‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ በኢትዮጵያ ሐቅ፣ ፍትሕ እና ዕርቅ

0
927

ኢትዮጵያ በባሕሪው ያልተለመደ ዓይነት የፖለቲካ ለውጥ እያስተናገደች ነው። ይህንን ለውጥ ተከትሎ ባለፉት ዓመታት ሲፈፀሙ የነበሩ ሰብኣዊ ጥቃቶች በምን መንገድ ፍትሕ ያግኙ የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ ሆኗል። አዲ ደቀቦ ርዕሰ ጉዳዩን በማንሳት ስለ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ምንነት፣ እንዲሁም ለአሁኑ ነባራዊ የኢትየጵያ ተሞክሮ ምን ይደረግ በሚለው ላይ ሙያዊ አስተያየታቸውን ጽፈውልናል።

 

 

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚገኙ የሰው ልጆች ላይ እጅግ በጣም አሰቃቂ የግፍ ተግባራት ተፈፅመዋል። ከእነዚህ አሰቃቂ የጭቆና እና የግፍ ተግባራት ዋነኞቹ የተፈፀሙት ተቀዳሚ ሥራቸው ሥልጣናቸውን ማስጠበቅ በነበረ አምባገነን መንግሥታት እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ። በጭቆናውና በግፍ ተግባሩ የተነሳ የተጠለፉ፣ የጠፉ፣ የተገደሉ፣ የኅሊናና የአካል ስቃይ የደረሰባቸው፣ በግዳጅ የተደፈሩ፣ መገለልና ሌሎች በደሎች የደረሰባቸው ተበዳዮች በርካታ ናቸው። ጊዜ ይወስድ እንደሁ እንጂ እነዚህን መሰል የግፍ ተግባራት ሲፈፅሙ የነበሩ መንግሥታት አልፈው፣ በአዲስ መንግሥት መተካታቸው እና የሰው ልጆች የሕይወት ጉዞ መቀጠሉ አይቀርም። ይህ ሲሆን ታዲያ “በቀድሞው መንግሥት የተፈፀሙ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶችን አዲሱ መንግሥት እንዴት ይመለከታቸዋል?” የሚለው ጥያቄ ‘‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’’ (Transitional Justice) በመባል ይታወቃል።
‘‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’’ ቀድሞ ለተፈፀሙ ስልታዊና ሰፋ ያሉ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶች ምላሽ የሚሰጥ ነው። ዓላማውም የተበዳዮችን በደል ዕውቅና መስጠት፣ ቀጣይነት ያለው ሠላም፣ እርቅና እውነተኛ ዴሞክራሲን ማስፈን ነው። አንደ ችግሩ ስፋት ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ረዘም ላሉ ዓመታት ወይም እጅግ በጣም ባጠረ ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይችላል። የዚህ ዓይነቱ የፍትሕ ስርዓት እ.አ.አ. በ1980ዎቹ መጨረሻና በ1990ዎቹ መጀመርያ አካባቢ በላቲን አሜሪካና ምሥራቅ አውሮፓ የተጀመረ ስለመሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ። በወቅቱ በእነዚህ አገራት የሚገኙ ምሁራን አገራቶቻቸው በሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ከሚታወቁ አምባገነን መንግሥታት አገዛዝ ተላቀው ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር የሚያደርጉት ጥረት የፖለቲካ ለውጡን በማያውክ ወይም በማያሰናክል መልኩ እንዴት ይከናወን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ባደረጉት ጥረት የበሰለ ስርዓት ነው።
