ነገረ አባይ – እነርሱ ምን አሉ?

0
1186

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአባይን ዝማሬ ቀይሮታል። አሁን አባይ የግርማ ሞገስና የውበት መገለጫ ብቻ ሳይሆን፣ የሉዓላዊነት አጀንዳ ላይም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። በተለይም በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል ባለው ድርድር፣ በመገናኛ ብዙኀን ሽኩቻና በሕዝቦች ትኩረት መካከል፣ አባይ ራሱን የቻለ የታሪክ ምዕራፍ ተከፍቶለታል።

ኢትዮጵያውያን አሁን የአባይን ነገር መስማት ብቻ ሳይሆን ማድመጥ፣ ማየት ብቻ ሳይሆን መመልከት ጀምረዋል። ከታሪክ አውድ ላይም የአባይ ሥም በጉልህ ተጽፏል። ታሪክ ነገረ አባይን እንዴት ያየዋል?

ኢብራሂም ሙሉሸዋ ታሪክ አጥኚ እና ፖለቲከኛ ናቸው። አሁን ደግሞ ከባልደረባቸው ዑመር መኮንን ጋር በመሆን በአዋሽ ኤፍ ኤም በየሳምንቱ ቅዳሜ ከ7 ሰዓት እስከ 9 የሚዘልቅ ‹ከአባይ ጓዳ› የተሰኘ መሰናዶ እያዘጋጁ ነው። በዚህ መሰናዶ በዋናነት በሳምንቱ የአረቡ መገናኛ ብዙኀን ስለኢትዮጵያ እና ስለሕዳሴ ግድቡ ምን አሉ የሚለውን ሲያነሱና በባለሞያ ሲያስተነትኑ፣ ለዘለቄታው ደግሞ ኢትዮጵያና የሩቅ ምሥራቅና የአረብ አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ስላላቸው ግንኙነቶች የሚያወሳ ነው።
ታድያ ኢብራሂም ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ፣ ታሪክ የአባይን ነገር እንዴት ያየዋል የሚል ጥያቄ ተነስቶላቸዋል። እርሳቸውም አሉ፤
‹‹ታሪክ የምናጠናው ይጠቅመናል ብለን ስናስብ ነው። ከሕይወት ጋር ሲያያዝ ነው ታሪክ የሚነሳው። እስከ ዛሬ ከአባይ ጋር የተገናኘ ሥልጣኔያችንን አላጠናንም።

ይጠቅመናል ብለን ስላላሰብን። ታሪክ የሚጠናው ለታሪክነቱ ብቻ ሳይሆን ከሕይወታችንም ጋር ስለሚያያዝ ወይም ሲያያዝ ነው። እስከ አሁን አባይን አላያያዝነውም ነበር። ከአሁን በኋላ የታሪክም ጥናት ተስፋ አለን። የአባይ ታሪክ አሁን መጻፍ ይጀመራል። እስከዛሬ ምን ተጻፈ የሚለውን ማጥናትም እንጀምራለን፣ ነገሥታቱ ምን አደረጉ እንላለን። ታሪክ ተጽፎ ሳይሆን እንቅስቃሴ የሚጀመረው፣ እንቅስቃሴ ነው ታሪክን የሚጀምረው።››

ታድያ የምናውቀው ታሪክ ምን ይለናል? ጋዜጠኛና የታሪክ ተመራማሪ ጥበቡ በለጠ ደግሞ ወዲህ በአባይ ጉዳይ ላይ ተደርገው ስለነበሩ ስምምነቶች አውስተዋል። ይልቁንም የ1929 እና የ1959 የሚባሉ ውሎች ነበሩ ይላሉ። በአብዛኛው ታድያ ውሎቹን የተዋዋሉት ግብጽ እና ሱዳን ናቸው። ኹለቱም አገራት ደግሞ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ነበሩ።

ስምምነቱ እንዴት ተደረገ ቢባል፤ ውሉ ሱዳን ውስጥ ያለ እንግሊዛዊ ግብጽ ካለው እንግሊዛዊ ጋር ነበር የተከናወነው ማለት ነው። እነዚህም የቅኝ ግዛት ውሎች ናቸው። ኢትዮጵያ ደግሞ በቅኝግዛት አልተገዛችምና፣ እንኳን ያኔ አሁንም በየትኛውም የቅኝ ግዛት ውል አትተዳደርም። ውሎቹም አይመለከቷትም።

