በቤንሻንጉል ጉምዝ በባምባሲ ወረዳ በተፈጠር ግጭት የ10 ሰዎች ሕይወት አለፈ

0
385

በቤኒሸንጉል ጉምዝ አሶሳ ዞን በባምባሲ ወረዳ በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው ማህበረሰብ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ።

የክልሉ የወንጀል መከላከል ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ጃሮ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ችግሩ የተፈጠረው ግንቦት 26/2012 ሲሆን፣ በእለቱ በባምባሲ ወረዳ የፀጥታ አካላትና ሕገ ወጥ ተግባር ለመፈጸም በእንቅስቃሴ ላይ በነበሩ ወጣቶች መካከል በተፈጠረው አመግባባት ወጣቶች የፀጥታ ኃይሎችን የማገትና መሳሪያ የመንጠቅ ሙከራ በማድረጋች የፀጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ የሶስት ሰዎች ሕይወት ወዲያውኑ በርካቶች ቆስለው የነበረ ሲሆን አስካሁን የሟቾች ቁጥር 10 መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።

በግጭቱ ከ10 ሰዎች ሂወት ህልፈት በተጨማሪ ሦስት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን እንዲሁም ሰባት ቤቶች መቃጠላቸውን እና አንድ የመንግስትና አንድ የግለሰብ ኹለት ተሸርካሪዎች ላይ የንብረት ውድመት ማጋጠሙን ምክትል ኮሚሽነሩ ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ተናግረዋል።

በችግሩ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ ተጠርጣሪ አካላት ውስጥ እስካሁን አንድ የወረዳው የፖሊስ አባልና አንድ የክልሉ ልዩ ኃይል በግድያው ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፤ ተጨማሪ 37 ሰዎች ከረብሻ እና ሕገ ወጥ ተግባር ጋር በመሳተፍ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና ሌሎች 17 ተጠርጣሪዎች ያልተያዙ እንዳሉ ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

በተፈጠረው ችግር የፀጥታ ኃይል የተወሰደው እርምጃ ተገቢነት ላይ መጠየቅ ያለበትን አካል ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
የችግሩ መነሻ መንስኤ በተለምዶ በአካባቢው ማህበረሰብ ብዝሀ ሕይወት በመባል የሚታወቅ ደን ላይ በአካባቢው በሚኖሩ ሰዎች የእርሻ ሥራ እየተከናወነ ነው በሚል በአቅራቢያው በሚገኙ የቀበሌ 48 ወጣቶች በደኑ ውስጥ የእርሻ ሥራ ያከናውናሉ የተባሉ ሰዎችን ለማጥቃት በሚጓዙበት ጊዜ የወረዳው ፖሊስ ጥቃቱን እንዳያደርሱ በመከልከሉ የተነሳ ፀብ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል።

ኮሚሽነሩ እንደሚሉት የፀቡ መነሻ ነው የተባለው ደን የአካባቢውን ማህበረሰብ በማያጣላ መልኩ የህግ የበላይነትን ባማከለ መልኩ በህግ አግባብ መፈታት ያለበት ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል። ብዝሃ ሂወት በሚባለው ደን ላይ ተከናውኗል የተባለው የእርሻ ሥራ በአካባቢው ባለው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል። የሚነሳው የመልካም አስተዳደር ቸግርም አርሶ አደሮች ልጆቻችን ተምረው ሥራ አጥነት ብዝቷል የምናርሰው የእርሻ መሬት የለንም ይሰጠን የሚሉ ቅሬታዎች መሆናቸው ተጠቁሟል።

በቦታው ላይ የሚገኙ የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደሚሉት ችግሩ የተፈጠረው እና የሰው ሕይወት የጠፋው በመንግስትን ልዩ ኃይሎችና በህብረተሰቡ መካከል ቢሆንም፣ በመንግስት ልዩ ኃይል የተገደሉት ሟቾችን ማንነት ተከትሎ ችግሩ የብሔር መልክ እንዲይዝ አድርጎታል ብለዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ጃሮም የችግሩን የብሔር መልክ ለማስያዝ ልዩ ፍላጎት ባላቸው ሰዎች እንደተሞከረ አምነው፣ አሁን ላይ የብሔር መልክ የያዘ ለማሰመሰል የተሞከረው ሙከራ የዞኑና የወረዳው ፖሊስ ከክልሉ መንገስት የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የማህበረሰቡን ሰላም ወደ ነበረበት እንደተመለሰ ጠቁመዋል።

በአካባቢው ማህበረሰብ መካከል በተፈጠረው ክፍተት ሌላ ችግር እንዳይፈጥርና ማህበረሰቡን ለማግባባት ትናንት አርብ ሰኔ 5/2012 ህዝብ ለህዝብ ኮንፈረንስ መካሄዱን መክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። አሁን ላይ የአካባቢው ማህበረሰብ በመረጋጋት የግብርና ሥራውን እያከናወነ መሆኑን መታዘባቸውንም ምክትል ኮሚሽነሩ ተነግረዋል።

በወረዳው ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ግጭቶች የሚስተዋሉበት እና የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፍ እና ንብረት መውደም ምክንያት የሆኑ አለመረጋጋቶች መከሰታቸው የሚታወስ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here