የመርካቶ ነጋዴዎች በማናውቀው ሕግ እየተዳደርን ነው ሲሉ ቅሬታ አሰሙ

0
514

‹‹በንግድ ስርዓቱ ተማረናል›› በሚል ከሰሞኑ አድማ ለማድረግ አስበው ነበር የተባሉት ነጋዴዎች በምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማና የነጋዴዎቹ ጊዜያዊ ኮሚቴ አባላት አግባቢነት ለውይይት ተቀምጠዋል።
ባለፈው ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 11 በኢንትር ኮንትኔንታል ሆቴል ከምክትል ከንቲባው ጋር የተወያዩት ነጋዴዎቹ ‹‹ከውጭ አገራት በሚቀዱና ፍፁም የኛ ባልሆኑ፣ ባልተወያየንባቸው ሕጎች እንድንመራ መደረጋችን አግባብ አይደለም›› በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ሒሳባቸውን ኦዲት አስደርገው ለግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ቢያቀርቡም ልክ አይደለም በሚል በግምት ከአቅማቸው በላይ ግብር እንደሚጣልባቸው ያነሱት ተወያዮቹ ‹‹የግብር ስርዓቱ ግልፅ እንደለም›› ሲሉም ለምክትል ከንቲባው አቤት ብለዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ በአንድ ወር ብቻ ከ80 በላይ ነጋዴዎች ከዋጋ በታች ሸጣችኋል በሚል የንግድ ሱቆቻቸው እንደታሸጉባቸውም አንስተዋል። በአንፃሩ ‹‹በራችን ላይ ግን እኛ ሱቅ ውስጥ የምንሸጣቸው እቃዎች በሕገ ወጥ ነጋዴዎች ሲቸረቸሩ እንመለከታለን›› በማለትም ‹‹የንግድ ስርዓቱ ሕገ ወጥነትን የሚያበረታታ ነው›› ሲሉ አማረዋል። ሕገ ወጥ ንግዱ በተሸከርካሪና በድምፅ ማጉያ ሳይቀር እየተከወነ በመሆኑ መላ እንዲበጅላቸው ምክትል ከንቲባውን የጠየቁት ነጋዴዎች በሕገ ወጥ ንግዱ ‹‹የውጭ ዜጎች ጭምር እየተሳተፉ ይገኛሉ›› ሲሉም አክለዋል።
ከ2008 ጀምሮ በአገሪቷ ላይ በነበረው አለመረጋጋት ሥራቸው ቢቀዘቅዝባቸውም የንግዱ ማኅበረሰብ ያልሠራውንና የተጋነነ ግብር እንዲከፍሉ እየተደረገ ነው በሚልም ጥያቄ ተነስቷል።
‹‹ባለ ብዙ ታሪኳን መርካቶ ታሪካዊ ይዘትዋን ጠብቀን ለማልማት በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ምላሽ ሳናገኝ ቀርተናል›› ያሉ ተሳታፊዎችም በአክሲዮን ተደራጅተው መርካቶን እንዲያለሙ ጠይቀዋል።
የተነሱት ጥያቄዎች ትክክል መሆናቸውን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው ለተፈጠሩ ስህተቶች መንግሥት ኃላፊነት እንደሚወስድ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚንስትሩም እንደ መንግሥት በይፋ ይቅርታ ከጠየቁባቸው ጥፋቶች መካከል አንዱ ይኸው ቅሬታ መሆኑንም አክለዋል።
ከግብር ሰብሳቢው ተቋም ጋር በተገናኘ በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመራ የታክስ ስርዓት ሪፎርም በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ያስታወሱት ምክትል ከንቲባው ግለሰቦች የሚያበላሹትን ስርዓት ለማስተካከል ግን ቁርጠኞች እንደሆኑ ተናግረዋል። አንዱ ሕጉን ስለሚያስፈፅም የሚጠቀምበት ሌላኛው ተገልጋይ ስለሆነ የሚጎዳበት አካሄድ እንደማይኖርም አጽንኦት ሰጥተዋል። አክለውም በየሦስት ወሩ ከነጋዴው ጋር ተመሳሳይ መድረክ እንደሚኖራቸውም ጠቅሰዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here