ጥበቡ ታሪክን አውስተው እንዳሉት፣ ግብጾች ከብዙ ዓመታት ጀምሮ አባይን ከምንጩ የመቆጣጠር እቅድ ነበራቸው። በጦርነትም ይሁን አልያም ሰላም በመንሳትና በዲፕሎማሲ ተጽእኖ በማድረግ፣ ኢትዮጵያን የማዳከም ፕሮጀክት በግብጽ ዘንድ ነበር። በአንጻሩ ደግሞ የኢትዮጵያ ነገሥታትም ‹አባይን እንገድባለን› ብለው በተደጋጋሚ ተነስተዋል።

ታድያ በየዘመኑ ከተሠሩ ሥራዎች ውስጥ ጥበቡ ጥቂቶቹን ጠቅሰዋል። ይልቁንም ከቅዱስ ላሊበላ ዘመን ጀምሮ፣ ንጉሡ አባይን እገድባለሁ ይል ስለነበር፣ የግብጽ ነገሥታት በየዓመቱ ወርቅን በስጦታ ይገብሩ ነበር። በኋላ ዘመናትን ተሻግሮ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥትም ትልቅ ሥራ መሠራቱን ነው ጥበቡ የሚያወሱት። በጊዜውም ንጉሡ የግድቡን ነገር አስጠንተው ፕሮጀክት አሠርተው ነበር።

በደርግ ዘመነ መንግሥትም ‹የሸለቆዎች ልማት› በሚል መሥሪያ ቤት ተቋቁሞ መገደብ እስኪቻል በአባይ ውሃ ልማትን ለማካሄድ ተጥሯል። አባይ ያንንም አልፎ ኢሕአዴግ ከመጣ በኋላ ዓመታትን ቆይቶ የግድቡ ነገር ዳግም ተነሳ። ዛሬም ላይ ደረሰ።

‹‹አባይ ትልቅ የሥልጣኔ መገለጫ ነው። ግብጾችም ትልቅ የተባሉት በዛ ነው። ኢትዮጵያ ግን ከዛ ተጠቃሚ ሳትሆን ቀርታለች። ድርቅ ተደጋጋሚ አግኝቷታል። አፈሯ ተሸርሽሯል።›› ሲሉ ጥበቡ ይገልጻሉ። ብዙ ወንዞች ያሏት ኢትዮጵያ ሰባ በመቶው ግን ከአባይ ጋር የሚገናኝና የአባይ መጋቢ ነው። ማለትም ሠላሳ በመቶ ብቻ ነው በኢትዮጵያ ብቻ የሚቀሩት የውሃ አካላት።

ጥበቡ አክለው እንዲህ አሉ፤ ‹‹አባይ ሀብት ነው። ኢትዮጵያ ዜጎቿን ድርቅ ያጠቃቸው ነበር። ስለዚህ አልምታ የመጠቀም ኃላፊነት የራሷ ነው። የምትጠቀመው በራሷ ድንበር ያለውን ነው። ገድባ አላስቀረችም። ልማት ነው የምታካሂደው። ችግሮችን በማስወገድ፣ በዲፕሎማሲና የውስጥ ዘረኛ ፖለቲካን በማጥፋት፣ አገራዊ የአንድነት ጥንካሬን ማምጣት ያስፈልጋል።›› ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በግብጽ በኩል የኢትዮጵያ ጥያቄ በትክክል መረዳትን ያገኘ አይመስልም። በአንድ ወገን በቅኝ ግዛት ዘመን በነበረ ውል በሌላ በኩል የኢትዮጵያን የመጠቀም መብት በሚጋፋ መልኩ፣ ነገር ግን ከስጋት የመነጨ በሚመስል ስሜት ግብጽ ስሜቷን ስታንጸባርቅ ቆይታለች። መገናኛ ብዙኀንም የግብጽን ሕዝብ የሚያሳስቱና በኢትዮጵያ በኩል ያልተባሉ፣ የግብጽ ባለሥልጣናት በሥልጣን ላይ የሚያቆያቸውን ሐሰተኛና ትክክል ያልሆኑ መረጃዎች ሲያቀብሉ ከርመዋል። ይህም ገና ግድቡ ሲወጠን የጀመረ ሲሆን፣ አሁን የውሃ ሙሌት ዋዜማ ላይ ተባብሷል።

