“ሕወሓት ያለው አንድ አማራጭ ሥልጣን ለሕዝብ አስረክቦ ተቃዋሚ ሆኖ መቀጠል ነው”

0
1133

አብረሃ ደስታ የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት (ዓረና) ሊቀመንበር ናቸው። አብረሃ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር ትምህርት መምህር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ ሲሆን በይበልጥ ቀደም ሲል በዜግነት ጋዜጠኝነታቸው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በመብት ተሟጋችነት እና ፖለቲከኛነት ይታወቃሉ። በሚያደርጉት እንቅስቃሴም እስከመታሰር የደረሱ ቢሆንም ትግላቸውን ግን አሁንም አላቋረጡም፤ በትግራይ ብሔራዊ ክልል ውስጥም በንጽጽር ተደማጭነት አላቸው ከሚባሉ ግለሰቦች መካከል ይመደባሉ። የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ በወቅታዊ ጉዳዮችና በዓረና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ መቀሌ ከሚገኙት አብርሃ ደስታ ጋር በስልክ ቆይታ አድርጓል።

ቅዳሜ ታኅሣሥ 6/2011 መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ውይይት ላይ የድርጅታችሁ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አምዶም ገብረሥላሴ ንግግራቸውን እንዳይቋጩ አቦይ ስብሃትን ባካተተ ጭብጨባ እንዲቋረጡ ተገደዋል። ብዙዎች የሕወሓትን አፋኝነት ለአደባባይ አጋልጧል ሲሉ ይደመጣል። በእናንተ በኩል ምን ትላላችሁ?
ሕወሓት ሁሌም በእንደዚህ አይነት ዝግጅቶች ላይ ወጣቶችን አደራጅቶ ወደ አዳራሽ ይዞ በመግባት በትልልቆቹ እንዲመራ ያደርጋል። ትልልቆቹ ሲያጨበጭቡ ወጣቶቹ ያለማቋረጥ ይቀጥላሉ። ባለፈው [ቅዳሜ] የተደረገውም ይኸው ነው። የዓረና ሰዎች ወይም እነሱን [ሕወሓት] የሚቃወም ሐሳብ ሲነሳ እንዲያቋርጡ፣ ተስፋ እንዲቆርጡ፣ እነሱን መቃወም እንዲያቆሙ ለማድረግ ሆን ብለው ያደረጉት ነው። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሲሠሩት የነበረው የአፈና መንገድ ነው።
ከዛ በኋላ በአምዶም ላይ በፀጥታ አካላት የተቃጣ ወከባና ጥቃት ተደርጓል በሚል ወሬዎች እየተራገቡ ይገኛሉ። አሁን አንዶም በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
በወሬ ደረጃ እኛም እንደማንኛውም ሰው ሰምተናል ይሁንና እስከአሁን ድረስ አምዶም ላይ የደረሰ ምንም ጉዳት የለም። አሁን አምዶምን ሊያስሩ የሚችሉበት ደረጃ ላይ አይደለም ያሉት።
ተፎካካሪ ፓርቲ እንደመሆናችሁ በትግራይ ውስጥ ያላችሁ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? በተለይ ከክልሉ ገዢ ሕወሓት ጋር አያይዘው ቢነግሩን።
በእንቅስቃሲያችን አማራጭ [ሐሳብ] እናቀርባልን፣ ዴሞክራሲ መስፈን አለበት ብለን ሕዝብ እናስተምራለን፣ እናደራጃለን። ነገር ግን አሁን የፖለቲካ አቅጣጫ ትረካውን ሕወሓቶች ቀይረውታል። በዶ/ር ዐቢይ የሚመራ የፌደራል መንግሥት ኃይል የመጣው ሕወሓትን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የትግራይን ሕዝብ ማንነት፣ ክብር፣ ጥቅም እንዲሁም ኅልውና ለማጥቃት ስለሆነ በፖለቲካ ሕወሓትን መቃወም በመተው የሚሰነዘር ጥቃትን መከላከል ማድረግ ነው የሚገባን በሚል ሕዝቡን እያደናገሩት ነው። [ሕወሓቶች] ሕዝቡን ለጦርነት መዘጋጀት እንዳለበት ነው የሚቀሰቅሱት። ይህ በመሆኑም በተወሰነ መልኩ እኛም በፖለቲካ ላይ አተኩረን እንዳንሠራ አድርጎናል፤ እንቅስቃሴ ማድረጋችንን ግን እንደቀጠልን ነው።
እናንተስ ያላችሁን አማራጫ ሐሳብ ለማቅረብ እና ተጽዕኖ ለማሳደር ምን እየሠራችሁ ነው?
