ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ከገባ ሦስት ወራትን ተሻግሯል። አካሄዱም እንደ አጀማመሩ አይደለም፣ ይልቁንም በየእለቱ በቫይረሱ መያዛቸው የሚረጋገጥ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ወደ ኹለት፣ ከኹለት ወደ ሦስት አሃዝ አድጓል። የጤና ስርዓቱ፣ የሕክምና ባለሞያዎች ሙያና አገልግሎት፣ መንግሥትና የመንግሥት ተቋማት በብዙ ተፈትነዋል። በጉዳዩም ላይ አዲስ ማለዳ አንድ ባለሞያ አናግራለች።
ጥር ወር አጋማሽ ላይ ነበር የኢትዮጵያ የሕክምና ማኅበር ፕሬዝዳንት ሆነው የተሰየሙት። ሐኪም፣ የኅብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስት እንዲሁም በጤና ዘርፍ የሰው ሀብት ባለሞያ ናቸው፣ በኢትዮጵያ የጤና መስክ የከፍተኛ የትምህርት ስርዓት ከ18 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፤ ዶክተር ተግባር ይግዛው። የጤና ስርዓትን እንዲሁም የሕክምና ትምህርትን በሚመለከት ከልምዳቸው ብዙ የሚያውቁ፣ በዘርፉም በኢትዮጵያ ለውጦች እንዲመጡ ከእውቀትና ከጉልበታቸው ለመስጠት ያልሰሰቱ ባለሞያ ናቸው።
አሁንም በሚመሩት የሕክምና ማኅበር፣ እንዲሁም ወረርሽኙን በሚመለከት የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራውን ለማገዛ በጤና ሚኒስቴር በተቋቋመው ግብረ ኃይል ድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። ወረርሽኙ ወደፊት በጤና ዘርፉ ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ እንዲሁም የጤና ባለሞያዎች እየገጠማቸው ያለውን ተግዳሮትና ኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመከላከል እየሄደችበት ያለውን ጉዞ በሚመለከት ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተከታዩን ብለዋል።
ኮቪድ 19 ወደ አፍሪካ ይልቁንም ወደ ኢትዮጵያ የገባው ዘግይቶ ነው። በኢትዮጵያም ከገባ በኋላም ሳይቀር ለኹለት ወራት ገደማ የስርጭት መጠኑ ዝቅተኛ የሚባል ነበር። ጊዜውን ለዝግጅት በሚገባ ተጠቅመንበታል ማለት ይቻላል?
ስለ ዝግጅት ስናነሳ፣ ዝግጅት በደንብ ተደርጓል። ግን የሚፈለገውን ያህል ተደርጓል ወይ ካልን የምንፈልገው ደረጃ ላይ አልደረሰም። ግን ሊጠቀስ የሚችል ተጨባጭ ሥራ ተሠርቷል።
ለምሳሌ የላቦራቶሪ ምርመራ አልነበረም፣ አሁን ላብራቶሪ ማቋቋም ተችሏል። የሕክምና ተቋማት አልተዘጋጁም ነበር እሱን ማዘጋጀት፣ ጤና ባለሞያዎች አልሠለጠኑም ነበር፣ እነርሱን ማሠልጠን። በአገር ዐቀፍም ሆነ፣ በክልል ወይም በሙያ ማኅበራት ደረጃ በማማከርም፣ በእውቀትም የሚያግዙ ሰዎችን በማሰባሰብ ተባብረው የሚሠሩበትን መንገድ ለመፍጠር ተሞክሯል።
በግብዓት ደረጃም የሚያስፈልጉ ለምሳሌ አልኮልና ሳኒታይዘር፣ የጤና ባለሞያዎች የሚጠቀሙባቸው ራስን መከላከያ ቁሳቁሶች ግዢ ተደርጓል። ቬንትሌተርን ስናነሳ፣ ኢትዮጵያ ወስጥ ውስን ነበር። በቁጥር 243 አካባቢ ነበሩ። ይሄ የተመንፈስ ችግር ያለባቸውን የሚረዳ መሣሪያ ጊዜ ቢወስድም ተገዝቷል።
