የሰቆጣ የብረት ማዕድን ማውጣት ፕሮጀክት ከፍተኛ ችግሮች ተደቅነውበታል

0
495

ሰቆጣ ማይኒንግ ኃ.የተ.ማ በዋግ ሕምራ ዞን የብረት ማዕድን ለማውጣት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የቅድመ አዋጪነት ጥናትም ሆነ የአዋጪነት ጥናት አጥንቶ የጨረሰ ሲሆን ወደ ተግባር ለመግባት ግን ብዙ ችግሮች ተደቅነውበታል ሲሉ የኢትዮጲያ ብረታ ብረት ጥናትና ፕላን ዳይሬክተር ጥላሁን አባይ ገለጹ፡፡
ጥላሁን ኹለቱም ጥናቶች ተጠናቅቀው በቦታው ላይ አፈር የማውጣት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ፕሮጀክቱን ወደ ተግባር ለማስገባት ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ስለሚያስፈልግ እና ይህ ከፍተኛ ካፒታል ፕሮጀክቱ ላይ ቢውል እምቁ ሃብት ምን ያህል ዓመት ያስኬዳል የሚለው መታየት ይኖርበታል ሲሉ ጥላሁን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እርሳቸው እንደሚሉትም የብረት ማዕድን ይዘታቸውን አስመልክቶ ጥናት በተደረገባቸው ቦታዎች ያለው የማዕድን መጠን አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት በአዋጭነት ጥናቱ እንደ ምርጫ የተቀመጠው ማዕድኑን ማውጣት ሳይሆን ማዕድኑን እና አፈሩን ከውጭ አምጥቶ የተቀሩትን ሒደቶች ኢትዮጲያ ውስጥ ማስኬድ ነው፡፡
ጥላሁን በጥናቱ በሰቆጣ የታየው የብረት ማዕድን የክምችት መጠን 47.027 ሚሊዮን ቶን ሲሆን ኢትዮጲያ ውስጥ አሁን ያለው ፍላጎት መጠን 10 ሚሊዮን ቶን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የፍላጎት መጠኑ እየጨመረ እንደሚሔድ ግምት ውስጥ ሲገባ የክምችት መጠኑ አነስተኛነት እየጎላ ይመጣል ባይ ናቸው ጥላሁን፡፡ ነገር ግን ይሄም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ጠቀሜታ የለውም ማለት አይደለም ሲሉ አክለው የገንዘብ አቅም ኖሮ በአገር ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች መሰራት ቢጀምሩ ውጪ ያሉ ትላልቅ ድርጅቶች እንዲገቡ እና አብረውን መሥራት እንዲፈልጉ ይጋብዛል፤ በዚህም ብዙ ነገር ይቀላል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ‹‹ማዕድኑን ማውጣቱ ቀርቶ እራሱ ማዕድኑን እና አፈሩን ከውጪ አስመጥተን በጥናቱ መሰረት በኹለት ጊዜ ሂደት 10 ሚሊዮን ቶን ለማምረት የአባይ ግድብ ወጪን አራት እጥፍ የሚጠጋ ወይንም 14 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ሲሉ ጥላሁን ይናገራሉ፡፡

አብዛኛውን የአገር ሀብት በውጭ ምንዛሬ ከሚባክንባቸው ዘርፎች ውስጥ ለአምራች ዘርፉ ግብዓትነት የሚውሉ የጥሬ እቃዎች ማስመጣት አንዱ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪው ዋነኛው እንደሆነ ተገልጿል።

በአገር ውስጥ የሚመረቱት እቃዎች በመጨመራቸው እና ጥሬ እቃዎች አገር ውስጥ በመመረታቸው ምክንያት ከፍተኛ እጥረት የሚታይበት የውጪ ምንዛሪ ወጪ ይቀንሳል ብለዋል ጥላሁን፡፡

መንግሥት ከሚያወጣው ወጪ ውስጥ አብዛኛው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለብረታ ብረት ኢንዱስትሪው ነው ያሉት ጥላሁን፣ ትኩረት ተሰጥቶት ቢሠራ በዘላቂነት የሚወጣውን ወጪ ቀንሶ ትርፋማነቱን ማብዛት ይቻላል ብለዋል።

ጥላሁን የብረት ማዕድንን በአገር ውስጥ የማውጣት ሥራው ቢጀመር ወይንም ከውጭ አገር እያስመጡ ቀሪ ሂደቱን እዚሁ የማከናወን ሥራ ቢጀመር ከገንዘብ ሌላ ትልቅ ተግዳሮት የሚሆነው የመሰረተ ልማት ውስንነት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች ከምንም ፕሮጀክቶች በላይ የኃይል አቅርቦት እና ከፍተኛ የሆነ የከርሰ ምድር ውሃ በበቂ ሁኔታ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here