‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ያለፉትን ጊዜያት ወንጀሎች እንዴት እንሻገር?

0
1165

ኢትዮጵያ እንግዳ የሆነ የፖለቲካ ‘ሽግግር’ እያካሔደች ነው። ምንም እንኳን የገዢ ቡድኑ ባይቀየርም፣ አመራሮቹ ብቻ በመቀየራቸው ባለፉት ዓመታት የተፈፀሙ በደሎች መንግሥታዊ ዕውቅና ተችሯቸዋል። “ከይቅርታ” ጀምሮ እስከ “ሕጋዊ ተጠያቂነት” ሥራዎች በተግባር ላይ ናቸው። ባለፉት ዓመታት በመንግሥት ከፍተኛ ሰብኣዊ ወንጀል የተፈፀመባቸው፣ ሕይወታቸው የተመሰቃቀለባቸው ግለሰቦች ፍትሕ ይፈልጋሉ። የፍትሕ አሰጣጡ ሒደት ለዴሞክራሲያዊነት መሠረት የሚጥል እና የሕግ የበላይነትን መሠረት ያደረገ መሆን ይኖርበታል። የዚህ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ምን መምሰል አለበት በሚለው ላይ በፍቃዱ ኃይሉ የተለያዩ ባለሙያዎችን በመጠየቅ ያጠናቀረው ሐተታ ዘ ማለዳ እነሆ።

ከፍያለው ተፈራ ኢትዮጵያ ከኋላዋ ጥላ ለማለፍ እየተፍጨረጨረች ባለው ስርዓት ከፍተኛ ሰቆቃ የደረሰበት ሰው ነው። በፖለቲካ እስሩ ወቅት ሁለት እግሩን አጥቷል። ሲታሰር በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ‘የእፅዋት ሳይንስ’ ሦስተኛ ዓመት ተማሪ የነበረ ሲሆን ከዐሥራ ሁለት ዓመታት በኋላ የዕድሜ ልክ ፍርዱ በፖለቲካ ውሳኔ ተቋርጦ ሰኔ 16 ቀን 2010 ሲፈታ ግን ሥራ አጥ አካል ጉዳተኛ ሆኖ ነው ወኅኒን የተሰናበተው። ከፍያለው እንደሚናገረው ለደረሰበት ጉዳት ተጠያቂ የሆነ አካል እስካሁን የለም። ለደረሰበት ጉዳት ያገኘው ካሣም ሆነ ይቅርታ የለም። ይሁንና እሱና ችላ የተባሉት መሰሎቹ ራሳቸውን በራሳቸው መልሰው ለማቋቋም እየተፍጨረጨሩ ነው፤ የቀድሞ እስረኞች ማደራጃ ማኅበር የተባለ ሲቪል ማኅበር መሥርተው በደላቸው ያልተነገረላቸውን ጉዳተኞች በማሰባሰብ እና በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሒደትም የበኩላቸውን ተሳትፎ ማድረግ የሚችሉበትን ዕድል ለመፍጠር ምዝገባ ፈፅመዋል። ማኅበራቸው መንግሥት ጉዳተኞቹን መልሶ ለማቋቋም ሊያደርገው ይገባ የነበረውን ሊሠራ የተቋቋመ እንደሆነ ከፍያለው ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
ደረጃው ይለያይ እንጂ ባለፉት ዓመታት ውስጥ በበርካታ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶች ውስጥ ያለፉ ብዙዎች ናቸው። ከዕድሜዋ ከ9 ዓመታት በላይ በፖለቲካ እስር የተሰረቀባት ጫልቱ ታከለ፣ ከራሷ አልፎ ቤተሰቧ የተበተነባት እማዋይሽ ዓለሙ እና ሌሎችም የግፉ ሰለባዎች ናቸው። ዮናስ ጋሻው በ2008 አማራ ክልል ውስጥ ከነበረው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ከታሰረ በኋላ በደረሰበት ስቃይ ዘር መተካት እንዳይችል መደረጉን ከመግለጹም በላይ ጤናው በከፍተኛ ቀውስ ላይ ነው። ዮናስ ጋሻው ጥሩ ሕክምና ለማግኘት የገንዘብ አቅሙ ስለማይፈቅድለት፥ በጎፈቃደኞች በበይነመረብ ላይ ገንዘብ ሲያሰባስቡለት ከርመዋል። ለመሆኑ ይህንን ማድረግ የማን ኃላፊነት ነበር? ለደረሰው በደልስ ፍትሕ እንዴት ይገኛል? ከበደል ፈፃሚዎቹስ ጋር ተጠቂዎቹ እንዴት በአንድ አገር በሠላም ሊኖሩ ይችላሉ? እነዚህና መሰል ጥያቄዎች የዚህ ሐተታ መነሻ ናቸው።
ሽግግር እና ፍትሕ