የግብጽ መገናኛ ብዙኀንና ሐሰተኛ መረጃዎች
እናም አሁን አባይ አጀንዳ ሆኗል። ያም ብቻ አይደለም፣ የህዳሴ ግድቡ ወደ ማጠናቀቂያ ሥራውና ወደ ውሃ ሙሌቱ ሲቃረብ፣ ግብጽም በዛው ልክ ውጥረቷ ጨምሯል። እናም በየእለቱ ከግብጽ የሚሰሙ ዜናዎች የብዙዎን ትኩረት ይስባሉ።

‹ግብጽና ግብጻውያን ምን እያሰቡ ይሆን?› ብዙዎች መልሱን ማወቅ የሚፈልጉት ጥያቄ ነው። በተለይም ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን በመሥራትና በመጠቀም ውስጥ ማንንም ልትጎዳ የማትፈልግ መሆኗን ዓለሙ ቢያውቅና ቢረዳ ብለው የሚመኙ ብዙዎች፣ ነገሩ ሁሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ይመኛሉ። ስለዛም ግብጽ የምትፈጥራቸውን እያንዳንዳቸውን ኮሽታዎች በትኩረት ይከታተላሉ።

የግብጽ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለራሱ የፖለቲካና የሥልጣን ትርፍ አባይን እርሾ ማድረጉ አይቀሬ ነው። ይህም የሚያሰጋቸው በርካቶች፣ የግብጽ መገናኛ ብዙኀን ያንን ተከትለው የሚነዙት መረጃ ጉዳይ ያስጨንቃቸዋል። የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ሲወጠን የጀመረው የግብጽ ቅሬታና ማጉረምረም፣ ግንባታው ሲካሄድና ሲጋመስ እንዲሁም አሁን መጠናቀቂያው ላይ ሆኖ የውሃ ሙሌት ሲቃረብ፣ እየናረ መጥቷል።

ኢብራሂም ሙሉሸዋ ከላይ የጠቀስነውን ከአባይ ጓዳ የተሰኘውን መሰናዶ ከባልደረባቸው ጋር በመሆን ከጀመሩ ሦስት ሳምንታትን ዘልቀዋል። በአገራዊና ቀጠናዊ ትስስር ጥናት ማእከል (Center for National and Regional Intelligence) እና በአዋሽ ኤፍ ኤም ትብብር የሚቀርበው ይህ መሰናዶ፣ ስለመካከለኛው ምሥራቅና አጠቃላይ ስለአረብና ሙስሊሙ ዓለም በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ስላላቸው ግንኙነት ያነሳል።

‹ጆሮ ለራሱ ባዳ ነው› እንዳይባል፣ ግብጽን ጨምሮ በአረቡ መገናኛ ብዙኀን ስለኢትዮጵያ የተባለውን በትርጉም ትርጉም ነበር የምንሰማው። ይህ ግን የዲፕሎማሲያዊ ሥራ ለመሥራትም ሆነ ስህተቶችን ከስር ከስር ለማረም የሚያግዝ አይደለም። ‹ከአባይ ጓዳ›ም በሳምንቱ ስለአባይ ምን ተባለ የሚለውን ጉዳዩ አድርጎ፣ የተባለውን ለባለሞያዎች በመግለጽ እንዲተነትኑና ሐሳብ እንዲሰጡበትም መድረኩን ፈጥሯል።

ይህም ብቻ አይደለም። አሁን ላይ ሥማቸውን እየሰማነው ያለ በአረብኛ ቋንቋ በየመገናኛ ብዙኀኑ ቀርበው የኢትዮጵያን ወገን የሚያስረዱ ኢትዮጵያውያን ታይተዋል፤ ተሰምተዋል። የብዝኀ ቋንቋ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ አረብኛ በጊቢዋ የሚነገር አንዱ ቋንቋ ቢሆንም፣ በቋንቋ ላይ አሁንም መሥራት ያለባት እንዳለ ይህ ማመላከቻ ነው። ለጊዜው ግን እነዚህን ለአገር የደረሱ ባለውለታዎች ማመስገን ተገቢ ነው።

