ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ የሠራተኞችን ደኅንነት ነው መጠበቅ ያለበት እንጂ ፈቃድ ውስጥ መግባት የለበትም

0
1188

በኢትዮጵያ ከጥበቃ ሥራ ጋር በተገናኘ የሠራተኞችን ቅሬታ መስማት የተለመደ ነው። ይልቁንም ቃል ከተገባላቸው ደሞዝ በእኩል ያነሰ ደሞዝ ከማግኘትና ከሥራ ጫና መብዛትም ጋር በተገናኘ በተለይ የጥበቃ ሠራተኞች በማማረር ሲናገሩ ይሰማል። እንደ ኤጀንሲ ታይተን ባልተገኘንበት ተከሰናል የሚሉ የጥበቃ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በአንጻሩ፣ ወቀሳው ሁሉ እንዲቀርና ችግሮችም እንዲቀረፉ ከመመሪያና ደንብ እንዲሁም አዋጅ ጀምሮ ዳግም ዳሰሳ የሚፈልጉ ጉዳዮች አሉ በማለት ይሞግታሉ።
ላየንስ የጥበቃ አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት 2001 ነው የተመሠረተው። በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎችና በኹለቱ ከተማ አስተዳደር ላይ ከአምስት ሺሕ በላይ ሠራተኞችን ያስተዳድራል። ‹አገልግሎት ሰጪ እንጂ ኤጀንሲዎች አይደለንም።› እያለ ስለሌሎች ድርጅቶችም የሚሞግተው ላየንስ፣ ተመሳሳይ ደርጅቶች ከውልና ኢንሹራንስ ጀምሮ፣ የሠራተኛን መብት ማስከበር፣ ደሞዝ መክፈል፣ የደንብ ልብስ ማልበስ፣ የጤና መድኅን ሽፋን መስጠት፣ ለሴቶችም የወሊድ ፈቃድን ጨምሮ ፈቃድ መስጠትን ያካተተ ሥራን ይሠራል።
አቤል ወርቁ የላየንስ የጥበቃ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። በዘርፉ ከመሠረቱት ድርጅት እኩል ልምድን አዳብረዋል። ለዘርፉ ትኩረት ካለመሰጠቱ የተነሳ ያሉትን ችግሮች የሚጠቅሱት አቤል፣ በተለይም ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጋር ያለውን ሁኔታ አግባብነት በሚመለከት ቅሬታቸውን በተደጋጋሚ አንስተዋል። ይህንን እና ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከትም ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ያደረጉት ቆይታ ተከታዩን ይመስላል።

ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በተፈጠረው ክስተትና አለመረጋጋት በርካታ ንብረቶች ወድመዋል። በጥበቃ ሥራ ላይ የነበሩም ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በጠቅላላውም ከሠራተኞቻችሁ የሥራ ላይ ደኅንነት በተመለከተ ሲነሱ የምንሰማቸው አስተያየቶች አሉ። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ስምንት ቦታዎች የመስታወት መሰበር ገጥሟል። እንዳይከፋም የጥበቃ ሠራተኞቻችን ተከላክለዋል። እኛም ድጋፍ አድርገናል። አሥራ አንድ መኪናዎች አሉን፣ በዛ ነው ድጋፍ ያደረግው። ስንራወጥ ነው የዋልነው። ደንበኞቻችን ሲጨነቁና ደጋግመው ሲደውሉም ነበር።

ኢንሹራንስን በሚመለከት እንዲህ ያሉ አደጋዎችን የሚሸፍን ኢንሹራንስ የለም። እኛ የገባነው እምነት ማጉደል፣ እውቀትን ተጠቅሞ የሚደረግ ጥፋትና ሠራተኛ ላይ አካል ጉዳት ቢደርስ፣ መጨረሻ በሞት ቢለይ በሚል ነው። በረብሻና ብጥብጥ ግን አልተካተተም። ግን እኛ ሰው መሆን አለብን። የሕሊና ሕግ አለን። ፈጣሪ አያምጣብን! የእኛ ልጅ [የጥበቃ ሠራተኛ] ቢደበደብ እናስታክማለን። ምክንያቱም ሰው ስለሆንን ብቻ። የተጻፈ ነገር ብቻ ሊገዛን አይገባም። ያልተጻፈውም ሊገዛን ይገባል።

ጥበቃዎቻችን ንቁዎች ናቸው። እኛም ክትትልና ቁጥጥር እናደርጋለን። አለቃሽ ቁጥጥር ሲያደርግ ወይም መጥቶ ሥራ እንዴት ነው፣ ምን ችግር አለ ማለቱ ቀላል ነገር አይደለም። እኛ ደግሞ በሥራ ባህላችን አለቃ ካልተቆጣጠረ አንሠራም።

