የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ የወንጀል ችሎት በወንጀል ምክንያት ንብረቶቻቸው በመንግሥት እንዲወረሱ የተወሰነባቸው ከበደ ተሰራ የንብረቶቹ ወቅታዊ ዋጋ በመክፈል ንብረታቸውን መረከብ የሚያስችላቸውን ውሳኔ አስተላልፏል።
በአራጣ ማበደር፣ ታክስ ማጭበርበር፣ የሀሰት ማስረጃና ሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር 25 ዓመት ተፈርዶባቸው በእስር ላይ ያሉት ከበደ ተሰራ በድር ሕንፃ ነጋዴዎች ኃ/የተ/የግ/ማኅበር እና ኅብረት ባንክ አክሲዮን ማኅበር ያሏቸው አክሲዮኖች በመንግሥት እንዲወረስ በተለያየ ጊዜ ተወስኖባቸው ነበር።
ግለሰቡ በብድር ሕንፃ ነጋዴዎች ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ያላቸው አክሲዮን እንዲወረስ በተወሰነበት ሐምሌ 5 ቀን 2002 በማኅበሩ የነበራቸው እያንዳንዳቸው አንድ ሺህ ብር ዋጋ ያላቸው 1284 የአክሲዮን ድርሻዎች ሲሆኑ በጠቅላላ 1,284,000 ብር ዋጋ አላቸው። ከሳሽ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ከውሳኔው በኋላ የግለሰቡ የአክሲዮን ድርሻ ወደ 1,824,000 ብር አድጓል በተጨማሪም በማኅበሩ የተቀመጠ ያልተከፈል የትርፍ ድርሻ ብር 348,303.17 ስላለ ይህም ተጨምሮ ሊወረስ ይገባል ሲል ክሱን አቅርቧል፡፡ ግለሰቡም ውሳኔው በተሰጠበት ወቅት ስለነበረው የአክሲዮን ድርሻዎች እንጂ ስለተቀረው አክሲዮን እና ውሳኔ ስላልተሰጠበት የትርፍ ድርሻ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ይህንንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ስለሆንኩ ጉዳዩ ወደ ፍርድ አፈፃፀም መሔድ አያስፈልገውም ሲሉም ተከሳሽ ከበደ ተሰራ ለፍርድ ቤቱ መልስ ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል በአራጣ ወንጀል ምክንያት በመንግሥት እንዲወረስ ውሳኔ የተላለፈበት 3.7 ሚሊዮን ብር ጋር በተያያዘ የታገዱት ኅብረት ባንክ አክሲዮን ማኅበር ያሉት አክሲዮኖች ግለሰቡ ይህንኑ ገንዘብ በመክፈላቸው ምክንያት እግዱ እንዲነሳላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ግለሰቡ በብድር ሕንፃ ነጋዴዎች ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ያላቸው አክሲዮን እንዲወረስ በተወሰነበት ወቅት ውሳኔው ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ ግለሰቡ በአክሲዮኖቹ ላይ ያላቸውን መብት ሙሉ በሙሉ የሚያጡ ስለሆነ በአክሲዮኖቹ ምክንያት የሚገኙ ማንኛውም ጥቅሞች በመንግሥት እንደተወረሱ ይቆጠራል ሲል በይኗል፡፡ በመሆኑም 1,824,000 ብር የሚያወጣው አክሲዮናቸው እና 348,303.17 ብር የትርፍ ድርሻ እንዲወረስ ወስኗል፡፡
ነገር ግን የአክሲዮን ድርሻዎቹ መንግሥት ይውረሳቸው ተብሎ ቢወሰን መንግሥትን የማኅበሩ አባል የሚያደርገው ስለሆነ የአክሲዮኖቹ ወቅታዊ ግምት የሆነን ዋጋ ለመንግሥት እስከከፈሉ ድረስ የአክሲዮኖቹ ባለቤትነት የግለሰቡ ሆኖ እንዲቀጥል ወስኗል፡፡ በኅብረት ባንክ አክሲዮን ማኅበር የሚገኙትን የግለሰቡን አክሲዮኖች በተመለከተም አቃቤ ሕግ ተቃውሞ ስላላቀረበ እና ግለሰቡም ይክፈሉ የተባለውን 3.7 ሚሊዮን ብር እዳ የከፈሉበትን ማስረጃ ስላቀረቡ አክሲዮኖቻቸው ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
ከበደ ተሰራ ከሌሎች 91 ታራሚዎች ጋር በፕሬዝደንት ሙላቱ ተሾመ ይቅርታ ተደርጎላቸው ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ይቅርታው የተሰጠው በስህተት ነው በሚል ምክንያት ከዐሥር ቀን በኋላ በድጋሜ መታሰራቸው ይታወቃል፡፡
25 ዓመት የተፈርደባቸው በእስር ላይ የሚገኙት ግለሰቡ የፌደራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ በመሻሻሉ ምክንያት የእስር ቅጣቴ ይቀነስልኝ የሚል አቤቱታ አቅርበው የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳያቸው በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲታይላቸው መወሰኑን አዲስ ማለዳ ከሳምንታት በፊት ዘግባ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ግለሰቡ አሁን ውሳኔ የተላለፈባቸውን ንብረቶቻቸውን ለማስለቀቅ ቀድመው ገቢ ያደረጉትን 3.7 ሚሊዮን ብር ጨምሮ በአጠቃላይ 5.8 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት የሚከፍሉ ይሆናል፡፡
ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011