እሱን እያደረግን ነው። ብዙ ውሸቶች እንዳሉ፣ ሕወሓት በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያደርጋቸው ጥረቶች መሆናቸውን፣ የትግራይ ሕዝብና ሕወሓት የተለያዩ መሆኑን፤ በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚደርስ ምንም ዓይነት ችግር ሊኖር እንደማይችል እያስረዳን ነው ያለነው። በአሁኑ ሰዓት ብዙ አባላት እያፈራን ነው ያለነው።
በትግራይ ሕዝብ ውስጥ ያላችሁ ተቀባይነት ምን ይመስላል? ስንት አባላትና በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎችስ ስንት ቢሮዎች አሏችሁ?
ሁሌም እንደምናደርገው ቢሮዎች እንከፍታለን፣ እንቅስቃሴ እናደርጋለን እንዲሁም ሰዎች እናደራጃለን። በየአካባቢው አባላት አሉን። ነገር ግን የሕወሓት ‹ፕሮፓጋንዳ› እና አሁን አሁን ዘጋቢ ፊልሞች ተብለው የሚሠሩት እንቅፋት እየሆኑብን ነው። ስለዚህ ‹‹አሁን ፖለቲካ የምናወራበት ጊዜ ነው ወይ ያለነው›› በሚል ሰው እየተጠየቅን ነው። ሕዝብ ለማጥፋት የመጡ ኃይሎች አሉ በሚል በትንሹ በፖለቲካ እንቅስቃሴያችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አድርሷል።
አሁን ያላችሁ የአባላት ብዛት ስንት ነው? ምን ያክል ቢሮዎችስ አሏችሁ?
የአባላት ቁጥርን አሁን አንናገርም ምክንያቱም ጥቃት ስለሚደርስባቸው። ከእያንዳንዱ ዐሥር አባላት አንዱ አባል ብቻ ነው እንዲታወቅ የምናደርገው። ቢሮዎችን በተመለከተ በክልሉ ሁሉም ዞኖች እና በ15 ወረዳዎች ላይ ከፍተን ሥራ እየሠራን እንገኛለን።
የምትንቀሳቀሱት በሕቡዕ ነው ማለት ነው?
