የሲዳማ ክልል መሆንና ያስከተለው ሌላ ጥያቄ

0
966

የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት (ደቡብ ክልል) “የትንሿ ኢትዮጵያ” ተምሳሌት በመባል ይታወቅ ነበር፡፡ ደቡብ ክልል “የትንሿ ኢትዮጵያ” ተምሳሌት ተብሎ የሚጠራው ከሃምሳ በላይ የዘውግ ቡድኖችን(ብሔረሰቦችን) በአንድ ክልልነት ያቀፈ ብሎም ልዩነትንና አንድነትን አሰማምቶ ለሌሎች ተምሳሌት ክልል ስለሆነ ነበር።

የቀድሞው ደቡብ ክልል አንዱ ዞን የነበረው ሲዳማ ዞን የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት በሚፈቅደው መንገድ ክልልነት ጥያቄ አንስቶ፣ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አማካኝነት ሕዝባዊይ ውሳኔ ተካሂዶ ክልል የመሆኑ ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ፣ የቀድሞው ሲዳማ ዞን ዛሬ የኢትዮጵያ አስረኛ ክልል መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ይህን ተከትሎ በደቡብ ክልል ከሚገኙት ዞኖች ወስጥ 12 ዞኖች የክልልነት ጥያቄ አንስተው ይገኛሉ፡፡

በክልሉ በሕገ መንገስቱ መሰረት ክልል ለመሆን የሚስፈልገውን መስፈርት ማሟላታቸውን በመግለጽ የክልልት ጥያቄ ካነሱት ውስጥ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጉራጌ፣ ሐድያ፣ ስልጤ፣ ከንባታ ጠንባሮ፣ ከፋ፣ ዳውሮ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ እና ጌድዮ ዞን እንደሚገኙበት እየተጠቆመ ይገኛል፡፡

ሲዳማ እና ደቡብ ክልል በይፋ ፍቺ ከፈፀሙ ጀምሮ በደቡብ ክልል ውስጥ የነበሩ ዞኖች የክልል እንሁን ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ጉባኤውን ያካሄደው የደቡብ ክልል ምክር ቤት በህዝበ-ውሳኔ ክልል መሆኑን ላረጋገጠው የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አሸኛኘት አድርጓል፡፡

በመክሰም ዋዜማ ላይ የሚገኘው የደቡብ ክልል ምክር ቤቱን አባላት በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት ከሁለት ሳምንት በፊት ስብሰባ አካሂዷል ከስብሰባዎቹ አጀንዳዎች አንዱ የደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች ሥልጣን ርክክብ ነበር፡፡ በስብሰባውም የደቡብ ክልል መንግስት 10ኛው የሀገሪቱ የክልል መንግስት መሆኑን ከወራቶች በፊት በህዝበ ውሳኔ ላረጋገጠው አዲሱ ሲዳማ ክልል ሥልጣን አስረክቧል፡፡

በክልሉ የክልል እንሁን ጥያቄ ካቀረቡት ዞኖች መካከል በደቡብ ክልል ምክር ቤት የሚገኙ የዎላይታ ሕዝብ ተወካዮች እራሳቸውን ከምክር ቤት አባልነት አግልለዋል፡፡የብሔሩ ተወካይ አባላት ራሳቸውን ከምክር ቤት አባልነት ያገለሉበት ምክንያት የዎላይታ ሕዝብ እራሱን በራሱ ለማስተዳደር ያስችለኛል በሚል ላቀረበው በክልል የመደራጀት ጥያቄ ምክር ቤቱ ተገቢውን ምላሽ አልሰጠም በሚል ነበር፡፡

የወላይታ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አበበች እራሾ እንዳሉት የወላይታ ብሔር በክልል የመደራጀት ጥያቄ በኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 መሠረት በዞኑ ምክር ቤት ፀድቆ በ2011 ለክልሉ ምክር ቤት በማቅረብ ሕዝበ ዉሳኔ እንዲደራጅለት ጠይቆ ነበር ፡፡

አፈ ጉባኤዋ አያይዘውም “የደቡብ ክልሉ ምክር ቤት ጥያቄው በቀረበ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከምርጫ ቦርድ ጋር በመነጋገር ሕዝበ ውሳኔ ማደራጀት ሲገባው ምንም ምላሽ አልሰጠም። በ2011 ባካሄዳቸዉ ሁለት መደበኛ ጉባኤዎችም ጉዳዩ በአጀንዳነት እንዲቀርብ በጽሑፍም ሆነ የጉባኤው አባላት በሆኑ የብሔሩ ተወካዮች ተጠይቆ ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል ።

