በተለያየ ጊዜ ሁለት ህፃናትን በማታለል ያደፈሩ ግለሰቦች ከ11 እስከ 25 ፅኑ እስራት ተቀጡ

0
1501

በተለያዬ ጊዜ ሁለት ህፃናትን በማታለል የደፈሩ የ65 ዓመት አዛውንት በ25 ዓመት እንዲሁም ያሳደጋትን የእንጀራ ልጁን የደፈረው ግለሰብ በ11 ዓመት ከዘጠኝ ወር ፅኑ እስራት መቀጣታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቋል።

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ገላን ጉራ አካባቢ በሚገኝ የአንድ የግል ድርጅት ውስጥ በጥበቃ ስራተኛነት ሲሰሩ የነበሩ የ65 ዓመት ግለሰብ በተለያዬ ጊዜየ 8 እና የ9 ዓመት እድሜ ያለቸውን ሁለት ህፃናት በማታለል ወንጀሉ እንደተፈፀመባቸው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህጻናትና ሴቶች ምርመራና እንክብካቤ ዲቪዚዮን ኃላፊ ኮማንደር አጸደ ወርዶፋ ገልፀዋል፡፡

ግለሰቡ በ2011 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ በተለያዩ ጊዜያት ብር እሰጣችኋለሁ ቤቴ ውሰጥ ትጫወታላችሁ በማለት እና በማግባባት ተከራይተው ወደ ሚኖሩበት ቤት ህፃናቱን ካስገቧቸው በኋላ በህጻናቱ ላይ በድግግሞሽ ወንጀሉ እንደተ ፈፀመባቸው በፖሊስ የምርመራ ሂደት መረጋገጡን ዳኛ አቶ ዮናስ መኮንን አብራርተዋል፡፡

የወንጀል ድርጊት የተመለከተው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቃቂ ቃሊቲ ምድብ ወንጀል ችሎት በሰኔ 16 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሹን ያስተምራል ሌሎችን ያስጠነቅቃል በማለት በ25 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ኮሚሽን አስታውቋል ፡፡

በተመሳሳይ ዜና በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ ከህፃንነቷ ጀምሮ ያሳደጋትን የ15 ዓመት የእንጀራ ልጁን የደፈረው ግለሰብ በ11 ዓመት ከ9 ወር ጽኑ እስራት እንደተቀጣ ኮማንደር አጸደ ወርዶፋ ጨምረ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በህፃናት ላይ የሚፈፀመውን ልዩ ልዩ ጥቃቶችን ለመከላከል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ኮማንደሯ አስታውቀው ህጻናትና ሴቶች ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ዜጎች ወንጀሉን እንዲከላከሉ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባሻገር አጥፊዎች ላይ አሰተማሪ ውሳኔ እንዲወሰንባቸው ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው የፍትህ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

 

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here