በሕግ የጸደቀውን የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅን አይተገብሩም በሚል ሥማችሁ ይነሳል። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አላችሁ?
አይተገብሩም! መቼ ተወያየን? እኔ በሥራው አስራ አንድ ዓመቴ ሆኖኛል። ደብዳቤ ተልኮልኛል፣ እታወቃለሁ። በዚህ ሥራ ላይ ምን ችግርና ተግዳሮት አለ፣ ሐሳብ ስጠን ቢባል መልካም ነበር። በጉዳዩ ተደርጓል የተባለው ጥናት ደግሞ የተጠናው ቻይና፣ ቬትናም፣ ጅቡቲ፣ ሶማሌን ማእከል አድርጎ ነው። ኢትዮጵያን መሠረት አድርጎ መጠናት አልነበረበትም? ነበረበት። እኛ መጠየቅ ነበረብን።

ሠራተኛና ማኅበራዊ ያወጣው መመሪያ አንደኛ የአገሪቱን ሕግ የሚጻረርም ነው። በፌዴራል ዐቃቤ ሕግ መመዝገብና ተመዝግቦ መፈተሽም አለበት። ምክንያቱም መመሪያዎች የትኛውንም አዋጅ መጻረር የለባቸውም። ለምሳሌ ዝውውርን በሚመለከት አንድ ሠራተኛ በእድገትም በጸባይም ምክንያት ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ሊዘዋወር ይችላል። እኛ ጋር ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ተቋምም ሠራተኛም ከድሬዳዋ አዲስ አበባ ሄደህ ሥራ ይባላል። እኛ ጋር ያሉት ብቻ ናቸው ወይ ሠራተኛ የሚባሉት?
እኛ የተሻለ ደሞዝ እንከፍላን። አሁን እየከፈልን ካለነው አነስተኛ የሚባለው ሦስት ሺሕ ብር ነው። ይህም ሠራተኛው 12 ሰዓት ሠርቶ 24 ሰዓት አርፎ ነው። ሠራተኛውም ስንት እንደሚከፈለው በደንብ ያውቃል። ግን የእኛ የጥበቃ ድርጅት ብቻ ነው ወይ መታየት ያለበት? የመንግሥት ተቋም እንዲሁም ሆቴል የሚሠሩ አሉ፣ እነሱም መጠየቅ አለባቸው። ስለዚህ እነዚህ ድርጅቶች ከሚያተርፉት ላይ 80 ከመቶ ይክፈሉ ነው የተባለው። ሆቴልም ሄደው መመሪያውን ብሏልና ከምታገኘው ላይ 80 በመቶ ክፈል ሊል ነው።
ይህ ሕገ መንግቱን ይጥሳል፣ መሆን የለበትም። እናም ጥናቱ እኛን ያሳተፈ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው። ብዙ የሚጣረሱ ነገሮችም አሉ።

ኅዳር ወር ላይ በተላከልን ደብዳቤ የሐሳብ ግብዓት እንድንሰጥ በደብዳቤ ጥሪ ደረሰን። በወቅቱ በመድረኩ ላይ እኔም መድረክ መሪዎችን ጠይቄ ነበር። ብዙ እሮሮ ባለበትና ትልቅ ዘርፍ በሚሠራት መድረክ ላይ ቢያንስ መገናኛ ብዙኀን መኖር ነበረባቸው። ከክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ፣ ከፓርላማ፣ ከኢሠመጉ ብዙ ሰው ሲመጣ፣ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ግን ኹለት ሰው ነው የመጣው። ቃለ ጉባኤ አልተያዘም። የጠያቂው ሐሳብ በአግባቡ አልተስተናገደም።

ይህን ሐሳብ በወቅቱ ሳቀርብ መድረኩ ለመነሻ እንደሆነ ነው የተነገረኝ። ቀጣይ የሚስተካከል ነው አሉኝ። በኋላ ግን እኛ በሌለንበት (ሰነዱ እኔ ጋር አለ) አጽድቀውት ሰነዱን ላኩልን። ከታኅሳስ ጀምሮ የነበረው አዋጅ መቀየሩን ጠቅሰው ፈቃዳችን እንደሚበላሽና እንድናድስ ነገሩን። ይህን ሲያደርጉ ከሠራተኛ ወክለዋል ወይ? ይህ እንዳንቀበለው አድርጓል። የማንቀበለውና የምንከራከረው ለራሳችን ብቻ አይደለም። ለአገርም ነው። ይህ ትክክል አይደለም። መንግሥትና ሕግ ይይልን የማለት መብት አለን ብዬ አስባለሁ። ሁላችንም ለአገራችን ነው የምንሠራው።

