መጻሕፍትና ንባብ – በኮቪድ ወቅት

0
1102

ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ላለፉት አስራ ሰባት ዓመታት በየአስራ አምስት ቀኑ በመጻሕፍት ዙሪያ የውይይት መድረክ ሲያዘጋጅ ነበር፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለአፍታ እንዲገታ ግድ አለው እንጂ። እስካለፈው ሦስት ወር ገደማም 492 የሚጠጉ መጻሕፍት ለውይይት ቀርበዋል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) አዳራሽ የሚከወነውና በኢትዮጵያ ደራስያን የተጻፉ አልያም በተተረጎሙ መጻሕፍት ላይ የሚካሄደው ውይይት፣ ተደራስያን ከደራስያንና ከሥነ ጹሑፍ እንዲሁም ሥነ ጥበብ ባለሞያዎች እንዲገናኙ ድልድይም ነበር።

ይህን ማሳያ ስንጠቅስ ካስቆጠረው እድሜም አንጻርና በጽናት የቆየበትን ዘመን ከማክበር የተነሳ ነው። በተመሳሳይ ታድያ የጀርመን ባህል ማእከል ጎቴ ከእናት የማስታወቂያ ድርጅት ጋር የሚያካሂደው ወርሃዊ የመጻሕፍት ላይ ውይይትም ተጠቃሽ ነው። እነዚህም በወመዘክር አዳራሽ ከሚካሄዱት ውስጥ ጥቂቶች ናቸው። እነዚህ ክዋኔዎች ወረርሽኙን ተከትሎ ሰዎች በብዛት እንዲሰባሰቡ ፈቃድ ባለመኖሩ ሊገቱ ግድ ብሏል።

ያም ብቻ አይደለም፣ የመጻሕፍት ሽያጭና አውደ ርዕዮች ቀርተዋል። የሥነ ጽሑፍ ምሽቶችና ግጥሞች የሚቀርቡባቸው መድረኮች የተመልካቾቻቸውን ጤናና ደኅንነት አስቀድመው ከሦስትና አራት ወር በፊት ባቆሙበት ‹ይቆየን› ብለዋል። ይሁንና ንባብ ተቋርጧል፣ ጸሐፍያኑን መጻፍ ትተዋል ማለት ግን አይደለም።

በሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ የመጻሕፍት ንባብ እና ውይይት አስተባባሪ ስንታየሁ በቀለ ለአዲስ ማለዳ ሐሳቡን ሲሰጥ፣ ምንም እንኳ የመጻሕፍት ላይ ውይይቶች ግድ ሆኖ ቢቀሩም፣ ንባብ እንደማይቋረጥ አንስቷል፣ ንባብ ላይ የሚሠሩ ተቋማትም ሥራቸውን እንደማይተዉ ጠቅሷል። ሚዩዚክ ሜይዴይም ወረርሽኙ ጋብ ብሎ የወትሮው እንቅስቃሴ በሚመለስበት ጊዜ፣ የተሻለ ሥራና አሠራር ይዞ ለመቅረብ የውስጥ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ጠቁሟል።

ይህን ጊዜም በተመሳሳይ አንዳንዶች መንደርደሪያ ጊዜ ለማድረግ ሲጠቀሙት፣ አንዳንዶች ደግሞ በዚህ ጊዜም ያሉትን አማራጮች በመመልከት አጋጣሚዎችን እየተጠቀሙ ይገኛሉ። እነማን የተባለ እንደሆነ፣ ጉዳያችን ከንባብና ከመጻሕፍት ጋር ነውና፣ መጻሕፍት አቅራቢዎች ተጠቃሽ ናቸው። በየፊናቸው አዳዲስ ሐሳብ ሰንቀው ተፍ ተፍ ሲሉም ይስተዋላል። ለአንባቢዎች መጻሕፍትን በየቤታቸው የማድረስን አገልግሎትም ብዙዎቹ ተቀላቅለዋል።

ወጣቶች ጊዜያቸውን በማኅበራዊ መገናኛዎች ላይ በማድረጋቸውም በማኅበራዊ ገጾች በኩል በድምጽ የተተረኩ መጻሕፍትን ከማቅረብ ጀምሮ፣ ጊዜው የሚፈቅደውን መንገድ ሁሉ እየተጠቀሙ ያሉ ጥቂት አይደሉም።

