የደረሰው ሳይሆን የሚደርሰው ጥቃት!

0
672

የሴቶችና ሕጻናት ጥቃት በየጊዜው ተፈጸመ ሲባል ይሰማል። መፍትሄ ሳይገኝ ግን ተመሳሳይና የከፋ ሌላ ጥቃት ይደርሳል። ሰዎችም በየጊዜው የደረሰውን ጥቃት እንጂ ወደፊት ሊደርስ የሚችለውንና እየደረሰ ያለውን ልብ አይሉም። ይህም በሰብአዊ መብትና በሰብአዊነት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አለው። መቅደስ ቹቹ ይህን ሐሳብ አንስተው፣ ችግሩን አምኖ መቀበልና መጋፈጥ ያስፈልጋል በሚል ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

በየጊዜው ለምንሰማቸው ዜናዎች የምናሳየውና የምንሰጠው ግብረ መልስ በጊዜው በተሰማን ስሜት ላይ መሠረት ያደረገ ነው። ጊዜ በሰዓታትና በቀናት አልፎም በወራት ሲሻገር፣ ያንኑ ዜና ደግመን ስንሰማው የምናሳየው ግብረ መልስ እንመጀመሪያው ሊሆን አይችልም። ለምሳሌ ሃና ላሎንጎ የተባለች ልጅ በመኪና ተጠልፋ፣ በተለያዩ ወንዶች ተደፍራ፣ ተጥላ ስትገኝና ሕይወቷ ማለፉ ሲሰማ፣ የነበረው ግብረ መልስ መንግሥት የሚገለብጥ ይመስል ነበር።

አሁንስ? ዛሬስ የሃና ላሎንጎ ስም ሲነሳ ምን እንላለን። ‹እምጥ!› ከንፈር መጠጣ ብቻ። በቀደምስ ሕጻናት ወንዶችም ሴቶችም የመደፈራቸው ዜና ተነገረ። ድንጋጤውና እንባው ጩኸቱና ‹ይበቃል› የሚለው ድምጽ ጎልቶ ተሰማ። ዛሬስ? አሁንስ? አሁን ከንፈር መምጠጥ ላይ የደረሱ ሰዎች ጥቂት አይደሉም።

አሁን የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከፈጠረው የማኅበራዊ ሕይወትና ኑሮ መስተጓጎል ጋር ተያይዞ የሚሰሙ ጥቃቶች፣ ተባባሱ እንጂ ያልነበሩ አይደሉም። ከአንዲት የሥራ ባልደረባዬ ጋር ይህን ጉዳይ አንስተን ሐሳብ ስንለዋወጥ፣ ‹አባት እንዴት ቢጨክን ልጁን ይደፍራል!› የሚለው ሐሳብ ይዞኝ፣ ያንን ተሻግሮ በአባቷ የተደፈረች ሴትን ሥነ ልቦና ጉዳትና መሰበር ማሰብ ለአእምሮዬ አቀበት በሆነበት ሰዓት ‹‹ይህምኮ አዲስ አይደለም።›› አለችኝ።

የፖሊስ ጣቢያ መዛግብት እንደ ንስሐ አባት የሰዉን ኃጢአት በየገጻቸው አስፍረው ይዘውት እንጂ፣ በእርግጥ እንዲያ ያሉ በደሎች ተፈጽመው አያውቁም ማለት አይቻልም። ዓለማችንም በተለይ በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት በየጓዳው የነበረ ገበናዋ ተገልጧል። ምን ይደረግ የሚል ለዘመቄታው የሚሆን መፍትሄ የሚሰጥ ግን የተገኘ አይመስልም።

ዓለም እንዴት ቆየች?
ከወረርሽኙ ጎን ለጎን ዓለማችን ሰው ሠራሽ ችግሮችንም በብዛት አስተናግዳለች፣ እያስተናገደችም ነው። ይልቁንም ጉዳያችን እንዲሆን ከጀመርኩት የሴቶችና ሕጻናት ጾታዊ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ፣ ከቀደመው ጊዜ በተለየ ከፍተኛ ጭማሬዎች መታየታቸውን ነው ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኀንም የሚናገሩት።