በብዙ አገራት የተሟላ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ሥራን ለመሥራት አዳጋች ሁኔታዎች ያጋጥማሉ። ከቀድሞ ስርዓት የሚመነጩ ችግሮች እጅግ በጣም ሰፊና ውስብስብ መሆናቸው እና የፖለቲካ ሚዛኑን ሊያዛቡ የሚችሉ የፖለቲካ መረጋጋት እጦቶች መኖር ለዚህ እንደ ምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ከዚህም ባለፈ ከቀድሞ ስርዓት የሚመነጩ ችግሮች እጅግ በጣም ሰፋ ያሉና ውስብስብም ሊሆኑ ይችላሉ። ለዚህም ሲባል ነው በቀድሞ አጥፊዎች ላይ የወንጀል ክስ ማቅረብ ብቻውን እንደ አማራጭ በቂ ስላለመሆኑ የሚነሳው። ትልቁ ጥያቄ የበዳይና የተበዳይ ቁጥር ሲበዛ፣ በደሉ ሲበረክት እና የክሱን ሒደት ሊመሩ የሚችሉ ተቋማት ደካማ ሲሆኑ፣ የለውጡን ሒደት በወንጀል ክስ ብቻ ለማለፍ መሞከር ከመፍትሔው ይልቅ ችግሩን ያባብሰዋል። የፍትሕ ተቋሙ የቀድሞ አጥፊዎች ሁሉ ለመክሰስ የአቅምም ሆነ የፍላጎት እጥረት ሊያጋጥመው ስለሚችል ሊከሰሱ የሚገባቸውን ሰዎች የመምረጥ ተግባር ውስጥ ገብቶ ከፊል ፍትሕ ለመስጠት መገደዱ ከችግሮቹ አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል። በዚህ ወቅት የቀድሞ በደል ፈፃሚዎች ናቸው ተብለው ለፍትሕ የሚቀርቡ ሰዎች ከሌሎች ተለይተን ተከሰናል እንዲሉ እና ደጋፊዎቻቸው የክስ ሒደቱን መርጦ ፍትሕ የሚሰጥ (Selective Justice) እና የአሸናፊዎች ፍትሕ (Victorious Justice) ሰጠ በማለት እንዲኮንኑት በር የሚከፍት መሆኑ አያጠራጥርም።
ለዚህም ሲባል ካለፉት ሦስት ዐሥርት ዓመታት ወዲህ ‘በሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ላይ መልካም የሚባለው ተሞክሮ በሽግግር ወቅት ሁሉን ዐቀፍ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ መሣሪያዎችን በአገልግሎት ላይ ማዋል ነው።
ሰሞንኛው ሁነት
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ያለውን ሰሞንኛ ሁኔታ ብንመለከት መንግሥት ራሱ ባመናቸውና በወንጀል የማጣራት ሒደት የተገኙትን ውጤቶች ለሕዝብ ይፋ በተደረገው መሠረት ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ሰፊ ስልታዊ የሰብኣዊ መብቶች ረገጣ እንደነበር ተነግሯል። ለዚህም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይቅርታ ጠይቀው የመንግሥት አስተዳደር ሥራቸውን በዕርቅና ፍቅር እንዲሁም በመደመር ፍልስፍና መምራት እንደሚሹ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል። ከዚህም አልፎ በቀድሞ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ፈፅመዋል እንዲሁም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተው የሕዝብን ሀብት መዝብረዋል፣ ወይም ጥቅም አሳጥተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ታስረው የወንጀል ምርመራ እየተከናወነባቸው ይገኛል። በመንግሥትም በኩል በተነፃፃሪነት የተሻለ የሰብኣዊ መብቶች አያያዝ እየታየ የሚገኝ መሆኑ ሲታይ በመጠኑ ላይ አለመግባባት ካልተፈጠረ በስተቀር በሽግግር ላይ ስለመሆናችን ያመለክታል።
ይሁንና ይህም በመሆኑ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተለያዩ አመለካከቶች ሲንፀባረቁ ይስተዋላል። ምርመራውን “ለውጥ ተቀባይ” እና “ለውጥ አደናቃፊ” በሚል ፍረጃ ውስጥ እየተካሔደ ያለ የፖለቲካ በቀል ነው የሚሉ ሰዎች በአንድ ጎራ በኩል አሉ፤ በሌላ ጎራ ደግሞ፣ የፍትሕ ስርዓቱ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን እያረጋገጠ የሚገኝበት፣ ለቀድሞ የወንጀል ተግባር እየተሰጠ ያለ ፍትሕ ነው የሚሉም አሉ። “ተጠርጣሪዎቹን ተጠያቂ በማድረግ (ከሚዘመርለት) የዕርቅ ሐሳብ ጋር አይጋጭም ወይ?”፣ “ይቅር ተባብሎ ማለፉ አይበጅም ወይ?” የሚሉ ጥያቄዎችም እየተነሱ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ቄስ ዴዝመንድ ቱቱ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፦
