ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ የ250 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የድጋፍና የብድር ስምምነት በዛሬው በሰኔ 11 2012 ተፈራርመዋል።
ስምምነቱንም የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ እና በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ካሮልይን ቱርክ ፈርመውታል።
የገንዘብ ድጋፍና የብድር ስምምነቱ በመተግበር ላይ ያለው የኢትዮጵያ እድገትና የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት መርሐ ግብር ፖሊሲ ማስፈፀሚያ የሚውል መሆኑም ተገልጿል።
የድጋፍና የብድር ስምምነቱ በአጠቃላይ 250 የአሜሪካ ዶላር ወይም 8 ነጥብ 61 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከዚህም 125 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በብድር መልክ፣ 125 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደግሞ በድጋፍ የሚለቀቅ ነው።
እንደዚህ ዓይነቱ የድጋፍና የብድር ስምምነት በኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ ሚና በማስፋፋት ኢኮኖሚዋ እንዲያንሰራራ እና ዘላቂ ልማት ለማምጣት የሚረዳ መሆኑን ባንኩ አስታውቋል።
እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ እና መልካም አስተዳደር ተግባራትን በማስፈን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሽግግር የሚያፋጥን መሆኑም ተመልክቷል።
በአጠቃላይ የገንዘብ ድጋፍና ብድር ስምምነቱ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የሪፎርም ተግባራት እንዲሁም የሀገር በቀል ኢኮኖሚውን ተግባራዊነት ለማፋጠን የሚረዳ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም መንግሥት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሚፈጠሩ የፋይናንስ እጥረቶችን እንዲሸፍን እና በወረርሽኙ ምክንያት በኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳ ላይ የሚፈጠር ጫናን ለማቅለል እንደሚረዳ ተገልጿል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012



