‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ከዴሞክራሲ ጋር አብሮ ይሔዳል?

0
457

‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ በግርድፉ ሲተረጎም አንድ ግጭት ሲያስተናግድ ከነበረ ወይም አምባገነናዊ ስርዓት ወደ ሠላማዊ ወይም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግር በሚደረግበት ጊዜ ያለፈው ስርዓት ላደረሰው ሰብኣዊ ጉዳት የመቋጯ ፍትሕ ማቅረቢያ መንገድ ተደርጎ ነው። ይህ የሚደረግባቸው በርካታ መንገዶች መካከል በጣም ታዋቂው የሐቅ እና ዕርቅ ኮሚሽን አማራጭ ነው። በዚህ መንገድ በቀዳሚው ስርዓት ሰብኣዊ ጥቃቶችን የፈፀሙ ሰዎች በደላቸውን በአደባባይ በመናዘዝ ምኅረት የሚያገኙበት መንገድ ነው። ይህ የፍትሕ አሰጣጥ ስርዓት በተለይ ከተለመደው ዓይነት የፍትሕ አሰጣጥ ስርዓት የተለየ ነው።
በወንጀል ሕግጋት እንደሚመለከተው ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች በሕግ ማስከበር ሥነ ስርዓቱ ውስጥ አልፈው ፍትሐዊ ዳኝነት እንዲያገኙ ይጠበቃል። ይህ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ አካሔድ ግን ከዚህ የተለየ የፍትሕ አሰጣጥን ነው የሚከተለው። በብዙ አገራት በተግባር ላይ የዋሉ የሐቅ ወይም የዕርቅ ኮሚሽኖች የሠሩትን ወንጀሎች የተናዘዙ የቀድሞ ባለሥልጣናትን ለፍርድ አያቀርቡም። አሁን በኢትዮጵያ ያለው ተረቅቆ ለመፅደቅ ጊዜ እየጠበቀ ያለው “የዕርቀ-ሠላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ” በአንቀፅ 17 (1) እንዳመለከተው፦ “ማንኛዉም ሰው በኮሚሽኑ ፊት ቀርቦ በሚሰጠው ቃል መሠረት ክስ ሊመሠረትበት እንደዚሁም የሰጠው ቃል በእርሱ ላይ ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብበት አይችልም”።
ከዴሞክራሲ መሠረታዊ መርሖዎች አንፃር የሕግ የበላይነት ዋነኛው ነው። ይሁን እንጂ ወንጀለኞች በአደባባይ ወንጀላቸውን አምነው ይቅርታ በመጠየቃቸው ብቻ ከሕግ ተጠያቂነት የሚያመልጡ ከሆነ፥ የአለመጠየቅ (‘impunity’) ባሕልን ስለሚያበረታታ የግድ መጠየቅ አለባቸው የሚልም አካሔድ አለ። በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ አዲ ደቀቦ “መንግሥት የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት የፈፀሙ ሰዎችን ያለመክሰስ ሥልጣን የለውም” ይላሉ። በተለይም ደግሞ ‘ጭፍን ምኅረት’ (blank amnesty) ወይም እየመረጡ ምኅረት ማድረግ የሕጋዊ አለመጠየቅን ባሕል የሚያበረታታ እና ከዴሞክራሲያዊ መርሖዎች ዋነኛውን የገደፈ ተግባር ነው የሚሆነው።
በእንግሊዝ የኬሌ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር እና የፖለቲካ ተንታኙ አወል ቃሲም አሎ (ዶ/ር) ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ‘የፖለቲካዊ ውሳኔ የፖሊሲ ጉዳይ ነው’ ይላሉ። ከአምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር በሚደረግበት ወቅት በአምባገነናዊው ስርዓት የተፈፀሙ በደሎችን አርሞ ለመሻገር የሚደረግ ጥረት ቢሆንም፥ ሙሉ ለሙሉ በሕግ አግባብ ብቻ የሚፈታ ቀላል ነገር አይደለም የሚሉት ቃሲም፣ በተለያዩ ሌሎች መንገዶች የዕርቅ ስሜት በመፍጠር ሽግግሩን ማሳካት የመንግሥት ኃላፊነት ነው ይላሉ።
በዚህ ረገድ ሲገመገም ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ከዴሞክራሲ ጋር በቀጥታ ስምም (compatible) ነው ማለት አይቻልም፤ ነገር ግን ወደ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመሻገር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here