በአዲሲቷ ዓለም አዲስ የሥራ ባህል

0
639

የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የዓለምን መልክ እየቀየረው ይመስላል። የተለያየ ዘርፍ ላይ ወደፊትም ወደኋላም በማየት የተካኑ ባለሞያዎችም፣ ድኅረ ኮሮና ዓለም ምን መልክ እንደሚኖራት ከወዲሁ እየሳሉና በዛ ውስጥ ለመኖር የሰው ልጆች ማድረግ ስለሚገባቸው ለውጦች እያሳሰቡ ይገኛሉ። አብርሐም ፀሐዬ ይህን ሐሳብ መነሻ አድርገው ይልቁንም የሥራ ባህል እንዴት ሊቀየር ይችላል የሚለውንና በዛ ውስጥም መደረግ ይገባቸዋል የተባሉትን ጉዳዮች አንስተዋል።

ድኅረ ኮሮና አዲሲቷን ዓለም ይሰጠናል። ኮቪድ 19 ቢጠፋም ባይጠፋም አዲስ የኑሮ ልማድ፣ አዲስ የሥራ ባህልና አዲስ አስተሳሰብ አስረክቦናል። በተለይ ከአዲስ አሠራር አንጻር በፔንሲልቫኒያ ዩኒቨርስቲ የአመራርና የተቋማት ሥነ ልቦና ጉዳዮች ፕሮፌሰር የሆኑት አዳም ግራንት (Adam Grant)፣ ሠራተኞች ቀጥረው እያሠሩ ያሉ ተቋማት አሠራራቸውን ሊቀይሩ የሚገደዱበት ጊዜ እንደመጣ ይናገራሉ።

ድርጅቶች ሠራተኞቻቸው ላይ ሊያደርጉ ከሚገባቸው ለውጥ መካከል ኹለቱን ብንመለከት፣ ተቀጣሪዎቻቸው የተሰጣቸውን ሥራ በራሳቸው የጊዜ ልኬት ውስጥ እንዲሠሩ ማመቻቸት አንዱ ነው። ሌላው ደግሞ ሥራውንም ከተለመደው የሥራ ቦታ ውጪ እነሱን ባመቻቸው ስፍራዎች እንዲከውኑ መፍቀድ ይኖርባቸዋል።

ይህ አሠራር ከዚህ ቀደም እንደነበረው ሠራተኞችን በቢሮ ውስጥ ቀጥሮ ወይም በሥራ ቦታቸው ላይ በማምጣት በቅርብ ቁጥጥር ማሠራት አይደለም። ይልቁንም አንድን ሥራ በጊዜ ገደብ ለክቶ ኃላፊነት በመስጠት እንዲሠሩ መፍቀድ ድርጅቶች ሊከተሉት የሚገባው አዲሱ የኮቪድ ዘመን አስገዳጅ ለውጥ መሆኑን አዳም ግራንት ተናግረዋል።

ባለሙያው የዓለም የምጣኔ ሀብት ፎረም ላይ ተጠይቀው በሰጡት ገለጻ፣ ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየገፋን ያለው ኃላፊነትን እና ተጠያቂነትን ለሠሪው ለራሱ እንዲሰጥ ማድረግ ሆኗል። አንድ ሠራተኛ የሥራ ባህሪው መኖሪያ ቤት ውሰጥ እንዲሠራ ከፈቀደለት፣ ያንን ማድረግ ይገባል። አሁን ላይ በተወሰነ ደረጃ ሥራዎች በመከፈት ላይ ቢሆኑም፣ በርካታ የዓለም ሕዝብ ያለሥራ ቤቱ ቁጭ ብሏል። ይህም አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ የሆኑ አሉታዊ ተጽእኖዎችን ፈጥሯል።

በዚህ የተነሳ አብዛኛው ሠራተኛ ከወረርሽኙ በኋላም ቢሆን እንኳ በቀላሉ ከድብርት አይወጣም። በፍርሃትና በሞት ድባብ እንዲሁም ከገቢ ማሽቆልቆል የተነሳ የሠራተኞች ውስጣዊ ጥንካሬ ተዳክሟል። ስለሆነም ሥነ ልቦናቸው ሊገነባ ይገባል።

እንደሚታወቀው ደግሞ ማንም ሰው ውስጣዊ ብርታቱ ከደከመና በአጠቃላይ ሥነ ልቦና ችግር ከተጠቃ፣ በሥራው ምርታማ እንደማይሆን ጥርጥር የለውም። ቀጣሪ ድርጅቶች ይህንን ማሰብና የተለያዩ ሥልጠናዎች እና ማበረታቻዎች በማድረግ ሊታደጓቸውና ምርታማ ሠራተኛ ሊፈጥሩ እንደሚገባ ከወዲሁ ማቀድ አስፈላጊ ነው ሲሉ ምሁሩ አሳስበዋል።
ይህ የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አዲስ እየወለደውና ተግባራዊ ሊያደርገው የሚጠበቅበት የሥራ ባህሪ አለ። ይኸውም የድርጅቶች አሰራሮች ላይ ክለሳ በማድረግ ከሁኔታዎች ጋር ተስማሚነት ያለው የሥራ አካሄድ መዘርጋት (Redesigning)፣ በፈጠራ የታገዘ የሥራ ባህል ላይ ማተኮር (Cultures of creativity) እና በመመጋገብ ላይ የተመሠረተ የቡድን ሥራ (Generosity in team) ናቸው።