“የተደረገው ይቅርታና ዕርቅ የሆነው በደል እንዳልሆነ ለማስመሰል አይደለም። እውነተኛ እርቅ ጉዳትን፣ ክፋትን፣ በደልንና እውነትን አጉልቶ ያሳያል። አንዳንዴም ከነበረው ሁኔታ ወደባሰ ያመራል። እጅግ አስጊ ሥራ ቢሆንም ውጤቱ ግን ያማረ ነው። ምክያቱም በሐቅ ላይ ያልተመሠረተ እርቅ ሐሰተኛ ዕርቅ በመሆኑ ነው።”
አንዳንድ ሰዎች ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ቀድሞ በሚመጣ ሽግግር ወይም በእነርሱ ቋንቋ “መንግሥታዊ ለውጥ ባልተደረገበት እንደምን ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ሊኖር ይችላል?” ሲሉ ይሞግታሉ። በዚህ ረገድ የሌሎችን አገሮች ልምድ ብንወስድ ቺሊ፣ አርጀንቲና እና ደቡብ አፍሪካ ላይ ከመንግሥታዊ ለውጥ በኋላ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ የተተገበረ ሲሆን በጋና፣ ሴራሊዮን፣ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ እና ዩጋንዳ ላይ, የተደረገው ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ከቀድሞ መንግሥት ሙሉ ንጥጥል ባልተደረገበት ሁኔታ የተደረገ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ነው። የኢትዮጵያም ሁኔታ በሁለተኛው ዘርፍ ውስጥ የሚመደብ ነው። ምክያቱም የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት የተካሔደው በኢሕአዴግ ዘመን ሲሆን፣ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ይሰጥ እየተባለ ያለውም በዚሁ ዘመን በመሆኑ ነው። ስለዚህም አዲሱ የመንግሥት አመራር ለዲሞክራሲ ቆራጥ አቋም ያለው እስከሆነ ድረስ የሽግግር ፍትሕ ሊካሔድ የማይችልበት ምክንያት የለም።
መንግሥት ጭፍን ምሕረት የማድረግ መብት አለው?
በኢትዮጵያ ሁኔታ፣ “መንግሥት የወንጀል ክስ ማቅረቡ ስህተት ነው ወይ? መንግሥትስ ያለመክሰስ ወይም ያለቅድመ ሁኔታ የሚሰጥ ምሕረት (Blanket Amnesty) መስጠት ይችላል ወይ?” የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት አለባቸው። በዚህ ረገድ የአገሮች ልምድ እንደሚያመለክተው ከመሠረቱ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ን የሚያራምዱበት ምክንያት እውነታን ለማውጣትና ከነበረው ስህተት ተምሮ ድጋሚ እንዲህ ዓይነት በደል አይፈፀምም የሚል ቃል ለመግባት ነው። የተወሰኑ ሰዎችን መርጦ ክስ ማቅረብ ብቻ በራሱ እውነታን ከሚያወጣው ይልቅ የሚሸፋፍነው ይበልጣል፤ ከዚህ አንፃር ነገሩ በይቅርታ ብቻ ይታለፍ የሚል ክርክርም ቢሆን መንግሥት የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ፈፅመዋል ለተባሉ ሰዎች ይቅርታ የማድረግ ሥልጣን ያልተሰጠው ከመሆኑ አንፃር ሊታይ ይገባዋል።
ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው የዓለም ዐቀፍ ሥምምነቶች መካከል የአለም ዐቀፉ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን አንቀፅ 2 ሥር እንደተመለከተው፣ አገራት ሰብኣዊ መብቶችን ማክበር እንዳለባቸው የተደነገገ ሲሆን፥ መብቶች ተጥሰው ሲገኙ መንግሥት ክስ የማቅረብ ግዴታ ያለበት ስለመሆኑ አህጉራዊ የሰብኣዊ መብቶች ፍርድ ቤቶች፣ በተለያዩ ወቅቶች ውሳኔ ሰጥተዋል። የአለም ዐቀፉ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን ሥር የተዋቀረው የሰብኣዊ መብቶች ኮሚቴም በተመሳሳይ መልኩ የውሳኔ ሐሳቦችን በተለይም በንዲአ ባውቲስታ፣ በኮሎምቢ ላይ ባቀረቡት ክስ እንዲሁም የኮንጎ ሪፐብሊክ ሙቴባን በተመለከተ በዛየር ላይ ላቀረበው ቅሬታ፣ ይህንኑ የአገሮች ግዴታን በአፅንዖት ገልጾ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ያለ ሐቅ የመናገር ግዴታ የሚስሰጥ ምሕረትም በራሱ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ስለመሆኑም ተገልጾ ይገኛል።
መንግሥት ለተበዳዮች ካሣ ከፍሎ ጉዳዩ በዕርቅ ቢታይ፣ የሚለው አካሔድም አንዳንዴም አጥጋቢ አይደለም። ምክያቱም በክስ ወይም በሌሎች አማራጮች በተለይም የሐቅ ኮሚሽን ፊት ቀርበው ተበዳዮች የደረሰባቸውን በደል በአግባቡ ሳይገልጹና በዳዮችም ያደረጉትን ተናዘው እውነታው ባልወጣበት ሁኔታ በካሣ ሥም የሚከፈል ክፍያ የተበዳዮችን ዝምታ በገንዘብ እንደመግዛት ይቆጠራል። ስለዚህም “የኢትዮጵያ ሽግግርም እንዴት ይካሔድ?“ ለሚለው ጥያቄ ሊደረጉ የታሰቡ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ አማራጮች እውነታን የሚያወጡና የዕርቅ ሒደቱ ላይ አስተዋፅዖ የሚኖራቸው ሊሆኑ ይገባል። በዚህ ረገድ፣ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶቹ ሰለባ የሆኑ ሰዎች እውነቱ እንዲወጣ፣ ፍትሕ እንዲሰፍንና ዕርቅ ኖሮ ዳግመኛ እንዲህ ዓይነት ተግባር እንዳይፈፀም እንደሚሆን መገመት አይከብድም።
አምስት ጥቆማዎች
አሁን ያለው “የሽግግር ሒደት” በኢትዮጵያ በሚከተለው መልኩ ሊካሔድ ይገባል።
አንደኛ፣ ያደረገውን በደል ተናዝዞ ይቅርታ ያልጠየቀ ሰው የወንጀል ክስ ሊቀርብበት ይገባል ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪ እጅግ ጥቂት ነገር ግን እጅግ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ አንዳንድ ወንጀሎች ተለይተው ክስ የማቅረብ ሥራ (prosecution) መሠራት አለበት። መንግሥት ይህን ጉዳይ በተመለከተ ክስ አለማቅረብም ሆነ በምሕረት ማለፍ አይችልም። በዚህ ዕይታ በአሁኑ ጊዜ እየተካሔደ ያለው የወንጀል ምረመራ ተገቢ ነው የሚያስብል ነው። ይሁንና አሁን ያሉት ክሶች ከ‘ሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ አንፃር ሲቃኙ ከ‘ሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ መሣሪያዎች ውስጥ አንደኛው ብቻ ተነጥሎ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ስለመሆኑ ያመላክታል። ከላይ እንደተመለከተው የወንጀል ክስ ማቅረብ የሽግግር ጊዜ ተግባራት ውስጥ የሚካተት ቢሆንም፣ እነዚህ ሁሉ ውሳኔዎች ከመወሰናቸው በፊት አዲስ አዋጅ ወጥቶ በአዋጁ መሠረት ዘርፈ ብዙ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ መሣርያዎች በሥራ ላይ እንዲውሉ ቢደረግ የተሻለ ነበር። በልዩ ሁኔታ በምሕረት ሊያልፋቸው የሚችላቸው ድርጊቶች ለተበዳይ እውነቱንና በደሉን እንዲናገር ተፈቅዶለት እና በዳይም ተናዞ እና ተፀፅቶ ሲቀርብ ብቻ ነው። ይህም እውነትን በማውጣቱ የሚሰጥ ማበረታቻ ነው።