ወዲህ ወደ መገናኛ ብዙኀኑ እንመለስ። ኢብራሂም እንዳሉት መገናኛ ብዙኀኑ ምን አሉ የሚለውን ማወቅ ለሕዝብም፣ በዘርፉ ለሚንቀሳቀሱ ባለሞያዎችም ጥቅሙ የጎላ ነው። ‹‹እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግብጾች ምን እያሉ ነው የሚለውን አናውቅም። ብዙ ጊዜ የትርጉም ትርጉም ነው የምንሰማው። ትክክለኛ ነገር ከተነገረ እናርማለን፣ የተሳሳተ ነገር ከጻፉ ደግሞ ለወደፊቱ እንዴት አድርገን ግብረ መልስ እንደምንሰጥ እንሠራለን። ወደፊትም ለባለሞያዎች ስለእኛ ያለውን እውቀትና የተዛባ መረጃ እንዲሁም አመለካከት እናውቅበታለን። እንዳየነው ብዙዎቹ የሚስተካከሉ ናቸው።›› ብለዋል።

ታድያ ከታዘቡት ሲያነሱ፣ በግብጽ ባሉ መገናኛ ብዙኀን በኩል የማን-አለብኝነት መንፈስ እንደሚነበብ ሳይጠቅሱ አልቀሩም። ይልቁንም መልስ የሚሰጥና የሚሞግታቸው እንደሌለ ሁሉ፣ ትክክለኛ ያልሆኑና ያልተጣሩ መረጃዎችን ሳይቀር ያቀርባሉ፤ ይጽፋሉ። ‹‹የእኛ ሰው እንደሌለ ያስታውቃል። በግዴለሽነት ነው የሚጽፉት። ይህ ነገር በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ሁኔታ ማስረዳት እንዳለብን የሚሳየን ጉዳይ ነው።›› በማለት አስረድተዋል።

ታድያ እንደተባለው ይህ አውድ እነርሱ ምን አሉ የሚለውን ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ወገን ያለውንም ለእነርሱ ማድረስንም ይመለከታል። ከላይ እንዳነሳነው በዚህም ላይ እውቀት፣ ጉልበትና ጊዜያውን ሰጥተው ለማገልገል ያልሰሰቱ ሰዎችን እየታዘብን ነው። ከእነዚህም መሐመድ አል አሩሲ፣ አብዱረህማን ዩሱፍ፣ ዮስራ ሲራጅ፣ ዑመር ረዲ፣ ዑመር አሊ ምራህ፣ አንዋር ኢብራሂም፣ ኑር ጣህር ተጠቃሽ ናቸው።

ኢብራሂም እንዲህ አሉ፤ ‹‹ኹለት ነገር ያስፈልጋል። አንደኛ እኛ ስለእነርሱ ያለን እውቀት። አረብኛ ማወቅ ብቻ አይለደም። ባለሞያዎች አሉ፣ ግን ቋንቋውን አያውቁም። ቋንቋ የሚውቁ ደግሞ የዲፕሎማሲ እውቀት የሌላቸው አሉ። ኹለቱን ማገናኘት ላይ ነው መሠራት ያለበት።›› ብለዋል።

አያይዘውም ‹‹የአረቦችን ወደዚህ ወደ እኛ ስንተረጉም ለእኛ ምሁራን፣ ጋዜጠኞችና ዲፕሎማቶች መሣሪያ እየሰጠን ነው። እነርሱ ደግሞ ይህን ተረድተው የሚያመርቱትን እውቀት ወደ አረብኛ መተርጎም ያስፈልጋል። አሁን ቢሮክራሲና ዲፕሎማሲ ውስጥ ያሉ፣ በዲፕሎማሲ ልምድና እውቀት ያላቸው አለ፤ ቋንቋውን ግን የማይችሉ። አሁን ኹለቱን አንድ ላይ አምጥተን እንዴት እንሠራለን የሚለውን አተኩረንበት ነው እየሠራን ያለነው።›› ሲሉም በኹለት ወገን የሰላ ለመሆን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ጠቅሰዋል።