ወመዘክር – መጻሕፍት እና ኮቪድ 19
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ለበርካታ ዓመታት ንባብን የሙጥኝ ብሎ የሠራና እየሠራ ያለ ተቋም ነው። ንባብ ላይ እንሠራለን ያሉ ሰዎችም የወመዘክር አዳራሽ ቤተኛ ናቸው። ይህን ተከትሎ ነበር ተቋሙ አዳራሹን አሰማምሮና አሻሽሎ ለተሻለ አገልግሎት ታዳሚውን የቀጠረው።
በመካከል የተከሰተው ወረርሽኝ እንዲገቱ ካስገደዳቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተቋሙን ሥራ አንዱ ነበር። አሁን በኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ጥቂት የማይባሉ ደራስያን፣ በርካታ ተማሪዎችና የጥናትና ምርምር ሥራን የሚሠሩ ባለሞያዎች ሳይረግጡት የማይውሉት ጊቢው ጭር ብለዋል። ይልቁንም የ24 ሰዓት አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ቤተ መጻሕፍቱ ጎብኚዎቹ ቀርተውበታል።

በዓመት ቢያንስ ኹለት ጊዜ እና ከዚያ በላይ በተቋሙ ይዘጋጅ የነበረ የንባብ ጉዞም ለጊዜው ገታ ተደርጓል። ተቋሙ ግን አገልግሎቱን ለተጠቃሚዎቹ ለማድረስ ጥረት እያደረገ ነው። ለዚህም ከወረርሽኙ መከሰት ጀምሮ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።

አዲስ ማለዳ ከተቋሙ የሕዝብና ዓለማቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ተወካይ አዘዘ ጌትነት ጋር ቆይታ አድርጋለች። አዘዘ መለስ ብለው በማስታወስ ንግግራቸውን ይጀምራሉ። ቫይረሱ በኢትዮጵያ ተገኘ በተባለ ቀናት ውስጥ ማለትም መጋቢት 7/2012 ተቋሙ መደበኛ አገልግሎቱን ከመስጠት መታቀቡን ተከትሎ፣ ለሠራተኛውም ሆነ ለአንባቢ እንዴት እንደርሳለን የሚለው ላይ ነበር የተሠራው ይላሉ።

ተቋሙ ከኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ጋር በመተባበር ‹ቤት እንቀመጥ፣ በመጻሕፍት እንመሰጥ፣ ከሞት እናምልጥ፣ እናንብብ› በሚል መሪ ሐሳብም፣ ደራስያን ቤታቸው የተቀመጡ ሰዎች መጻሕፍትን እንዲያነቡ እንዲያነቃቁ ለማድረግ ሠርቷል። ይህም ውጤታማ እንደሆነና በተለይም ኤሌክትሮኒክስ ሚድያው እንዳገለገለ ነው አዘዘ ያነሱት።

ፋና፣ አርትስ ቲቪ፣ ኢቢኤስ፣ ዋልታ እና ሌሎችም ጣቢያዎች ደራስያንና ገጣምያን፣ ድምጻያውን እንዲሁም የፊልም ባለሞያዎች ከመጻሕፍት የተመረጡ ገጾችን እያነበቡ ለተመልካች እንዲደርሱ እያደረጉ ነው። ይህም በተመልካች ላይ ለንበብ አዲስ እይታንና መነቃቃትን ይፈጥራል። አንድም ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች በማንበባቸው፣ አንድም የተመረጠውና የሚነበበው አንቀጽ አጓጊና ለንባብ የሚጋብዝ ስለሆነ ነው።

