የጤና ሚኒስቴር በቀን 15000 ሰዎችን ለመመርመር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

0
388

የጤና ሚኒስቴር በአገር አቀፍ ደረጃ የኮቪድ 19 እለታዊ ምርመራን ወደ 15000 ከፍ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በአገራችን የኮሮና ቫይረስ መገኘቱ ሪፖረት ከተደረገበት ከመጋቢት 4/ 2012 ዓ.ም ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተከናወኑ ዋና ዋና ስራዎችን አስመልክቶ ዛሬ ሰኔ 16/2012 ዓ.ም ለጋዜጠኞች በተሰጠው መግለጫ እንዳብራራው በየጊዜው ከፍ እያለ የመጣውን የመመርመር አቅም በአሁኑ ሰኣት በብሔራዊ ደረጃ 8000 ማድረስ የቻለ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ ከወረርሽኙ መዛመት ጋር በተጓዳኝ የምርመራ አቅምንም ለማሳደግ ተገቢ መሆኑን በመታመኑ በቅርቡ 19 ተጨማሪ ምርመራ ጣቢያዎች ወደ ስራ እንደሚገቡ እና የምርመራ አቅምንም በቀን ወደ 15 ሽሕ ከፍ እንደሚያደርገው ታውቋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመግለጫው እንዳስታውቀው መንግስት የችግሩን ጥልቀት አስቀድሞ በመገንዘብ የተለያዩ አደረጃጀቶችን ሚኒስቴር መስርያ ቤቶችን ጭምር በማደራጀት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ በሙሉ ዓቅሙ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጠጠር ከመደበኛ ባለሙያዎች ውጪ ሌሎች ባለሙያዎችንም አሰልጥኖ ማሰማራት አስፈላጊ በመሆኑ 4,500 ያክል ቅጥር ባለሙያዎችን እና 12,000 የበጎ ፍቃድ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ወደ ስራ ማሰማራት ተችሏል ተብሏል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በአሁኑ ወቅት 223,341 የላብራቶሪ ናሙና ምርመራዎች የተካሄዱ ሲሆን ለ767,008 መንገደኞች የኮቪድ 19 የልየታ ስራ ተሰርቷል፡፡ ከጥር 15/2012 ዓ.ም ጀምሮ 32 ሚሊዮን ሰዎች በቤት ለቤት ዳሰሳ ታይተዋል፡፡ ክትትል ለሚስፈልጋቸውም አስፈላጊው ክትትል ተደርጓል፡፡

32,957 ሰዎች ደግሞ ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ንኪኪ ያላቸው የተለዩ ሲሆን፤ በዚህም አጠቃላይ 4,848 ያክል ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የተገኝቶባቸው 1,412 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል፡፡ የ75 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህወታቸውን አልፏል፡፡

በተጨማሪም ኮሮና ቫይረስን በአገር አቀፍ ደረጃ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በፌደራል፣ በየክልሎችና በየተቋማቱ ያሉትን አደረጃጀቶችና ተቋማት አቅም ለማጠናከርና ለመደገፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ለኮቪድ -19 ወረርሽኝ ለመከላከል ለሕክምና ግብአት ግዥ ፤ ለላብራቶሪ ምርመራ እና ለሌሎች ተግባራሮቶች ከፌዴራል መንግስት ለክልሎች የተለያዩ ድጋፎች መደረጋቸውም ተገልጿል፡፡

በዚህም መሰረት ይህ ሪፖርት እስከተጠናከረበት ድረስ፣ በልዩ ሁኔታ ለክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች ብር ከ400 ሚሊዮን በላይ ብር ለመደገፍ ተችሏል፣ ኮቪድ 19 ላይ ለተሰማሩ የፌደራል ተጠሪ ተቋማትና ሆስፒታሎች ጨምሮ ብር 250 ሚሊዮን በላይ ድጋፍ ተደርጓል፣ በስራ ላይ ደህንነት መጠበቂያና ሌሎች መከላከያ ግብዓቶች ድጋፍን ለክልሎች ብቻ ድጋፍ 513,000.000 ( አምስት መቶ አስራ ሶስት ሚሊዮን) ብር ተደርጓል ተብሏል፡፡

ወረርሽኑን መከላከልና ለመቆጣጠር የሚረዱ 2724 ያህል አምቡላንሶች ለክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች ተከፋፍለው ወደ ስራ መግባታቸውም ተገልጿል፡፡ ይህም በብር ሲተመን 3315108 000.00 (ሶስት ቢሊዮን አንድ መቶ አስራ አምስት ሚሊዮን መቶ ስምንት ሺ) መሆኑ የተገለፀ ሲሆን እንደየሁኔታው ድጋፎቹ የሚቀጥሉ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አሁን ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ለኮቪድ 19 ህክምና ብቻ 273 ያክል መካኒካል ቬንትሌተር አገልግሎት እየሠጡ ሲሆን፣ 100 በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በኩል በቅርብ ጊዜ ለህክምና ተቋማት የሚሰራጭ ይሆናል ተብሏል፡፡ እንዲም 300 ያክል ደግሞ በግዢ ሂደት ላይ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

የኳራንቲን፣የለይቶ ማቆያና የለይቶ መታከሚያ ማዕከላት በከተማ መስተዳደሮችና በሁሉም ክልልች የአለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መሰረት እንዲደራጁና አገልግሎት እንዲሰጡ ጥረት ተደርጓል ተብሏል፡፡

በእነዚህ መሰረት 13,859 የለይቶ መታከሚያ አልጋዎች እና 3,576 ደግሞ የለይቶ ማቆያ አልጋዎች በአጠቃለይ በአገር አቀፍ ደረጃ 17,435 (አስራ ሰባት ሺ አራት መቶ ሰላሳ አምስት አልጋዎች መኖራቸውም በመግለጫው ተብራርቷል፡፡

በሌላ በኩል የላብራቶሪ ዝግጅትን በተመለከተ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ናሙና ምርምራን እያደረጉ ያሉና ሙሉ ለሙሉ ወደስራ የገቡ 32 የምርመራ ማዕከለት ሲሆኑ በእነዚህም በቀን እስከ 8000 የሚደርስ የምርመራ አቅም መፍጠር ተችሏል ተብሏል፡፡

በዝግጅት ላይ ያሉ 19 ላብራቶሪዎች ሲጨመሩ እንዲሁም በቀጣይ የባለሙያና የምርመራ ጣቢያዎችን በሙሉ ዓቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡ በቀን የምርመራ ዓቅማችን 15,000 እንደሚደርስ ተገልጿል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here