በመሃል ካነሱት ነጥብ መካከል፣ አንድ ሠራተኛ ሲቀጠር 20 በመቶ ብቻ እንድትወስዱ ሕጉ ቢያዝም፣ ያንንም እየተገበራችሁ እንዳልሆነ ነው የተነሳው። በዚህስ ላይ ምን አስተያየት አላችሁ?
አስቀድሞ እንዳለልኩት፣ ስለእኔ ድርጅት ስናገር እኛ ማስታወቂያ ሪፖርተር ላይ እናወጣለን። መጥተው ይመዘገባሉ። ሠራተኛውን አናስገድደውም። በራሱ የነጻናት መብት በዚህ ደሞዝ ይስማማኛል ብሎ ነው ለሥራ የሚመጣው። ስለዚህ እኛ ድርጅት አንድም ሠራተኛ ተቃውሞ አያስነሳም። ምክንያቱም ተስማምቶ፣ አምኖበት፣ ሠልጥኖ፣ ደስተኛ ሆኖ ነው ወደ ሥራ የሚገባው። ግን ችግሮች ያሉት ሥራው ቁጥጥርና ባለቤት ስለሌለው ነው።

ለምሳሌ ኹለት ሺሕ እከፍላለሁ ብሎ በኋላ አንድ ሺሕ ይላቸዋል። አማራጭ የለኝም ብሎ እያለቀሰ ይሠራል። ይህ ሊኖር ይችላል፣እናስተካክል። አሠርቶ ደሞዝ ላይከፍል ይችላል። ይህ ጭቅጭቅም ሊያመጣ ይችላል።

እናም አንደኛው ግልጽ መሆን አለበት። ይህ የሚጠነክረው ጠንካራ ማኅበር ተመሥርቶ፣ እውቅና ተሰጥቶት መንግሥት ሲደገፍ እነዚህ ችግሮች በሙሉ ይቀረፋሉ። 80/20 ለተባለውም ሕገ መንግሥቱ አይፈቅድም። 80 በመቶ ለሠራተኛ ክፈል ሲባል ቀሪው 20 በመቶ ነው። ከዚህ 11 በመቶ ለጡረታ ኤጀንሲ ይከፈላል፣ 9 በመቶ የደንብ ልብስና አስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ የቢሮ ኪራይ፣ የመኪና ነዳጅ፣ የአስተዳደር ሠራተኞች ደሞዝ ወዘተ ብዙ ወጪ አለ።

እናም ያንን በሙሉ ማእከል ያደረገ መሆን አለበት። ለጽድቅ አይደለም የተቋቋምነው። ሠራተኛና ማኅበራዊ ሚኒስቴር የሠራተኞችን ደኅንነት ነው መጠበቅ ያለበት እንጂ ፈቃድ ውስጥ መግባት የለበትም። የፈቃዱ ነገር የሚመለከተው ንግድና ኢንዱስትሪ ነው። ፈቃድ እሰርዛለሁ ይላል፣ በየትኛው አዋጅ ነው ይህን ማድረግ የሚችለው? ፈቃድ የሚሰርዘው ንግድና ኢንዱስትሪ ነው።
እኛ የሙያተኛ ሥራ ስለምንሠራ ፌዴራል ፖሊስ ነው የብቃት ማረጋገጫ ሊሰጠን የሚገባው። ንግድና ኢንዱስትሪ የቲን ቁጥርን ጨምሮ የንግድ ፈቃድ ይሰጠናል። ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ማድረግ ያለበት፣ የትኛውም ቦታ ያሉ ሠራተኞች የእርሱ ሀብት ናቸው።

ሠራተኛው የሚጠቀመው ደግሞ፣ የዓመት ፈቃድ በገንዘብ ቀይራችሁ ስጡኝ ሲል ይሰጠዋል። በየትኛውም ሰዓትና ቀን ድንገት ሄደሽ ብታይ ነጻ ነን። እኛ አብዛኛውን ጊዜ ከዓለማቀፍ ተቋማት ጋር ነው የምንወዳደረው።

ዋናው ዓላማ የሠራተኛውን መብት ማስጠበቅ፣ የራሳችንን ሥም መቀየር፣ ምን ያህል የሰው ኃይል እንደያዝንና ስላለን ጥቅም ለመንግሥት ማሳየት የእኛ የማኅበራችን ድርሻ ነው። መንግሥት ከጎናችን ከሆነ ሠራተኛው ደሞዝ አነሰኝ ተቆረጠብኝ የሚለውን በጥቂት ጊዜ ልናስተካክለው እንችላለን።

