ሽምግልና የማይከበርባት. . .!?

0
377

ሰሞኑን የብዙዎችን ቀልብ የሳበው እና መነጋገሪያ የሆነው ጉዳይ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ 52 (43ቱ ብቻ ናቸው የሚሉም አሉ) አባላት የያዘ የልዕካን ቡድን ወደ መቀሌ ያደረገው ጉዞን በመንተራስ ከግራና ከቀኝ የሚወረወሩ የሐሳቦች ልውውጥ፣ ጭቅጨቅ ሲብስም ዘለፋዎች በሰፊው በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ ተስተናግደዋል።

የልዕካን ቡድኑ የተለያዩ ሃይማኖቶች መሪዎችን፣ ጉምቱ የሆኑ ምሁራንን እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦችንን ያካተተ እና በግል ተነሳሽነት ተሰባስቦ በትግራይ ክልል መንግሥት (ሕወሓት) እና በፌደራሉ መንግሥት (ብልጽግና ፓርቲ) መካከል እየተካረረ የመጣውን እንካ ሰላንቲያ እና የቃላት ውርወራዎች በተግባር ታግዘው ኢትዮጵያን ወደ ባሰ ችግር እና የኅልውና ፈተና ላይ እንናዳይጥላት ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ በንግግር ብቻ እንዲፈቱ ለማድረግ የተወጠነ እንደሆነ አንድ የልዑኩ ቡድን አባል በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። የጉዞ ወጪውን ታላቁ የረጅም ሩጫ ንጉሥ እና ባለሀብት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እንደሆነ፤ እንዲሁም የምሳ ወጪያቸውን ደግሞ የፕሪዝን ፌሎሺፕ እና ጁስቲስ ፎር ኦልን የሚመሩት ፓርስተር ዳንኤል ገብረሥላሴ ወይም ሕወሓት ነች የሸፈነችው ሲሉ ውስጥ አዋቂዎች ነን ባዮች ተናግረዋል።

ይህ የሽማግሌ ልዑክ ከሔደበት ዋና አጀንዳ ባሻገር ፋይዳ የሌላቸው ጥቃቅን ጉዳዮች በተለያዩ የፖለቲካ አሰላለፍ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ለቀናት ቃላት አወራውሯል። አንደኛው ቡድን በተለይ የሕወሓት ደጋፊዎች ፌደራል መንግሥቱ ገና እግር ልሶ ሕወሓትን ማሪኝ ይላታል፤ የትግራይ መንግሥትም የሽማግሌዎቹን ሐሳብ ዝም ብሎ መቀበል የለበትም፤ ቅድመ ሁኔታ ሊያስቀምጥ ይገባዋል ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል። በሌላ በኩል የሕወሓት ደጋፊዎች ሆነው ነገር ግን ብልጽግና ፓርቲ ሽምግልና መላኩ ልብ ለመግዛት እየተንደረደረ ለመሆኑ ማሳያ ነው በማለት ሳይረፍድበት ድርድሩ ተጀምሮ ኢትዮጵያ ልትወጣው ወደማትችለው የእርስበርስ ጦርነት ከመግባቷ አስቀድሞ ሕወሓትን በፌደራል አመራር ደረጃ የሚመጥኗትን ቦታዎች በማሲያዝ በተካነችው የመንግሥት አመራር ጥበብ እና ብልሃት ኢትዮጵያን ልትታደግ ይገባል ሲሉ ምክራቸውን ጀባ ብለዋል።

በሌላ ጽንፍ ደግሞ ሽማግሌዎቹን የላካቸው ብልጽግና ፓርቲ ሆነ የፌደራል መንግሥቱ እንዳልሆኑ እያወቁ ለርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ሕወሓትን እና ደጋፊዎቿ የሚከሱ አሉ። በአንድ የሕወሓት ከፍተኛ አመራር ‘‘አገር በሽምግልና አትመራም’’ ተብሏል የሚለውን እንደማስረጃ በማቅረብ የተቃወሙት ድምጻቸውን አሰምተዋል። ሕወሓት የመጨረሻ እድሏን የማትጠቀምበት ከሆነ ወደ ባሰ መነጠል ወይም ደግሞ እስከወዲያኛው ድረስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚኖራት ቦታም ሆነ የምትጫወተውን ሚና ታጣለች ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