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አሁን የምንገኝበት ጊዜ ከወሳኝ ምዕራፍ መጀመሪያዎች አንዱ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራር ብርሃኑ ነጋ (ዶ/ር) ወቅቱን “ሦስተኛው የለውጥ መታጠፊያ” ሲሉ ይገልጹታል፤ ኢትዮጵያ በ1966ቱ አብዮት ወቅት፣ ቀጥሎም ከ1983ቱ የአገዛዞች ለውጥ ጋር በማወዳደር። ይህ የፖለቲካዊ ለውጥ ሒደት በአግባቡ ካልተመራ ኢትዮጵያ ያለፈው የጭቆና አዙሪት ውስጥ እንደምትገባ የፖለቲካ ተንታኞች እየተነበዩ ነው። በአንድ በኩል፣ ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት በመክሰም ላይ ያለው እና በሕወሓት የበላይነት ቆሞ የነበረው የኢሕአዴግ መንግሥት ለፈፀማቸው በደሎች እና ሰብኣዊ ጥቃቶች ፍትሓዊ ርምጃ ያስፈልጋል የሚል፥ በሌላ በኩል፣ ‘በይቅርታ መሻገር’ የሚሉ ጉዳዮች አነጋጋሪ ሆነው ሰንብተዋል።
ከ1998 ጀምሮ ያሉ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶችን አቃቤ ሕግ በዝርዝር መዝግቦ የማስቀመጥ ሥራ እየሠራ ነው። በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው እየተመረመሩ ያሉ እና በፖሊስ እየተፈለጉ ያሉ አሉ። ከዚያም ውጪ በቀድሞው ስርዓት ውስጥ ወሳኝ ሚና ኖሯቸው አሁንም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች አሉ። እነዚህ ተቃርኖዎች አሁን እየታየ ያለው ለውጥ እና ፍትሕን የማስፈን ጥያቄን እንቆቅልሽ የሚያደርጉ እውነታዎች ናቸው።
‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ምንድን ነው?
‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ምንድን ነው በሚለው ጥያቄ ላይ ወጥ የሆነ መልስ የለም። እንደየዐውዱ እና የአገሩ ሁኔታ ይለያያል። በአፍሪካ እና የአፍሪካ ኅብረት ጉዳዮች ላይ የጥናትና ምርምር ተቋም የሆነው አፍሪካ አማኒ መሥራች ሰለሞን አየለ ደርሶ (ዶ/ር) ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ማለት “አገራት በግጭት፣ በጦርነት፣ አምባገነናዊ በሆነ ስርዓት ውስጥ ከርመው ወደ ሠላም ወይም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግር በሚያደርጉበት ጊዜ የሚደረግ የፍትሕ እና ዕርቅ ሒደት ነው” በማለት ሊያጠቃልሉት ይሞክራሉ።
ይሁን እንጂ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ጽሑፋቸውን የቀይ ሽብር ተጠቂዎች ተሳትፎ በደርግ ባለሥልጣናት የዳኝነት ሒደት ውስጥ ምን ይመስል ነበር እንደነበር በመዳሰስ የጻፉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርት አመርቲ ሰለሞን ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ትርጉም ላይ ወጥ የሆነ ሥምምነት እንደሌለ ይናገራሉ። እንደመምህርቷ “ሁሉንም ትርጓሜዎች የሚያስማማቸው በአንድ በኩል ሽግግር አለ። ይህ ሽግግር ወደ ዴሞክራሲ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ከዚያ በፊት የተፈፀሙ ወንጀሎች አሉ። ፈፃሚው ደግሞ የመንግሥት አካል ሲሆን ነው።”
‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ እነዚህ ላይ ተመሥርቶ አንድም የሕጋዊ ተጠያቂነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ፣ አንድም ደግሞ የተጎጂዎች በደል ያለ ካሣ ወይም እርምት ወይም ይቅርታ እንዳይታለፍ የሚደረግ ፍትሕ የማስፈን ሙከራ ነው። የሆኖ ሆኖ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ዓላማ የመንግሥት ስርዓት ሲለወጥ በቀደመው ጊዜ በነበረው ግጭት ወይም ጦርነት ወይም አምባገነናዊ አስተዳደር ወቅት የተፈፀሙ ዓይን ያወጡ እና ያፈጠጡ ግዙፍ የመብቶች ጥሰቶችን በዝምታ ላለማለፍ እና አስማሚ ፍትሐዊ እርምጃ ወስዶ ለመሸጋገር የመሞከር ሒደት ነው።
አመርቲ ይህንን ለማስቻል መንግሥት የመቅጣት (retributive) ወይም በማስታረቅ የማረም (restorative) መንገዶችን ወይም የሁለቱንም ጥምረት ሊከተል ይችላል ይላሉ።
ይህንኑ የሚያጠናክሩት በእንግሊዝ የኬሌ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር እና የፖለቲካ ተንታኙ አወል ቃሲም አሎ (ዶ/ር) ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት “አምባገነን መንግሥታት የቅቡልነት ምንጫቸው ኃይል በመሆኑ፥ ከአምባገነን ስርዓት ወደ ዴሞክራሲ ስርዓት ሽግግር ሲደረግ አምባገነኖቹ ይፈፅሟቸው የነበሩ ግዙፍ የመብቶች ጥሰቶች ይጋለጣሉ። መንግሥት እነዚህን በዝምታ ቢያልፋቸው የተጠያቂነት አለመኖር ወይም የቂም በቀል ስሜት ሊያኖር ስለሚችል፣ በሁለት መንገድ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ እንዲያገኙ ሊያደርግ ይችላል። የመጀመሪያው በሕጉ መሠረት የወንጀል ድርጊት ፈፃሚዎችን ተጠያቂ ማድረግ ነው። ሁለተኛው፣ የመጀመሪያው በቂ አይደለም ወይም ከድርጊቱ ተሳታፊዎች ብዛት አንፃር ወይም ከድርጊቱ ውስብስብነት አንፃር በመደበኛው የፍርድ ሒደት መዳኘት ስለሚቸግር የሐቅ እና እርቅ መንግድ ሊፈልግ ይችላል።”
‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ዓላማዎች
‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ተቀዳሚ ዓላማ በተለወጠው ስርዓት ውስጥ የተንሰራፋውን ተጠያቂ ያለመሆን (‘ኢምፕዩኒቲ’) ሁኔታ በማስቆም በሕግ የበላይት የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማቋቋም ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው። በተጨማሪም የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶችን መለየት እና ፈፃሚዎቹን ተጠያቂ በማድረግ ጥሰቶቹን ለዘለቄታው ማስቆም፣ ለተጠቂዎች ካሣ ማቅረብ መቻል፣ ለወደፊቱ ሊፈፀሙ የሚችሉ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል፣ የፀጥታ ተቋማትን መልሶ ለማዋቀር፣ ሠላምን ለማስፈን እንዲሁም ግለሰባዊ እና ብሔራዊ ዕርቆችን ለመፈፀም ነው። በጥቅሉ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ በሐቅ ላይ ተመሥርቶ እና ለተጠቂዎች ካሣ እና እፎይታ የማግኛ ዕድል በሚሰጥ መልኩ የወንጀል ፈፃሚዎችን ተጠያቂ በማድረግ የሕግ የበላይነት የሚከበርበት ስርዓት ለመመሥረት የሚያስችል ተቋማዊ ተሐድሶ ማድረግ ማስቻል ነው።
የኢትየጵያ “የሽግግር ጊዜ”
‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ከመደበኛው ወይም ከወትሮው የፍትሕ አሰጣጥ ሒደት የሚለየው የስርዓት ለውጥ ሽግግር ወቅት የሚደረግ እና የፍትሕ አሰጣጡ ሒደትም የቀድሞው ስርዓት ኃላፊዎች የፈፀሙትን ወንጀል በሕግ አግባብ ወይም በዕርቅ መፍታት ነው። ይሁንና በኢትዮጵያ ያለው “የሽግግር ጊዜ” ያልተለመደ መሆን ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ እንዴት ሊሰጥ ይችላል የሚለውን አጠያያቂ አድርጎታል።
በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ የለውጥ ሒደት የሚከናወነው ‘አምባገነናዊ’ን ስርዓት ይመራ በነበረው ገዢው ግንባር (ኢሕአዴግ) አሁንም በሥልጣን ላይ እያለ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል። ሰለሞን አየለ “አሁን ያለንበት ለየት ያለ የሽግግር ጊዜ ነው” ይላሉ። “የቀድሞዎቹ የፍትሕ አካላት ውስጥ የሚሠሩት ሰዎች አሁንም ሥራቸውን አላቆሙም፤ የፍትሕ ሒደቱም በነበረበት ነው የቀጠለው” ይላሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ማካሔድ እንዴት ይቻላል የሚለው ትልቁ የቤት ሥራ ነው የሚሆነው ይላሉ።
የፍትሕ አካላቱ ከወገንተኝነት ያልፀዱ እንደነበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ንግግሮቻቸው ጠቃቅሰዋል። ሚያዝያ 7 ቀን 2010 በሚሌኒየም አዳራሽ ተገኝተው ባደረጉት ንግግራቸው ውስጥ “…የዲሞክራሲ እውነተኛ ጥንካሬ መለኪያና አመላካች ተደርገው ትልቅ ትኩረት ከሚሰጣቸው [ጉዳዮች] መካከል የፍትሕ ስርዓቱ ተቋማዊና ሙያዊ ብቃት ቀዳሚነት እንደሚይዙ ይታወቃል። የሕዝባችን ብሶት ምንጭ የሆኑት የፍትሕ አካላት ነጻነታቸውንና ሙያዊ፣ ሥነ ምግባራዊ ብቃታቸውን ባረጋገጠ መንገድ እንዲሠሩ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተጠያቂ እንዲሆኑና የፍትሕ ስርዓቱ ላይ ለውጥ እንዲመጣ የሚያስችሉ መፍትሔዎችን በመውሰድ አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል” ማለታቸው ይታወሳል።
በዚሁ መሠረት ይመስላል 13 አባላት ያሉት እና በሥሩ በርካታ የሥራ ቡድኖችን ያቀፈ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ የተቋቋመው። ጉባዔው አፋኝ ናቸው በሚል ትችት ሲሰነዘርባቸው የነበሩ አዋጆችን ከማሻሻል ጀምሮ የፍትሕ አካላቱን እስከማዋቀር ድረስ የሚዘልቅ ኃላፊነቶች ተሰጥቶታል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሥራዎች ተከናውነው ሳይጠናቀቁ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ለማካሔድ መሞከር ችግር ሊያመጣ እንደሚችል እና ጉዳዩም ፖለቲካዊ አንድምታ ሊኖረው እንደሚችል ብዙዎች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ አፈፃፀም ስልቶች
‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ በበርካታ ስልተ መንገዶች ሊተገበሩ ይችላሉ። እስካሁን በዓለማችን ውስጥ ከግጭት በወጡ የተለያዩ አገራት በተግባር ላይ የዋሉት መንገዶች ወይም ስልቶችን በተመለከተ የተለያዩ ድርሳኖች እንደሚያመለክቱት በዋነኝነት የክስ እና ፍርድ ሒደት፣ የጅምላ ምኅረት፣ የሐቅ እና/ወይም የዕርቅ ኮሚሽን፣ የካሣ አፈፃፀም እና የተጠቂዎች መታሰቢያ ማኖር ይጠቀሳሉ። እነዚህን ስልቶች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ አሠራር አንፃር የቱ ይተገበራል፣ የቱስ ያስኬዳል በሚል በአጭሩ እንመለከታቸዋለን።