ድርጅቶችም የምንወዳደረው ትርፍና የአስተዳደር ወጪዎች ብቻ ላይ ነው። ቀጣይም ሠራተኛው የደሞዝ እርከን ወጥቶለት የማይጎዳበትና የማይበዘበዝበት አውድ መፍጠር ነው። ጥሩ ያልሆኑም ካሉ እንዲወድቁ ማድረግ። ችግር የለብኝም የሚል ሰው ደካማ ነው። ችግር ሲኖርብሽ ነው፣ ለችግሩ መፍትሄ ስትፈልጊ ውጤት የምታመጪው።

ድርጅታችሁ ከተነሳበት ዓላማ አንጻር ምን ያህል ውጤታማ ሆኗል ትላላችሁ?
ውጤታማ ነን ብዬ አስባለሁ። አንደኛ ሰው ጥቅሙን ሲያይ ነው የሚመጣው። እኛም የአገር ውስጥና የውጪ እንዲሁም ዓለማቀፍ ደንበኞች አሉን። ተደራሽ ሆነናል። ለመንግሥት ተቋምም ከ50 በመቶ በላይ የምንሸፍነው እኛ ነን። በርካታ ተቋማትን፣ ማደያዎችንም እንጠብቃለን።

የእኛ ክፍተት ግን፣ አለመታደልም ሆኖ መሰለኝ፣ ማኅበር መፍጠር ነበረብን። ይህን አድርገን ቢሆን ኖሮ ማንነቱ ይታወቅ ነበር። እኛ ግን ሥም የለምን፣ እንደ ኤጀንሲ አብረን ተጨፍልቀን ነው የገባነው። ብዙዎች ግራ ይገባቸውና ኤጀንሲ አይደላችሁም ወይ ይሉናል፣ እኛ አዋዋይ አይደለንም። ምክንያቱም ሙያተኛ የሆኑ ሠራተኞችን አሠልጥነን፣ በቦታው መድበን እየተቆጣጠርን፣ ደሞዝ እየከፈልን የምናስተዳድር ነን። የደንበኛውን ጫና ሙሉ ለሙሉ ወስደናል።

ደንበኞቻችን 24/7 እንደምናገለግል ይጠይቃሉ። ምንአልባት አንድ ሠራተኛ የጤና እክል ቢገጥመው፣ በግል ጸባይ ምክንያት ቢነሳ በፍጥነት ሌላ ምደባ ይመደባል። ተደራሽነታችንም ሰፊ ነው።
እንዳልኩትን ግን ችግራችን ኅብረት መፍጠር አለመቻል ነው። ያንን ብናደርግ መከባበር ይመጣል። የእኛን ዘርፍ የትኛውም ሰው ድንገት ይመጣና ይገባበታል። ይገባና ዘርፉን ያበላሸዋል፣ ሠራተኛ ይበድላል። አንዳንዴ በዚህ በኩል መንግሥት ላይም ቅሬታ አላቀርብም። ግን ለምን አላወያየንም አላናገረንም ብዬ ሠራተኛና ማኅበራዊ ዋስትናን ነው የምወቅሰው።

ሠራተኛ ይበደላል። ለምሳሌ ድንገት ተነስቶ ሥራ የጀመረ ሰው የሠራተኛውን ደሞዝ አልከፍልም ይላል። ይሄኔ ሠራተኛው ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ወይም ፍርድ ቤት አልያም ኢሠመጉ ሄዶ ጫና ይፈጥራል። ማኅበር ብንመሠርት ኖሮ ግን እንዲህ ያሉ ድርጅቶች ወደ መስመር እንዲገቡ፣ የማይችሉ ከሆነ ደግሞ እንዲወጡ ከመንግሥት ጋር በጋራ እንሠራ ነበር። ትልቁ ክፍተታችንም ያለው በዚህ ላይ ነው።

ተደራሽነት ላይ አልታየልንም እንጂ በጣም ተደራሽ ነን። እንዳልኩት የሰዎችን ንብረት መጠበቅ ሕይወትና ሰነድ መጠበቅ፤ ያለምንም ክፍተት ማለት ነው። ለመንግሥትም ደግሞ የሰው ኃይል መቅጠር ነው። ድሮ እንደምናውቀው ጥበቃ ተብሎ ሕንጻ ከሆነ አንድ ጥበቃ ቀን፣ ሌላው ምሽት ኹለት ጥበቃ ነበር የሚቀጠረው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ላይ ብዙ ችግር የለም ስለሚባል።
እኛ ግን ስንገባ 6 ወይም 8 እና 10 ሰው ነው የምናስቀጥራቸው። በሦስት ፈረቃ ብለን። ኹለት ሰው ሲቀጠር የነበረውን ተጨማሪ ሰው በማድረግ የሥራ እድል ፈጥረናል። በተጨማሪም ለመንግሥት የሥራ ግብር፣ ጡረታና መሰል ክፍያዎችን እንፈጽማለን። የእኛ ድርጅት ባለፈው 2011 ብቻ 16 ሚሊዮን ብር በላይ ከፍለናል።

