መንግሥት ሊያከናውናቸው ቃል ከገባቸው ዘርፎች ውስጥ የፍትሕ ስርዓቱን ነጻና ፍትሐዊ አድርጎ መልሶ ማዋቀር አንዱ ነው። በዚህ ረገድ በርካታ አዎንታዊ እርምጃዎች እየተሔዱ ነው። ፍቃዱ አዱኛ እነዚህን ሒደቶች መነሻ በማድረግ የፍትሕ ተቋማትን ነጻ ለማድረግ የሚያስፈልጉ እርምጃዎችን በዚህ ጽሑፍ ጠቁመዋል።
አሁን ባለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ በተለይም በኢሕአዴግ ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣኑን የያዘው የለውጥ ኃይል፣ በተለያዩ ጊዜያት ኢሕአዴግ ‘ተሐድሶ አድርጌአለሁ’፣ ‘ተለውጫለሁ’፣ ‘መጪው ጊዜ ከእኛ ጋር ብሩህ ነው’ ከሚል የተስፋ ዳቦ ለየት ባለ መልኩ በትክክልም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ተጨባጭ የሆኑ የለውጥ እርምጃዎን መውሰድ የጀመረ ይመስላል። ይህንኑ በመንተራስ በዚህ ጽሑፍ በቅርቡ በተለይም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንትን በአዲስ አመራር በመለወጥ ‘ሀ’ ተብሎ የተጀመረውን በፍትሕ ስርዓት ማሻሻይ ዙሪያ የሚኖሩ ተግዳሮቶች፣ ተቋማዊ የቀጣይነት ጥያቄዎችና መፍትሔዎችን ለመዳሰስ እሞክራለሁ።
የነጻና ገለልተኛ የዳኝነት አካላት አስፈላጊነት
ፍርድ ቤቶች ከሁለቱ የመንግሥት (ሕግ አውጪ እና አስፈፃሚ) አካላት በተለየ መልኩ ነጻና ገለልተኛ ሆነው ሕግን የመተርጎም ሥራ እንዲሠሩ የሚጠበቅባቸው የዳኝነት አካላት ናቸው። ፍርድ ቤቶች ነጻ መሆን አለባቸው ሲባል በዋነኛነት አሠራራቸው ከአስፈፃሚው አካል ወይንም በተለምዶ መንግሥት ከሚባለው ኃይል ተፅዕኖ ሥር እንዳይወድቅ ከሚል መርሖ በመነሳት ነው። ለዚህ መሕ በዋነኝነት የሚጠቀሰው ምክንያት መንግሥት ወይም አስፈፃሚው አካል ራሱ እንደ አንድ ተቋም በፍርድ ቤቶች ውስጥ ግለሰቦችን ሊከስ ወይም በዜጎች ሊከሰስ ስለሚችል ነው። መንግሥት የዜጎችን መሠረታዊ መብት ሲጥስና ሲጋፋ ተበድለናል ብለው ፍትሕን ፍለጋ ሊሔዱበት የሚችሉት ተቋም ፍርድ ቤት ነው። መንግሥትም በሕግ አውጪው አካል የወጡት ሕጎች በዜጎች አልተከበሩም ወይም ተጥሰዋል ብሎ ሲያምን አጥፊዎችን ለማስቀጣት ክስ የሚመሠርተው በእነዚሁ ፍርድ ቤቶች ነው። ስለሆነም በመንግሥት ተፅዕኖ ሥር የወደቀ ፍርድ ቤት የሕዝቦችን መብቶችና ነጻነት ቸል በማለት ለመንግሥት ጥቅም ብቻ ዘብ ስለሚቆም ፍርድ ቤቶች ከአስፈፃሚው አካል ተፅዕኖ ነጻ ሆነው መዋቀራቸው ለዴሞክራሲያዊ መንግሥት ግንባታ የእስትንፋስ ያህል አስፈላጊ ነው። ፍርድ ቤቶች ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት የሚችሉት በተለይም ጠንካራ ጉልበት ካለው አስፈፃሚ አካል ተፅዕኖ ውጪ በመሆን ማስረጃ መዝነው፣ ምስክሮች ሰምተው እና ሕግና ሕግን ብቻ ተንተርሰው ፍትሕን መስጠት የሚችሉበት ነጻነት ላይ ሲገኙ ነው።
ነጻ የዳኝነት አካል እንዴት ሊቋቋም ይችላል?