1) ክስ እና ዳኝነት
ይህ ስልት ከሽግግር ጊዜው በፊት በተፈፀሙ ወንጀል አድራጊዎች ላይ መደበኛ የወንጀል ማጣራት አድርጎ ክስ በመመሥረት እና በፍትሐዊ ዳኝነት እንዲቀጡ የማድረግ ስልት ነው። በተለይም ደግሞ እንደ ዘር ማጥፋት፣ በሰብኣዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች እና የጦር ወንጀሎች ሲኖሩ ተመራጭ ነው። የሕግ የበላይነት እንዲከበርም አዎንታዊ አስተዋፅዖ አለው። ይሁንና ከወንጀል ድርጊቱ ውስብስብነት እና ብዙ ሰዎችን አሳታፊነት አንፃር ብቻ ሳይሆን፥ ተጠቂዎች ምስክር ሆነው ከመቅረብ ውጪ በውጤቱ ላይ የመወሰን ወይም የጎላ ተሳትፎ የማድረግ ዕድል ስለማይሰጣቸው በዕርቅ ስሜት የመሻገር ዕድል አይፈጥርም የሚሉ አስተያየቶች አሉ።
እንዲያም ሆኖ የኢትዮጵያ መንግሥት ግዙፍ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ፈፅመዋል በሚል የጠረጠራቸውን 33 ሰዎች በቁጥጥር ሥር አውሎ ቅድመ ምርመራ እያካሔደባቸው ነው። አሁንም በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ የማጣራት ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ የእስር ዘመቻ በ‘ሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ዓይን ሊታይ ይችላል፣ አይችልም የሚለው እያነጋገረ ነው። ሰለሞን አየለ የሰሞኑን እስር ከ‘ሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ አንፃር ለመመልከት “የዳኝነት ሒደቱ በወትሮው የፍርድ ሒደት እየተካሔደ ነው ወይስ በተለየ መንገድ?” የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት አለበት ይላሉ። አክለውም “በሒደቱ ላይ ግልጽነት ይጎድላል፤ ስለዚህ እንዲህ ነው አይደለም ለማለት ይቸግራል” ይላሉ። አመርቲም በበኩላቸው እስካሁን እየተደረገ ያለው በሙሉ ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ “አሁን ባለው ሁኔታ ሕዝቡ ዝም ብሎ ነው የሚያየው” ብለዋል፤ ይሁን እንጂ “ሽግግር አለ ለማለት የሚያስችሉ ነገሮች አሉ፣ ባለፉት ዓመታት ተፈፅመዋል የተባሉ በርካታ ወንጀሎች አሉ፣ ወንጀሉን የፈፀሙት የመንግሥት ኃላፊዎች ሥልጣናቸውን ተገን አድርገው ነው ተብሏል። በሚዲያ የተነገረውም በዚሁ ምክንያት ነው የታሰሩት በሚል ነው። ስለዚህ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ አካል ነው ማለት ይቻላል። ነገር ግን ይህ አይበቃም፤ ብዙ ማኅበረሰቡን ማሳተፍ ያለባቸው ጉዳዮች አሉ።”
በሌላ በኩል የአሁኖቹ እስሮች በርካታ የወንጀሎቹ ፈፃሚዎችን እና ተባባሪዎችን ያላካተተ፣ መዋቅራዊ የተቋም ለውጥ ባላካሔደ የፍትሕ ስርዓት ውስጥ የሚያልፍ መሆኑ ከትችት አልዳነም። እንዲያውም ከዚህ በፊት በ1983 ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲቆጣጠር በደርግ ኃላፊዎች ላይ ከወሰደው እርምጃ የማይለይ “የአሸናፊዎች ተሸናፊዎችን የመቅጣት” ዓይነት እርምጃ ነው የሚሉም አሉ። “ባለፈው ስርዓት ጉልሕ ተሳትፎ ኖሯቸው ያልታሰሩ ሰዎች አሉ” በሚል “ለውጡን ያልደገፉትን መምቻ” እንጂ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ባሕሪ የለውም የሚል ትችት ደርሶበታል።