በግልጽ እየታወቁ የሚንቀሳቀሱት ከእያንዳንዱ ዐሥር አባላት አንዱ ብቻ ሲሆን የተቀሩት ዘጠኙ አባላት ግን የአባልነት ክፍያ እየፈፀሙ ዝም ብለው ይቆያሉ። ምክንያቱም ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው በማለት ነው። ለምሳሌ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እኔና ሁለት ሦስት በአባላት ብቻ ነን የምንታወቀው፤ ሌሎች አባላት የሉንም ማለት ግን አይደለም።
አንዳንዶች በትግራይ የአንድ ሐሳብ ልዕልና እንዲኖር ያደረገው የሕወሓት ጠንካራ መሆን ብቻ ሳይሆን የዓረና ደከም ብሎ መታየት ነው ይላሉ። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ትክክል ነው የሕወሓት ጥንካሬ አይደለም። ይሁንና ደግሞ የሕወሓት አፈና አለ። ለምሳሌ መሐል አገር ሕወሓት በነበረበትና ሕወሓት በሌለበት ያለው እንቅስቃሴ ልዩነቱ ይታወቃል። ትግራይ ውስጥ እስካሁን ድረስ ሕወሓት አለ። ምን ያክል አፋኝና ጨቋን እንደሆነ እንዲሁም ምንም ዓይነት የተለየ ሐሳብ ማስተናገድ እንደማይፈልግ ይታወቃል። ማኅበራዊ መሠረቱን ባደረገበት ትግራይ ውስጥ የተለየ ሐሳብ ያለው ሰው አለ እንዲባል ስለማይፈልግ የተለየ ተጽዕኖ ይፈጥራል። ነገር ግን አብዛኛው ሰው ሕወሓትን ሊቀበል ይችላል፥ ‹‹ይገለናል ያጠፋናል›› በሚል ፍርሃት። ምክንያቱም ሕወሓት ብዙ ሰው አጥፍቶ፣ ብዙ ሰው ገድሎ ነው እዚህ የደረሰው።
የእኛ አባላት የሆኑ የጠፉ፣ የተገደሉ፣ የታሠሩ አሉ። እስካሁንም አልተፈቱም። ስለዚህ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ብታደርግ ብትቃወም በምጣኔ ሃብት፣ በንግድ እንድትታገድ ወይም እንድትገለል እንደሚያደርጉ እያወቅክ ነው ፖለቲካ ውስጥ የምትገባው።
ትግራይ ውስጥ ተቃዋሚ ሆኖ መንቀሳቀስ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ትልቅ ቁርጠኝነት ይጠይቃል። ለምሳሌ አዲስ አበባ ላይ ተቃዋሚ ሆነህ መኖር ትችላለህ፣ ሥራ መሥራት ትችላለህ። ትግራይ ውስጥ ግን ብዙ ችግሮች ስለሚደርሱብህ የእኛ እንቅስቃሴ ጎልቶ እንዳይወጣ አድርጎታል። የሚዲያ ሽፋንም ስለማይሰጠው ጭምር ማለት ነው። ይሁንና አሉ ከሚባሉ ድርጅቶች መካከል ድርጅታዊ ጥንካሬ እኛ የተሻልን ነን ብለን እናምናለን።
በቅርብ ጊዜ አባላታችሁንና አመራሩን ያጋጠማቸው ማዋከብ፣ አፈና፣ እስር እና እንግልት በተጨባጭ ማስረጃ በማስደገፍ ሊገልጹልኝ ይችላሉ?
አዎ! የእኛ አባላት በተለይ አርሶ አደሮች ውኃ እንዳያገኙ ተደርገዋል፣ ከብቶቻቸው እንዲሞቱ ተደርጓል፣ በፖሊስ ሲደበደቡ ፍርድ ቤት ሔደው መክሰስ እንዳይችሉ፥ ፍትሕ እንዳያገኙ ተደርጓል። እኛም ብንሆን ጉባዔ ማድረግ አንችልም። ሆቴሎች እኛን እንዳያከራዩ ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው፤ ከኛ ጋር የሠሩትን አለአግባብ ግብር እየተጨመረባቸው (እየተጠየቁ) ብዙ በደል ደርሶባቸዋል። የእኛ አባላት ወይም የእኛ ቤተሰብ የሆኑ በሙሉ ከሥራ እንዲባረሩ እየተደረገ ብዙ ችግር ነው እየደረሰ ያለው።
ዓረና የተጋሩ ብቻ ፓርቲ እንዳልሆነ ይጠቀሳል ይህ ምን ያክል እውነት ነው? ከተጋሩ ውጪ ምን ያክል አባላት አሏችሁ?
እኛ የብሔር ፓርቲ ሳንሆን የክልል ፓርቲ ነን። ፕሮግራማችንና ፖሊሲዎቻችን ለመላው ኢትዮጵያ የሚሠሩ አገራዊ ናቸው። ነገር ግን እኛ የምንቀሳቀሰው በትግራይ ክልል ብቻ ነው። ትግራይ ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ሰው የድርጅታችን አባል መሆን ይችላል። ከትግራይ፣ ከኩናማ፣ ከሳሆ፣ ከአፋር፣ ከአማራ፣ ከኦሮሞ፣ ከደቡብ፣ ከቤኔሻንጉል፣ ወዘተ አባላት አሉን። በተለያየ ምክንያት ትግራይ ክልል የሚኖሩ ማለት ነው።
ከትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ጋር የጀመራችሁት አብሮ የመሥራት እንቅስቃሴ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?
