳት ሀብት ልማት ማእከልም በኢጋድ ይገኛል። ይሁንና መንግሥታቱ ተቋሙን በአግባቡ የሚጠቀሙበት አይመስለኝም። ይህም የመንግሥታቱ ድርሻ ነው፣ በጋራ መሥራት ወይም ለየብቻ መሆን። ፋኦ በኹለቱም መንገድ በአግባቡ ሥራውን ይሠራል።

የኢትዮጵያ እንዲሁም የበርካታ አፍሪካ አገራት የግብርና ፖለሲ፣ ትንንሽ እርሻዎችን በመደገፍ ምርታማነትና ተረፈ ምርት ማስገኘት ላይ ያተኩራል። ይህ የአፍሪካን ግብርናን ያዘምናል ብለው ያምናሉ?
በትክክል። በትናንሽ የእርሻ ማሳ ሥራ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል። በርካታ አገራት ለምን ይህን ሐሳብ እንደሚያራምዱም ይገባናል። ይህ የሆነው አርሶ አደሮቻቸው አነስተኛ እርሻ ሥራ ላይ ስለተሰማሩ ነው። ነገር ግን እነዚህ አገራት ይህን አሠራር ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ ደረጃ ወደ ከፊል የንግድ እንቅስቃሴ ሊያሳድጉት፣ ቀጥሎም ወደ ንግድ እርሻ ሊያደርሱት ይገባል። ይህ ሲሆን ብዙና የተሻለ ማምረት ይቻላል።

የአነስተኛ እርሻ ሥራ ሊጠቅም የሚለው አርሶ አደሮቹን በመደገፍ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ወደ ገበያ እንዲያቀርቡና ወደ ንግድ መቀየር የሚቻል ከሆነ ብቻ ነው። የዓለም የምግብ ድርጅትም ይህን አቅጣጫ ነው እየሞከረ ያለው። የአፍሪካ አገራት መንግሥታት በአንበጣ መንጋው እንዲሁም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ላይ ተከታታይና ፈጣን የሆነ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እፈልጋለሁ።

ቫይረሱን መከላከል፣ የበረሃ አንበጣውን መቆጣጠር፣ በዛውም ምርት ማምረትን መቀጠል አለብን። የግብርና ምርት እንዲሁም የምግብ ዋስትና የመንግሥታቱ ቀዳሚ የትኩረት ጉዳዮች መሆን አለባቸው፣ ቀጥሎ ከዚህ የባሰ አስከፊ ነገር ቢከሰት እንኳ፣ እነዚህ ጉዳዮች ዋና ትኩረታቸው ሊሆኑ ይገባል።

በአፍሪካ የግብርና ምርትን ለመጨመር በዘረመል የተለወጡ ዝርያዎችን (ጂኤምኦ) መጠቀምን በሚመለከት የተለያዩና መጠቀም ጉዳት አለው፣ የለውም ብንጠቀም ጥሩ ነው ወዘተ የሚሉ ሐሳቦች ሲነሱ ይሰማል። በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
በእነዚህ ዝርያዎች ላይ የድርጅታችን ፖሊሲ የታወቀ ነው። ተፈጥሮአዊ የሆኑ ዝርያዎችን በመጠቀም ምርትን ማሳደግ የሚያስችል አቅምና ቴክኖሎጂ አለን። ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርታማነትን ለማሳደግ እነዚህን ዝርያዎች የሚጠቀሙ አገራት አሉ። እናም እነዚህን ዝርያዎችን የመጠቀምና ያለመጠቀሙን ጉዳይ የየአገራቱ የምርጫና የውሳኔ ጉዳይ እንዲሆን የተተወ ነው።

በድርጅታችን እንዲህ ያሉ አዳዲስ ቴክኖለጂዎች ሲመጡ አካባቢ ደኅንነት ላይ ስለሚያደርሱት ተጽእኖም የሚያጠና ኮሚቴ የምንመሠርትበት አሠራር አለን። እስከ አሁን ያ ኮሚቴ ሊጠቀስ የሚችል ችግር አገኘሁ አላለም። ኮሚቴው እንዲህ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚያሳድሩትን የረጅም ጊዜ ጉዳትም ይመለከታል።
ነገር ግን በጥቅሉ ያሉን የተፈጥሮ ሀብቶችና ቴክኖሎጂዎች፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃም ቢሆን፣ አስፈላጊ የሆነውን የምግብ መጠን ለማምረት በቂ ናቸው።

ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here