የፍድ ቤቶችን ነጻነት ከሁለት አቅጣጫዎች መመልከት ተገቢ ይሆናል። የመጀመሪያው የነጻነት ዕሳቤ ፍርድ ቤቶች እንደተቋም ከመንግሥት አሠራርና መዋቅራዊ የዕዝ ሰንሰለት ውጪ እንዲቋቋሙ የሚያስገድደው የተቋማዊ ነጻነት መርሕ ነው። ይህም አስፈፃሚው አካል ፍርድ ቤቶችን በቀጥታ የማዘዝም ሆነ የመቆጣጠር ሥልጣን እንዳይኖረው፣ በሚሰጡት ውሳኔም ሆነ በሚከተሉት የአሠራር ሒደት ጣልቃ መግባት እንዳይችል ያደርጋል። ይህ ማለት ታዲያ ፍርድ ቤቶች ከመንግሥት ጋር ምንም ግኝኙነት የሌላቸው ተቋማት ሆነው ይመሠረታሉ ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያክል ዳኞች በአስፈፃሚው አካል አቅራቢነት በሕግ አውጪው መሾማቸው የዳኝነት አካላት ከቀሪዎቹ የመንግሥት አካላት ጋር ያላቸውን ጤነኛ ግንኙነት ያሳየናል።
ሁለተኛው የነጻነት መርሕ ግለሰባዊ ነጻነት ሲሆን፣ ከተቋማዊ ነጻነት በተለየ መልኩ በፍርድ ቤቶች የሚሾሙ ዳኞችን ግለሰባዊ ነጻነት ይመለከታል። ዳኞች እጅግ ከፍ ያለውን የሥነ ምግባር፣ የዕውቀትና የክኅሎት ደረጃ እንዲኖራቸው የሚጠበቅ ሲሆን የሥራ ኃላፊነታቸውም በዜጎች ሕይወት፣ ንብረትና ነጻነት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ የሚኖረው የሚሰጡት ውሳኔም በአገር ኅልውና ላይም ጭምር ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው። ለዚም ነው በደኅንነታቸው እና በገቢያቸውም ጭምር ነጻነታቸው እንዲጠበቅ የሚፈለገው። ዳኞች ከተፅዕኖ ፍፁም ነጻ ሆነው በግለሰብ ደረጃ ያላቸውን ፖለቲካዊም ሆነ ሃይማኖታዊ አቋም ወደ ጎን በመተው ለሕግና ለሕሊናቸው ብቻ መገዛት ይኖርባቸዋል። ዜጎችን በዘር፣ በኢኮኖሚ ደረጃ፣ በፆታም ሆነ በሌላ ማናኛውም መሥፈርት ለይቶ መጥቀምም ሆነ የመጉዳት ፍላጎትና ባሕሪ የሌላቸው ዳኞች መሾማቸው ከተቋማዊው ነጻነት ጎን ለጎን የዳኝነት አካሉን ነጻ ገለልተኝነት የሚያረጋግጥ ይሆናል።
አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
በ1987 የፀደቀውን ሕገ መንግሥት ተከትሎ በፌደራል ደረጃ ሦስት እርከን ያለው የፍርድ ቤት መዋቅር ተዘርግቷል (በክልሎች ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በዚ ጽሑፍ አይዳሰስም)። የፌደራል የመጀመሪያ፣ ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ያላቸው ሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 25/1988 እና በማሻሻያው ላይ የተገለጸ ሲሆን የፍርድ ቤቶቹን ዳኝነት ሥልጣን መተንተን ባለመሆኑ ቀድመን ካነሳነው ተቋማዊና ግለሰባዊ ነጻነት ጋር ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመፈተሸ እሞክራለሁ።
የኤፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 78/1 ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንደሚቋቋሙ መገለጹ ቢያንስ በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ገለልተኛ እና ነጻ ፍርድ ቤቶችን እንድንጠብቅ ሊያደርገን ቢችልም እውነታው ግን መፈተሽ ያለበት በተግባር ላለፉት ዓመታት ከነበሩ ሁኔታዎች አንፃር ነው። ከዚህ አንፃር ፍርድ ቤቶቹ በተግባር ነጻና ገለልተኛ ስላለመሆናቸው አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ለዚህ ማረጋገጫ የሚሆኑ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ የሚቻል ቢሆንም ከመንግሥት ተፅዕኖ ውጪ ሆኖ የዜጎችን ድምፅ በእኩልነት የሚያዳምጥ እና ፍትሕ ሲሰጥ የነበረ የዳኝነት አካል አለመኖሩን መንግሥትም በአደባባይ አምኖ የተቀበለው እውነታ ነው።
በሌላ በኩል፣ የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች አሿሿምን ስንመለከት ግልጽና ወጥነት ያለው መሥፈርት የሌለ ከመሆኑም በላይ፣ በግልጽ የገዢው ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች እንዲሁም በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የመንግሥት ሹመኛ ሆነው ያገለገሉ ግለሰቦች ዳኞች ሆነው የሚመደቡበት አሠራር ሰፍኖ ቀይቷል። አልፎ ተርፎም በገዢው ፓርቲ ውስጥ በነበረው የብሔር አደረጃጀት መሠረት ዳኞች ከየክልሉ በኮታ መልክ ለዳኝነት የሚሾበት ሁኔታም ነበር። በጣም ከቅርብ ጌዜ ወዲህ ዳኞችን ማስታወቂያ አውጥቶ እና በፈተና አወዳድሮ የመመደብ አሠራር እየተስተዋለ የመጣ ቢሆንም፣ ይሄም በርካታ ቅሬታዎች የሚቀርቡበት ከመሆን አልዳነም። ስለሆነም በግልጽ ለገዢው ፓርቲ ወገንተኝነት ያለው የዳኝነት አካል የተገነባ ስለመሆኑ አያጠያይቅም። በተለይም አንዳንድ የፖለቲካም ይሁን ሌላ ካፍተኛ የመንግሥት ጥቅም አላቸው ተብለው የሚታሰቡ ጉዳዮች ለማየት በችሎት የሚመደቡ ዳኞችን ስንመለከት በእርግጥም የመንግሥት እጅ ፍርድ ቤቶች ውስጥ ዘው ብሎ ስለመግባቱ መካድ የማይቻል ይሆናል።
ምን ዓይነት ማሻሻያ ያስፈልገናል?