ኅብረተሰቡን ማስተማር፣ ትምህርት ቤቶችና የእምነት ተቋማት እንዲዘጉ ማድረግ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ሰዉ እጁን እንዲታጠብ ወዘተ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሂደት ወይም ሥራዎች ናቸው። ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም፣ አነሰም በዛ፣ በየዘኑ ስንት ሰው በቫይረሱ ተያዘ፣ ስንት ሰው ሕይወቱ አለፈ የሚለውን እያሳወቀን ነው።
ግን እንዲህ ያለ ወረርሽኝ ለመቋቋም ያለውን ጊዜ ሁሉ በሚገባ ተጠቅመንበታል ወይ ስንል፣ የጎደለውን ነገርም ማየት አለብን። አንደኛ በተጠናከረ ሁኔታ፣ በፍጥነትና በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችል ከፌዴራል መንግሥት እስከ ቀበሌና ማኅበረሰብ ድረስ ተናብቦና ተቀናጅቶ ለመሥራት የሚያስችል ስርዓት አለ ወይ? ፍጥነት እንዲሁም በክልልና በፌዴራል የሚፈለገው ቅንጅት አለ ወይ? ወዘተ ሲባል፣ በሚፈለገው ደረጃ አይደለም።
ከላይ የተንጠለጠለ ስርዓት ብቻ አይደለም በሽታ መቆጣጠርን ውጤታማ የሚያደርገው። እያንዳንዱ ወረዳና ማኅበረሰብ አቅም ሊኖረው ይገባል። ለምሳሌ የታመሙትን ሰዎች መለየት፣ ማፈላለግ፣ ኅብረሰተቡን ማስተማር፣ ማስተባበር፣ የተቸገሩትን መርዳት፣ ይህ አቅም ሁሉም ጋር መኖር አለበት። ይህ ሁሉ የለም። ይህ ግን በኹለትና ሦስት ወር የምታመጪው ሳይሆን፣ መጀመሪያ የሚገነባ ስርዓትም ነው።
በሚገባ አልሠራንም ብዬ የማስበውና በፊትም የነበረ ሌላው ችግር ሎጂስቲክስ ነው። የሕክምና ግብዓቶችን ማሟላት፣ እነዛን መግዛትና በአገር ውስጥ የሚመረተውን ማምረት፣ የሚፈለገው ቦታ በፍጥነት ማድረስ ችግር አለ። አሁንም ቢሆን ማስክ የለም፣ ጓንት የለም፣ ግዢ ሂደት ላይ ነው ሲባል ይሰማል።
የተለያዩ ማነቆዎች አሉ። መንግሥትንም መውቀስ አትችይም። ከውጪ የሚገዙ ከሆነ አሁን ዓለማቀፍ እንቅስቃሴውም ፈተና ውስጥ ገብቷል። ሁሉም አገር ለራሱ ስለሚፈልግ፣ መላክ አቁመው ነበር። የአየርና የባህር ትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴ ሁሉ እንደድሮው አይደለም። ስለዚህ ይህም ሁሉ የሚፈጥው ችግር አለ። በጥቅሉ ውስብስብ ነው።
በአንድ በኩል በፊት የተገነባ ስርዓት ጠንካራ መሆን ወሳኝ ነው። የአገር ውስጥ አቅምን ማጎልበት። ለምሳሌ አብዛኛውን ነገር አገር ውስጥ የምታመርቺ ቢሆን፣ በዚህ ዓይነት ጊዜ በቀላሉ፣ መሠረታዊ ማስክና መሰል ቁሳቁሶችን ማግኘት ይቻላል። በፊት አገር ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በዚህ ላይ እንዲያተኩሩ አድርገን ቢሆን ኖሮ፣ ይህን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን አበረታተን ቢሆን አሁን ይቀለን ነበር።
