ቸሊና የሺወንድም (በመድረክ ስሟ ቸሊና) በሕይወቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ማይክራፎን የጨበጠችው የዕውቅ የሙዚቃ ባለሙያዎች ጥምረት ከሆነው ከአንጋፋው ኤክስፕረስ ባንድ ጋር በቀድሞው ኤሊዜ የምሽት ክበብ የዶርሲ ሞርን ‹ሚስቲ ብሉ› የተሰኘ ሙዚቃ ለአድማጮች ባሰማችበት ወቅት ነበር። በጊዜው ከዚህ በፊት የሙዚቃ መድረኮች ላይ ተጫውታ የማታውቅ የአስራ ዘጠኝ ዓመት ታዳጊ የነበረች ሲሆን ‹‹በጣም ከመፍራቴ የተነሳ እንቀጠቀጥ ነበር… የባንዱ አባላት ፍርሃቴን አይተው ከመደንገጣቸው የተነሳ ‹እናቋርጠው ወይስ ትጨርሰው›› በሚል ማመንታት ውስጥ ሆነው ነበር›› ትላለች ድምፃዊት ቸሊና ከዓመታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዝብ ፊት ሙዚቃ ያቀረበችበትን ሁኔታ በትዝታ መለስ ብላ ስታስታውስ። የሙዚቃ ዝንባሌዋን ያስተዋሉት እናቷ ነበሩ ቸሊናን ከኤክስፕረስ ባንድ አባላት ጋር ያገናኟት። ከዛ በፊት ለራሷ እና ለጓደኞቿ ማናጎራጎር እንጂ ሙዚቃን በሙያ ደረጃ ለመሥራት አስባ እንደማታውቅ የምትናገረው ቸሊና በመጀመሪያ እናቷ ያቀረቡት ሐሳብ አስፈርቷት አንገራግራ እንደነበረ አትዘነጋውም። ከባንዱ ጋር ተዋውቃ ለሙከራ ባንጎራጎረችበት ቅፅበት ከኤክስፕረስ ባንድ ጋር እንድትሠራ ጥያቄ ቀረበላት።
ይህ በሆነ በሳምንቱ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መድረክ ወጥታ ለመዝፈን አድማጮች ፊት የቆመችው። ‹‹የመጀመሪያውን ዘፈን እንደጨረስኩ ሁለተኛውን ሳልደግም ትቼው ወደ ቤቴ ሄድኩ… ቤተሰብ ተሰብስቦ አፅናናኝ… ለተወሰነ ጊዜ ሙዚቃን ባቆምም የባንዱ አባላት አበረታተውኝ ተመልሼ መሥራት ጀመርኩኝ›› በማለት ነበር ቸሊና የመጀመሪያ የመድረክ ትውስታዋን ሳቅ እየተናነቃት ለአዲስ ማለዳ ያጫወተችው።
ከኤክስፕረስ ባንድ ጋር መሥራት በጀመረች ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ታድያ ጃዝ አምባን ጨምሮ ከሌሎች ባንዶች ጋር በተለያዩ ቦታዎች ሙዚቃን መጫወት ጀመረች። በወቅቱ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወስዳ ውጤቷን በመጠባበቅ ላይ የነበረችው ቸሊና ከጥቂት ወራት በኋላ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ሕግ የምታጠናበት ዕድል ቢገጥማትም የልቧ ሚዛን አዲስ ለጀመረችው የሙዚቃ ሙያ ስላደላ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብታ ለመማር መርጣለች። በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የጀመረችውን ትምህርት ባትቀጥልበትም መካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ የጃዝ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብታ በዋናነት ጊታርን ለሦስት ዓመታት ተከታትላ ተመርቃለች።