2) የጅምላ ምኅረት
የጅምላ ምኅረት በቀደመው ስርዓት የተፈፀሙ ወንጀሎችን በሙሉ በይለፍ እና በይርጋ ለመርሳት የመሞከሪያ መንገድ ሲሆን፥ “ለመንግሥት የሕዝብን ጥቅም ከሚነኩ ወንጀሎቹ ይቅርታ በማድረግ ማለፍ ነው” በሚል አመርቲ ሰለሞን በጥናታቸው ላይ ጽፈዋል። ይሁን እንጂ የጅምላ ምኅረት የሕጋዊ ተጠያቂነትን ነገር ያንኳስሳል፤ የቂም በቀል ስሜትን አይሽርም በሚል ይወቀሳል። አመርቲ ሰለሞን “እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ሠላም እና ፍትሕን ለማመቻመች (‘ቱ ኮምፕሮማይዝ’) የሚደረግ ነገር ነው” ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣነ መንበሩ የመጡባቸው የመጀመሪያ ሳምንታት ላይ ያደርጓቸው የነበሩ ንግግሮች ያመለክቱ የነበሩት የጅምላ ምኅረት አዝማሚያ ቢሆንም፥ ከወራት በኋላ የተካሔዱት በትልልቅ የሙስና እና የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት የተጠረጠሩ ሰዎች መታሰር የጅምላ ምኅረት እንደሌለ አመላክተዋል። ይህም ሆኖ የጅምላ ምኅረት አለመኖሩ ያስቆጣቸው አካላት አሉ። የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የእስሩን ዜና ተከትሎ በሰጡት መግለጫ “ነገሩ ከሰብኣዊ መብትና ሙስና ጥያቄዎች ወጥቶ ይህንን ሕዝብ ወደ መምታት የፖለቲካ እርምጃ ሔዷል፤ ለዚህም ነው አንቀበለውም ያልነው” በማለት እስሩን ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ሳይሆን የፖለቲካ አድርገው እንደሚረዱት ያመለከቱት።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጨምረውም “በኢሕአዴግ ውስጥ ይቅርታና ምኅረት ለሁሉም እንዲሆን ነበር የተወያየነው። አንዱን እየፈታህ ለሌሎቹ አታስርም፤ በተለያዩ ወንጀሎች የተፈረደባቸው በምኅረት ሲለቀቁ ካሁኑ መልክ ይያዝ ነው ያልነው። ካልሆነ ግን የተለቀቁት ተመልሰው እንዲያዙ ነበር የተባባልነው” በማለት ምኅረት ተደርጎላቸዋል ብለው የሚያምኑት የፖለቲካ እስረኞች የነበሩትን እና በቅርቡ ከእስር የተለቀቁትን ተጠቂዎች መሆኑን አመላክተዋል።
3) የሐቅ ወይም/እና ዕርቅ ኮሚሽን
ይህ ‘ የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ማስፈፀሚያ ስልት በተለይ ተጠቂዎችን አሳታፊ በመሆኑ የተለየ እና ለወንጀል ፈፃሚዎችም ሐቁን በአደባባይ በመናዘዝ በይቅርታ እና ዕርቅ ችግሮች እንዲፈቱ የሚሞከርበት መንገድ ነው። በሕጋዊ ዳኝነት እና በጅምላ ምኅረት መሐል አማካይ መፍትሔ የሚፈለግበት ስልት ነው። እንደዚህ ዓይነት ኮሚሽኖች በጊዜያዊነት፣ የፍትሕ ስርዓቱ አካል ባልሆኑ ተቋማት፣ በመንግሥት እና ዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰብ ጥረት ሐቁን ለማውጣት፣ ተጠቂዎች የደረሰባቸውን ግፍ የመናገሪያ መድረክ እንዲያገኙ ዕድል የሚሰጥ ስልት ነው። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የዕርቀ ሠላም ኮሚሽን” ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በኅዳር 26 ቀን 2011 ያወጣ ሲሆን፥ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የሐቅ ወይም/እና ዕርቅ ኮሚሽን በብዙ አገራት ተሞክሮ መልካም ውጤት ያመጣ ቢሆንም፥ የኢትዮጵያው ረቂቅ ግን በርካታ አደናጋሪ አናቅፅት የያዘ ነው። የረቂቁ መግለጫ እንደሚያመለክተው ኢሕአዴግ “ጥል ሳይሆን የፖሊሲ ልዩነት ነው ያለው” በሚል የዕርቅ ኮሚሽን ጉዳይ ከዚህ በፊት እንዳልታሰበበት ከገለጸ በኋላ፣ “ላለፉት በርካታ ዓመታት እርስ በእርሳችን ስንዋጋ፣ አንዱ ሌላውን ሲበድል እና ሲያቆስል ከመቆየቱ የተነሳ የውጭ ወራሪዎች ካደረሱብን ሰብኣዊና ቁሳዊ ጥቃት ይልቅ እርስ በእርሳችን አንዱ በሌላው ላይ ያደረሰው ጉዳት በብዙ እጥፍ ይበልጣል” በሚል፣ “በሐሳብ ልዩነትም ይሁን በብሔር ሥም ተቧድነን ተገዳድለናል። ስለሆነም አንዱ በሌላው ላይ ቂምን ቋጥሯል። አንዱ ሲያሸንፍ ሌላው ቂም ይዞ ለበቀል ቀንን ይጠብቃል።” በማለት የዕርቀ ሠላም ኮሚሽኑ ዓላማ በሕዝቦች መካከል ለዕርቅ እንደሚሠራ አመላክቷል።
የሐቅ ወይም/እና ዕርቅ ኮሚሽን በዳይ በደሉን አምኖ በመናዘዝ ይቅርታ የሚጠይቅበት፣ ተበዳይ የደረሰበትን ተናግሮ ይቅርታ የሚያደርግበት መድረክ እንደመሆኑ ሕዝቦች መካከል ዕርቅ ለመፍጠር መሞከር የማኅበረሰብ ክፍሎችን በዳይ ተበዳይ በማሰኘት የሌላ ጭቅጭቅ መንስዔ እንዳይሆን ያሰጋል። አመርቲም ይህንን አስመልክተው ሲናገሩ “ዕርቁ ማንን ከማን ነው? ተጠቂውን ጥቃት ከፈፃሚው ግለሰብ ወይስ ሕዝብን ከሕዝብ?” በማለት ይጠይቃሉ።
የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በሌላ በኩል እንደሚያመለክተው “የኮሚሽኑ ዓላማ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ሠላም፣ ፍትሕ፣ ብሔራዊ አንድነትና መግባባት፣ እንዲሁም ዕርቅ እንዲሰፍን መሥራት ነው”። በዚሁ መሠረት የሚሰጡት ተግባራት ዝርዝር ሕዝብን ከሕዝብ እስከ ማስታረቅ የሚደርስ የቤት ሥራዎች ይኖሩታል።
4) የካሣ ስርዓት
ይህ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ማስፈፀሚያ ስልት ተጠቂ ግለሰቦች እና ቤተሰቦቻቸው ካሣ እንዲጠይቁ በማስቻል ጥገናዊ ፍትሕ ለማስፈን የሚሞከርበት ስልት ነው። ይህ ግን ተጠቂዎች ለደረሰባቸው ጥቃት በቁስ የማይተመኑ ጉዳቶች ፍትሕ መስጠት የማያስችል ከመሆኑም በላይ ተበዳዮች የደረሰባቸውን በመናገር የሚተነፍሱበት ዕድል፣ ወንጀለኞችም በመናዘዝ አሊያም ሕጋዊ ቅጣት በመቀበል ተጠያቂ የሚሆኑበትን በር ይዘጋል። በ‘ሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ላይ ጥናት የሚያደርጉት የሕግ መምህርና አማካሪ አዲ ደቀቦ እንደሚሉት፣ ጉዳዩን በካሣ ብቻ ለመዝጋት መሞከር ፍትሕን በገንዘብ እንደማምለጥ ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ አወል ቃሲም “ጥቃት የደረሰባቸው ዜጎች ካሣ የማግኘት መብት እንዳላቸው መዘንጋት የለበትም” ይላሉ።
5) የተጠቂዎች መታሰቢያ ማኖር