በዚህ መልክ አንድ ድርጅት ህልውናውን ማስጠበቅና ምርታማነቱን ማሳደግ ይገባዋል። በጥቅሉ ጊዜው የሚጠይቀው ድርጅቶች ወይም የሥራ አመራሮች መሪነትን ለራሳቸው ለሠራተኞች በመስጠትና እምነት በማሳደር አዲስ የአሰራር ባህል መፍጠር ነው።

እዚህ በአገራችን በአብዛኛው የመንግሥት ተቋማት ተጽፈው ነገር ግን የማይነበቡና የማይተገበሩ የሥነ ምግባር መመሪያዎች በየግድግዳው ላይ ተለጥፈው እናያለን። እነዚህ ቅንነት፣ ኃላፊነት፣ ታማኝነት ወዘተ የሚባሉት የሥነ ምግባር መርሆዎች ቢተገበሩ ምን ያህል በመርህ የመመራት ልማድ እንደሚፈጠርና ሊለካ የሚችል ውጤት ማግኘት እንደሚቻል ማመን ይቻል ነበር። መገመት እንደሚቻለው ግን ምን ያህሉ ወደ መሬት እየወረዱ ነው ቢባል አጠያያቂ ነው።

አሁን ያለንበት የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ግን በመርህ የመመራት አስፈላጊነትን የምናምንበት ብቻ ሳይሆን የምንቀበልበት ጊዜ ላይ ነን። ግራንት እንደሚናገሩት ድርጅቶች የሠራተኞቻቸውን ለሥራ ዋጋ የመስጠት፣ የቁርጠኝነት፣ ያላቸው እሴት፣ ፍላጎት፣ ትጋት፣ ተነሳሽነት የሚባሉትን ወሳኝ ባህሪያት የሚለዩበት ወቅት እንደሆነ ይመክራሉ።
ተቀራርቦ መሥራት አስቸጋሪ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ ሠራተኞች ሥራዎችን በየራሳቸው ኃላፊነት በቤታቸው ወይም ተነጣጥለው እንዲከውኑ መፍቀድ ሰነፉ ከጎበዙ፣ ወሬኛው ከሠራተኛው፣ ሌባው ከሐቀኛው ይለይበታል። በሌሎች ትከሻ የተደገፉ ሸክም የሆኑ ሠራተኞች ለየብቻ በሚሰጥ ሥራ አማካይነት በአግባቡ ይለዩበታል።

ሥራን በወቅቱ ማጠናቀቅ የሚጠይቁ ሥራዎችን ማን የራሱን ግላዊ ብቃት ተጠቅሞ በተገቢው ጊዜ በጥራት እንደሚያቀርብ ለመለየትም ያግዛል። የቱ ሠራተኛ የራሱን ፈጠራ ተጠቅሞ የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግብና በስተመጨረሻም ትጉህና ጥሩ የፈጠራ ባለሙያ የሆኑ ሠራተኞችን ይዞ ለመጓዝ አመቺ ጊዜ ነው።

በአጠቃላይ ተቋማት ከድርጅታቸው የሥራ ባህሪያት ጋር የሚሄድ አሰራር በመዘርጋት ሠራተኞች የቤት ውስጥ ሥራን ጭምር ልምድ እንዲያደርጉና እንደተባለውም ምናልባት የተሻሉ የሥራ ልማዶች እንደሚፈጠሩ መገመት የሚቻልበት ዘመን ላይ ነን።

እንዲህ ያሉ የየዘመኑ ፈታኝ ወቅቶች ትላንትም የነበሩ፣ ዛሬም የሚኖሩ እንዲሁም ነገም የሚቀጥሉ ናቸው። የዕለት ከዕለት የአኗኗር ዘይቤዎች ላይ አስገዳጅ ለውጥ የሚያመጡ በመሆናቸው ከለውጡ ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ማጤን ይኖርብናል።

ዓለማችን የሚገመቱም የማይገመቱ ክስተቶችንም የምታስተናግድ ፕላኔት ናት። በተለይ አሁንም ይሁን ወደ ፊት የተፈጠሩና የሚፈጠሩ ተግዳሮቶችን መቋቋም የሚቻለው ቢቻል ለችግሩ መፍትሄ በመፈለግ ማስወገድና መቆጣጠር ነው። ካልሆነ ግን ያለው አማራጭ ከችግሩ ጋር ሊያስማማ የሚችል ልማድን ማዳበር ይሆናል።
ፕሮፌሰር አዳም ግራንት ይህንን እውነት ለማጠንከር በጠቀሱት ምሳሌ እንቋጭ።

‹‹ዳርዊን ስለ ዝግመተ ለውጥ ባስቀመጠው ቲዎሪ ላይ ህልውናቸው ወይም ዝርያቸው በየዘመኑ ሳይጠፋ ሕይወታቸውን የሚያስቀጥሉ ፍጡራን ጠንካራ የሆኑት ወይም ተፈጥሮን ያሸነፉ ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸውን ከሚፈጠረው አደጋም ይሁን ተፈጥሯዊ ለውጥ ጋር ማስማማት የቻሉትም ናቸው።›› ሲሉ ገልጸውታል። (Darwin wrote when he was building his theory of evolution that natural selection favors a sense of flexibility. It’s not always the strongest species that survives; it’s sometimes the most adaptable.)

አብርሐም ፀሐዬ የቢዝነስ አማካሪና ጋዜጠኛ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው geraramc@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here