አሜሪካ ግን በኢትዮጵያ ላይ ድርሻዋ ምን ያህል ነው?

0
666

አገራት ልዕለ ኃያልነት ከጊዜያት ወዲህ እንደቀደሙት ኣመታት አይሁን እንጂ ከቴክኖሎጂ ጋር አብሮ በመዘመን ምናልባትም ለሚዘምነው ቴክኖሎጂም የራሰቸው (አስተዋጽኦ መኖሩ ባያጠራጥርም) አብረው እየገነኑ ለቀሪው ዓለም ገናናነታቸውን ማሳያ ካደረጉ ውለው አድረዋል።

ይኸው ልዕለ ኃያልነት እና የጡንቻ ውድድር ታዲያ ኃያላን አገራት እርስ በራስ ከሚያደርጉት ፍጥጫ ተሻግሮ በታዳጊ እና ደሃ አገራት ላይ በሚኖራቸው ድርሻ እና በሚያሳድሩት ተጽዕኖ እንደሚወሰንም በተለያዩ ጊዜያት ያየናቸው የውጭ ፖሊሲያቸው እና ጉዳዩ ምንም በማይመለከታቸው አገራት ላይ የሚደረገው ጫና ግን ወለል ብሎ የሚታይ ተግባር ነው።

አገራት ጦርነቶቻቸውን ወደ ደሃ አገራት በማምጣት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ብረዛዎችን እና በእያንዳንዱ ጉዳያችሁ ላይ የራሳችን የሆነ ድርሻ አለን አይነት ሀሳብ በየጊዜው ለደሀ አገራት የሚሰጡትን ምንዳ እና ድጋፍ መሰረት አድርገው ይናገራሉ።

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ከሌሎች አገራት ጋር ስትተያይ ለጋ ዕድሜ ያላት እና ዓለምን ባላት ልዕለ ኃያልነት ራሷን የዓለም ፖሊስ ቀሪውን የዓለም ክፍል ደግሞ የዓለም ሌባ አደርጋ በምትቆጥረው የኹለት ክፍለ ዘመን ዕድሜ ባለቤቷ አሜሪካ ነው። እንደእኔ ዓይነቱ በካፒታሊዝም ርዕዮት ዓለም ውስጥ ተተክሎ ለበቀለ ከሳጥን ውስጥ ወጥቶ በማሰብ ካፒታሊዝምን ለመንቀፍ የሚያስችል ሞራል ይኖረዋል ተብሎ ባይታሰብም ቅሉ እኔ ግን እሞግታለሁ፤ የካፒታሊዝም እና የኒዮ ሊበራሊዝም ወላጅ እናት የሆነችውን አሜሪካንም በአገሬ ኢትዮጵያ ላይ ያላትን ድርሻስ እስከምን ደረስ ነው ስልም አበክሬ እጠይቃለሁ።

አሜሪካ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የድኅነትን ወለል ዘልቀው ለገቡበት አገራት በረከት ያሉ ጓዳ ጎድጓዳን በሚያምሱ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ ዘው ብላ በመግባት አድራጊ ፈጣሪ በመሆን የማይሽር ጠባሳዎችን በመጣል አገራት እንዳያገግሙ ወይም ውጥንቅጡ ጠፍቶባቸው በማያውቁት አዙሪት ውስጥ እንዲዘፈቁ በማድረግ ‹‹አይይ አሜሪካ ገብታ የፈተፈተችው ጉዳይ መቋጫ የለውም ›› እስኪባል የማይፈታ የሕይወት ዘመን ቋጠሮ ሰጥታ እንደምትወጣ ይታወቃል።