በፍትሕ ስርዓቱ ላይ የሚደረገውን ለውጥ ተቋማዊ ይዘት ለመስጠት ሥር ነቀል የሆነ ማሻሻያ ማድረግ ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም። ከምንም በላይ ግን ማሻሻያው ከላይ የተጠቀሱትን ተቋማዊና ግለሰባዊ የፍርድ ቤቶችን ነጻነት በሚያስጠብቅ መልኩ መቀረፅ ይገባዋል። ፍርድ ቤቶችን ፍፁም ገለልተኛ በሆነ መልኩ እንደገና በማዋቀር በሰው ኃይል፣ በግብዓት እና በቁሳቁስ በማደራጀት የፍትሕ ስርዓቱ ምቹና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ብዙ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል። በተለይም የፍርድ ችሎቶችና የዳኞች ቢሮዎች ለዜጎች እና ለመገናኛ ብዙኃን ምቹ በሆነ ቅርፅ ተገንብተው፣ የሥራ ተነሳሽነትን የሚያጎለብቱ እንዲሁም የዳኝነት ስርዓቱን ግልጽነት እና ተጠያቂነት የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ ያስፈልጋል። በተጨማሪም በዳኞች በአንድ ጊዜ የሚታይ መዝገቦችን ብዛት እና ጫና በመቀነስ የቀጠሮ ድግምግሞሽን እና የፍርድ ሒደት መጓተትን ለማስቀረት ከኢተዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን የዳኞች እና የድጋፍ ሰጪ አካላት ስብስብ ያስፈልጋል። የመዛግብት አደረጃጀት፣ የመዝገብ ቤት እና የችሎት ጸሐፊዎች እንዲሆም በዋነኝነት ዳኞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲታገዙ በማድረግ ቀልጣፋ አሠራር መዘርጋት ተቋማዊ ለውጡ በግንባር ቀደምትነት ሊተገብራቸው ከሚገቡ መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚዎቹ ሊሆኑ ይገባል።
በሌላ በኩል በግልጽ በፓርቲ አባልነታት እና ደጋፊነታቸው የሚታወቁ፣ በሙስናና ግልጽ በሆነ የአቅም ችግር ቅሬታ የሚቀርብባቸውን ዳኞች ከሥራ ኃላፊነታቸው ማንሳት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ እርምጃ ነው። ዳኞች የፍትሕ ስርዓቱ እስትንፋስ እንደመሆናቸው የዜጎችን መብት በማስከበር እና ፍትሕን ከማስፈን አንፃር የሚጠበቅባቸውን የጎላ አስተዋፅዖ እንዲወጡ፣ በራስ መተማመናቸው እንዲጨምር እና ያለምንም መሸማቀቅ እና ፍርሓት ሁሉንም በእኩልነት እንዲያስተናግዱ፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ሥልጣን እና የገንዘብ አቅምን ሳያገናዝቡ ለሕግ እና ለሕሊናቸው ብቻ ተገዢ እንዲሆኑ ብቃት ያላቸውን ዳኞች ከመሾም ባለፈም እነኚህ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ የሚያደርግ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ቁርጠኝነት ካለ ከወረቀት ያለፈ በተግባር ነጻና ገለልተኛ የሆነ የዳኝነት ተቋም መገንባት እንደሚቻል ብዙ ማሳያዎች አሉ። አሁን ባለንበት ታሪካዊ አጋጣሚ ኃላፊነት ከተረከቡ ግለሰቦች ባለፈ ወደፊት እንድትኖረን የምንሻት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሁላችንም የበኩላችንን ልናበረክት ይገባል። በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻና ገለልተኛ ፍርድ ቤት ተቋቋመ ማለት በእኔ የግል አመለካከት የአገሪቱ የፖለቲካና የዴሞክራሲ ችግር ከግማሽ በላዩ እንደተፈታ ይቆጠራል። ነጻና ገለልተኛ ፍርድ ቤት ከተተቋቋመ ሰሚ ያጣው የዜጎች እሮሮና ጩኸት ምላሽ ያገኛል። ጡንቻውን እንዳሻው በዜጎች ላይ የሚያሳየው አስፈፃሚው አካል አደብ ይገዛል። የምርጫዎች ፍትሓዊነት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ጥያቄም በአመፅና ጦርነት ሳይሆን በሠላማዊ መንገድ ይፈታል። እናም ለዚህ ዓይነት ነጻ ገለልተኛ የፍትሕ አካላት መደራጀት ሁሉም የበኩሉን ማበርከት ይጠበቅበታል።
ፈቃዱ አዱኛ የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው
fekaduadu@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011