በእርግጠኝነት ከእኛ ዘርፍ በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢን መንግሥት ያገኛል። ሠራተኛም በሚሊዮን የሚቆጠር ነው ያለው። ፌዴራል ፖሊስ 284 የጥበቃ ድርጅቶች እንዳሉ ባለፈው ባወጣው ዘገባ አስታውቋል። አንዳንዱ ድርጅት 32 ሺሕ ሠራተኛ ያለው አለ። ያ ሁሉ ሠራተኛ የሚኖረውን ቤተሰብም መገመት ይቻላል።

ዘርፉ ባለቤት እንደሌለው ሆኗል ትኩረትም አልተሰጠውም ብለዋል። በተጨማሪም ለጥበቃ ሙያ ያለው አመለካከትም ጥሩ የሚባል አይደለም። ይህን ለመቀየር ያደረጋችሁት ጥረት አለ?
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሠራተኛና አሠሪ ግንኙነት አዋጅ 1156 ብሎ አውጥቷል። የአገር ውስጥና የውጪው አንድ ላይ ነበር በአዋጁ የተካተቱት። ነገር ግን የውጪ አገሩ ላይ ትኩረት ተደረገና ተለየ። ምክንያቱም እህቶቻችን ውጪ እየሄዱ አላግባብ ጉልበታቸው ይበዘበዛል፣ ጉዳት ይደርስባቸዋል የሚለው ጉዳይ ትኩረት ስላገኘ፣ የአገር ውስጡ ወደቀ።

የአገር ውስጥ የሚለውም ስምሪት በመባሉ አልስማማም። እኛ ስምሪት የምናደርግ ሰዎች አይደለንም። እኛ አገልግሎት ሰጪ ነን። ከዚህ ጋር በተያያዘ ላነሳ የፈለኩት፣ አዋጅ ከወጣ በኋላ፣ አንደኛ በፌዴራል ዐቃቤ ሕግ መመሪያው ሊከለስና ቁጥር ሊሰጠው ይገባ ነበር። የወጣው መመሪያ እኛን አሳትፏል ወይ? አላሳተፉንም። ጠሩን፣ በር ላይ ስንገባ ፈርሙ ብለው አስፈረሙን። እሱን እንደተስማማን አድርገው ወሰዱ፣ በጣም አዝናለሁ።

ደብዳቤ ተልኮልኛል። አስቀድሞ እንደጠቀስኩት፣ መጋቢት 3 ኢሌሌ ሆቴል መመሪያ ልናወጣ ስለሆነ ግብዓት አምጡና እንወያይ ብለው ጠሩን። እነርሱ ግን ቀድሞ ጨርሰውት ነበር። ይህ ከሕገና ሕገ መንግሥት ጋርም ይጣረሳል። አዋጅ ከወጣ በኋላ ዐቃቤ ሕግ ደንብ ያወጣል፣ ከዛም መመሪያ ይወጣል። መመሪያ የሚያወጣው ተቋም ደግሞ ከብዙ አቅጣጫ መቃኘት አለበት። የመንግሥትን አዋጅና ደንብ እነካለሁ ወይ፣ የፍርድ ቤቶችንስ የሚለውን አይቶ ተጠንቅቆ መሆን አለበት።

መመሪያው ለሠራተኛው ብቻ ሳይሆን ለእኛም ነው የሚያገለግለው። ከዚህ አኳያ ነው ችግር አለበት የምንለው። ለሙያው የሚሰጠውን ግምት ካየን፣ ትኩረት ያልተሰጠበትን ምክንያት ይህ ነው ብዬ ማስቀመጥ አልችልም። እኛ የሰው ኃይል ማቀፋችን፣ ግብር መክፈላችንን ነው የምናየው። ኅብረተሰቡ ጋር ግን ጥሩ ሥም የለውም። አንቺ ራስሽ ይኸው ሥራዬ ብለሽ በማኅበር ግልጽ ካላወጣሽ አስቸጋሪ ነው።

እኛም ይህን መመሪያ መሠረት አድርገን ማኅበር አቋቋምን። እውቅና ያላቸውንና ረጅም ጊዜ የሠሩትን በማካተት ሰባት ሆነን ነው የመሠረትነው። ‹አባይ የግል ጥበቃ አሠሪዎች ማኅበር› ይባላል። ግንቦት 06/2012 ነው የእውቅና ሰርተፍኬት ያገኘነው። አሁን ወደ ሠላሳ አካባቢ ድርጅቶችን ማካተት ችለናል። የማኅበሩ አባል መሆኛ መስፈርቶችም አሉ።