ጤና ስርዓቱም ላይ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በፍጥነትና በቅንጅት ታች ድረስ ለማውረድ ይረዳ ነበር። ዝግጅት የሚለካበት ሌላው ቴክኖሎጂ ነው። አሁን ላይ ሳንወድም በግድ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ተገደናል። ስብሰባም፣ መረጃም በኢንተርኔት ሆኗል። አስቀድመን ቴክኖሎጂ ተጠቅመን፣ ሁሉም ቦታ ኢንተርኔት አገልግሎት ቢኖርና ርካሽ ቢሆን፣ አሁን የትምህርት መቋረጥ ራሱ በዚህ ልክ ላይረበሽ ይችል ነበር።
በጤናው ስርዓትም የታመሙ ሰዎች፣ ከታመሙ ጋር ንክኪ ያላቸውን ማፈላለግ፣ ችግረኛን ገቢው ዝቅተኛ የሆነን ሰው መለየት የሚለው በራሱ፣ ጠንካራ የሆነ የመረጃ ስርዓት አስቀድሞ ቢኖር አያስቸግርም ነበር። በአንድ ክፍለ ከተማ ይህን ያህል ችግረኛ አለ ብሎ በማስቀመጥ እነዛን ለሦስት ወር ለመርዳት ምን ያህል ያስፈልጋል የሚለውን ቀድሞ ማወቅ ይቻል ነበር። ጠንካራ የመረጃ ስርዓት የበለጠ ይረዳ ነበር።
እና ብዙ የተሠሩ ነገሮች አሉ። የምንፈልገውን ያህል ግን አይደለም። ያ የሆነበት አንዱ ምክንያት በፊት ያላዳበርነውና ያልሠራነው ነገር ስለሆነ፣ ብንሮጥም የምንፈልገው ደረጃ አንደርስም ነው። በአንጻሩ ደግሞ ባለን ጊዜ ከዚህ በተሻለ መፍጠን፣ መነጋገር፣ መቀናጀት ብንችል፣ መተባበር ብንችል የተሻለ ውጤት ማምጣት ይቻላል ነው።
በማኅበረሰብ ደረጃ እያስተማርን ነው። በቂ አላስተማርን ይሆናል። በማኅበረሰብም ውስጥ መልካም የሚባሉ ለውጦች አሉ። ግን ደግሞ ብዙ ጉድለቶችም አሉ። ርቀት መጠበቅን ስናይ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም ቦታ አጥጋቢ አይደለም። ማስክ አጠቃቀምም በአዲስ አበባ ጥሩ ነው ግን የአጠቃቀም ችግር አለ። ይህ ግን ሊሻሻል ይችላል። ከአዲስ አበባ ውጪ ጭራሽ ማስክ መጠቀም የሚባል ነገር የለም።
ወረርሽኙ የጤና ስርዓቱን ከማዳከም ይልቁ በድኅረ ኮሮና አሁን ካለበት ሊሻሻል ይችላል የሚሉ አሉ። በተለይም ልምድና ተሞክሮ ይገኝበታል በሚል እምነት። ይህ ሊሆን ይችላል?
ትክክል ነው። ትልቅ እድል ነው። እንዲህ ያሉ ፈተናዎች ያለንና የሌለንን፣ ድክመትና ጥንካሬን ለመለየት ያስችላል። አንዱ የሚጠበቅና ዘመናዊ የሚባል የሚማር የጤና ስርዓት የሚባለው ከውድቀቱም፣ ከጥንካሬውም፣ ከድክመቱም የሚማር ነው። ስለዚህ በዚህ ጊዜ እንደማኅበረሰብም ምኑ ጋር ነው ችግራችን የሚለውን ተረድተናል። እንደ ጤና ስርዓትም የጤና ተቋማት ችግሮች ምንድን ናቸው? የሚለውን አይተናል።
እድሉን ከተጠቀምንበት ብዙ የምንማረው አለ። ከጤና ሚኒስቴር ጋር የተቋቋመውና የሙያ ማኅበራት ያቋቋምነው ምክር ቤት አንዱ ዓላማ፣ መንግሥት በዚህ ሂደት ውስጥ፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር፣ የጤና ስርዓታችን እንዲሁም ማኅበረሰብባችን ምንድነው የሚማረው የሚለውን ማየት ነው።
ነገ ተመሳሳይ ችግር እንዳይገጥመን ምንድን ነው የምናስተካክለው፣ ችግር ቢገጥመን ደግሞ ከአሁኑ በተሻለ ሁኔታ በሽታ ሳይሰራጭና ብዙ ጉዳት ሳያደርስ እንዴት መቆጣጠር እንደምንችል እንዴት ነው የምንማረው?
