በአማራ ክልል ከ3600 በላይ ሰዎች በእብድ ውሻ መነከሳቸው ተገለጸ

0
1528

በአማራ ክልል በ2012 ብቻ ከ3600 በላይ ሰዎች በእብድ ውሻ በሽታ መነከሳቸውን እና 15 ሰዎች በበሽታው ሕይወታቸውን እንዳጡ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ይህ ቁጥር ወደ ሕክምና ተቋም መጥተው ሕክምና የተደረገላቸው ሰዎች ሪፖርት የተደረገ ብቻ ሲሆን፣ በአብዛኛው በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች ወደ ባህላዊ ሕክምና እንደሚሄዱ እና ወደ ባህላው ሕክምና የሚሄዱ ታማሚዎች ቁጥር ከዚህ ቁጥር ሊበልጥ እንደሚችል ተጠቁሟል።
በክልሉ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባሻገር የእብድ ውሻ በሽታ ከዚህ በፊት ከነበረው ስርጭት መጠን እየተባባሰ መምጣቱን እና በሽታውን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የግብዓት አቅርቦት ባለመኖሩ ችግሩ በክልሉ ሌላ ስጋት መሆኑን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት የኅብረተሰብ ጤና መልሶ ማቋቋም ባለሙያ አብርሃም ኃይሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ለችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ መባባስ ምክንያት የሆነው መሠረታዊ የመከላከያ ዘዴዎችን በተገቢው መከወን ባለመቻሉ መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል። እንደ ባለሙያው ገለጻ መሰረታዊ የእብድ ውሻ በሽታ መከላከያ ዘዴዎች ከሚባሉት ውስጥ አንደኛው ውሾችን በአግባቡ እንቅስቃሴያቸውን ገትቶ መያዝ መሆኑን አመላክተዋል። ባለሙያው አክለውም እንደ አገር ቅደመ መከላከል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የመሥራት ባህል ባለመኖሩ በክልሉም ይህን በሽታ ለመከላከል የቅድመ መከላከል ሥራ አለመሠራቱ ለችግሩ መባባስ ሌላኛው ክፍትት መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እና ታማሚዎችን ከሞት ለመታደግ የድኅረ ተጋላጭነት ክትባት በስፋት አለመኖሩ በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ለሞት እንደሚዳረጉ አብርሃም ጠቁመዋል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ለበሽታው ክትባት የሚያገለግሉ የሕክምና ግብዓቶች ምርት ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣሙ መሆኑን አብርሃም ተናግረዋል።
ለበሽታው ሕክምና የሚያስፈልጉ ሕክምና ግብዓቶች በከፍተኛ ደረጃ እንዳለ የገለጹት ባለሙያው፣ ችግሩን ለመፍታት በተደጋጋሚ የሕክምና ግብዓት እንዲቀርብላቸው ቢጠይቁም እስከ አሁን ምላሽ አለመገኘቱን ተናግረዋል።
በዚሁ ምክንያት በበሽታው የተጠቁ ታማሚዎች በጤና ተቋማት የሚሰጠው ሕክምና በቂ ባለመሆኑ እና ኅብረተሰቡ ጤና ተቋማት ለበሽታው ፈውስ ይሰጣሉ የሚለው እምነቱ ስለተሸረሸረ፣ በአብዛኛው ወደ ባህላዊ መድኃኒት ቀማሚዎች እንደሚሄዱ ባለሙያው አመላክተዋል። በዚህም ባህላዊ መድኃኒት የሚጠቀሙ የበሽታው ተጠቂዎች ለሞት የሚዳረጉ እንዳሉ ባለሙያው የገለጹ ሲሆን፣ በዚያው ልክ ከበሽታው የሚድኑም እንዳሉ አክለው ተናግረዋል።
በእብድ ውሻ የተለከፈ ሰው ወደ ባህላዊ ሕክምና ከመሄድ ይልቅ በአስቸኳይ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ሕክምና ማድረግ እንዳለበት ባለሙያው ምክረ ሐሳባቸውን አመላክተዋል።
ችግሩ በየዓመቱ የሚከሰት በመሆኑ ችግሩን ለመቀነስ ከ2010 ጀምሮ ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተሠራ እንደሆነ የጠቆሙት ባለሙያው፣ የሚሠራው ሥራ በሚፈለገው ልክ ውጤታማ አለመሆኑን ተናግረዋል። ውጤታማ ካልሆነበት ምክንያት አንዱ ለተላላፊ በሽታዎች የሚሰጡ ቅድመ መከላከል ሥራዎች ባለመሠራታቸው እንደሆነ አብርሃም ተናግረዋል። አብርሃም አክለውም በበሽታ መከላከል ረገድ ከተጠቁ በኋላ የሚደረግ ሕክምና ብቻ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አያስችልም ብለዋል።
የእብድ ውሻ በሽታ በማንኛውም እንስሳት ላይ የሚከሰት ገዳይ በሽታ መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው፣ በብዛት በውሾች እና በድመቶች ላይ የሚከሰት መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም የበሽታው የመዛመት እድል ከፍተኛ በመሆኑ ኅብረተሰቡ የበሽታውን መነሻ በመረዳት ራሱን የመጠበቅ እና ውሾችን በአግባቡ ተቆጣጥሮ መያዝ እንደሚገባ ባለሙያው አመላክተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here