ድርጅቶች የማኅበር አባል በመሆን ምን የተለየ ጥቅም ያገኛሉ?
መንግሥት በገቢዎች ሚኒስቴር ሕጋዊ ያላቸውን ድርጅቶች ዘርዝሮ አስቀምጧል። እነዚህ ድርጅቶችም ወደ እኛ ሲመጡ፣ አንደኛ የተበላሸ ነገራቸውን ያስተካክላሉ። ርዕያቸውንም ያሳካሉ። አሁን ችግር ውስጥ ነው ያለነው። ዘርፉ ሕልውናው ሊጎዳ ስለሆነ ጥበቃ ያገኛሉ። ይህም የሚሆነው ከመንግሥት ፈቃድ አግኝተናል። ይህንንም በይፋ ለማሳወቅ አስበን ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ረብሾታል። ግን ለሁሉም ተቋማት በኢሜይል አሳውቀናል።

አብሮ ከመጨፍለቅም ይድናሉ። የሥራ ግብር ከማይከፍሉ ጋር ለምን ይጨፈለቃሉ? በተያያዘ ፌዴራል ፖሊስ ስብሰባ ጠርቶን ነበር። ይህም መጋቢት 03/2012 ላይ ንግድ ባንክ ልደታ አዳራሽ ጠርቶ፣ ምን ይሻላል ባንክ ላይ ችግር እየተፈጠረ ነው ብሎ ጠየቀን። አሁን የፌዴራል ፖሊስ አጋዥ ልንሆን ነው። መጀመሪያ ለራሳችን ነው። ከዛ ደግሞ አልፎም ለመንግሥትና ለአገር መጥቀም አለ።

የማኅበሩ አባል ለመሆን ከድርጅቶች የሚጠየቁ መስፈርቶች ምንድን ናቸው?
የታደሰ ንግድ ፈቃድ፣ የምዝገባ፣ የአሻራ ቁጥር (ቲን)፣ የቫት የምስክር ወረቀት ሊኖረው ይገባል። ሌላው ብዙ ጊዜ ቅሬታ የሚቀርብበት የጡረታ ጉዳይ ነው። የግል ጡረታ ኤጀንሲ ጡረታ ከፋይ መሆንን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ይሰጣል። እናም ያንን ካላመጣ የእኛ አባል አይሆንም።

ሌላው ሠራተኛና ማኅበራዊ ቢሮ፣ የፌዴራል ፖሊስ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀቶች ያስፈልጋሉ። ከግብር ነጻ ክሊራንስም ያስፈልጋል። ለማኅበሩ ኮሚቴ የቢሮ አድራሻን ማሳየትም ይጠበቃል። ቢሮ የሌለው አለ። ችግም የሚፈጥረውም ይህ ነው። ስለዚህ ቢያንስ ቢሮውን እናያለን። ይህም አምስትና ስድስት ክፍል ሊኖረው ይገባል። ይህ የግድ ማሟላትና ለእኛ ማስጎብኘት አለበት።

በተጨማሪ የሠራተኛ የመለዩ ልብስን የሚመለከት ነው። ይህ በጣም የሚያሳዝን ነው። በአሁኑ ሰዓት ቦሌ ኤድናሞል ጋር ብትሄጂ፣ የመከላከያን ልብስ አድርጎ የሚሠራ ጥበቃ ድርጅት አለ። ማነው ይህን ሰው የሚቆጣጠረው፣ መንግሥትስ እንዴት ዝም ይላል ነው። ካዛንችስ ዑራኤል አካባቢ ደግሞ የፌዴራል ፖሊስን ዓይነት መለዮ የሚለብስ ጥበቃ አለ። ስለዚህ ድርጅቱ የመለዮውን ናሙና ማቅረብ አለበት አልን። ሲያቀርብም የመንግሥትን ደኅንነት መለዮ የሚመስል ወይም ከሌላ ድርጅት ጋር የሚመሳሰል ከሆነ እንጥልበታለን።

ከዚህ ባለፈ ደግሞ የድርጅቱን መመሥረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ ማቅረብ አለበት። በዚህም ትክክለኛና የሚመለከተው ሰው ነው ወይ ወደእኛ የመጣው የሚለውን እንለያለን። ሌላ ከፌዴራል ፖሊስ ከወንጀል ነጻ መሆኑን ማሳያ ምስክር ወረቀት እንፈልጋለን። እንዲሁም የውሎ አዳር ሪፖርት የ24 ሰዓት ለማኅበራችን በኢሜይል አልያም ባሉ አማራጮች መላክ አለበት። ፌዴራል ፖሊስ ሪፖርት ይፈልጋል።