ይህ ግን በደንብ ማሰብ ይፈልጋል። ትምህርት ካላስተዋልሽ ካላቀድሽ፣ ሳይንሳዊ በሆነ መነጽር እና ለመማር ዝግጁ በሆነ አስተሳሰብ ካልተቀረጸ፣ ጥሩ ጥሩው ብቻ ከላይ እያየሽ ድክመት በግልጽ ካልተመረመረና ካልተያዘ፣ ካልተፈተሸ፣ ካልተጻፈ፣ ጊዜው ሲያልፍ የሰው ልጅ ይረሳል። ይህ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መፈተሸ አለበት፣ ጠንካራም ደካማም ጎኑ።
ለምሳሌ ውሳኔ አሰጣጣችን፣ ፍጥነታችን እንዴት ነበር? የሚያስፈልገውን ሎጂስቲክስ በማድረስ የሄድንበት ርቀት እንዴት ነበር? ጤና ተቋማት ዝግጁነት እንዴት ነበር? ምን ምን ነበር ያልነበሩን? ቀድመን ማዘጋጀት የነበረብን አሁን ግን በዚህ ወረርሽኝ ጊዜ እንደሌለ የተገነዘብነው ነገር ምንድን ነው? የሚለውን ተምረሽ መተግበር።
የጤና ተቋማት፣ መሠረተ ልማት ቢያንስ ውሃ እንደሌላቸው ከተገነዘብን፣ ዛሬ ነገ ሳንል ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በኋላ የጤና ተቋም ተብሎ፣ ጤና ጣቢያ፣ ሆስፒታል ወይም ክሊኒክም ይሁን፣ አነሰ ቢባል ሁሌም የማይቋረጥ የውሃ አገልግሎት መኖር አለበት። ውሃ ሳይኖር ስለሌላ በሽታ መከላከል ልታወሪ አትችይም። ውሃ እንዲኖር ማድረግ አለብን። ከሌላ ማምጣት ካልተቻለ፤ የራሳቸውን ቆፍሮ እንዲኖር ማድረግ።
መብራት ያስፈልጋል። ከዋና ማግኘት ካልተቻለ ሶላር እንዲኖር መደረግ አለብት። ይህን ችግር በፊት ማኅበረሰቡ ላይረዳው ይችላል። የጤና ተቋማትና የባለሙያዎች ችግር፣ ግብዓት አይሟላላቸውም፣ መድኃኒት የለም ሲባል ችግሩን ኅብረሰተሰቡ አልተገነዘበም ነበር።አሁን አፍጥጦ ገሃድ ሆኖ ሲወጣ፣ መንግሥት የሚመድበው በጀት ዝቅተኛ ስለሆነ ነው ወይ? ያለንን ሀብት አጠቃቀም ችግር ነው? መመልከት ያለብን ነገር አለ ወይ? የሚለውን እናያለን? ስለዚህ ከተጠቀምንበት ብዙ የመሻሻል እድል ይሰጣል።
የሕክምና ባለሞያዎች አሁን ላይ እየገጠማቸው ያለው ተግዳሮት ምንድን ነው?
የኮቪድ ወረርሽኝ ለጤና ባለሞያዎች ብዙ ፈተና ይደቅናል። የመጀመሪያው አሁን ፊት ለፊት ያለው አስጨናቂ ነገር ጤና ባለሞያዎች ከሌላው ማኅበረሰብ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። ምክንያቱም ሌላው ሰው ቤቱ ቁጭ ካለና ርቀቱን ከጠበቀ ምንም አይሆንም። ጤና ባለሞያዎች ግን ሥራቸው ነው። የኮቪድ ታማሚን ሆነ ሌላ ዓይነት የጤና አገልግሎት የሚፈልግን ሰው እንክብካቤ መስጠት አለባቸው፣ ከታካሚ ጋር ይገናኛሉ።
በዚህ ምክንያት ብዙ ባለሞያዎች ለበሽታው እየተጋለጡ ነው። እስከ አሁን ባለኝ መረጃ 200 በላይ ጤና ባለሞያዎችና የድጋፍ ሠራተኞች በኮቪድ ተይዘዋል። ይህ ቀላል ቁጥር አይደለም። ካለው ባለሞያ ከአምስት በመቶ በላይ ነው። ይህ ቁጥር ስናይ በኢትዮጵያ ከሦስት ሺሕ በላይ ሰው በቫይረሱ ተይዟል እያልን ነው። ይህ ከ110 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ ነው። ጤና ባለሞዎች ግን 212 እያልን ያለነው፣ ከ300 ሺሕ ከማይበልጡ የጤና ባለሞያዎች ነው።
