በአዲስ አበባ በሦስት ክፍለ ከተሞች የወንጀሎች ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ

0
905

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሦስት ክፍለ ከተሞች የወንጀል ቁጥር ከቀደመው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በአምስት በመቶ መጨመሩ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው በቦሌ፣ የካ እና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተፈጽሙ ወንጀሎች ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በአምስት በመቶ ጨምረዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የ2012 የዘጠኝ ወራት በከተማዋ የተከሰቱ የወንጀል ክስተቶችን በገመገመበት ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚፈጸሙ እና ለኅብረተሰቡ ስጋት ናቸው የተባሉ ሰው መግደል፣ መኪና መስረቅና የመኪና እቃ መስረቅ እንዲሁም የኪስ ስርቆት እና የተደራጁ ዘረፋዎች የመሳሰሉ ከባድ ወንጀሎችን 20 በመቶ ለመቀነስ አቅዶ ነበር። ሆኖም በቦሌ፣ በየካ እና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ክተሞች እስከ አሁን ከእቅዱ በተቃራኒ በአምስት በመቶ ከቀዳሚው ጊዜ በበለጠ ወንጀል መበራከቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በሦስቱ ክፍለ ከተሞች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ የተፈጸሙ ወንጀሎች ከእቅዱ በተቃራኒ ሆነው የተገኙት በክፍለ ከተሞቹ በተለይም በቦሌ ክፍለ ከተማ የመሰረተ ልማት ሥራዎች የተሟሉ ባለመሆናቸው ነው ተብሏል። ይልቁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ለወንጀል መፈጸም ምቹ የሆኑ መብራት የማያገኙ ጨለማ ቦታዎች በመኖራቸው፣ በክፍለ ከተሞቹ የሚገኙ የግል ድርጅቶች የሚቀጥሯቸው የጥበቃ ሠራተኞች ብዛት ከድርጅቶቹ ቅጥር ግቢ ስፋት አንጻር ያልተመጣጠነና የሰው ኃይል አናሳ በመሆኑ እንዲሁም በክፍለ ከተሞቹ የፖሊስ አባላት እጥረት መኖሩ እንደ ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን የኮሚሽኑ የሕዝበ ግንኙነት ዳይሬክተር ጠቁመዋል።

በአንፃሩ በቂርቆስ፣ በልደታ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች በዘጠኝ ወር ውስጥ የተመዘገቡ ወንጀሎች ከ25 እሰከ 46 በመቶ፣ እንዲሁም በአቃቂ ቃሊቲ እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች ከስድስት እስከ ስምንት በመቶ መቀነሳቸውን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አመላክተዋል። በጥቅሉ ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ በኹሉም ክፍለ ከተሞች በዘጠኝ ወር ውስጥ እቀንሳለሁ ብሎ ካቀደው የ20 በመቶ ወንጀል ውስጥ 17 በመቶ ማሳካቱን ኮማንደር ፋሲካ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በተለይ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ወዲህ በከተማዋ በኮቪድ-19 መከሰት ምክንያት ከማረሚያ ቤት በወጡ አካላት እና በሌሎች የስርቆት እና ዘረፋ ላይ በተሰማሩ አካላት የምሽት ዘረፋዎች እና የተለያዩ ወንጀሎች እየተከሰቱ መሆኑን ኮሚሽኑ በሚደርሰው ተባራሪ ጥቆማ መሰረት በተወሰኑ ክፍለ ከተሞች ላይ ችግሩ መኖሩን ማረጋገጡን ኮማንደር ፋሲካ ተናግረዋል።

ኮማንደሩ አንድ ግለሰብ በየካ ክፍለ ከተማ ከማረሚያ ቤት ወጥቶ ወደ መኖሪያው እያቀና ባለበት ወቅት ቤቱ ሳይገባ ዲያስፖራ አደባባይ አካባቢ በሚገኝ ሱፐር ማርኬት ውስጥ ገብቶ ተንቀሳቃሽ ስልክ ሲሰርቅ እጅ ከፍንጅ ተይዞ ተመልሶ ወደ ማረሚያ ቤት መግባቱን ለአብነት ጠቅሰዋል። በተጨማሪም ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ በየክፍለ ከተማው በተመሳሳይ ከማረሚያ ቤት የወጡ ታራሚዎች እጅ ከፍንጅ እየተያዙ ተመልሰው ወደ ማረሚያ ቤት የሚገቡ መኖራቸውን ኮማንደር ፋሲካ አክለው ጠቅሰዋል።

ኮሚሽኑ በከተማዋ የሚታዩ የወንጀል ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን የጠቆሙት የኮሚሽኑ የሕዝበ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካው፣ እያንዳንዱ የከተማው ነዋሪ ወንጀልን በመከላከል ረገድ እገዛ ማድረግ እንዳለበት እና እራሱን ከወንጀል ድርጊቶች እንዲከላከል ሲሉ አሳስበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here