የሕወሓት’ን የሽማግሌዎች አቀባበል በተመለከተ ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ላይ የተደረገውን ክብረ ነክ ፍተሻ ለአብነት በመጥቀስ ሕወሓት በኢትዮጵያ የነበረውን የሽምግልና እሴት በሥልጣን ዘመኗ ያዋረደችውን እና ዋጋ ያሳጣችውን በአደባባይ ያረጋገጠችበት ነው ሲሉ በቁጭት የተንገበገቡም ነበሩ። ልምምጡ ቀርቶም ፌደራል መንግሥቱ አፋጣን እርምጃ መውሰድ ነው የሚገባው ሲሉ ቆፍጠን ያለ እርምጅ እንዲወሰድ የወተወቱም አልታጡ።

የሽምግልናው ዋና ዓላማ በትግራይ እና በፌደራሉ መንግሥታት መካከል ያሉ ፖለቲካዊ ልዩነቶች በሰከነ መልኩ፣ የአገር ኅልውናን ባስጠበቀ ሁኔታ በውይይት እንዲፈቱት የታቀደ እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን የደጋፊዎች የቃላት ውርወራ ትኩረት ግን ትልቁን አጀንዳ ጥሎ የማይረባውን በማንጠልጠል የተካሔደ መሆኑ ለትችት ተጋልጧል። በተለይ የሽምግላናው ሐሳብ በአገር ሰላምን ለማምጣት እና የቃላት ጦርነት ወደ ጦር መማዘዝ እንዳያድግ ለማድረግ መሆኑ እየታወቀ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት አንዱ አንበርካኪ ሌላው ተንበርካኪ ተደርጎ የተሳለበትን ሁኔታ ጉንጭ ከማልፋት የዘለለ ፋይዳ የለው ሲሉ ትኩረት መደረግ የሚገባው ሰላም መምጣቱ ላይ ነው ሲሉ ትዝብታቸውን ያጋሩም ነበሩ።

የሆነው ሆኖ የልዑክ ቡድኑ የትግራይ ክልል መንግሥት በፌደራል መንግሥቱ ደረሰብኝ ያለውን ችግሮች በመዘርዘር ለሽማግሌዎቹ አቅርቧል። ችግሩ የአንድ ክልል ወይም ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ችግር ነው ያሉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረጺዮን፣ ፌደራሊስት የሚባሉት ኀይሎች ሁሉ በሽምግልናው መሳተፍ አለባቸው ሒደቱንም መገናኛ ብዙኀን ሽፋን ሊሰጡት ይገባል በማለት በትግራይ በኩል ቀድመን ጦርነቱን አንጀምርም ሲሉ ለሽማግሌዎቹ አስታውቀዋል።

በተለይ ከፍተኛ የኦሮሚያ ብልጽግና አመራሮችም ሽምግልናውን ፓርቲያቸው እንደማያውቀው ከመግለጽም ባሻገር መንግሥት ጉዳዩን በአንክሮ ሊከታተል ይገባዋል ሲሉም አሳስበዋል። ከሕወሓት ጋር ያሉ ችግሮች በሽምግልና ይፈታል ብሎ መጠበቅ ‘ላም አለኝ በሰማይ . . .’ እንደማለት ነው በማለት ከዓመታት በፊት ቅንጅት ላይ የተፈጸመውን ሸፍጥ በአስረጅነት በመጥቀስ አጣትለውታል። ሕወሓት ወንጀለኛ ባለሥልጣኖቿን አሳልፍ ሳትሰጥ ሽምግልናው ፍሬ እንደማያፈራ ከወዲሁ በርግጠኝነት ደምድመዋል።

የሆነው ሆኖ የሽምግልናው ልዑክ በዕለቱ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰ ቢሆንም መቼ ከፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እንደሚያገኙ የታወቀ ነገር የለም።

ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here