ቸሊናን ብዙዎች የሚያውቋት በተለያዩ መድረኮች ላይ እጅግ ልዩ በሆነ የድምፅ አወጣጥ ክህሎት በጃዝ፣ በሶል እና በሬጌ ስልት በምትጫወታቸው ሙዚቃዎች ነው። ‹‹አብሬያት በምጫወትበት ወቅት በድምፅ አወጣጧ የምደነግጥባቸው ጊዜያት ነበሩ›› የሚለው የሙዚቃ ባለሙያው ሄኖክ መሀሪ ‹‹የማይገመቱ አዳዲስ የአዛዚያም ቴክኒኮችን ስለምትጠቀም አብረዋት የሚሠሩ ሰዎች እንኳን የማይለምዱት ተሰጥዖ ነበራት›› ሲል ይገልፃታል። ‹‹እንደሙዚቀኛ የሚያስቡ ዘፋኞች በሌሉበት አገር ከማስጨፈር ባለፈ ስለሙዚቃው ተጨንቀው እና ሙያውን አክብረው ከሚሠሩ ጥቂት ሙዚቀኞች ውስጥ አንዷ ቸሊና ናት› ሲልም አድናቆቱን አልሸሸገም። አገር ውስጥ በተለያዩ ፊስቲቫል እና ኮንሰርቶች ላይ ከመጫወት አልፋ እ.አ.አ. በ2017 ስፔን ላይ በተደረገው በዓለም ዐቀፉ ‹ሮቶቶም ሰን ስፕላሽ› የሬጌ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ ከሌሎች አርቲቶች ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ወክላ ተካፍላለች።
በቅርቡ ‹ሳይ ባይ› በተሰኘ ነጠላ ዜማዋ እና በተሰራለት የሙዚቃ ቪዲዮ ከበርካታ የሙዚቃ አድናቂዎች ጋር የተዋወቀችው ቸሊና በተለየ ለአዲስ ማለዳ እንዳጫወተችው በዛሬው ዕለት ‹ቸሊና› የተሰኘ በስሟ የተሰየመ የመጀመሪያ አልበሟን ለአድማጮች ታደርሳለች። አልበሙ ሰባት በሬጌ ዘፈኖችን ጨምሮ በጃዝ እና በሶል የሙዚቃ ስልት የተሰሩ 14 ዘፈኖችን አካቷል። በሙዚቃ ቅንብር፣ ሚክሲንግ፣ ማስተሪንግ እና የመሣሪያ ጨዋታ ያምሉ ሞላ፣ ኪሩቤል ተስፋዬ፣ ብሩክ አፈወርቅ፣ ዘሩባቤል ሞላ፣ ጆርጋ መስፍን፣ ጣሰው እና ሄኖክ ተመስገን ተካፍለውበታል። በግጥም እና ዜማ ድርሰት ያምሉ ሞላ እና ቸሊና በዋናነት የተሳተፉበት ሲሆን ወጣቱ አርቲስት እሱባለው ይታየው (የሺ) እና ብሩክ አፈወርቅም የአልበሙ የግጥም እና ዜማ ድርሰት ላይ ተሳትፈዋል። ከዘጠኝ የዜማ ድርሰቶች በተጨማሪ ‹ባቲ›፣ ‹ጥቁር ወፍ› እና ‹በይቅርታ› የሚሉ የዘፈን ግጥሞችን ቸሊና ራሷ የደረሰቻቸው ሲሆን ‹‹አልበሜ ስሜቴን እና የሕይወቴን እውነተኛ ጥሩ እና መጥፎ ገጽታ የገለፅኩበት ነው። በዚህም የአልበሙ መጠሪያ የራሴ ሥም ሊሆን ችሏል›› ስትል ድምፃዊቷ ለአዲስ ማለዳ ተናግራለች።
ስለ ስኬት ስትናገር ቸሊና ‹‹እስካሁን ከዕውቅ የሙዚቃ ሰዎች እና ባንዶቸች ጋር እንዲሁም ትልልቅ መድረኮች ላይ የመሥራት ዕድል ቢገጥመኝም እንደ ትልቅ ስኬት ልቆጥረው አልችልም። ምንአልባትም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከሚታወቁት እንደ ቤን ሀርፐር እና ኤሪካህ ባዱን ከመሳሰሉ አርቲስቶች ጋር አብሬ መጫወት ስችል በእርግጥም ተሳክቶልኛል ብዬ ላስብ እችል ይሆናል›› ብላለች።
‹‹የቸሊና አዲስ አልበም አሁን ላይ ከሚሰሙት አልበሞች ተለይቶ በአዘፋፈን እና በሐሳብ ደረጃ አዲስ ነገር ይዞ የቀረበ፣ ሙዚቃዎቹም ዓለም ዐቀፍ እና ዘመናዊ ቀለም ያላቸው ናቸው› ሲል የገለፀው የሙዚቃ አቀናባሪው ኪሩቤል ተስፋዬ ሲሆን ‹‹ባለፉት ዐሥር ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ከመጡ ልዩ ተሰጥኦ ካላቸው አርቲስቶች መካከል በመጀመሪያ ደረጃ የማስቀምጠው ቸሊናን ነው›› ሲል አድናቆቱን ያለ ንፍገት የሰጣት ደግሞ አንጋፋው የቤዝ ጌታር ተጫዋች ሄኖክ ተመስገን ነው። ቸሊና አዲሱን አልበም ለማስተዋወቅ እና ለማስገምገም በትላንትናው ዕለት አንጋፋ እና ታዋቂ ዘፋኞች እንዲሁም የሙዚቃ ባለሙያዎች በተገኙበት የአልበም ማዳመጥ ድግስ (‹አልበም ሊስኒንግ ፓርቲ›) ያዘጋጀች ሲሆን በዝግጅቱ ላይ ድምጻዊቷ የተመረጡ ሥራዎቿን ለታዳሚዎች አቅርባለች። ድምጻዊቷ በቀጣይ ተከታታይ የመድረክ ሥራዎችን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኗን ለአዲስ ማለዳ ጨምራ ተናግራለች።
ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011