የዚህ አካሄድ የሰመረ መሆንን ተከትሎ፣ ሥራውን የቀጠለው ተቋሙ፣ ኹለተኛውን ፕሮግራም ጀመረ። ይህም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የሚሠራ ሲሆን፣ ከኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ በኳረንታይን ተለይተው ለሚቆዩ ሰዎች ለምን መጻሕፍት አናቀርብም በሚል የመጽሐፍ ማቅረብ ሥራ ጀመረ። አዘዘ እንደጠቀሱት፣ የሥነ ልቦና፣ የታሪክ፣ ልብወለድና ኢ-ልብወለድ እንዲሁም ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የተያያዙ፣ የተለያየ ይዘት ያላቸው የተመረጡ ዘጠኝ ሺሕ አምስት መቶ መጻሕፍትን ለለይቶ ማቆያዎች ለመስጠት ውሳኔ ላይ ተደረሰ።

የመጀመሪያው ዙር በአዲስ አበባ ለኤካ ኮተቤ ሆስፒታል 1300 መጻሕፍትን ከጤና ጥበቃ ጋር ተረካክበዋል። ከዚህ ቀጥሎም በክልል ከተሞች ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ መቀሌ፣ አክሱም፣ ሐዋሳ፣ ሐረር እና ድሬ ዳዋ በሚገኙ ለይቶ ማቆያዎች ለመስጠት በሂደት ላይ ነው። ይህም ከክልል ጤና ቢሮዎች እንዲሁም ከባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ጋር በትብብር የሚደረግ ነው፤ እንደ አዘዘ ገለጻ።

ይህ በለይቶ ማቆያ የሚገኙ ሰዎች ቆይታቸው አስጨናቂ እንዳይሆን ሐሳባቸውን ማሳረፊያ ሌላ አማራጭ የሚሰጣቸው እንደሚሆን ይጠበቃል። ታድያ ግን መጻሕፍት ሲገቡም ሆነ ሲወጡ ትልቅ ጥንቃቄ እንደሚጠይቅና ቫይረሱም በወረቀት ላይ የመቆየት ጸባይ እንዳለው ይታወቃልና፣ አዲስ ማለዳም እዚህስ ላይ ምን ተዘየደ ስትል ጠይቃለች።

አዘዘ እንዳሉት መጻሕፍቱን የማሸግ ሥራ በጥንቃቄ ተከናውኗል። ከጤና ሚኒስቴር ጋር ትብብር ስለተደረገም፣ የባለሞያዎችን ምክረ ሐሳብ ተግብረዋል። ‹‹ንክኪ እንዳይኖር ጥረት አድርገናል። መጽሐፉም እንደ ስጦታ ነው።›› ሲሉ ገልጸዋል። በለይቶ ማቆያ ያለ አንድ ሰው ለማንበብ የተቀበለውን መጽሐፍ ለሌላ ለማንም መስጠት ጉዳት ስለሚኖረው መጽሐፉ አብሮት ይቆያል ማለት ነው።

መጽሐፍትን ማሳተምና ማተም
ገጣሚ ዩሱፍ ግዛው ከኹለት ሳምንት ገደማ በፊት ነበር ‹ናፍቆት› የተሰኘ የበኩር የግጥም ስብስብ መጽሐፉን ለንባብ ያበቃው። አዲስ ማለዳም ይህን ገጣሚ፣ በዚህ ወቅት መጽሐፍ ማሳተፍ አያስፈራም ወይም አያሰጋም ወይ ስትል ጠይቃለች። ዩሱፍም አለ፤ ‹‹እንደ እኔ የሚያስፈራ አይደለም። ጸሐፊ ዓላማው ሰው ጋር ማድረስ ነው። የህትመት ብርሃን አግኝቶ አንድም ሰው ጋር ብቻ ቢደርስ በቂ ነው።›› ሲል የራሱን ሐሳብ አካፍሏል።

በእርግጥ በኢትዮጵያ መጻሕፍትን በአዘቦቱም አሳትሞ፣ አሰራጭቶ ለአንባቢ ማድረስ መጽሐፉን ከመጻፍ የበለጠ አድካሚ ሥራ ነው። ብዙ ደራስያንም በተለይ የመጻሕፍት ስርጭትን በሚመለከት ሲማረሩ ይሰማል። በየቤታቸው ብዙ መጻሕፍት እንዳሉ የሚናገሩ ደራስያን አልያም ጥሩ የሚባሉ መጻሕፍትን ሳይቀር መንገድ ላይ በ25 ብር ለመሸጥ ግድ ያላቸው መጻሕፍት አቅራቢዎች ለዚህ ምስክር ናቸው።