ስርዓቶች እንዲለወጡ ወይም እስኪለወጡ ድረስ በርካታ ሰዎች በመስዋዕትነት ያልፋሉ። ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ለነዚህ መስዋዕት ለሆኑ ዜጎች መታሰቢያ በማኖር በአንድ በኩል ለመስዋዕትነታቸው መታሰቢያ፣ በሌላ በኩል ድርጊቱ እንዳይደገም ለማሳሰብ መታሰቢያ ሐውልቶችን፣ ሙዚዬሞችን ማኖር የለመደ ነው። በኢትዮጵያ የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም በሚል የተቋቋመው ለዚህ አገልግሎት ቢሆንም በፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ዓላማውን በትክክል የሚገልጽ ሙዚየም አልተገነባም የሚል አስተያየት ይደመጣል።
በዚህ የኢትዮጵያ “የሽግግር” ጊዜ መጀመሪያ ላይ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ ሲታወጅ በሰብኣዊ መብቶች መጣሺያ ማዕከልነት ለሦስት ስርዓተ መንግሥታት አገልግሎት የሰጠው “ማዕከላዊ” ሙዚየም እንደሚሆን ተነግሯል። ይህ ተግባራዊ ሲሆን ትዕምርታዊ ማስተማሪያ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል። ይሁን እንጂ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ለማስቆምም ሆነ ለደረሱ ጥቃቶች አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ እንዲሁም ጥቃቱ የደረሰባቸውን ለመካሥ ምንም ሚና አይኖረውም።
ከነዚህ ውጪ የፍትሕ እና የፀጥታ አካላቱን መልሶ ማወቀርን እንደ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ እርምጃ የሚቆጥሩት አሉ። ይሁን እንጂ የትኛውም ስልት ተተገበረ የትኛውም ስልት ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ እንደሆነ አጥኚዎች ይናገራሉ። አወል ቃሲም (ዶ/ር) እንደሚሉት ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ አሰጣጥን ጉዳይ “በጥንቃቄ መተግበር ካልተቻለ ‘ለሽግግሩ’ ራሱ እንቅፋት ሊሆን ይችላል።”
ተመራጩ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’
ይሔንኛው ስልት ከዚያኛው ስልት የተሻለ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ይሰጣል የሚል መደምደሚያ የለም። ሰለሞን አየለ (ዶ/ር) “ዋናው ቁምነገር ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ የሚሰጥበትን አካሔድ ፍኖተ ካርታ (‘ሮድማፕ’) ማዘጋጀት ነው። አሁን ግን ግልጽነት የጎደለው አካሔድ ስላለ የትኛው እርምጃ ምን እንደሆነ ለመረዳት አስቸጋሪ ሆኗል” ይላሉ። መምህርት አመርቲ ሰለሞን “ሁሉንም ያጣመረ መፍትሔ መፈለጉ ከሁሉም የተሻለ ነው” ይላሉ። በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ምሁራን በሙሉ የሚያስጠነቅቁት ግን “ተጠቂዎች በሒደቱ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑበት እና የደረሰባቸውን የሚናገሩበት መድረክ መመቻቸት አለበት” የሚለውን ነው። ይህንን አስመልክቶ ከአዲስ ማለዳ የትኛው ቢተገበር ይሻላል በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው እና ሁለቱንም እግሮቻቸውን በእስር ወቅት በግፍ ያጡት ከፍያለው ተፈራ “ከመርማሪዎች ጀምሮ የሰው ሕይወት የሚያበላሽ ፍርድ እየፈረዱ የኖሩ ዳኞች በሙሉ ሕዝብ ፊት ቀርበው ይቅርታ እንዲጠይቁ ቢደረጉ፣ ካልሆነ ግን ለሕጋዊ ተጠያቂነት ቢቀርቡ” በማለት የተጣመረው መፍትሔ የተሻለ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here