ሁለተኛ፣ ከላይ ለተመለከተው እውነት የማውጣት ሥራ ይረዳ ዘንድ የሐቅ ኮሚሽን (Truth Commission) ማቋቋም አለበት። የሐቅ ኮሚሽን ሥራም ከዚህ ቀደም ከነበረው ለየት ባለ መልኩ ለሕዝብ ክፍት በሆነ መልኩ ቢቻልም በሚዲያ አማካኝነት በሚቀርብ መልኩ ተበዳዮች አካላዊ፣ የሥነልቦናዊ፣ ምጣኔሀብታዊ እና ሌሎች ጉዳታቸውን የሚያቀርቡበት ሁኔታ መኖር አለበት። የሐቅ ኮሚሽን ሥራ የአጣሪ ኮሚሽን (Inquiry Commission) ሥራ አይደለም። የአጣሪ ኮሚሽን የምርመራ ሥራን በምሥጢር የሚያከናውን ሲሆን የሐቅ ኮሚሽን ሥራ በባሕሪው እንደ ፍርድ ቤት ለሕዝብና ብዙኃን መገናኛዎች ክፍት በሆነ መልኩ የተበዳይ ቃል የሚደመጥበት ሆኖ ከፍርድ ቤት የሚለየው የጥፋተኝነት ፍርድ ከመስጠት ይልቅ በአጠቃላይ ስለነበረው የሰብኣዊ መብቶች ጥሰጥ ሰፊ ሪፖርት የሚያወጣና ለተበዳዮችም ሊደረግ ስለሚገባው ካሣ ምክረ ሐሳብ ያወጣል። ይህም የነበረውን እውነታ መዝግቦ የሚያስቀምጥበት ስርዓት ነው። ለምሳሌ ባለፉት 27 ዓመታት በምን ዓይነት ወንጀል፣ ምን ያህል ሰዎች ጉዳት ደረሰባቸው? ምን ያህል ሰዎች ተሰወሩ? ምንስ ያህል ሰዎች ተገደሉ? የሚሉ ጉዳዮችን በሙሉ በሪፖርቱ ማካተት ያስፈልጋል።
ሦስተኛ፣ በደል ለደረሰባቸው ሰዎች (የግል ተበዳዮች) ካሣ ክፍያ መፈፀም (Reparation) እንዲሁም ያለአግባብ የተወሰዱ ንብረቶችን አስመልክቶ ለግለሰቦች ንብረት የመመለስ (Restitution) ሥራ ያስፈልጋል። አራተኛ፣ በደል ለደረሰባቸው ሰዎች መታሰብያ ማዘጋጀት የሚያስፈለግ ሆኖ ለሞቱና ለተሰወሩ ሰዎች ማንነታቸው ተለይቶ በአንዳች ሙዝየም ወይም ሌላ መታሰቢያ ቦታ ላይ ሥማቸውን ማተም ጨምሮ ሌሎች የመታሰብያ ሥራዎች ያስፈልጋሉ። በንፅፅር እጅግ የሰፋ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች መንገዶችን በሥማቸው እስከመሰየም የሚደርሱ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ።
አምስተኛ፣ መንግሥታዊ መዋቅርና የፍትሕ ዘርፍ ለውጥ ማምጣትን እና ሌሎች ተግባራትን ያጠቃልላል። ለሰብኣዊ መብቶች በደል አስተዋፅዖ የነበራቸው ተቋማት፣ እንዲሁም በደሎች ሲደርሱም ሆነ ከመድረሳቸውም በፊት የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት ለውጥ ያስፈልጋቸዋል። ከመሠረቱ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ዓላማም የአይደገምም ቃል ማስረጪያ መሆኑ ነው። ተቋማዊ ለውጥም ለማምጣት በፖሊስ፣ ዐቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤት እና ሌሎች የዲሞክራሲ ተቋማት ላይ ሲሠሩ የነበሩ ሰዎች በሕገ መንግሥቱና እና ዓለም ዐቀፍ ሕግጋት አንፃር የፈፀሟቸው ሥራዎች ተመዝኖ ከሥራ የሚሰናበቱበት አሠራር መኖር አለበት።
መታወስ ያለበት ከእነዚህ መሣርያዎች አንዱ ለብቻው ተነጥሎ የተዋጣለት ውጤት ሊያስከትል የሚችል ባለመሆኑ እነዚህን መሣርያዎች በማጣመር መተግበር ያስፈልጋል። ለዚህም ከመንግሥታዊ ውሳኔዎች በፊት በአዋጅ ሁሉን ዐቀፍ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ስርዓት ቢበጅለትና እንደ ግለሰብም ይሁን እንደ ማኅበረሰብ ከስህተቶቻችን ተምረን ዲሞክራሲ የሰፈነባት የጋራ አገር ብንገነባ መልካም ነው።

አዲ ደቀቦ የሕግ መምህር፣ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው adidekebo@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here