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ አስገድዶ መደፈርን እንዲሁም አካላዊ ጥቃትን በሚመለከት አሳውቁኝ የሚለው ሬይን (RAINN, the Rape, Abuse and incest National Network) የተባለው ተቋም፣ ከኹለት ወራት በፊት ባወጣው ዘገባ፣ በወር ውስጥ በነጻ የስልክ መስመር የመጣለትና የተቀበለው ስልክ ካለፈው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር 22 በመቶ እንደጨመረ ጠቅሷል። ይህም እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ያደረሱት ጥሪ ነው። በድርጅቱ ታሪክም ይህ ከፍተኛ የሚባል ቁጥር ነው።

በሚያሳዝን ሁኔታ ከእነዛ ደዋዮች መካከል 67 በመቶ የሚሆኑት ጥቃት የደረሰባቸው በቅርብ የቤተሰብ አባላቸው ነው። ከእነዚህም ውስጥ 79 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከእነዚህ ጥቃት አድራሾች ጋር በጋራ ለመኖር የተገደዱ ናቸው። ሬይን የተባለው ተቋምም አሳስቦኛል ያለው፣ እነዚህ በለጋ እድሜ ላይ ያሉ ልጆች በደወሉ ሰዓት በድምጻቸውና በመንፈሳቸው ያለው መሰበር አሳሳቢ በመሆኑ ነው።

እናም ተቋሙ የመጨረሻ ድምዳሜውን ያደረገው፣ ‹እርግጥ ነው የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠርና ለመግታት በቤት ውስጥ መቀመጥ ትክክለኛ ተግባር ነው። መኖሪያ ቤትም ከቫይረሱ ለማምለጥ መጠለያ ነው። ለበርካታ ሕጻናትና አዳጊ ልጆች ግን ቤታው የሚከለሉበት ቦታ አይደለም።›› ሲል ነው። ይህ ግን መፍትሔ የሚያመጣ ሐሳብ እንዳልሆነ ይታወቃል። ሰው ከቤቱ ወዲያ ወዴት ይሄዳል?

አንዳንዶች እንደሚሉት ዘገባዎች አሁን ላይ በብዛት እየወጡ መሆናቸው ቁጥሩን የበለጠ ከፍ እንዲል አድርጎት ይሆናል። ሬይንም በሪፖርቱ ይህን አንስቷል። ለምሳሌ 34 በመቶ ሕጻናት በቅርብ ቤተሰባቸው ጾታዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ይህም ትምህርት ቤት በመዘጋቱ የመጣ ሲሆን፣ የበለጠ ደግሞ ጥቃቱ እንደደረሰባው የሚያመለክቱበትና ሌሎችም ተመልክተው የሚያሳውቁበት አጋጣሚ ጠባብ በመሆኑን የተከሰተ ነው።

ተቋሙ ታድያ በአንዳንድ አገራት ተወሰደ ያለው አካሄድ እንዲህ ነው። ልጅን ለማሳደግ በጉዲፈቻ ለመውሰድ የጠየቁ ቤተሰቦች ላይ ድንገተኛ ፍተሻ እንደሚደረግ ሁሉ፣ አሁንም ሕጻናት እንዳሉ የሚታወቅባቸው ቤቶች ድንገተኛ ፍተሸና ጉብኝቶች ይካሄዳሉ። በውጪው ዓለም በመንግሥት በኩል ለሕጻናት ትኩረት ስለሚሰጥና ተግባራዊነት የሚያጠያይቅ ቢሆንም፣ የልጆችን ዓለም የሚጠብቅ የሥራ ክፍል ስላለ፣ ባለሞያዎቹ ናቸው ይህን ድንገተኛ ፍተሻ የሚያከናውኑት።

ከዚህም ባሻገር በሕጻናት ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ተቋማት፣ ጥቃትና አደጋ እየደረሰባቸው ያሉ ልጆች ለሚመለከተው አካ የሚሳውቁበትን ቀላል መንገድ በማዘጋጀትም ላይ ናቸው። በተለይም ልጆች በየቤታቸው ሆነው በኢንተርኔት አገልግሎት በቀጥታ ስርጭት ትምህርትን በሚከታተሉባቸው አውዶች፣ የሚደርስባቸው ጥቃት ካለ እንዲያሳውቁ ለማድረግም ጥረት እንደተደረገ ነው ያነሱት። በዛ ለልጆች የሚደርስላቸው አለ!