ከትዴት ጋር መዋሃድና አንድ ላይ ሆኖ መታገል እንዳለብን ተስማምተናል። አሁን የሚቀረው ተዋህደናል ብለን ማሳወቅ ብቻ ነው።
የፖለቲካ ተሳትፏችሁን ከማጠናከር አንፃር የመዋሃዳችሁ አንድምታ ምንድን ነው?
እነሱ ልምድ አላቸው፣ አባላታቸው ለእኛ አቅም ነው የሚሆኑት እንዲሁም በውጪ አገራት የሚገኙ ብዙ ደጋፊ ስላላቸው በገንዘብም በሞራልም ያግዙናል፣ ያጠናክሩናል።
ዓረና ከሕወሓት ጋር መሠረታዊ ልዩነት እንደሌለው በብዙዎች ይታመናል። ለዚህም እንደ ምክንያት ከአመሠራረታችሁ ጋር በተያያዘ ከሕወሓት ተገፍታችሁ የወጣችሁ መሆኑ ይገለፃል። ከሕወሓት ጋር መሠረታዊ ልዩነታችሁ ምንድን ነው?
ዓረናና ሕወሓት ምንም የሚያገናኛቸው ነገር የለም፤ በጣም የተለያዩ ናቸው። ለምሳሌ በርዕዮት ዓለም ደረጃ ሕወሓት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሲከተል እኛ ግን ሊብራል ዴሞክረሲን ነው። ዓረና ከሕወሓት ጋር ሳይስማሙ ከቀሩ ከአምስት ከማይበልጡ [ሰዎች] በስተቀር በወጣት ምሁራን የተመሠረተ ፓርቲ ነው።
ሌላው ከሕወሓት ጋር የፖሊሲ ልዩነት አለን። ኢሕአዴግ ግብርና መር ኢንዱስትሪን ሲከተል እኛ ግን ሁለቱም በአንድ ላይ ተቀናጅተው መሔድ አለባቸው ነው የምንለው። በፍትሕ ስርዓቱ ላይም አጠቃለይ ልዩነት አለን። ለምሳሌ የፌደሬሽን ምክር ቤት ሕግ የማውጣት ሥልጣን እንጂ ሕግ የመተርጎም ስልጣን ሊሰጠው አይገባም ብለን እናምናለን። በአጭሩ ከሕወሓት ጋር መሠረታዊ የሆኑ ልዩነቶች አሉን።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትግራይ ብሔራዊ ክልል መንግሥት እና በፌደራል መንግሥት መካከል ግልጽ የሆነ የአቋም ልዩነቶች እየተንጸባረቁ ይገኝሉ። አሁን ባለው አካሔድ የሕወሓት ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው?
ሕወሓት አሁን ካለው የፌደራል መንግሥት ጋር ተስማምቶ ለመኖር ጥረት ማድረግ የሚችል ይመስለኛል። ቢሆንም ሕወሓት በጣም የተጠላ ድርጅት ነው። በጣም ብዙ ችግር፣ ግፍ ሲፈጽም የነበረ ነው። ማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ አይቀበለውም፤ የትግራይ ሕዝብም አይቀበለውም። በመሆኑም በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ይቀበሉታል ብለን አናስብም። በዚህ ሁኔታ ሕወሓት ያለው አንድ አማራጭ ሥልጣን ለሕዝብ አስረክቦ ተቃዋሚ ሆኖ መቀጠል ነው። በትግራይ ክልል ከተመረጠ ግን ሊያስተዳደር ይችላል። ስለዚህ የግድ ከፌደራል መንግሥት ጋር ስላልተስማማ ይጠፋል ማለት አይደለም።
ሕወሓት ከኢሕአዴግ ራሱን አስማማቶ ባይቀጥልስ?
