በጋምቤላ ለሰፋፊ የእርሻ ልማት የዋለው መሬት ክልሉን ጎድቷል ተባለ

0
944

በጋምቤላ ለሰፋፊ የእርሻ ልማት የዋለው መሬት በጥናት ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ በክልሉ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዑሞድ ኡጁሉ ተናገሩ።
ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ከ2000 ጀምሮ በክልሉ በሰፋፊ እርሻ ልማት ላይ እንዲሰማሩ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች በዘርፉ ያላቸው አቅምና ብቃት አልተፈተሸም። በክልሉ ለሰፋፊ እርሻ የሚውል 683 ሺህ ሔክታር መሬት ለ623 የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ተላልፏል። ለባለሀብቶቹ ከተላለፈው መሬት ውስጥ ልማት ላይ የዋለው 18 በመቶ ብቻ እንደሆነ በ2009 በተካሄደ ጥናት ተረጋግጧል።
በመሆኑም ባለሀብቶች የወሰዱትን መሬት በማልማት ለወጣቶችም የሥራ ዕድል ባለመፍጠራቸው ክልሉ ማግኘት የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሳያገኝ መቆየቱን ዑሞድ ገልጸዋል። ከ10 ዓመት በፊት በጋምቤላ ክልል ለባለሀብቶች በሚሰጠው መሬት ላይ በፌዴራል መንግሥትና በክልሉ ባለሥልጣናት መካከል ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት ተፈጥሮ እንደነበርም አስታውሰዋል።
የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብነት በስፋት ነበር ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ “በስልክ ትዕዛዝ ብቻ የእርሻ መሬት እንዲሰጥ ይደረግ ነበር” ብለዋል። በወቅቱ ክልሉ እስከ 500 ሔክታር መሬት ድረስ ለባለሀብቶች እንደሚያስተላልፍ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በፌዴራል መንግሥት በኩል ግን ከተባለው ሔክታር በላይ ነበር ብለዋል። በወቅቱ የነበረው አሰራር በተፅዕኖ ሥር የወደቀ ስለነበረ በክልሉና በፌዴራል መንግሥት በኩል ለባለሀብቶቹ የሚሰጠው የመሬት ካርታ መደራረብ የታየበትና ለሙስና የተጋለጠ ነበርም ነው ያሉት።
በመሆኑም በካርታ አሰጣጥ ላይ የሙስና ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ሕግ ፊት ቀርበው እንዲቀጡ ተደርጓል ብለዋል። በክልሉ 284 ሺህ 796 ሔክታር መሬት ተመንጥሮ ሳይለማ እንደተቀመጠ የገለጹት ዑሞድ የክልሉ መንግሥት ባሳለፈው ውሳኔ ወደ መሬት ባንክ ገቢ ተደርጓል ብለዋል። ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በክልሉ የሚከናወኑ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግባራት ከፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብነት የፀዳ መሆኑንም ተናግረዋል።
በጋምቤላ ክልል በሰፋፊ የእርሻ ልማት ለመሰማራት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት 623 ባለሀብቶች መካከል የ360 ባለሀብቶች ፈቃድ ተሰርዟል፤ የወሰዱትም መሬት እንዲመለስ ተደርጓል።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here