ወዲህ ወደእኛዋ አፍሪካ እንምጣ። ሲኤንኤን በናይጄሪያ ሌጎስ በሠራው ዘገባ አኒታ ኬሚ የተባሉ የሕክምና ባለሞያን መግቢያው አድርጓል። ዶክተሯ ማልደው ተነስተው ከቫይረሱ የሚከላከሉበትን አልባሳትና ቁሳቁስ ሁሉ ያሟላሉ። ይህን የሚያደርጉት በኮቪድ 19 ምክንያት ማቆያ ያሉ ታካሚዎችን የሚከታሉ ሆኖ አይደለም፣ ይልቁንም በናይጄሪያ አስገድዶ መድፈር የደረሰባቸው ሴቶች የሚቆዩበት ማእከል ውስጥ ስለሚሠሩ ነው።

በአገሪቱም በጾታዊ ጥቃት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውና የሥነ ልቦና ጫናው ውስጥ ያሉ ሴቶችና ሕጻናት የሚያገግሙበት ማእከል አለ። ጉዳዩም በአገሪቱ እንደ እኛዋ ኢትዮጵያ ሁሉ አሳሳቢ ሆኖ ኖሯል። በቅርቡ በናይጄሪያ የተከሰቱ ኹለት ጥቃቶች ግን፣ ተቃዋሚዎች ‹ለውጥ እንፈልጋለን› ብለው አደባባይ እንዲወጡ ግድ እንዲሆን አድርገዋል።

የሆነው እንዲህ ነው። የ22 ዓመት የማይክሮ ባዮሎጂ ተማሪ ሴት ደም በመላው የውሃ ገንዳ ውስጥ እርቃኗን ተገኘች። በሕይወት አልቆየችም፣ ለሕክምና ብትወሰድም ሳትተርፍ ቀረች። ይህች ወጣት በወረርሽኙ ምክንያት ዩኒቨርስቲዎች በመዘጋታቸው ጊዜዋን ላታሳልፍበት በመረጠችው የአምልኮ ስፍራ ነው። የሞቷ ምክንያት ሲጣራ፣ ጥቃት የፈጸሙባት ሰዎች አስገድደው ደፍረዋት ነው።

ሌላም ተሰማ። ይህም የሰብአዊ መብት ቡድን የሚባለው አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ያወጣ ነው። ወጣቷ ተማሪ በቤት ውስጥ ዘረፋ ወቅት ተደፍራ ተገድላለች።
የሕክምና ባለሞያዋ ዶክተር አኒታ፣ ‹‹በእኛ አገር አስገድዶ መድፈር ወረርሽ ነው›› አለች። በዚህ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ደግሞ የበለጠ ፈተና እንደሆነባቸው ነው የጠቀሰችው።

ሂውማን ራይትስ ወች በድረገጹ ባስነበበው ዘገባ፣ ልጆች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ጠቅሷል። ተቋሙ ስጋቱን ሲያነሳ አካላዊ ጥቃትን ብቻ ሳይሆን ሕጻናት በትምህርት ምክንያት ኢንተርኔት በመጠቀም ብዙ ጊዜ የሚያሳልፉ በመሆኑ፣ በአውዱ ሕጻናትን ለመሸጥ ለሚፈልጉም ተጋላጭ ናቸው ብለዋል።
ከዛም ውጪ በአገራቸው ሰላም በማጣት ምክንያት ለስደት የተዳረጉ ሕጻናትም በተመሳሳይ ከፍተኛ ስጋት ውስጥን የጥቃት ሰለባም መሆናቸው ተጠቅሷል። እናም ሂውማን ራይትስ ወች የአገራት መንግሥትታ በየራሳቸው እርምጃ እንዲወስዱና እንዲያስተካክሉ ጥሪውን በአደራ አቅርቧል። በተለይም ትምህርት በተገኘው አጋጣሚ እንዲቀጥል፣ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ ቤተሰቦች የኢኮኖሚ ድጋፍ ማድረግ፣ የነጻ ስልክ ጥሪ መቀበያዎችን ማመቻቸት ወዘተ ያስፈልጋልም ብለዋል።