ለእኔ ምሽት ላይ ሪፖርት ይደርሰኛል። ሁሉ ሰላም ከሆነ ሰላም መሆኑን፣ ችግር የተፈጠረበት አካባቢ ካለም እንደዛው ችግር እንዳለ መረጃው ይመጣል። ይህን መረጃ ድሮ እኛው ጋር የሚቀርና ለማንም የማንሰጠው ነበር። አሁን ግን እያዘጋጀን ባለነው ስርዓት ሁሉም የማኅበር አባል ይልካል፣ ማኅበሩ ደግሞ ለፌዴራል ፖሊስ ሰብስቦ ይልካል። ከዚህም ፌዴራል ፖሊስ ያልደረሰበት ቦታ ላይ ያለውን መረጃ ያገኛል።

ይህም ለአገር ደኅንነትም ትልቅ አስተዋጽኦ እናደርጋለን። ኃላፊነትም አለብን። የፖሊስን ትልቁን ሥራ እንሠራለን። መተዳደሪያ ደንባችን ላይ ይህን ያላከበረ ከአባልነት ይሰረዛል ይላል። እና ፖሊስ በእኛ አልተጠቀመም የምንለውና በፖሊስ ስር መሆን አለብን የምንለው ለዚህ ነው።

ወር በገባ በአምስተኛው ቀን አዲስ የተቀጠሩ ሠራተኞችን ለሠራተኛና ማኀበራዊ፣ ለስታትስቲክስ ኤጀንሲ እንዲሁም ከፌዴራል የሥራ ፈጠራ ምክር ቤት የቁጥር መረጃውን እናስገባለን። ይህ መረጃ በእነዚህ ተቋማት ይፈለጋል፣ ግን በተቀናጀ መልኩ አይሰበሰብም ነበር። አሁን ግን አንድ ወጥ በሆነ መልኩ በማኅበሩ በኩል ይቀርባል ማለት ነው።

በአባል ድርጅቶች ተቀጥረው ከሚሠሩ ውስጥ የተሰናበቱም ካሉ መታወቅ አለበት። አንድ ክልል ላይ ወንጀል ሠርቶ ወደ ሌላው ሄዶ ለመቀጠር የሚፈልገውን ለማግኘትና ለማናበብ ይረዳል።
ሌላው በየወሩ የሥራ ግብርና ጡረታ መሰል ክፍያዎች የተከፈለበትን ደረሰኝ ለማኅበራችን ይልካል፣ እያንዳንዱ አባል። ያላስገባ ካላ ሲስተሙ ራሱ ይጠይቀዋል። በዚህም የመንግሥት ገቢ በአግባቡ መደረጉን እናያለን። መንግሥትም 200 በላይ ድርጅቶች ጋር ከሚሄድ እኛ ማኅበር ጋር ሄዶ የእገሌን ዳታ ማግኘት እፈልጋለሁ ካለ ቀጥታ ያገኛል። በአግባቡ የማይከፍሉ ሰዎች ካሉ እኛ ጋር ይያዛል ማለት ነው።

አንድ ሰው እኛ ማኅበር መጥተው ይህን መስፈርት አይተው፣ ይህን ለምን እናደርጋለን እናንተ የገቢዎችን ሥራ ነው ወይ የምትሠሩት አሉን። አይ! እየታማንበት ስለሆነ፣ ደግሞም ለመልካም ነገር ስለሆነ ችግር የለም ነው መልሳችን።

ዓመታዊ ግብር ከመክፈል ባሻገር በኦዲት የታየውም መቅረብ አለበት። የሚቀጠሩ ሠራተኞችም በቂ ዋስ፣ አሻራ፣ የቀበሌ ድጋፍ፣ መታወቂያ ያስፈልጋቸዋል። አንዳንዱ በቀበሌ መታወቂያ ይቀጠራል። በዛ ዘርፎ ይሄዳል። እኛ ጋር ብትመጪ በጣም ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው። ያለዋስትና አይቀጠርም። ገንዘብና መታወቂያ ሳይሆን፣ የመንግሥት ወይም የታዋቂ ተቋም ተቀጣሪ የሆነና ከዛም ደብዳቤ ተጽፎ መምጣት አለበት። የመኪና ሊብሬና ካርታ መምጣት አለበት። ዋስታና ካልጠነከረ ዝርፊያ ይከተላል። ይህም የአንድ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ለመንግሥትም ችግር ነው የሚያመጣው። ይህን በዚህ እንፈታለን ብለናል።

ከዛ ውጪ የአባልነት ጥያቄን በጽሑፍ የሚያቀርብና መመሪያና ደንቡን የሚያከብር ነው ወደ ማኅበሩ የሚገባው። ለአባላነት ከጠየቁት ውስጥ ብዙ ጥለናል፣ መስፈርቱን አላሟሉም። አሁን ሠላሳ ነን ያለነው። ፌዴራል ፖሊስን እየጠየቅን ያለነውም፣ የሚያወጣው መመሪያ በማኅበር ያልታቀፈ የጥበቃ ድርጅት ፈቃድ ሲያድስ ወደ ማኅበሩ እንዲመጣ ነው። በዚህ አላስፈላጊ ያልሆነ ሌብነትና ስርቆት አይኖርም።

