. ከሐምሌ 1/2010 እስከ ኅዳር 30/2011 ሰባት ጋዜጦችና 16 መጽሔቶች የምዝገባ የምስክር ወረቀት የብቃት ማረጋጋጫ ወስደዋል
በኢትዮጵያ ያለው የመገናኛ ብዙኃን ኢንዱስትሪ መነቃቃትን ተከትሎ፣ ኅዳር 1/2011 ሳምንታዊና የቅዳሜዋ አዲስ ዘይቤ ጋዜጣ የሕትመት መገናኛ ብዙኃን ዘርፉን ስተቀላቀል በተለያዩ ዐቢይ የአገሪቱ ኩነቶች ላይ መረጃዎችን ለአንባቢያን ለማደርስ ሕልም ሰንቃ እንደነበር የጋዜጣዋ መራሔ አዘጋጅና የጋራ ባለቤት የነበረው አቤል ዋበላ ያስታውሳል።
ጋዜጣዋ ስትጀመርም በአዲስ አበባ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ መረጃ ለአንባብያን ለማድረስ ቃል ገብቶ ነበር። በዚህም መሠረት በሳምንት በአማካይ እስከ ሦስት ሺሕ 500 ቅጅ እየታተመች ላንባቢያን መድረስም ጀምራ ነበር። ይሁን እንጂ በ10 ብር ለአንባብያን ትደርስ የነበረችው አዲስ ዘይቤ፥ ዕድሜዋ ከሦስት ሳምንት በላይ ሊዘልቅ አልቻለም። “በአጭር ጊዜ ውስጥ ማቋረጥ ቀርቶ፣ ቃል ከገባነው ፈቅ እንላለን ብዬ አላሰብኩም ነበር” ሲልም አቤል ስላጋጠመው ነገር ያስረዳል።
ምናልባትም ይህ ዓይነቱ ችግር ከዚህ ቀደም ሲያጋጥም እንደ ዋነኛ ምክንያት ይገለጽ የነበረው መንግሥት ለመገናኘ ብዙኃን ዘርፍ ማደግ ፍላጎት ያልነበረው መሆኑና ሌሎች ፖለቲካዊ ምክንያቶች ነበሩ። አቤልን አሁን ያጋጠመው ግን ከዚህ ቀደሙ በፍፁም የተለየ ነው።
“የአገሪቷ የፖለቲካ ሁኔታ ለኅትመት መገናኛ ብዙኃን ከዚህ ቀደም ከነበረው አንፃር አሁን ላይ ምቹ ቢሆንም፣ የኅትመት ኢንዱስትሪው ከማተሚያ ቤት ጀምሮ እስከ ስርጭት ድረስ በተወሰኑ አካላት መዳፍ ውስጥ መውደቁ የተገኘው ለውጥ በዜሮ እንዲባዛ ትልቁን ሚና እንደተጫወተ እና ለጋዜጣው መዘጋት ምክንያት መሆኑን” አቤል ያስረዳል።
በኢትዮጵያ የኅትመት መገናኛ ብዙኃን ኢንዱስትሪው ወዴት?
በኢትዮጵያ የኅትመት ኢንዱስትሪው ከተጀመረ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም፥ ዘርፉ የዕድሜውን ያክል ጉዞ ሊያሳይ አልቻለም።
ለአገሪቷ የመጀመሪያ ከሆነውና በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን 1902 ከተጀመረችው አዕምሮ ጋዜጣ አንስቶ እስከ 20 ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ድረስ የግሉ ፕሬስ ተሳትፎ አናሳ መሆኑ ይነሳል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የኅትመት ኢንዱስትሪው ሚና ከመንግሥት አገልጋይነት ያልዘለለ ነበር ቢባል ማጋነን እንደማይሆንም የተለያዩ መረጃዎች አስረጂ ሆነው ይቀርባሉ።
በ1984 የወጣውን የፕሬስ ሕግ ተከትሎ ግን የኢትዮጵያ የኅትመት ኢንዱስትሪ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ታይቶ የማይታወቅ ዕድገት ስለማስመዝገቡም ይነገራል። የመንግሥት መረጃ እንደሚያሳየው ከጥቅምት 1985 እስከ ሐምሌ 1989 ድረስ ወደ 265 ጋዜጦችና 120 መጽሔቶች ነበሩ።
ከዚያም የጋዜጠኞች መታሰርንና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በኃይል መዘጋትን ጨምሮ፣ በኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በተወሰዱ የተለያዩ እርምጃዎች ምክንያት የኅትመት ኢንዱስትሪው ቀዝቃዛ ውኃ የተደፋበት ያክል ለዓመታት መቀዛቀዝን አሳይቶ ነበር። ይህ ግን ብዙም አልቆየም፤ ከ1993 አንስቶ የጋዜጣዎችም ሆነ የመጽሔቶች ዕድገት 430 እና 130 በቅደም ተከተል በመድረስ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ ነበር።