ፋር ኢስት ትሬዲንግ በኢትዮጵያ የበርካታ ተነባቢ መጻሕፍትን ሕትመት ሥራ አከናውኗል። በቅርቡም የዓለማየሁ ዋሴ እሸቴ (ዶ/ር) ‹ሰበዝ› የተሰኘ መጽሐፍ ያሳተመ ተቋም ሲሆን፣ መጽሐፉ በግንቦት ወር ብቻ ኹለት ጊዜ ታትሟል። በተቋሙ የመጻሕፍት ዋጋ ግምት ክፍል ባለሞያ ረድኤት ሞገስ ለአዲስ ማለዳ በሰጠችው አስተያየት፣ የመጻሕፍት ህትመት እንቅስቃሴው በሌላው ዘርፍ እንደተፈራው አይደለም ትላለች።

‹‹እንደ አምናው ባይሆንም ሥራ ጥሩ ነው። እየተንቀሳቀስን ነው።›› ያለችው ረድኤት፣ በድጋሚ እንዲታተሙ የሚጠየቁ መጻሕፍት መኖራቸውን በማንሳት፣ ያ የሆነው ቢነበብላቸው ነው ብላ እንደምታምን አንስታለች። አያይዛም አለች፤ ‹‹እኛ ጋር በፊትም ጥሩ ደንበኞች ነበሩን። በመጽሐፍ ህትመት ላይ የታወቀ ሥም አለን። የተዘጉ ማተሚያ ቤቶች እንዳሉ እናውቃለን። ግን እንደ ደንበኛው ነው።›› በማለት አስተያየቷን አክላለች።

አስቀድሞ ከፍተኛ የሚባለው አንድ መጽሐፍ እስከ ኻያ ሺሕ ቅጂ የታተመበት ጊዜ መሆኑን የምታወሳው ረድኤት፣ አሁንም ላይ አንድ መጽሐፍ አምስት እና ዐስር ሺሕ ቅጂዎች እንደሚታተም ጠቅሳለች።

እያነበብን ነው?
ሰዎች ቤታቸው ብቻ ሲሆኑና ይህም አዲስ ልምድ ሲሆንባቸው፣ ተያይዞ ሌላም ከዚህ ቀደም ያልሞከሩትን ልምድ ያገኛሉ ብለው የሚያምኑ አሉ። ለምሳሌ ምግብ ማብሰል አንደኛው ነው። የእንቅስቃሴ ገደብ የነበረበትና የኮሮና ቫይረስ የገባ የመጀመሪያ ሰሞን፣ ‹እንጀራ መጋገር ቻልን› ብለው በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ምስላቸውን የሚያሳዩ ሰዎችን ታዝበናል። ይህም አስቀድሞ የማያውቁትን ምግብ ማብሰል፣ እንደ አዲስ እየተማሩ ያሉ ሰዎች እንዳሉ ያሳያል።

ለንባብም እንደዛ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ አለ፤ የንባብን ነገር ማስተዋወቅና መቀስቀስ፣ ሳቢ እንዲሆን በፈጠራ ሐሳብ ማገዝ ከተቻለ። ዩሱፍ በዚህ ላይ ሐሳቡን ሲሰጥ፣ ሰዎች በተለየ በቤት ውስጥ በመሆናቸው ያነባሉ ወይም ቤት ለመቀመጥ መገደድ ለንባብ ያቀርባል የሚል እምነት እንደሌለው አንስቷል። ይልቁንም የንባብ ነገር ከመሠረቱ ሊገነባ የሚገባ ነው የሚል እምነት አለው።

እንደውም አስቀድሞም ለንባብ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ወትሮ የነበረው የንባብ ውይይት በመታጎሉ፣ ስለመጽሐፍት የሚነጋገሩባቸው አውዶች በመዘጋታቸው፣ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች በመቅረታቸው ከንባብ እንዳይርቁ የሚል ስጋት አለው። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኙም ብዙ እንዳሳጣ አያይዞ አንስቷል። ‹‹በነበሩት ጥበባዊ መድረኮች ለመጻሕፍት ቅርብ የሆነ ሰው ነበር የሚታደመው። እነዛም ክዋኔዎች መቅረታቸው በጣም ይጎዳናል። እነሱን ተከትሎ መጽሐፍትን የሚያነብም ጥቂት አይደለም›› በማለት ያስረዳል።

