ደኅንነት ለሁሉም!

0
612

ከሰሞኑ በሚያሳዝን ሁኔታ በክፉ ሰዎች ድርጊት ሕይወቱን የተነጠቀው ሀጫሉ ሁንዴሳ በከፍተኛ ሁኔታ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በተለይም የግድያው ሁኔታና ከዛም አልፎ የቀብር ስነስርዓቱን በማስተጓጎል በኩል የታዩ ድርጊቶች የብዙዎችን ልብ የሰበሩ ናቸው። በእነዚህ ተከታታይ ድርጊቶችም የሌሎችም በርካታ ሰዎች ክቡር ሕይወት አልፏል። ይህም እጅግ የሚያሳዝን ነው።

በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የደረሱ የንብረት ዝርፊያና ማውደም የመሳሰሉ ኹነቶችን ታዝበናል። ይህም በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞችም እንደተከሰቱ ነው የሰማነው፣ የታዘብነውም። በዚህ ጊዜ ታድያ ብዙዎች ይሉ የነበረው፣ የሰው ሕይወት ውድ እንደሆነና እንደማይተካ፣ የወደመው ንብረት ግን ሊተካ እንደሚችል ነው።

እውነት ነው! የሰው ሕይወት የማይተካና ውዱ ነገር ሆኖ ሳለ፣ ንብረት የሚተካ መሆኑ ላይ ጥርጥር የለም። ግን በተመሳሳይ ልብ ብለን ስናስብ፣ ሀብት በተለይም ሰዎች የእውነት ለፍተውና ደክመው የሚያፈሩት የእኔ ያሉት ንብረት ሲባክን አብሮ የሚጠፋው ነገርም ቀላል አይደለም።

ከንብረት ጋር እድሜ፣ ጉልበት፣ እውቀት፣ ጊዜ፣ ተስፋና እምነት አሉ። ሰው ንብረቱ ሲሰረቅና ሲበላሽበት ልቡ ይሰበራል፣ ያንን ለማግኘት ያሳለፈው ውጣ ውረድ ያመዋል። ያዝናል። ደግሞ አፍራሽና አጥፊስ አገሩ የት ነው? ማንስ ይክፈለው ማን፣ የት ሄዶ ሊገበያይ ነው?

እርግጥ ነው የጠዘረፈና ንብረቱ የወደመ ሰው ዋናው ጤና ነው ይላል። ንብረት ይተካል የሚል መጽናኛ ቃል ከአንደበቱ አይጠፋም ይሆናል። ነገር ግን ያንን ንብረት ለማፍረት ያወጣው ዋጋ የማይተመንለት የሰውነት ጊዜው፣ እድሜው በምንም የሚተካ አይደለም። ጽናት ያላቸውን፣ ንብረታቸው ወድሞ፣ ተቀምተውና ተወርሶባቸው ጭምር ተመልሰው ከትንሿ ጀምረው ራሳቸውን የሚያቋቁሙ ሰዎች ጥቂት አይደሉም። ይህ የጽናት ተምሳሌትነት ነው። ነገር ግን አስቀድሞስ ንብረት ባይወድም ምን አለ?

በአዲስ አበባ ጀሞ አካባቢ በኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን አስተባባሪነት ከተለያዩ አካላት በተገኘ ድጋፍ ዘመናዊ የጉሊት ወይም የንግድ ማእከል ከተመሠረት ጥቂት ዓመታት አልፈዋል። ጉሊት በተለያየ የንግድ ሥራ ላይ የነበሩ፣ በሚያሳዝን ሁኔታ ኑሯቸውንም ሥራቸውን ይገፉ የነበሩ ሴቶች፣ ይህን የሥራ ማእከል ያገኙ ጊዜ የነበራቸውን ደስታ በጊዜው የእጣ ማውጣት ስነስርዓቱ ላይ ለዘገባ በመገኘቴ የምረሳው አይደለም።

ለልጆቻው እንዲሁም ለቤተሰባቸውና ለራሳቸው የተሻለ ቀን እንደሚመጣም እርግጠኛ ሆነው ከፍ ባለ ሞራል ነው ስፍራውን የተረከቡት። የእነዚህ ሴቶች ይህ የንግድ ማእከል ታድያ ከሰሞኑ በነበረው ወከባና ረብሻ ምክንያት የአጥፊዎች ሲሳይ ሆኖ ጉዳት እንደደረሰበት ነው አዲስ ማለዳ የዘገበችው።

ያሳዝናል። በእርግጥ ይህ ነገር በብዙዎች ላይ የደረሰ መሆኑ ይታወቃል። እንዲህ ኑሮን ለማሸነፍ ያላቸውን ሸጠው የሚባዝኑት ላይ ሲደርስ ደግሞ የበለጠ ልብ የሚሰብር ክስተት ይሆናል። በእርግጥ እንደተባለው ሀብትና ንብረት መተካቱ አይቀርም፣ ግን እንዲህ ባለ መልኩ አንዱ ጉዳይ ኮሽ ባለ ቁጥር ሕይወትና ንብረት ጉዳት ላይ የሚወድቁ ከሆነ፣ አስቸጋሪ ነው።

ሌባን በምክር መመለስ ከባድ ነው። በእንቁላሉ ጊጊ ያልተቀጣ በሬ እየነዳ ቢሄድ፣ ከቅጣት ውጪ ማስተማሪያ አያገኝም። እናም አጥፊዎች በተለይም ንብረት ያወደሙ፣ አንዲት ድንጋይም ትሁን በሰዎች፣ በሰዎች ቤትና ንብረት ላይ የወረወሩ፣ ሰው ስላልገደሉ ተብሎ መታለፍ የለባቸውም። እያንዳንዱ ቅጣቱን ማግኘት፣ ያንንም ሕዝብ እንዲያውቅ ማድረግና ሌሎችመ በተመሳሳይ የጥፋት መንገድ ቢሄዱ የሚከተላቸውን ቅጣት እንዲያውቁ ማድረግ ይገባል።
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here