ከዚህም ባለፈ በአገራት ውስጥ በሚደረጉ ውዝግቦች እና አለመረጋጋቶች በሰላም ማስከበር ዘርፉ ውስጥ በመሰማራት እና ድጋፍ በማድረግ የአገራቱን አንጡራ ሀብት ለማሟጠጥ የሚቀድማት የለም። ወይም ደግሞ የፈራረሰውን አገር ለመገንባት ከራሷ እና በአሜሪካ በሚዘወሩ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ላይ ብድርን በማመቻቸት አገራት ከፍለው የማይጨርሱት የዕዳ አዘቅት ውስጥ እንደሚገቡም እሙን ነው። ለዚህ ደግሞ ሰሜን አፍሪካዊቷን የሙሐመድ ጋዳፊን አገር ሊቢያን ማየት ይበቃል። ‹‹ሕዝብ እንደሆነ መንግስተ ሰማያት ቢገባም ማጉረምረሙን አያቆምም ››በሚል ንግግራቸው ይታወቃሉ አወዛጋቢው ጋዳፊ። ሊቢያ በጋዳፊ ስልጣን ዘመን በሀብት ማማ ላይ ከተቀመጡ የአፍሪካ አገራት ሚስተካከላት እንዳልነበረ ቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በጋዳፊ አረንጓዴ መጽሐፍ ሊቢያዊያን በዜግነታቸው የሚያገኙት ጥቅማ ጥቅም ተዘርዝሮ አያልቅም ለእኛም ዝርዝሩን ብናወራው ሆድ ባዶ ይቀራልና ለአሁኑ እንለፈው። ይሁን እንጂ ሕዝብ በጅምላ ባይ ነቀፍም ሊቢያዊያን ግን ክፉ ዘመን ጓዳቸውን፣ ከአመድ ላይ አንስቶ ያከበራቸውን መሪያቸውን በአሜሪካ የዕጅ አዙር መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን አስወጥተው የውሻ ሞት እንዲሞት አድርገዋል።

ለመሆኑ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይስ ምን ያህል ነው ድርሻዋ? ይኸው ከቀደሙት ዓመታት ጀምሮ አሁንም ድረስ አሜሪካ በኢትዮያ የውስጥ ጉዳይ ላይ አፍንቻዋን ቀስራ ለማቡካት ከመሞከር ቦዝና አታውቅም። በኢህአዲግ ዘመን እንኳን በመጀመሪያ በመለስ ዜናዊ ዘመነ መንግስት ሲቀጥል በኃይለማሪያም አሁን ደግሞ በአብይ የስልጣን ዘመን ከአገራዊ ምርጫ እስከ ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ድረስ የውስጥ ጉዳያችሁ እኔንም ሊያካትተኝ ይገባል አይነት አይን ያወጣ ጣለልቃ ገብነትን ስንመለከት ባጅተናል።

ይኸው በታላቁ ኅዳሴ ግድብ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ድርድር በሚካሔድበት ወቅት በታዛቢነት ማልያ ገብታ የግድቡን ዕጣ ፋንታ እስከ መወሰን የደረሰ የውስጥ ጉዳይ ባለቤትነት ድርሻን ይዛ ቁጭ ብላለች። እንጠይቃለን አሁንም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላት ድርሻ ምን ያህል ነው። ለግድቡ ከአሜሪካ የቀረበውን የአንድ ድንጋይን ፈልጎ ማግኘት የማይታሰብ ነው። ለነገሩ እንኳን አሜሪካ የክፉ ቀን ወዳጅ ናቸው ያልናቸው አገራትም ግድቡን ለመገንባት ኢትዮጵያ ስትነሳ የእርዳታ ዕጃቸውን ከመዘርጋት ተቆጥበው ነበር፤ የድሃ ኩሪዋ አገሬ ግን ይህ የሚበግራት አልነበችም ይኸው የማንንም ዕጅ ሳታይ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ግድቡን አድርሳለች።

በዚህ ሰባራ ሳንቲም ባላወጣችበት እና ኢትዮጵያ በሚያክል ሉአላዊ አገር ዘው ብሎ ገብቶ ‹‹የተፋሰስ አገራት መካከል ስምምነት ላይ ሳይደረስ ኢትዮጵያ ውሃ ሙሊቱን ማቆም ይኖርባታል›› የሚል በአሜሪካ የደኅንነት መስሪያ ቤት የተሰጠው ማሳሰቢያ አዘል መልዕክት እጅግ ሲበዛ ውንብድና እና ማን አለብኝነት ከመሆኑም በላይ ራሷን አሜሪካን ‹‹ምን አግብቶሽ ነው እንዲህ ያለ መግለቻ ምትሰጪው›› የሚል ጥያዌ ቢቀርብላት ምላሽ ይኖራታል የሚል ዕምነት የለኝም።