አልዘገየም ወይ?
መገናኛ ብዙኀን የሕዝብ ትኩረት በመፍጠርና አጀንዳ በመስጠት በኩል ወሳኝ ሚና አላቸው። ነገረ አባይን አሁን ባለው መልኩ ምን ያህል ትኩረት ሰጥተውታል የሚለው ሲነሳ፣ አሁን ባለውና የአረብኛ ቋንቋንና ‹ግብጽ ምን አለች?› የሚለውን ባማከለ መልኩ ባይሆንም ሥራዎች ይሠሩ እንደነበር ብዙዎች ያነሳሉ።
‹‹መንግሥት ትልቅ ነገር ሠርቷል። ለእኔ ሕዝብን አንድ አድርጎ ግድቡን እውን ማድረግ የዲፕሎማሲ ድል ነው። ግብጽ ግድቡ ከመሠራቱ በፊትም በተግባር የበላይ ነበረች።›› ሲሉ ኢብራሂም ያነሳሉ። መንግሥት ግድቡ እንደሚሠራ ባበሰረበት ማግስት የግብጽ ድምጽ መሰማት ቢጀምርም፣ መንግሥት በአገር ውስጥ ያለውን ሥራ በማስቀጠል በኩል ትልቅ ሥራ ሠርቷል ይላሉ።

‹‹ግድቡ ከመሠራቱ በፊት እንዳይሠራ ነበር የምትለው፣ ልክ ሲጀመር እንዳትቀጥሉ ነበር የምትለው፣ አሁን እንደቀጠልን ስታውቅ ደግሞ ውሃ እንዳትሞሉ ነው እያለች ያለችው።›› በማለት የሚያወሱት ኢብራሂም፣ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ትግል እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቁመዋል። በተለይም መሬት ላይ ያለውን ነገር መለወጥ መቻልና ግድቡን አሁን የደረሰበት ደረጃ ማድረስ ቀላል ተግባር እንዳልሆነ ነው የጠቆሙት።

‹‹ጥያቄው ይሄ ከተሠራና እዚህ ከደረሰ በኋላ ግን የአረብ ሕዝቦች እንዲሁም ግብጾች ኢትዮጵያ ምን እየሠራች ነው ብለው ነው የሚያወሩት የሚለው ላይ ሠርተናል ወይ ነው።›› ሲሉ የሚጠቅሱት ኢብራሂም፣ ኢትዮጵያ ግድቡን እየሠራች ያለችው ለኢኮኖሚ ጥቅም ሳይሆን፣ ሆነ ብላ ግብጽን ለማስራብ ነው የሚል ፕሮፓጋንዳ እየተሠራ መልስ ሳይሰጥ መቆየቱ ላይ ነው ድክመታችን ይላሉ።

በኢትዮጵያ በኩል አልተሠራም የሚሉትም ይህንን ነው። እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ፤ ‹‹እኛም ጋር ያለው ድክመት ይሄ ነው። ስለ አረብ አገራት አናውቅም። የእውቀት ፕሮፓጋንዳ ያስፈልጋል። እሱ ላይ በጣም ክፍተት አለ።›› ይላሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ግብጽ ምን አለች የሚለውን ለማንሳትና በዛ ላይ መልስ ለመስጠትም ዘግይተናል ባይ ናቸው።

ለምን ዘገየን የተባለ እንደሆነ እርሳቸው ነገሩን ከመገናኛ ብዙኀን ነጻነት ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ። ‹‹እነዚህ ነገሮች ከዴሞክራሲ ጋር ይያያዛሉ። ለመሥራት ነጻነት አስፈላጊ ነገር ነው። ሰዎች የፈጠራ ሐሳብ የሚኖራቸው ነጻ ሲሆኑ ነው። እኛን ማንም አያስገድደንም። እንደፈለግን ተርጉመን ብንሠራ ነጻ ነን። በፊት ግን በመንግሥት ስር ነው። መንግሥት የሚችለውን ሠርቷል። ግን መብትና የአእምሮ ነጻነት በሌለበት ፈጠራ አይበረታታም።››