ይሁን እንጂ፤ ዕድገቱ ተለዋዋጭ የሆነው የኅትመት መገናኛ ብዙኃን ኢንዱስትሪ፥ በዚህ ዓይነት መልኩ መቀጠል የቻለው እስከ 1997 ነበር። በወቅቱ የነበረው ምርጫ ላይ የኅትመት ዘርፉ ለተቃዋሚው ጎራ ውጤታማ መሆንና ከፍተኛ መቀመጫ ማሸነፍ ዋነኛ ሚና መጫወቱን የተረዳው መንግሥት፣ የፀረ ሽብርተኝነት፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃንና መረጀ ነጻነት አዋጅን በተለመለከቱ ባወጣቸው ሕግጋት የብዙኃን መገናኛዎች ላይ ብርቱ ክንዱን እንዳሰረፈም ይገለጻል፡፡ ይህም ለኅትመት መገናኛ ብዙኃን መቀጨጭ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል። የኅትመት ዋጋ መናር፣ ከጋዜጠኞችና ጦማርያን መታሰር ጋር ተዳምሮ የግል ጋዜጦችን ቁጥር እስከ 2010 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ወደ አራት ዝቅ እንዲል ምክንያት ሆኖ አልፏል።
ይሁን እንጂ፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ በታየው ለውጥ ምክንያት የኅትመት ኢንዱስትሪው ማንሰራራት ጀምሯል። በዚህም ከሐምሌ 1/2010 እስከ ኅዳር 30/2011 ሰባት ጋዜጦችና 16 መጽሔቶች ከኢትዮጵያ ብርድካስት ባለሥልጣን “የምዝገባ የምስክር ወረቀት የብቃት ማረጋጋጫ” ወስደዋል፤ (የወሰዱት ሁሉ ግን ኅትመት አልጀመሩም)። ይህ ማለት ግን የኅትመት ኢንዱስትሪው ካለበት ፈተና ተላቋል ማለት አይደለም። ለዚህም እንደ አብነት የምትጠቀሰው “ከስርጭት ጋር ተያይዞ ባጋጠመ ችግር” ምክንያት አራተኛ እትሟን ሳትደግም እንደተዘጋች የሚነገርላት አዲስ ዘይቤ ጋዜጣ ነች።
አንደ አቤል ገለጻ አሁን ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ የኅትመት ገበያው ከሽንኩርትና ቲማቲም ግብይት የተለየ አይደለም።
ከ1997 በኋላ የኅትመት ውጤቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የተነቃቁበት ወቅት አሁን ቢሆንም፣ በሚፈለገው ልክ እንዳያድጉ የተለያዩ ደንቃራዎች እንዳሉ አቤል ይናገራል። ጋዜጦች በክልል ቀርቶ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በሙሉ እንደማይደርሱ የሚገልጸው አቤል፣ ችግሩን ለመፍታት ወጥ የሆነ አሠራር ሊተገበር እንደሚገባ ይመክራል።
በአቤል ሐሳብ የማይስማሙ ወገኖች በበኩላቸው ከኅትመት ስርጭት ጋር የተያያዘ ችግር አይገጥምም ባይባልም ዋናው ችግር እሱ እንዳልሆነ ያነሳሉ፡፡ ይልቁንም አሳታሚዎች በርካታ የገበያ (ማሰራጫ) አማራጮችን ካስተዋሉና የጋዜጦቹ ወይም መጽሔቶቹን ጥራት (በይዘትና ኅትመት) ካስጠበቁ የአንባቢና ማስታወቂያው ገበያውን መሳብ እንደሚቻል ይጠቅሳሉ፡፡ ስለሆነም ዋናው ችግር ሲነሱ በቂ ገንዘብ ያለመያዝና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል የሚያስችል ጥራትን ያለማስጠበቅ እንደሆነም ያምናሉ፡፡
የጊዮን መጽሔት ባለቤትና የኅትመት ውጤቶች ስርጭት ሥራ ላይ የተሰማራው ፍቃዱ ማኅተመወርቅ በበኩሉ ችግሩ ያለው ከስርጭት ሳይሆን የኅትመት ውጤቶቹ ይዘውት ገበያ ላይ የሚወጡት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ነው ይላል፡፡ ቀጣይነቱን ሊያረጋግጠው የሚችለውም ይኸው ጉዳይ ስለመሆኑ ያነሳል።
አቤል ይህን ሐሳብ ቢጋራም አሁን ላለው ችግር ግን ምክንያት ሊሆን እንደማይችል ያስረዳል። መንግሥት የኅትመት ውጤት አከፋፋዮች ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር አለማድረጉ አሳታሚዎችን ችግር ውስጥ እየከተታቸው መሆኑን ያስረዳል።
አዲስ ማለዳ ከተለያዩ ምንጮች ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የጋዜጦች ስርጭት በጥቂት ሰዎችና ድርጀቶች ቁጥጥር ሥር የወደቀ ሲሆን አንዳንዴም የጋዜጦች ሽያጭ መጠን በአከፋፋዮች መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ የሚሆንበት አጋጣሚ ይከሰታል። ይባስ ብሎ፣ አሰራጮች የጋዜጠኞችን ይዘትን እስከ መወሰን የሚደርስ ተፅዕኖ አላቸው ሲሉ አሳታሚዎች ያነሳሉ። የራስን ገበያና አንባቢ ጋር የመድረሻ ስልት በራስ መንገድ በመፈለግ ይሔን ፈተና ማለፍ ይቻላል የሚሉ ወገኖች ግን ይህን ጉዳይ እንደ ትልቅ ፈተና አያዩቱም፡፡ ዋናው ችግር የረጅም ጊዜ እቅድ ይዘው አለመነሳታቸው ነውም የሚሉ አሉ።