ስለዚህ ከሌላው ማኅበረሰብ በበለጠ በበሽታው እየተጠቃ ነው። ስለዚህ ባለሞያዎቻችን በቫይረሱ እንዳይያዙ መከላከል ላይ የተሻለ መሠራት አለበት። አስፈላጊ ቁሶችን ማሟላት አንዱ ነው። ጤና ተቋማት አካባቢ ያለውን የመከላከልና ቁጥጥር ስርዓቱን ማጠናከር፣ መሣሪያው ኖሮም በአግባቡ ካለመጠቀም መጋለጥም ይኖራል። በሽታው የሚይዘው ከታካሚ ብቻ ሳይሆን ከአካባቢ መበከልም ነው። ስለዚህ ጤና ተቋማት አካባቢ ያለው የንጽህና አጠባበቅ መጠናከር አለበት።
ሌላው የጤና ተቋማት የተሠሩበት መንገድ ነው። ከዲዛይን ጀምሮ ብዙ ታካሚ አንድ ቦታ የሚቀመጥ ከሆነ፣ የሰው መጨናነቅ ካለ፣ ቫይረሱ ያለበትን ሰው መለየት ካልተቻለ የመጋለጥ እድሉን ይጨምራል። ስለዚህ አንዱ ይሄ ተጋላጭነታቸው ነው።
ኹለተኛ ከዚህ ጋር ተያይዞ ትልቅ የሆነ የሥነ ልቦና ጫና አለ፣ በጤና ባለሞያዎች። ሥራው አለ፣ ፍርሃትና ስጋትም አለ። ይህ ተደማምሮ ለትልቅ የሥነ ልቦና ጫና እና የአእምሮ መቃወስ ሊጋለጡ ይችላሉ። ስለዚህ መደገፍና ማበረታታት፣ ራሳቸውን የሚጠብቁበትን መንገድ ማስተማርና ማገዝ ያስፈልጋል።
ታድያ የጤና ባለሞያዎች በዚህ መልክ እንዲታገዙ ምን እየተደረገ ነው?
ቀድሞ እንዳልኩት ብዙ ነገር እየተደረገ ነው። የሚያስፈልጉ ግብዓቶችና ቁሳቁሶች በድጋፍም፣ በመንግሥት እየተገዙ እየመጡ ነው። ከሙያ ማኅበራት ጋር በመሆንም በሺሕ የሚቆጠሩ የጤና ባለሞያዎች ራሳቸውን ጠብቀው ማከም እንዲችሉ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
በሙያ ማኅበራት በኩል አንድ የተዘጋጀ መመሪያም አለ። ይህም ራስን ስለመጠበቅና ለራስ እንክብካቤ ስለማድረግ ነው። ባለሞያዎች ራሳቸውን ከሥነ ልቦና ጫና እንዴት ይጠብቃሉ የሚል ነው። እንደ ኤካ ኮተቤ ባሉ ተቋማትም፣ ድጋፍ እንዲያደርጉ የተመደቡ የሥነልቦና እና ሥነ አእምሮ ባለሞያዎች አሉ።
ይህ ሌላ አገር አስገዳጅ እንዲሆን ነው የተደረገው። እኛ ግን እንደ አገርም፣ እንደ ማኅበረሰብም አልተለመደም። የሚያስጨንቅ ነገር ሲኖር እንደ ችግር እና በሽታ ቆጥረሽ ባለሞያ ጋር አትሄጂም። የሕክምና የጤና ባለሞያውም ከዚህ የተለየ አይደለም።
ብቻውን ችግሩን ይችላል እንጂ፣ ሐሳቡን አውጥቶ የማማከር የመግለጽ፣ እርዳታ ለማግኘት የመሞከር ነገር የለም። ሌላ አገራት እነአሜሪካም በዚህ ላይ የሚሳተፉ የጤና ባለሞያዎች በግዴታ የሥነ ልቦነ እና አእምሮ ባለሞያዎች ጋር እንዲነጋገሩ፣ ለዚህ የሚረዱ ስልቶችን ሥልጠና እንዲወስዱ ያደርጋሉ።