ምክር ቤቱ ሕዝባችንና የወከላቸውን ድምፅ ለማዳመጥ ፍላጎት የለውም። ይህም ብሔሩን የወከሉ አባላት በምክር ቤቱ ላይ ያላቸው እምነት እየተሟጠጠና እየተሸረሸረ እንዲመጣ አድርጎታል” ብለዋል። “በመሆኑም ሀሳባችን ካልተደመጠ በምክር ቤት አባልነት መቀጠል ለእኛም ሆነ ለሕዝባችን ጥቅም የለውም” ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ በዚህ መነሻም በደቡብ ክልል ምክር ቤት የሚገኙ 38 የብሔሩ ተወካዮች እራሳቸውን ከምክር ቤት አባልነት ማግለላቸውን አስታውቀዋል ። አክለውም ካሁን በኋላ ስለ ወላታ ህዝብ የሚያገባው የዞኑ ምክር ቤት ብቻ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የደቡብ ክልል ዞኖች የክልልነት ጥያቄ መነሻ
ለደቡብ ክልል ዞኖች የክልል እንሁን ጥያቄ መነሻ ምክንያት ከሚባሉት ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት፣ ፍትሐዊ ውክልና አለማግኘት እና በጥቅሉ ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ አሰራሮች መሆናቸውን የጋሞ ድሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ዳሮት ጉምአ እንደሚያምኑ ይናገራሉ፡፡

የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ክልል የተለያዩ ብሔረሰቦችን በአንድ ያቀፈ ክልል በመሆቡ ላለፉት 27 አመታት አሁን ጥያቄ ባቀረቡት ብሔረሰቦች ላይ ከኢ-ፍትሐዊ ተግባራት እስከ ማንነትን የመካድና የማጥፋት ሙከራዎች እንደሚደረጉ ዳሮት ያምናሉ፡፡

በክልሉ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች አሁን ላይ በስፋት የክልልነት ጥያቄዎችን እያራገቡ የሚገኙት ከነዚህ ችግሮች ለመላቀቅ እንጅ አንድነትን ጠልተው እንዳልሆነ ዳሮት ይገልጻሉ፡፡ በዚህም እስካሁን ጫና የደረሰባቸው ዞኖች በደቦ መቀጠሉ እንዳልጠቀማቸው እና በክልልነት መደራጀት ለችግሩ መፍትሔ ያመጣል ብለው በማመን ጥያቄውን እንዳነሱትም ዳሮት አክለው አመላክተዋል፡፡

የደቡብ ክልል ዞኖች በክልል የመደራጀት ጥቅምና ጉዳት
የደቡብ ክልል ዞኖች በክልል መደራጀት ዞኖቹ ላቀረቡት ጥያቄ መነሻ ለሆኑ ምክንያቶች መፍትሔ እንደሚሰጥ ሁሉ ሌላ የዞኖች ክልል መሆን የሚመጣው ሌላ ችግር እንደሚኖር ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ከሚጠበቁት ችግሮች መካከል በአንድነት የፖለቲካ ሚዛን መድፋት መቻላቸው ቀርቶ ለየብቻ መጓዛቸው የአንድነት ፖሊለቲካዊ ጉዟቸውን እንደሚደናቅፍ ያሰጋል የሚሉት ዳሮት፣ የተለያዩ ብሔረሰቦች በአንድነት የመገነቡት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት በመከፋፈል እንደሚቀር እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

የህብረ ብሔራዊነት ተምሳሌት የነበረው ደቡብ ክልል ወደ ተለያዩ ክልሎች መበተኑ ወደፊት የሚኖረውን ፖለቲካዊ ሚዛን ደፊነት እንደሚሳጣው የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ዞኖቹ አሁን ላይ የክልልነት ጥያቄ ላስነሳቸው ችግር ምላሽ ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በጊዜ ሂደት መለያየቱ ሌላ እስከትሎት የሚመጣው ችግር እንደሚኖር ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ከሁለት ሳምንት በፊት ከተለያዩ የደቡብ ክልል የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በጽፈት ቤታቸው ውይይት አካሂደዋል። ውይይቱ በዋንኛነት ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከክልሉ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ጋር ባካሄዱት የመልሶ ማደራጀት ጉዳይ ላይ ያተኮረ ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል።

የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ፣ የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ፣ የጌዴኦ፣ የሀድያ፣ ጉራጌ፣ ካፋ እና ሌሎችም የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ በቁጥር ከ10 የማይበልጡ የየድርጅቶቹ ተወካዮች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በመሩት በዚህ ስብሰባ ላይ የሠላም አምባሳደሮች ቡድን ሰብሳቢው አባዱላ ገመዳ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል። ከጥናታዊ ጽሁፍ መቅረብ በኋላም የፖለቲካ ድርጅቶቹ ተወካዮች ሃሳባቸውን አጋርተዋል። ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር) የደቡብ ክልልን መልሶ የማደራጀት ሥራ ሀገር ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ የጥድፍያ ሥራ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ ፕሮፌሰሩ ንግግር ደቡብ ክልልን ለመከፋፈል ጊዜው አሁን አይደለም ያሉ ሲሆን የሁላችንም ትኩረት ዜጎችን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መጠበቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል። የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ጋዴፓ/ ተወካይ “ወላይታ እና ጋሞ ጥሩ ጎረቤቶች ናቸው ነገር ግን በፍጹም በአንድ ክልል ሊደራጁ አይገባም” በማለት አባዱላ ባቀረቡትና ወላይታን ከጋሞ፣ ጎፋ እና ሌሎች አከባቢዎች ጋር በአንድ ላይ ያቀረበውን ምክረ ሃሳብ ተቃውመውታል።

የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ ተወካይ ጋሞን በሥም ጠርተው በሚዲያ የታገዘ የሥም ማጥፋት ዘመቻ ከፍቶብኛል በማለት የከሰሱ ሱሆን፣ የዎላይታ ህዝብ ፍላጎት የብቻውን ክልል መመስረት እንደሆነ በመግለጽ። ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ በጋዴፓ እና ዎብን ተወካዮች ሀሳብ ላይ በሰጡት ማብራሪያ በጋሞ እና ዎላይታ ብሎም በዎላይታ እና ሌሎች ዞኖች መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት በቅርቡ ወደ ሥፍራው አመራለሁ ማለታቸውም ተገልጿል።

ይሁንና ግን ይሄ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ጋሞ እና ዎላይታ በአንድ ክልል እንዲደራጁ አስማማለው ይሁን በተለያየ ክልል ሆነው ጥሩ ጎረቤት እንዲሆኑ አደርጋለው በግልጽ አልተቀመጠም። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽፈት ቤት በተካሄደው ስብሰባ ላይ የወላይታ ዞን ራሱን ችሎ በክልል እንዲደራጅ የስብሰባው ተሳታፊዎች ሀሳብ ማቅረባቸውን ተነግሯል፡፡

ደቡብን በመበተን አዲስ እንዲቋቋሙ ሀሳብ ከቀረበባቸው ክልሎች “ሰፋ ያለ ቦታ የሚያካልል ነው” የተባለለት በዋንኛነትም የጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ደራሼ፣ ቡርጂ፣ አማሮ እና ኮንሶ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል እንዲጠቃለሉ ከውሳኔ ላይ መደረሱ ተብሏል።

ሆኖም ሰኔ 17/2012 የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት አባላት አራተኛውን ዙር አምስተኛ ዓመት ሁለተኛ አስቸኳይ ጉባኤ ባደረገበት ወቅት ደቡብ ኦሞ ዞን ክልላዊ የራስ ገዝ አስተዳደር ጥያቄ ለማንሳት ወስኗል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኦሞቲክ የክልል አደረጃጀትን በተመለከተ ከጋሞ ዞን ተወካዮች የቀረበውን ተቃውሞ መቀበላቸው ተነግሯል።

በሌላ በኩል እንደ ወላይታ ሁሉ እልባት ያላገኘው ጉዳይ የጌዲኦ ዞን ጉዳይ እንደነበር ይገለጻል፡፡ የ“ሰላም አምባሳደሮች” የተሰኘው ቡድን ያዘጋጀው የቀደመ ምክረ ሃሳብ ላይ የጌዲኦ ዞን፣ ከቡርጂ እና አማሮ ወረዳዎች ጋር በመሆን አንድ ክልል እንዲመስርት ሀሳብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ከአካባቢው ህዝቦች ተቃውሞ በመነሳቱ አማራጩ ውድቅ መደረጉ ተገልጿል።

ከፍተኛ የሃሳብ ፍጭት የተስተናገደበት የውይይት መድረኩ በተለይም ከጋሞ ዞን ህዝብ ተወካዮች በቀረበ የተቃውሞ ሀሳብ የተነሳ ከስምምነት ላይ ሳይደርስ ቀርቷል። የጋሞ ዞን ተወካዮች ያቀረቡት ተቃውሞ የህዝብ ፍላጎት አይደለም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር ሀይለማርያም ደሳለኝ ቡድን ያቀረበው የመከራከርያ ሀሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱም ታውቋል።

በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) ከህዝብ ፍላጎት ውጪ የሆነን ውሳኔ አናሳልፍም በማለት እራሳቸው በአካል ወደጋሞ፣ ጎፋ እና ወላይታ ዞኖች በመሄድ ከህዝቡ ጋር እንደሚወያዩ በመድረኩ ላይ መናገጋቸው ይታወሳል።

ያም ሆነ ይህ የደቡብ ክልል ምክር ቤት የ2013 ዓመት ክልላዊ ባጀትን በተመለከተ የሚያጸድቀው ሀሳብ እያንዳንዱ ዞን እስካሁን ሲያገኘው በመጣው ቅጽ መሰረት ቀጣይ ክልሉ ወደተለያዩ ቦታዎች ሲበተን ይሄንኑ ኮታውን ይዞ እንደሚሄድ ታውቋል።

ከዚህን ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያየ ጊዜ ከክልሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተወያዩበት ወቅት “ክልል ሲኮን ባጀት የሚጨመር የሚመስለው ሰው አለ፤ ነገር ግን ሱሙኒ አይጨመርም” ባሉት መሰረት ቀጣይ ደቡብን በማፍረስ የተለያየ ክልል የሚሆኑት ዞኖች በዚሁ ምክር ቤት የሚጸድቀውን ባጀት ይዘው እንደሚሄዱ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here