ይህ ታዲያ በአሜሪካ እና አሜሪካ መሰል አገራት ቆየ ባህል ነው። አንድን አገር ለማደራደር እና ለመሸምገል በሚል ቅዱስ ሚመስል ሀሳብን ያነገበ ተልዕኮ ይዘው ወደ አገር ውስጥ ይገቡና ለዘመናት የማይፈታ ቋጠሮን ለራሳቸው በሚመች መልኩ ቋጥረው ውሊን አጥፍተው ይወጣሉ ወይም የዘመናት ባሪያቸው አድርገው ቁጭ ይላሉ ድርሻቸውም በአገራቱ ላይ እንደራሳቸው ቸርነት እንጂ እንደ አገራቱ ጥንካሬ መለካት ያቆማል ማለት ነው።

አሜሪካ በቅርቡ ቻይና ኢትዮጵያ ላይ ለምትገነባው የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል አይኗ ደም መልበስ ከጀመረ ሰንባብቷል። ይህም ደግሞ በነውጠኛው አመራሯ እና አወዛጋቢ ንግገሮችን እንዲሁም ውሳኔዎችን በማስተላለፍ በሚታወቁት ዶናልድ ትራምፕ አማካኝነት ወደ ቻይናው አቻቸው በመቅረብ የማዕከሉ ግንባታ ከመስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኢትዮጵያ ይልቅ ሰሜን አፍሪካ በመሔድ ሞሮኮ ላይ ቢገነባ መልካም ይሆናል የሚል በማያገባቸው ሲፈተፍቱ እንደነበር ሰሞኑን በተለያዩ ሚዲያ አካላት እየሰማን ነው። ይህ የኢትዮጵያን ጉዳይ በአንክሮ ለሚመለከተው የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ያለውን መልካም ያሆነ ስሜት መግለጫ እንደሆነም ለማወቅ ይቻላል። ይህ ደግሞ በሴራ ፖለቲካ እና ተንኮልን በትምህርት ደረጃ ወሰደችው ለምትመስለው አሜሪካ በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ የተቀነባበረ ጥፋት ለመፈጸም ትተኛለች ብየ በግሌ አላምንም። አሁን የምንነቃበት እና የአሜሪካን ድርሻ በውስጥ ጉዳያችን ውስጥም መንቅረን የምንጥልበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይመስለኛል።

በግድቡም ቢሆን ከመገንባት የሚያስቀረን አንዳች ምድራዊ ኃይል የለም ብሎ በአባቶች ወኔ እና ፉከራ መሸለል ሳይሆን እንዴት ነው ምድራዊውን ኃይል ቀልብሰን ግንባታውንም የምናሳልጠው የሚለው ጉዳይ በስፋት እየተዳሰሰ ቢመከርበት መልካም ይመስለኛል። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን የቀደመው ድርሻዋ እና ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪነት ሚናዋ በቀረባት ጊዜ ከፍ ያለ ብስጭት ውስጥ እንደምትገባ የሚታመን ነው።

እስኪ ሰውስ ቢፈርድ እንዲያው ግድቡ እንኳን ይሁን በአንድም በሌላም ቢሆን እንዲያው የመጋበዝ ዕድሉ ገጥሟት ነበር። ለመሆኑ በቻይና በኩል ለሚገነባው የበሽታ መከላከያ ማዕከል ያውም በቻይና መንግስት ወጪው ለሚሸፈነው፣ በአፍሪካ መሬት ያውም በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ለሚገነባው ማዕከል የአሜሪካ ቦታ መራጭነት እና ቀያሽነት ግን ልማድ እንደማይለቅ ማሳያ ይመስለኛል። እውነት ነዋ አሜሪካ ከኢራቅ እስከ ሶሪያ፣ ከየመን እስከ ሊቢያ ድረስ እጀ ረጅምነቷን በግልጽ የምታስነብብ ልዕለ ኃያል እንደሆነችም እንታዘባለን። ይህ የለመደችው ተግባርም ታዲያ በኃያልነት የሚገዳደሯትንም አገራት ለመተንኮስ ስትሞክር ከእፍረት ጋር የተመለሰችበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም።