ስለዚህ እኛ ጋር ለዚህ የሚረዱ የተዘጋጁ ግብዓቶች አሉ። ባለሞያዎቹ ራሳቸው ሊተገብሯቸው የሚችሉ መመሪያና ምክረ ሐሳቦችም ተዘጋጅተዋል። ጤና ሚኒስትርም ጋር ይህን ጉዳይ በማንሳት በየጤና ተቋማቱ ይህ እንዲሆንና፣ የጤና ባለሞያ ምክረ ሐሳብ ቢፈልግ የሚደውልበት የማማከሪያ የስልክ መስመር (ሆትላይን) ያስፈልጋል ብለን ይህን ለማቋቋም ጥረት እየደረገ ነው። ይህ ለማኅበረሰቡም ቢሆን የሚያስፈልግ ነው። ግን በቂ ሊባል የሚችል ነገር የለም።
የጤና ባለሞያዎች በዚህ ወረርሽኝ ሳቢያ የሚያገኙትና ለመደበኛ የጤና አገልግሎት ሊያገለግል የሚችል አዲስ ልምድና ተሞክሮ ይኖር ይሆን
ለሁላችንም፣ ለባለሞያውም፣ በፊት የምናውቀውም ቢሆን ወደፊት የበለጠ ያስተምራል ብዬ የማስበው አንደኛው መከላከልን ነው። የመከላከል ስርዓታችን በጣም ጠንካራ ካልሆነ፣ እንኳን እንደ እኛ ያለ ደሃ አገር ለሀብታምም አክመሽ አትችይውም። በሕክምና የታመመውን ሁሉ አታድኝም። መከላከል ሲሆን ግን በሽታው አይከሰትም፣ ሞትንም ትቀንሻለሽ። ኹለተኛ ወጪ አያስወጣም፣ ውጤታማና አዋጭም ነው።
ስለዚሀ የጤና ባለሞያዎችም ለመከላከልና የመከላከል ስርዓታችንን ለማጎልበት የምንሰጠውን ትኩረት ያጎለብታል ብዬ እስባለሁ። በአጠቃላይ ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ሲከሰት ቶሎ ለመለየትና ለመቆጣጠር የሚያስፈልገው ጠንካራ ስርዓት መኖር እንዳለበት ተምረን እናልፋለን፤ እንደ ባለሞያም እንደጤና ስርዓትም።
በጥቅሉ አስቀድሞ እንዳልኩት ወረርሽኝ መከላከል፣ መቆጣጠርና ምላሽ መስጠት ስርዓት ከላይ ተንጠልጥሎ ያለ ሳይሆን ታች መውረድ ያለበት ነው። ታች ድረስ የወረደ ጠንካራ ሰንሰለት ያለው በደንብ መረጃ የሚለዋወጥ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስርዓት ያስፈልጋል።
እሱን ሁሉ ተምረን እያለፍን ነው ብዬ አስባለሁ። አጠቃላይ የጤና ስርዓታችንን ስናይ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስርዓታችን ደካማ ነው። ለምሳሌ እንደ ማኅበረሰብ እጅ የመታጠብ ባህላችን ደካማ ነው። ብዙ ተላላፊ በሽታዎችን መቆጣጠር ሲቻል በዚህ በትንሽ ነገር አትቆጣጠሪውም። እናም ለዚህ የምንሰጠውን ትኩረት ያጎለብተዋል ብዬ አስባለሁ።
ተቋማትም የበለጠ ጠንካራ መሆን እንዳለባቸው ነው፣ በግብዓትና በአመራር። እያንዳንዱ ተቋም ከላይ ስለተነገረውና ስለተደገፈ ብቻ ሳይሆን ራሱን ችሎ የሚያስፈልገውን ዝግጅት እንዴት ነው የሚያደርገው? ራሱን እንዴት ነው የሚያዘጋጀው? የሚለውን ማሰብ ይቻላል። ለመማር ግን ማቀድ ያስፈልጋል።
ቫይረሱ በኢትዮጵያ ተገኘ የተባለ ሰሞንና መጀመሪያ መነቃቃትና ድንጋጤ ነበር። አሁን ግን ለምደነዋል። በድምሩ ግን እንደ አገር ወረርሽኙን በመከላከል በኩል አሁን ያለው አካሄዳችን እንዴት ይታያል?
