በአማራ ክልል የጠብ መንጃ ሽያጭ ተጧጡፎ ሰንብቷል

0
953

በአማራ ክልል በግላቸው ለሚታጠቁ ነዋሪዎች የጠብ መንጃ መያዣ ሕጋዊ ፈቃድ ሲሰጥ ሰንብቷል። በዚህም በርካታ አርሶ አደሮች የእርሻ በሬዎችን ሳይቀር እየሸጡ መሣሪያን እስከ 100 ሺህ ብር ሲገዙና የክልሉን መንግሥት የመሣሪያ ይዞ መንቀሳቀሻ ሕጋዊ ፈቃድ ሲጠይቁ እንደበር ተሰምቷል።
አዲስ ማለዳ በክልሉ ከሚኖሩ የተለያዩ ምንጮቿ እንዳረጋገጠችው በተለያዩ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም በኅቡዕ ይሸጥና ይያዝ የነበረው ጠብ መንጃ በይፋ ሲሸጥና ለሕጋዊ የጦር መሣሪያ ያዥነት ፈቃድ ሲቀርብ ነበር። ክልሉ የመሣሪያ ፈቃድን ለመስጠት ማስታወቂያ ማውጣቱን ተከትሎ ጠብ መንጃን የሚገዙ ሰዎች በየቦታው የፍተሻ ተኩስ ሲያሰሙ መሰንበታቸውንም ምንጮቻችን ተናግረዋል።
ማስታወቂያው መውጣቱን ተከትሎ ‹‹ድብቅ መሣሪያ›› የነበራቸው ግለሰቦች ሕጋዊ ፈቃድ ለማውጣትና መሣሪያቸውን በይፋ አንግቦ ለመንቀሳቀስ የሚስችላቸውን ሕጋዊነት ለማግኘት ወደየወረዳቸው አስተዳደር ሲቀርቡ እንደነበር ተጠቅሷል። ምንጮቻችን እንደሚሉት አጋጣሚውን በመጠቀም መሣሪያ መግዛት የሚፈልጉ ግለሰቦችም የእርሻ በሬዎችን ሳይቀር እየሸጡ በከፍተኛ ዋጋ የተለያዩ ጠብ መንጃዎችን ሲገዙና ሲያስፈቅዱ ነበር። በዚህም አንድ ክላሸንኮቭ ከ80 ሺሕ እስከ 100 ሺሕ ሲሸጥ እንደ ምንሽር እና መዉዜር ያሉ ኋላቀር የሚባሉት መሣሪዎቸ ደግሞ እስከ 30 ሺሕ ብር ሲሸጡ እንደነበር ታውቋል፡፡ በክልሉ ጃዊ የሚባል ወረዳ በጋራዥ ሥራ ላይ መሠማራቱ የተነገረለት አንድ ግለሰብ የራሱ ፈጠራ የሆነን ‹‹20 ጥይት ጎራሽ›› ክላሸንኮቭ ሰርቶ ማስፈቀዱም በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች መነጋሪያ ሆኖ ሰንብቷል። አንዳንድ አካባቢዎች የነበሩ የመሣሪያ ፍተሻ ተኩሶችም ለነዋሪዎች ስጋትን ሲፈጥሩ እንደነበር ተጠቅሷል።
ስለ ጉዳዩ አዲስ ማለዳ የጠየቀቻቸው የክልሉ መንግሥት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አሰማኸኝ አስረስ የመሣሪያ ፈቃድን መስጠት ያስፈለገው ሕገ ወጥነትን ለመከላከል ነው ያሉ ሲሆን የማስፈቀጃ ጊዜው እስከ ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 17 ድረስ ተራዝሞ መቆየቱን አክለዋል። ይሁንና እስከ ረቡዕ ድረስ ምን ያህል ግለሰቦች ፈቃድ ወሰዱ በሚሉትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት አልፈቀዱም።
በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ አያያዝን በተመለከተ ግልጽ የሕግ ማዕቀፍና የአሠራር ሥርዓት ባለመኖሩ የፀጥታ ኃይሉ ለመቆጣጠር ጭምር የማይችልበት ሁኔታ ላይ ደርሶ እንደነበር የገለጸው የፌደራሉ መንግሥት የመሣሪያ ዝውውርና አያያዝን የሚገዛ የሕግ ማዕቀፍ እየተረቀቀ መሆኑን አሳውቋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በይፋዊ የማኅበራዊ ገጹ እንደገለጸው የጦር መሣሪያ አያያዝና ቁጥጥርን በተመለከተ የተቀመጠ አዋጅና መመሪያ ባይኖርም ለጊዜውም ቢሆን ድርጊቱ እንዳይፈፀም ከአገር አልፎ ከጎረቤት አገሮች ጋር ሲሠራበት ቆይቷል። በኢትዮጵያ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያስረዳሉ።
የጉዳዩን አሳሳቢነት መንግሥትም ስላመነበት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በአንድ ማዕከል ኃላፊነት እንዲሠጠው ሆኖ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር አዋጅ የማርቀቅ ሥራ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እየተካሄደ መሆኑ ተጠቅሷል። ረቂቁ በአብዛኛው የተጠናቀቀ በመሆኑ በ2011 ወደ ተግባር እንደሚገባም ይጠበቃል ነው የተባለው።
እንደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መረጃ ለሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ምክንያት ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ወቅታዊ የሰላምና ደኅንነት ጉዳይ እንዲሁም ሰላሟን የማይፈልጉ ወገኖች ጫና ነው።
ሕገ ወጦች አጋጣሚውን ተጠቅመው ከጦር መሣሪያ ትርፍ ለማግኘት የሚሻሻጡበት መንገድም ሌላው ምክንያት ነው የተባለ ሲሆን ማኅበረሰቡ ከጦር መሣሪያ ጋር ያለው ቁርኝት እና ጠብ መንጃ እንደ አንድ ሀብት መለኪያ መወሰዱ ዋነኛው ጉዳይ መሆኑ ተጠቅሷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here