በድምሩ አሁን የሚታየው የግል ባለሞያዎችና የምሁራን እንዲሁም የጋዜጠኞች ተነሳሽነትን ኢትዮጵያ አስቀድሞ ያጣችውን ነገር የሚያሳይ ነው ባይ ናቸው።
ሌላው ይህን ሥራ ያዘገየው፣ እንደ ኢብራሂም ገለጻ፣ እስከ አሁን የነበረው ሽኩቻ የፓርቲ ፖለቲካ ላይ በመሆኑ ነው። ያኛው ፓርቲ ይምራ ወይም ይህኛው የሚለውን ትቶ፣ ማንም ይምራ ማን ኢትዮጵያ ይለፍላት የሚል ድምጽ ያስፈልጋል። ከፖለቲካ ጉዳይ ውጪ በሆነ መልኩ የአገር ጥቅም በሚያሳዩ ቦታዎች ላይ መሰማራትም ያስፈልግ ነበር። ሆኖም አጀንዳው ሁሉ የፖለቲካና የመብት ጉዳይ ብቻ ነበር፤ እናም ዛሬ ላይ የሚሠራውን ዓይነት ሥራ አስቀድሞ ለመጀመር ጊዜ አልተሰጠም።
‹‹አሁን ያለውን አንጻራዊ ነጻነት መጠበቅ ያስፈልጋል። ነጻነት የሌለው ሕዝብ በፍጹም ፈጣሪ አእምሮ አይኖረውም። አእምሮው የተያዘ ነው። አስቀድሞ ያዘገየንም፣ ስለማሰርና መታሰር ነው እንጂ ስለአገራችን ጥቅም አላወራንም።››

ሐሰተኛ መረጃ
በተያያዘ ሐሰተኛ መረጃዎችን ይነሳሉ። ‹‹ሐሰተኛ መረጃ በጀት ተይዞለት ሲሠራ ነው ያየነው። እኛ ደግሞ እውነቱን ለማስረዳት በጀት አልመደብንም። ግን ለዚህ በጀት መመደብ ያስፈልገል።›› ብለዋል፤ ኢብራሂም። በግብጽ መገናኛ ብዙኀን በኩል ሱዳንን እንከማስፈራራት የሚደርስ ሥራ በሰፊውና በብዙ በጀት እንደሚሠራም ከትዝብታቸው ጠቅሰዋል።

‹‹የኢትዮጵያ ግድብ ኻያ ዓመት ሳይሆነው ይፈርሳል እያሉ ነው የሚያወሩት። ይህንንም ሥራዬ ብለው አጀንዳ አድርገው ውይይት ያደርጉበታል፣ መጽሐፍ ይጽፉበታል። ኢትዮጵያ የምትሠራው ግድብ ፈርሶ ጎርፍ ሆኖ ሱዳንን ያጠፋል የሚል ዘገባም ያወጣሉ። ኢትዮጵያ ሆነ ብላ እንጂ ችግር የለባትምም ይላሉ። ሕዝቡም በእርግጠኝነት የምሁራኑን ድምጽ ነው የሚሰማው። ስለዛም ለምን እንጎዳለሁ ይላሉ።›› በማለት ያብራራሉ።

ለማጠቃለል
አሁን ላይ በርካታ የመገናኛ ብዙኀንና ግለሰቦችም ጉዳዩን ነገሬ ብለውታል። በተለይም ቋንቋ ችግር ሆኖ ኢትዮጵያ በሐሰት ስትወነጀልና በዚህም የተሳሳተ መረጃ በኹለቱ አገራት መካከል ግጭት እንዳይፈጠር፣ በተቻለ መጠን ሁሉን በሰላም ለማጠናቀቅም ይህ ዋጋው ትልቅ ነው። ምንም እንኳ የግብጽ አገር ገዢ ባለሥልጣናትን ምኞት፣ አልያም ኢትዮጵያን ሰላም ለማሳጣት የሚሹትን ፍላጎት መግታት ባይቻልም፣ ቢያንስ ይህ በዓለም አደባባይ እውነት ያላት ኢትዮጵያ የምትሟገትበት አውድ ነውና ዋጋው በቀላል የማይተመን ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here