አዲስ አበባን ከወሰድን ጥሩ ነገሮች አሉ። በመንግሥት የተወሰዱ በአገር አቀፍ ደረጃ መልካም እርምጃዎች አሉ፣ እንዲሻሻል የሚፈለጉ ነገሮችም አሉ። በማኅበረሰብ ደረጃ፣ እንዲሁም በጤና ስርዓታችንም መልካም ነገሮችና ጅምሮች አሉ፣ እንዲሻሻል የምትፈልጊያቸው ነገሮች ግን አሁንም አሉ።
እንደዛ አድርገን ማየት ነው የሚሻለው። አሁን ወረርሽኝን ለመቆጣጠር እያደረግን ያለነው በቂ ነው ወይ ከተባለ፣ በቂ አይደለም ነው የምለው። ይህን የምናውቀው በሽታው እየተስፋፋ ስለሆነ ነው። በቂ ቢሆን በሽታው አይስፋፋም።
አሁን እኛ ጥረታችንን መመዘን ያለብን ከውጤት አንጻር ነው። ይሄ ቫይረስ ከባድ ቫይረስ ነው። አይደለም እንደ እኛ ደሃ እና ብዙ ያላደገ የጤና ስርዓት ያለው፣ ያደጉና ገንዘብ እንዲሁም በጣም ብዙ ባለሞያ ላላቸው አገራትም ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ አይተናል።በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ400 ሺሕ በላይ ሰዎችን ለሞት ያበቃ ነው። ስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎችንም ያጠቃ ነው፣ ይህ ሁሉ በስድስት ወር ውስጥ የሆነ ነው።
ስለዚህ ወረርሽኙ ከባድ ነው። እና የእኛ ምላሽም ይህን የሚመጥን መሆን አለበት። እኛ አልሠራንም ሳይሆን የምንሠራው ነገር አጥጋቢ ነው ልንል የምንችለው ወረርሽኙን መቆጣጠር ስንችል ነው። መቆጣጠር ማለት በየቀኑ የሚገኘው በቫይረሱ የተያዘ ሰዎች ቁጥር ሲቀንስና ሲቆም ወይም ዜሮ ሲሆን፣ ሲጠፋ ነው።
መጀመሪያ እስቲ ቁጥሩ እየቀነሰ ነው ወይ። አሁን ያለፉትን ከግንቦት ጀምሮ ያለውን ስናይ ቁጥሩ እየጨመረ ነው። ያውም በቂ ሰው እየመረመርን አይደለም። አንዱ በጤና ስርዓቱ መሻሻል ያሳየንበትና አሁንም ግን በቂ ያልሆነ ብለን የምናስበው ይህ ነው። አሁን ኢትዮጵያ ከብዙ አፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጽር ቁጥሩ [የመመርመር አቅም] እየጨመረ አሁን በቀን እስከ ስድስት ሺሕ እየመረመርን ነው። ግን 110 ሚሊዮን ሕዝብ ላለው ይህ በቂ አይደለም።
ኢትዮጰያ ከ10 ሺሕ ሰው በላይ በቀን መመርመር አለባት። እነ ጀርመን ለአንድ ሚሊዮን ሰው ሠላሳ ሺሕ ነው የደረሱት። እኛ ገና ኹለት ሺሕ አልሞላንም። እና አሁን ካለው በብዙ እጥፍ ማሳደግ አለብን። ግን የመጣንበት ርቀት ትልቅ ነው። ከዜሮና ደቡብ አፍሪካ ልኮ ከማስመርመር፣ አሁን በርካታ ቦታ መመርመሪያ አለ፣ የመመርመር አቅምም አድጓል።
የምንፈልገውን እስካላገኘን ድረስ ማድረግ ያለብን፣ የፈለገውን ያህል ብንሮጥም ከዚህ የበለጠ መሮጥ እንዳለብን ነው። ወደ ማኅበረሰቡ ስንሄድ፣ መጀመሪያ አካባቢ ሰው እጁን ይታጠብ ነበር። አሁን መታጠብ ቀረ። ማስክ ማድረግ ተጀምሯል አበረታች ነው። ይህ አገራቀፍ ከሆነ ትልቅ ለውጥ ያመጣልናል ብዬ አስባለሁ። ግን ማስክ አጠቃቀም ላይ በትክክል የሚመከረው መንገድ ላይ ማሻሻል ያስፈልጋል።
አጠቃቀም፣ አወጋገድና አደራረግ ላይ መሻሻል አለብን። ብዙ ሰው አፍንጫውን ሳይሸፍን ዝቅ ያደርጋል። ማስኩን ይዞ ፖሊስ ሲይይ ለመሸፈን መሞከር ጥቅም የለውም።
ትልቁ ጉድለት ያለው ደግሞ ርቀትን መጠበቅ ላይ ነው። እንደ አገር የእለት ጉርሱን ለማግኘት የቀን ሥራ መሥራት በሚያስፈልግበት ቦታ፣ ሰውን ሁሉ ቤትህ ተቀመጥ ማለት አስቸጋሪ ነው። ሰው ማድረግ እየቻለ አላደረገውም ብዬ የማስበው፣ ግድ ብሎ ከቤት ከወጣሽ፣ ከዛ በኋላ በተቻለ መጠን፣ ከሰውም ጋር ስታወሪ ገበያና ባንክ ይሁን ወይም ቀበሌ፣ የትም ሲኬድ ርቀትን መጠበቅ ለምን አይሞከርም ነው። ስለዚህ በማኅበረሰብ ደረጃ ሁሉም ካላስተካከለ፣ በሽታውን መቆጣጠር አይቻልም።