በሌላ በኩል ግን ከአዲስ አባባ ውጭ ያሉ አከፋፋዮች ቁጥር አነስተኛ መሆን የግል ጋዜጦችን ተደራሽነት በአዲስ አበባ ብቻ የተገደበ እንዲሆን አድርጎታል የሚሉም አሉ።
ጋዜጠኝነት እና ወገንተኝነት
ከወገንተኝነት ነፃ መሆን ዋነኛ የጋዜጠኝነት ወሳኝ መርሕ መሆኑን በዘርፉ ያሉ ምሁሮች በተደጋጋሚ ያስረዳሉ። የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ምሩቁና በጋዜጠኝነት ሙያ ከ25 ዓመት በላይ በቢቢሲና አሶሼትድ ፕሬስ የሠራው ቶኒ ሮጀርስ በቅርቡ ባወጣው ጽሑፍ የጋዜጠኞች ዘገባ፣ በተለይም ዜና በሚሠሩበት ወቅት የራሳቸውን ፍላጎትና አስተያየት እንዲሁም ጥላቻ ቸል በማለት ከማንኛውም ወገን ነጻ መሆን እንዳለባቸው ገልጿል።
እውነተኛ ዘገባ ለመሥራት ጋዜጠኞች ነጻ እና ገለልተኛ መሆን እንዳለባቸውም ቶኒ ይመክራል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህሩ ተሻገር ሺፈራው (ዶ/ር) በቶኒ ሐሳብ ይስማማሉ። ምሁራኑ ከወገንተኝነት የፀዱ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ወሳኝ ናቸው ይበሉ እንጂ በኢትዮጵያ የአሁን ወቅት ተጨባጭ ሁኔታ ከዚህ በተቃራኒ እንደሆነ የሚሞግቱ አሉ።
የጋዜጠኝነት መርሖዎች በተለይም በኅትመት መገናኛ ብዙኃን በኩል በአግባቡ ሲተገበሩ አይስተዋልም የሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ተሻገር ከጋዜጠኞች አዘጋገብ ጋር በተያያዘ ከእውነታው ይልቅ ወገንተኛነትን እደሚያንፀባርቁ ይገልጻሉ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንድ ጋዜጦችና መጽሔቶች በፊት ገጻቸው ላይ የማኅበረስቡን እሴት በሚነካ መልኩ ዘገባዎችን ይዘው ሲወጡ ይታያሉ የሚሉት ተሻገር ጋዜጠኝነት ትልቅ የአገር እሴት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ በዚህ ሐሳብ የማይስማማው አቤል ሁሉም ጋዜጠኛ መርሕ ጠብቆ እስከሠራ ድረስ አቋም ሊኖረው ይገባል የሚል ሐሳብ አለው፡፡ በሌላ በኩል የጋዜጠኛ የግል አቋም ሥራው ላይ ሊንፀባረቅ እንደማይገባ የሚሞግቱ ወገኖች ጋዜጠኛ ሥራው ላይ ማንፀባረቅ ያለበት አቋም “እውነትንና ሚዛናዊነትን” ነው ይላሉ፡፡
የብሮድካስት ባለሥልጣን በተለይም ለኅትመት መገናኛ ብዙኃን የፍቃድ ማረጋገጫ ምስክር ወረቅት ከመስጠት በዘለለ በዘርፉ ያሉት ጋዜጠኞች ትክክለኛ ሥራ እየሠሩ ነው ወይ የሚለው ላይ ቁጥጥር አለማድረጉ በጋዜጦች እና መጽሔቶች አካባቢ ለሚታየው ክፍተት ምክንያት መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ። የባለሥልጣኑ ከፍተኛ ባለሙያው የሆኑትና ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሠራተኛ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ብቁ ባለሙያዎች የሌሉት ባለሥልጣኑ በሙያውም ሆነ በመገናኛ ብዙኃን ከወገንተኝነት አንፃር ለሚታዩ ችግሮች ተጠያቂ ሊሆን ይገባል።
ችግሩ ይብዛም ይነስም፣ እንደገና ማንሰራራት የጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪው ገና በእንጭጭ ደረጃ ላይ እንዳለ የሚስማሙ አካላት ትኩረት እንደሚፈልግ ይመክራሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ያነሰ ሕዝብ ባላት ኬኒያ 14 የግል ጋዜጦች ያሉ ሲሆን የአገሪቷም ትልቁ ጋዜጣ ዴይሊ ኔሽን በቀን 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች ያነቡታል። በአንጻሩ በኢትዮጵያ ያሉ ጋዜጦችና መጽሔቶች የዚህን ግማሽ ያህል ተደራሽ አለመሆናቸውም ይነሳል።
ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011