ከደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ታግተው በጠፉ ተማሪዎች ጉዳይ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች መያዛቸው ተገለጸ

0
366

ከስድስት ወር በፊት በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ በተከሰተ ግጭት ምክንያት ወደ ቤተሰቦቻቸው በመመለሰ ላይ እያሉ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በታገቱ ተማሪዎች ላይ ሲደረግ የነበረው ምርምራ ተጠናቆ፣ በምርመራው ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን እና የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በተያዙት ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ሊመሰርት መሆኑን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ ሰኔ 25/2012 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በጉዳዩ ላይ ምርመራ ተጠናቆ፣ ከተማሪዎቹ እገታ ጋር በተገናኘ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ላይ ክስ ሊመሰረት እንደሆነ ተናግረዋል።
የታገቱ ተማሪዎች ጉዳይ እስከ አሁን መንግሥት እገታውን በተመለከት በሚሰጣቸው መረጃዎች መዛባት ምክንያት በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል አለመተማመን ፈጥሮ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው። በመጨረሻም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ምርመራ አጠናቅቄ ክስ ልመሰርት ነው ብሏል።
ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ ምርመራው ተጠናቆ ክስ ሊመሰረት ከመሆኑ ያለፈ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም። የተገቱት ተማሪዎች ቁጥራቸው 17 ሲሆን፣ ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመመለስ ላይ እያሉ ማንነታቸው ባልታወቁ አጋቾች ከታገቱ ከስድስት ወራት በላይ አስቆጥረዋል። ነገር ግን ተማሪዎቹ ስላሉበት ሁኔታ እስከ አሁን በግልጽ የተነገረ ነገር የለም።

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here