ሁሌም የምሰጠው ምሳሌ አለ። አንድ ጫካ ውስጥ እሳት ቢነሳ፣ የተወሰነ ቦታ ላይ ብቻ አጥፍቶ የተወሰነ የሚነድ ቢኖር እሳቱን ልትቆጣጠሪ አትችይም። እናም ይህን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ግማሹ ሰው ጥንቃቄ ማድረጉ ሳይሆን አብዛኛው ሰው ብንችል ሁላችንም የሚመከሩትን ምክሮች መተግበር ከተቻለ፣ በሽታውን የመቆጣጠር ደረጃችን ከፍ ያደርጋል ነው።
በጤና ስርዓቱ በኩል ደግሞ ትልቅ መሻሻል ያለበት መመርመርና መለየት ነው። ብዙ መመርመር አለብን። በየቦታውና በሁሉም ክልሎችና ከተሞች፣ በሽታው ሊኖር ሊሰራጭ ይችላል በሚባልበት ቦታ ሁሉ መለየት አለብን። የተያዙ ሰዎች በፍጥነት ከብዙ ሰው ጋር ሳይገናኙ ለይተን እንዳያስተላልፉ፣ ቤታቸው እንዲቀመጡ ወይም ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ማድረግ አለብን። ይህ የበለጠ መጠንከር አለበት።
በመንግሥት በኩል ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው መልካም ነገር ነው። የእንቅስቃሴ ክልከላዎች የሚያደርሱት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዳለ እገነዘባለሁ፣ ግን በተቻለ መጠን ሚዛኑን ጠብቆ የማስፈጸሙ ነገር ላይ ብሎም ክልከላዎችን የመንግሥት ባለሥልጣናትም አረአያ በመሆን ማሳየት ያስፈልጋል። ማኅበረሰቡ በቲቪ የሚያየውንና በራድዮን የሚሰማውን ይተገብራል። እነርሱም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀውን ምሳሌ በመሆን መተግበር አለባቸው።
የሚያስፈልገውን ሀብት በመመደብ፣ በተለይ የመከላከያ መሣሪያዎችን በሚመለከት፣ መንግሥት ለዚህ ትኩረት ሰጥቶ የጤና ባለሞያዎች የሚያገኙበትን አጋጣሚ በማመቻቸትና በመመደብ እንዲሁም ቅንጅቱን በማሻሻል መረጃን በማጠናከር የተሻለ የመቆጣጠር እድል ይኖረናል ብዬ አስባለሁ።
እርስዎ ወደ ሕክምና ማኅበር ከገቡ አራት ወራት አልፈዋል። ማኅበሩ አሁን ላይ ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
የሕክምና ማኅበር ፕሬዝዳንት ስሆን፣ ዓላማውና እኔም በቆታዬ ማኅበሩ ጠንካራ የሙያ ማኅበር ሆኖ የማኅበረሰቡን ጤና ለማሻሻል፣ የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻል የሐኪሞችና የጤና ባለሞያዎችን ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅ የተሻለ እንሠራለን የሚል ነበር ግቡ። አሁን ኮቪድ ሲመጣ የሁላችንም ትኩረት፣ ቅድሚያ የሚሰጠውም ጉዳይ ስለሆነ፣ መቆጣጠር ላይ መጥቷል።
ይህ ደግሞ ግዴታም ኃላፊነትም ነው። ማንኛውም የሙያ ማኅበር ተቀዳሚ ተግባር የማኅበረሰቡን ጤና መጠበቅ ነው። ስለዚህ ቶሎ ብለን ከመንግሥትና ከሚመለከታቸው ጋር በመሥራት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረግን ነው።
ይህ ባይኖር ሌሎች የረጅም ጊዜ አጀንዳዎች አሉን። የሕክምና ትምህርት ጥራትን ማሻሻል፣ የሕክምና አገልግሎት ጥራትን ማሻሻል፣ በሕክምና ላይ ያለውን ጥናትና ምርምር ማጎልበት፣ ከሕክምና ሥነምግባር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮችን የተሻለ በማድረግ የኅብረተሰቡን ጤና ማጎልበት የመሳሰሉና ሙያውና የሙያ ማኅበሩን ማጎልበት ላይ ነው ትኩረት አድርገን ስንሠራ የነበረው። አሁን አጣዳፊና ጊዜ የማይሰጥ ስለሆነ በዚህ ላይ እየተረባረብን ነው። እናም ለሌላው ጉዳይ ጊዜ ለመስጠት አስቸጋሪ ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012