የመለየት ዕጣ ፈንታ ይደርስበታል
ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሔደ ያለው ለውጥ ከሞላ ጎደል በብዙ የኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ ድጋፍ ከማግኘትም አልፎ ዓለም ዐቀፍ ትኩረት እንዳገኘ ማሳያዎች አሉ። በትግራይ ክልል በተለይ በሕወሓት ግን ብዙም ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም ይባላል። በሕዝቡና በእናንተ በኩል ያለውን እውነት ቢገልጹልኝ?
እኛ ለውጥ መደረግ እንዳለበት እናምናለን፤ ለውጡንም እንደግፋለን። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ የለውጡ ሒደት በትክክል እየተመራ አይደለም ብለን እናምናለን፤ ምክንያቱም መጀመሪያ ትኩረት ማግኘት ያለበት የፀጥታ፣ ሠላም እና መረጋጋት መኖር ላይ ነው። መንግሥት በእያንዳንዱ አካባቢ ቁጥጥር ሊኖረው ይገባል። [ሁኔታዎች] ወዳልተፈለገ [መንገድ] እንዳያመሩ፣ ሕዝቡ እንዳይጋጭ ሕግ መከበር አለበት፣ ስርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል ምክንያቱም ሠላም ካልሰፈነ፣ መረጋጋት ከሌለ ለውጡ አይሳካም። ወደ ዴሞክራሲ የምናደርገው ሽግግርም ፈተና ይገጥመዋል፤ አካሔዱም ጥንቃቄ ስለሚያስፈልገው ውጤታማ የሚሆንበት ዕድል አነስተኛ ነው። በአጭሩ የለውጡ ሒደት በትክክል እየተካሔደ ነው ብለን አናስብም። ስለዚህ ወደ ዴሞክራሲ የምናደርገው ሽግግር የተሳካ እንዲሆን መደረግ ያለባቸው ነገሮች አሉ ብለን እናምናለን።
በነገራችን ላይ የትግራይ ሕዝብ እውነታውን ያውቀዋል። ነገር ግን ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህ ሕወሓት አሁን እየተካሔደ ያለውን ለውጥ ‹‹ፀረ ትግራይ የሆነ፣ የትግራይን ሕዝብ ለመምታት የተቃጣ እንጂ የትግራይን ሕዝብ ለመጥቀም አይደለም›› በሚል ነው እየሰበከ ያለው። የትግራይ ሕዝብም ‹‹ለውጡ ሕዝብን ለማጥቃት ወይስ ሕዝብን ለመጥቀም ነው እየተደረገ ያለው›› በሚል ጥርጣሬ ውስጥ ገብቷል።
የአማራና ትግራይ ክልል መንግሥታትን ግንኙነት እንዴት ይገልጹታል?
አሁን በሁለቱ መንግሥታት መካከል መስማማት አለ ለማለት እቸገራለሁ። ነገር ግን እንደምናስበው ላይሆን ይችላል ምክንያቱም የኢሕአዴግ ባሕርይን አናውቀውም። የሚናገሩትን ነገር ከሚሠሩት ነገር አይቶ መገምገም ይከብዳል። ስለዚህ ከኢሕአዴግ ባሕርይ አንፃር ‹‹በትክክል መግባባት አለ ወይስ መለያየት አለ›› የሚለውን ነገር ማወቅ አትችልም።
ብዙ ሰው አሁን እንደሚያስበው ልዩነት አላቸው ብዬ አላስብም።
ከማንነት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች የትግራይ ክልል በአግባቡ አያስተናግድም የሚል ወቀሳ ይነሳል። እንደማሳያ የወልቃይትና ራያ የማንነት ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል። በዚህ ላይ የእናንተ አቋም ምንድን ነው?
