“ባለአደራ ምክር ቤት” ረቡዕ የሰጠው መግለጫ ባልታወቁ ሰዎች ተበተነ

Views: 455

የአዲስ አበባ ባለ አደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) አመራሮች ረቡዕ፣ ሐምሌ 3/2011 በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ በመስጠት ላይ ሳሉ 7 በሚሆኑ ማንነታቸው ባልታወቁ ወጣቶች በተፈጠረ ኹከት ሊቋረጥ ችሏል። ኹከት ለመፍጠር መግለጫ ወደሚሰጥበት ቦታ ጎራ ያሉት ወጣቶቹ ባንዲራና ስለታማ መሣሪያ ይዘው እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።

በዕለቱም ወጣቶቹ የምክር ቤቱ አመራሮች መግለጫ ሰጥተው ከጨረሱ በኋላ፣ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ የባለአደራው ሊቀ መንበር እስክንድር ነጋ ምላሽ እየሰጡ በነበሩበት ወቅት ነበር በቦታው ተገኝተው ግርግር የፈጠሩት። ወጣቶቹ በቦታው ተገኝተው እስክንድር ነጋን በግልፅ በማስፈራራትና ዛቻዎችን በማሰማት የነበረውን ድባብ መልኩን እንዲቀይር አድርገዋል።

ባለአደራው በሊቀ መንበሩ አማካኝነት መግለጫ በሰጠበት ወቅት በሽብር ሕግ ተጠርጥረው የተያዙት አምስቱ የምክር ቤት አባላት ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው መሆናቸውን ገልጸው፣ እነዚህ ሰዎች የሕሊና እስረኞች ናቸው ያሉ ሲሆን፤ በአሜሪካን አገር የሚኖሩትን እና ቀድሞ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት ኤርሚያስ ለገሰ የምክር ቤቱ ምክትል ሊቀመንበር መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ባለ አደራው በመቀጠልም ሰኔ 15/ 2011 በባሕር ዳርና በአዲስ አበባ በሰዓታት ልዩነት በአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም በአገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ “በሽብር ጥቃት” ተጠርጥረው በአዲስ አበባ ከተማ የተያዙት አምስት የምክር ቤቱ አባላት ከተከሰሱበት ጉዳይ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸውና ምክር ቤቱን ለማዳከም የተደረገ ነው ሲልም በመግለጫው አትቷል።

ቅዳሜ፣ ሰኔ 29 በሽብር ሕጉ ተጠርጥረው 14 ሰዎች የተያዙ ሲሆን ተጠርጣሪዎቹ፣ ሐሰተኛ ማስታወቂያ በማዘጋጀት ለሽብር ጥቃቱ ተሳትፈዋል በማለት መያዛቸውን፣ ጠበቃቸው የሆኑት ሔኖክ አክሊሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com