‹‹ይህ ወረርሽኝ የብዙ አገራትን ትልቅ ድክመት አጋልጧል። በተለይም ከልጆች ደኅንነትና ጤና ሽፋን፣ እንዲሁም በድንገተኛ ክስተት ጊዜ አማራጭ የትምህርት መስጫ መንገዶች አለመኖር ታይቷል። አሁን ላይ የመንግሥታት ውሳኔ ወሳኝ ነው። ይህም የወረርሽኙን አስከፊ ጥፋት ለመቋቋም ብቻ ሳይሆን፣ ልጆችንም በሂደቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ነው።›› ብሏል፣ ሂውማን ራይትስ ወች።

እውነቱን መጋፈጥ
ይህ ከላይ ያልኩት ሁሉ ሲነገር የኖረ ጉዳይ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህ የዓለም እውነት መሆኑን ለማንሳትም ነው የተጠቀሰው። የደሃ ደሃ ከተባሉ አፍሪካ አገራት ጀምሮ በሥልጣኔ ጠርዝ ደርሰናል እስካሉት ድረስ፣ የሴቶችና የሕጻናት ጥቃት ይከሰታል፣ መጠኑ ቢለያይም። ለመስማት የሚያስነውሩ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፣ ለማሰላሰል የሚከብዱ ተግባራት ሆኑ ይባላል። ስለሆነ ልንሸሸው የምንችለው ጉዳይ አይደለም።

ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት የምትለይበት ብዙ ሊጠቀስ የሚችል መልክ አላት። ግን በኢትዮጵያ የምንገኘው ሰዎች ያው ሰዎች ነን። ወንጀል፣ ኃጢአት፣ በደልና ጥፋት እንፈጽማለን። ሌላው አገር የሆነና ኢትዮጵያ ውስጥ ያልሆነ ነገር ማግኘት ከባድ ነው። በግልጽ ያልተወራ ግን ብዙ አለ።

ይመስለኛል፤ ባህል፣ እምነትና ስርዓትን፣ ኢትዮጵያዊነትንም መልክ በነበረበት ማቆየትና መጠበቅ የሚቻለው ታድያ እነዚህን አሳፋሪ ወንጀሎች፣ በልጆችና በሕጻናት ላይ የሚደርስን በደል ‹አይ ጊዜ!› በማለት በማለፍና ‹እግዚኢ!› ብሎ ድንጋጤን በመግለጽ አይደለም። መጀመሪያ ችግር መኖሩን መቀበልና ማመን ያስፈልጋል። እንደው ለአፍ ሳይሆን፣ ከልብ። ያኔ ባህልን ለማቆየትና ማንነትን ለመጠበቅ የሚያስችል መንገድን ማግኘት ይቻላል። እየተወሻሸን፣ የደረሰውን በደል ብቻ አንስተን እየጣልን የሚደርሰውን በደል ቸል ብለን ከዚህ ማጥ መቼም አንወጣም።

በአሜሪካ የጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ዓለምን ነቅንቋል። በቆዳ ቀለም ምክንያት የሚደርስባው የዘረኝነት ጥቃት ያንገፈገፋው፣ ያንንም የሚቃወሙትን በነቂስ ወጥተዋል። መውጣት ብቻ አይደለም፣ እንደወትሮው በሳምንትና በኹለት ሳምንት ‹ይበቃል! ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ! ለውጡ በራሱ ጊዜ ይመጣል!› ብለው በየቤታቸው አልገቡም። ለውጡ እስኪመጣ ድረስ አናቆምም አሉ። አሁን ታድያ እነርሱ ተቃውሟቸውን አሰምተው ጨርሰው ወደየቤታቸው ሳይገቡ፣ ተግባራዊ ለውጦች ቢያንስ በአመራር በኩል እያገኙ ነው።

የእነዚህ ሰዎችን ዓይነት ጽናት ያስፈልጋል። በተለይም የሴቶችና ሕጻናትን መብት በማስከበር ረገድ፣ በደኅና እና ያለስጋት እንዲኖሩ ለማስቻልም። በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋል። እነዚህ ጉዳዮች የገቡን ይመስለናል እንጂ፣ ኢትዮጵያ በሞራልና ሰብአዊ መብት እንዲሁም በዜጎቿ ሥነ ልቦና ያለችበትን ደረጃ የምንመለከትበት ዐይን ቢከፈት፣ ወየው ለእኛ!

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here