በሩሲያ የውስጥ ፖለቲካ ገብታ ባለ ድርሻ አካል ነኝ ስትል ከኮስታራው እና ጅዶን ባህላዊ ስፖርት አድርጎ ካደገው የፑቲን አስተዳደር የአርፈሽ ተቀመጪ አሻፈረኝ የምትይ ከሆነ ግን አጸፋው የከፋ ይሆናል የሚል ቀጠን ያለ ማስጠንቀቂያ ሲደርሳት ጎመን በጤናን እያዜመች ዋሽንግተን ላይ ተሰብስባ ተቀመጠች።

ቀጠልን ደግሞ በቻይና እና ታይዋን የድንበር እና የማንነት ውዝግብ ላይ ያንጾለሌ የብር መስቀሌ እያለች ጉዳዩን ከእኔ ውጭ የሚፈታው የለም በሚል ስታቦካ እና ስትጋግር ከቻይና ወገን ይህ ጉዳይ የኹለቱ አገራት ብቻ እንደሆነ እና እንዲያው ሦስተኛ ወገን ካስፈለገም የቀጠናው አገራት ብቻ ለመሆናቸው አስረድተው አሰናብተዋለታል።ይሁን እንጂ አሁንም በውስጥ ጉዳይዋ የምትታመሰው አሜሪካ ኢትዮጰያን ቸምሮ በሌሎች አገራትም ላይ ይህ ነው የማይባል ሚና ለመጫወት አልቦዘነችም።

ወዲህ የዘረኝነት መድሎው ጥግ ደርሶብናል የሚሉ አፍሪካ አሜሪካዊያን እና ለህሊናቸው የሚኖሩ ነች አሜሪካዊያን ከአራቱም ማዕዘን መንግስትን ሲሞልጩት እና የአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት በከተሞች ላይ ተሰማርቶ ውጥረቱን ለማርገብ እስኪሞክር ድረስ ለያዥ ለገናዥ ያስቸገሩ ዜጎቿን ጉዳይ መፍታት ያቃታት አገር፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከቻይና ተነሳ በተባለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በየዕለቱ ዜጎቿን በሽዎች የሚቆጠሩትን ሕይወታቸውን ሲረግፍ ቆማ የምትመለከተው አሜሪካ ዛሬም የውጭ አገራት ጉዳይ ጉዳየ ነው ስትል ትሰማለች።

ለመሆኑ በኢትዮጵያ ላይ እኛ ያላወቅነው ድርሻ አላት? ሃይ ባይ ያጣች ይመስል በተደጋጋሚ ስትፈተፍት ዝምታን የመረጥንበት ጉዳይስ ድርድር ይበልጣል ከሚል አኳያ ይሆን እንዴ? በነገራችን ላይ ይህን የአሜሪከን ውሳኔ በተለይም ደግሞ በኅዳሴው ግድብ ዙሪያ ያውን አቋሟን ኢትዮጵያ የመቀበል አዝማሚያዋ ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አለም አቀፍ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመስራት የሚኖራቸው መነሳሳት ሊቀንስ እንደሚችልም ማሰቡ አይከፋም። ለምን ቢባል በአሜሪካ ከፍተኛ ባለ አክሲዮንነት የተቋቋሙት እነዚህ የገንዘብ ተቋማት አሜሪካን በውስጥ ጉዳየ ላይ አይመለከትሽም፣ በአገሬ ላይ ዕድል ፋንታ የለሽም ለሚሉ አገራት መቅጫ እና እርምጃ መውሰጃ መንገድ እንደሆነም ይታመናል።

ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here