እንደ ወመዘክር ያሉ ንባብ ላይ የሚሠሩ ተቋማት ታድያ አስቀድሞ ከጠቀስነውና እየሠሩት ካለው ሥራ በተጓዳኝ፣ ዘመነኛውን መሣሪያ በመጠቀም ላይ ናቸው። በዚህም መሠረት አንደኛው ከደራስያን ጋር በመተባበር የደራስያኑ ሥራዎች (መጽሐፋቸው) በራሳቸው አልያም በተራኪ ወደ ድምጽ ተቀይረው፣ በምስልም ቢሆን ተደግፈው፣ በተለያዩ ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ለአንባብያን በጆሮ በኩል እንዲደርሱ ማድረግ ነው።

አዘዘ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ በዚህ ላይ አክለው እንዳሉት፣ ይህ ሌላው በኤጀንሲው እየተሠራ ያለ ሥራ ነው። ‹‹የተተረኩትን ሥራዎች በድምጽ በቴሌግራም እንዲሁም በዩ-ትዩብ በምስል ማድረስ ላይም እየሠራን ነው። ይህንንም ከደራስያን ማኅበር ጋር ነው እየሠራን ያለነው። ለተወሰነ ጊዜ የሚቆይ አንድ የራድዮን ፕሮግራምም በቅርቡ የምንጀምር ይሆናል።›› ብለዋል።

ይህ እየተሠራ ያለው ታድያ በኤጀንሲው እየተካሄዱ ካሉ የውስጥ የለውጥ ሥራዎች በተጨማሪ ነው። አዘዘ እንዳሉት፣ ዝግ ሆኖ በቆየበትና በሚቆይበት ጊዜ ቤተ መጻሕፍቱን የመቀየር ሥራ እየተሠራ ነው። ይህም አዳዲስ መጻሕፍትን ማስገባትን ያካትታል። ተጠቃሚዎች ምቹ ከባቢ እንዲፈጠርላቸው በጊቢው ያሉ ገጽታዎችን ማስተካከል፣ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎችን ማደስ፣ መመሪያና ደንቦችን በሚመለከት ቅኝትና መታደስ የሚፈልጉትን ማየት ወዘተ እየተሠሩ ነው ብለዋል።
በመጨረሻ

ሰዎችን አንብቡ ማለት ፊልም ተመልከቱ አልያም ሙዚቃ አዳምጡ እንደማለት አይደለም። የንባብን ባህል ማምጣትና ሰዎችም ውስጥ መጽሐፍን እንዲገልጡ ፍላጎትን መፍጠር ጊዜ የሚወስድና ጊዜም የሚፈልግ የቤት ሥራ ነው። ብዙ ጊዜም ለልጅነትና ከለጋ እድሜ ይጀምራል። ታድያ በወረርሽኙ ምክንያት ቤታቸው ለተቀመጡ ሕጻናት፣ ተማሪዎችና ወጣቶች በተገኘው አጋጣሚ ይህን መስበክ የግድ ይላል።

ዩሱፍ ለአዲስ ማለዳ ሐሳቡን ሲሰጥ እንዳለው፣ አሁን ላይ የሠለጠኑ አገራት አስቀድሞ በተለያየ መልክ ወድቀት ሲገጥማቸው፣ ዳግም ያንሰራሩት በደራስያንና ሥነ ጽሑፍ ሰዎቻቸው ነው። እናም አዲስና በብልሃት የተዘየደ አሠራር፣ አንባቢዎችን ያፈራል፣ የሰላ ብዕር ያላቸው ደራስያንንም ያበዛል፣ በድምሩም ማስተዋል የሚችል ትውልድን ያፈራል። የሁሉም መልእክት ወዲህ ነው። እናንብብ! እናንብብ! እናንብብ!

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here