እኛ አቋም መያዝ ሳይሆን ሕዝቡን ሔደን ማዳመጥ ነው የመረጥነው። ‹‹የሕዝቡ ጥያቄ ምንድን ነው?›› የሚለውን ነው የወሰድነው። የሕዝብ ጥያቄ የፈለገው ይሁን ሊስተናገድ ይገባል። ጥያቄው ሊመለስለት ይገባል። እዛ ያለው አስተዳደር የሕዝብን ጥያቄ መመለስ አለበት። የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ ካልቻለ ግን የአስተዳደሩ ችግር እንደሆነ ነው የምንወስደው።
በትግራይ አካባቢዎች የተለያዩ ጥያቄዎች አሉ። የአስተዳደር፣ የአከላለል፣ የወረዳ፣ ወዘተ ጥያቄዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል የራያና የወልቃይት ጥያቄዎች ዋና ዋናዎቹ አይደሉም። ይሁንና የሁለቱ ጥያቄ ባጋጣሚ ከአማራ ክልል ጋር ስለሚገናኙ ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖራቸው ተደርጓል። በሌሎች አካባቢ ከዛ የከፋ ሌሎች የሕዝብ ጥያቄዎች አሉ። ለምሳሌ አድዋ አካባቢ የከፋ ሕዝባዊ ተቃውሞ ነበር። ሕዝብ ተሳትፎ ሕወሓት አትወክለንም ብሎ፣ የሕዝብ ተወካዮች ሆነው ተመረጡ የተባሉትን አትወክሉንም ብሎ እስከመጥራት ደርሷል። በተለያየ አካባቢ ፀረ ሕወሓት የሆኑ፣ ፀረ አስተዳደር የሆኑ ጥያቄዎች አሉ።
መቀሌ ዙሪያ ሕወሓት አያስተዳድረንም ብለው ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ አሉ። የመንግሥት መዋቅር የሌለበት አካባቢ አለ። ሕወሓትን ብቃት የላችሁም አታስተዳድሩንም ያሏቸው ሰዎች አሉ። አሁን ትንሽ የተረጋጋ ይመስላል። ነገር ግን ብዙ ጥያቄዎች አሉ። በአጠቃላይ የሕወሓት መንግሥት ከሥልጣን ከተባረረ በኋላ ሕዝባዊ መንግሥት ሕዝቡ ራሱ ይመሠርታል፤ ጥያቄዎቹን በራሱ ይመልሳል ብለን ነው አቋም የወሰድነው።
ሕወሓትና አዴፓ እሰጣ ገባ ውስጥ ገብተዋል። በእናንተ በኩል የሁለቱ መሠረታዊ ችግር ምንድን ነው ትላላችሁ?
ሕወሓትና ብአዴን (አዴፓ) መሠረታዊ ልዩነት አላቸው ብዬ አላምንም፤ በትክክል የተጣሉ አይመስለኝም። ነገር ግን የተጣሉ እንዲመስሉ ያደረጋቸው ነገሮች ግን አሉ። እነሱም የአማራ ክልል መንግሥት (አዴፓ) በክልሉ አሁን ለውጥ እየመጣ ነው፣ የሕዝብ ጥያቄ አለ፣ የለውጥ ፍላጎት አለ። ስለዚህ የለውጡ አካል ነኝ በማለት ገዢ ሆኖ የሚቀጥልበትን ዕድል ለማመቻቸት ‹‹ፀረ ትግራይ፣ ፀረ ሕወሓት ነኝ›› እያለ የተለያዩ ጠብ አጫሪ የሆኑ ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ እያደረገ ነው። የለውጥ አካል ነው እንዲባል፣ ከሥልጣን እንዳይባረርና ፀረ ለውጥ ነው እንዳይባል ማለት ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ሕወሓት የሕዝብ ድጋፍ እያጣ ሲሄድ የትግራይ ሕዝብ የሚደግፈኝ ጠላት ሲመጣ ነው ብሎ ያምናል።