በሕንጻ አስተዳደር ፍቃድ አውጥተው ጥበቃ የሚሠሩ ድርጅቶች አሉ። ቁጥጥርና ባለቤት የሌለው እንደሆነ የምታይው ለዚህ ነው። ዓለማቀፍ ድርጅቶችም ከእኛ ውጪ ሊሠሩ አይችሉም። ማኅበርም አንድ ብቻ መሆን የለበትም። ጠንካራ ሌላ ማኅበር ቢመሠረትና ፈቃድ ቢሰጥ ጥሩ ነው። ነገ ማንኛውም ሰው ይህን ሥራ ለመሥራት አቅም ያለው ሰው ይገኛል። ሥራው ፈተና አለው። በዚህም የተበላሸው ሥማችን ይስተካከላል።

ሠራተኞች ጠንከር ያለ ዋስ እንዲያቀርቡ ይጠየቃሉ ብለዋል። ነገር ግን የዛን ያህል ዋስትና ለማስያዝ አቅም የሌላቸውስ ሲመጡ፣ ምን ታደርጋላችሁ?
ይህ ከባድ ነው። ይሄዳል እንጂ ምንም ማድረግ አንችልም። ዋስትና ብቻ ሳይሆን ከስድስት ወር በፊት የተነሱትን ፎቶ እንጠይቃለን፣ ተቀጣሪውም ዋሱም። ዋስ በአካል እንዲገኝም ይፈለጋል። በተጨማሪም የቀበሌ ድጋፍ ያስፈልጋል። ይህም እገሌ የአካባቢያችን ነዋሪ ነው የሚል ነው። የፌዴራል ፖሊስ አሻራ እና ስድስት ወር ያላለፈው የቀበሌ መታወቂያ መቅረብ አለበት።
እለዚህን ካሟላ ብቻ ነው የሚቀጠረው። ይህን ካላሟላ ይቅርብን። ምክንያቱም ያላሰበውን ነገር ልታሳስቢ ነው። ለጥቅም ብሎ ይህን ማድረግ አስቸጋሪ ነው። ያ ሠራተኛ ዋስትና ስለሌለው ይህን ነገር ሰርቄ ብሄድስ ብሎ እንዲያስብ ይሆናል። ዋስ ካለው ግን ያንን ሰው ለማን ጥዬ፣ ያስይዙኛል ብሎ ተጠንቅቆ ይሠራል።

አንድ ሰው ዋስትና እና የተጠየቀውን ስላመጣ ብቻም አንቀበልም። ገጽንም እናያለን። ይጠጣል ወይ፣ ያጤሳል ወይ፣ አካሉስ ብቁ ነው ወይ የሚለውን እናያለን። መሮጥ ይችላል ወይ የሚለውንም እንደዛው። ስፖርት እናሠራለን። ያንን ሲያሟላ ነው እንጂ ወደዋስትና ማቅረብ የሚገባው፣ አስቸጋሪ ሰው እኛ ጋር አይቀጠርም። ምክንያቱም ኃላፊነት የሚሰማው ቤተሰብ የሚያስተዳድር ሰው ነው ጥበቃ ቦታ ላይ ሊመደብ የሚችለው።

እና ፌዴራል ፖሊስ ከደገፈን ማኅበሩ በስድስት ወር ውስጥ ውጤት እናሳያለን፣ የእኛንም የጠለሸ ስም እናድሳለን። በዚህም ለመንግሥት ትልቅ ድጋፍ እናደርጋለን።

ሴት ጥበቃዎችን በተመለከተስ፣ በድርጅታችሁ ምን ያህል ሴት ጥበቃዎች ይገኛሉ?
ሴቶች ከመቶ 25 ወይም 30 አካባቢ ናቸው። ፍተሻ ላይ ይሠማራሉ። አብዛኛውን ቦታ ላይ ይኖራሉ። ስምንት ሰዓት ነው የሚሠሩትም። ደሞዛቸውም ከፍ ይላል። የሚሠሩት አንድ ሥራ ስለሆነ ነው። ወንዶቹ በጥበቃ ሥራ ከ30 ቀን ውስጥ 20 ቀን እረፍት አላቸው። አንዳንዴ ገቢያቸውን ከፍ ለማድረግም ቀን ጨምረው ይሠራሉ። ሴቶች ግን በመደበኛ የሥራ ሰዓት ስለሚሠሩ ደሞዛቸውን ከፍ እናደርጋለን።

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here