የትግራይ ሕዝብ ከአማራ ክልል ‹‹ትግራይን እንወራለን›› የሚል ሥጋት ሲመጣና ሕወሓት ደግሞ ሆን ብሎ ‹‹መጥተው ይወሩሃል›› ብሎ ሲቀሰቅስ ሕዝቡ ከሕወሓት ሌላ ጠብመንጃ የያዘ፣ ሀብት ያለው፣ ሥልጣን ያለው አማራጭ አካል ስለሌለ ከሕወሓት ጎን ይሰለፋል። በአማራ የሚደረግ ፀረ ትግራይ እንቅስቃሴን ሕወሓት የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት ይጠቀምበታል።
ስለዚህ ለራሳቸው ሲሉ ሕወሓትም ሆነ አዴፓ ግጭቱን ይፈልጉታል። በዚህም ችግሩን እያባባሱት ያለ ይመስለኛል እንጂ መሠረታዊ ልዩነት አላቸው ብዬ አላምንም።
እንደፖለቲካ መሪ እርሶን በግል አንዳንዶች ሲተቹ ይሰማል። አንዳንዶች በፖለቲካ ርዮተ ዓለም እውቀትና ትንታኔ ሲያወድሶት በሌላ ወገን ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር ሆኖ ወደፊት ሕዝብን ሊመራ እንደሚችል መሪ ስሜቶን ባለመቆጣጠር ደካማ እንደሆኑ ይነገራል። ለዚህም እንደማሳያ በማኅበራዊ የመገናኘ አውታሮች ላይ ብሽሽቅ በሚያስመስል መልኩ የሚያካሒዱት ምልልሶች ተጠቃሽ ናቸው። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ቃሊቲ ከመታሰሬ በፊት ፖለቲከኛም ጋዜጠኛም ነበርኩኝ። ከፖለቲካ በተጨማሪ መረጃ የሚያደርስ ወይም የሚዲያ እጥረት ስለነበረ ‹‹በዚህ ቦታ እንዲህ ተፈጠረ፣ እንዲህ ሆነ›› እያልኩ እጽፍ ነበር። ስለዚህ ፖለቲከኛ ብቻ ሳልሆን የዜግነት ጋዜጠኝነት (‹ሲትዝን ጆርናሊዝም›) አካሒድ ነበር። አሁን ደግሞ ፖለቲከኛ ብቻ ሳልሆን አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፍው በመብት ተሟጋችነት ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የሚያስፈልገው የግንዛቤ ማስጨበጥ፣ የፖለቲካ ዕውቀት፣ የሕዝብ ማነቃነቅ (‹ሞቢላይዜሽን›) በመሆኑ ነው። በዚህ ምክንያት እንደ ፖለቲከኛ ብቻ አይደለም የምንቀሳቀሰው መባሉ ትክክል ነው። ስለዚህ በአጭሩ የመብት ተሟጋችም የፖለቲካ አመራርም ነኝ። ነገር ግን አሁን እየሠራሁት ያለው በአብዛኛው የመብት ተሟጋችነቱ ላይ ነው ። አሁን ብዙ መረጃ የሚያቀብሉ ስላሉ ጋዜጠኝነቱን ትቼዋለው።
በትግራይ ብዙ የመብት ተሟጋቾች ሲኖሩ ደግሞ ተሟጋችነቱን ትቼ ሙሉ ለሙሉ የፖለቲካውን ሥራ አካሒዳለሁ። በዚህ ምክንያት ፖለቲከኛነቱና ተሟጋችነቱ ስለሚቀላቀሉብኝ ነው ትችት የሚሰነዘርብኝ።
ትችቱን ይቀበሉታል ማለት ነው?
አዎ! ትችቱን እቀበለዋለው ምክንያቱም እኔ ፖለቲከኛ ብቻ ስላልሆንኩኝ ማለት ነው። ውሸትና ‹ፕሮፓጋንዳ› የሚጽፉ ሰዎችን ማጋፈጥ አለብኝ አለበለዚያ እነሱን እንደማበተረታታት ነው የምወሰደው። ስለዚህ መንጋን መቃወም አለብኝ። ያንን ሳደርግ ደግሞ ወደ እልህ እገባለሁ።

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here