መንግሥት የሕዝብ ደኅንነት የማስጠበቅ ግዴታውን ይወጣ!

0
1133

ሰኞ፣ ሰኔ 22 ምሽት ሦስት ሰዓት ተኩል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ገላን ኮንዶሚኒየም በሚባለው ሰፈር ባታወቁ ሰዎች የተገደለውን ታዋቂውን የኦሮምኛ ቋንቋ ድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን አሳዛኝ አሟሟት ተከትሎ በመዲናችን አዲስ አበባ እና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች እና ወረዳዎች ላይ ኹከት ተነስቶ ለበርካቶች ሕይወት መጥፍት፣ የአካል መጉደል እና የንብረት ውድመት ሰበብ ሆኗል።

ድምፃዊ ሀጫሉ በኦሮሚያ ይደረግ ለነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከፍተኛ እገዛ ያደረገ፣ እንዲሁም በትግሉ ውስጥም እስከ መታሰር የደረሰ ሚና የነበረው በመሆኑ ግድያው በርግጥም እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በብዙዎች እንደሚታመነው ከጀርባው ለመጫወት የተፈለገ የፖለቲካ ጨዋታ ለመኖሩ ከገዢው ፓርቲም ይሁን ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች የሚቀርቡት ሙግቶችን እንደአብነት መጥቀስ ይቻላል። ይዋል ይደር እንጂ የፖሊስ የምርመራ ውጤት እና የፍርድ ቤት ብይን እንቆቅልሽ ለሆነው ግድያ መልስ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትር መንበርን ከተቆናጠጡ ከመጋቢት 2010 ጀምሮ ለበርካታ ጊዜ የሕዝብን በሰላም ወጥቶ መግባት ደህንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ ክስተቶች ተፈጥረዋል። ለአብነት ለመጥቀስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን በያዙ በጥቂት ወራት ውስጥ የአዲስ አበባ እና የአቅራቢያ ከተሞች ነዋሪዎች ድጋፋቸውን ለማሳያት በወጡበት ሰኔ 16/2010 ላይ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ ቦንብ ፈንድቶ የሰው ሕይወት ቀጥፏል፣ በርካቶችም ቆስለዋል። በዓመቱ ሰኔ 15/2011 ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር ኀይሎች ኤታማዦር ሹም ነበሩት ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና ጡረተኛው ሜጀር ጀነራል ገዛዒ አበራ በአዲስ አበባ እንዲሁም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አምባቸው መኮንን፣ የርዕሰ መስተዳድር አማካሪ እዘዝ ዋሴ እና የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ምግባሩ ከበደ ግድያን ተከትሎ በተፈጠረ ኹከት የበርካታ ሰዎችን ሕይወት አሳጥቷል፤ ለአካል ጉዳትም ዳርጓል። በጥቅምት 2012 ደግሞ በወቅቱ የኦኤምኤን ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ታዋቂው አክቲቪስት ጀዋር መሐመድ መንግሥት የግል ጠባቂዎቼን ሊያነሳብኝ ነው ማለታቸውን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ ለ86 ሰዎች ሕይወት (በቅርቡ የሚወጡ መረጃዎች ደግሞ ቁጥሩን 97 ያደርሱታል) መቀጠፍ ሰበብ ሆኗል።

ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የፖለቲከኞች፣ የታዋቂ ግለሰቦች ግድያዎችን ተከትሎ በሚነሳ ኹከት እና ግርግር የሰዎች ሕይወት መነጠቅ እን ለአካል ጉዳት መዳረግ በምንም መልኩ አግባብነት የለውም። ይሁንናነ በተደጋጋሚ እንደነዚህ ዓይነት ክስተቶች መከሰታቸው በአጠቃላይ የሕዝብ ደኅንነት እና መረጋጋት ላይ የራሱ ተጽዕኖ አሳርፏል፤ ብሎም ለኹከት እን ግርግር መነሻ ሲሆኑ በተደጋጋሚ ተስተውሏል። በዚህ ሁኔታ እስከመቼ መቀጠል ይቻላል?

ለማንም ግልጽ እንደሆነው የመንግሥት ዋነኛ ተልዕኮ የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ፣ የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት እንዲሁም የመንቀሳቀስ እና የመኖር መብታቸውን ማስከበር ለመሆኑ አስታዋሽ አያስፈልግም። ይሁንና ሕዝብ መንግሥት ግዴታውን መወጣት ባልተቻለበት ሁኔታ በራሱ ተደራጅቶ የመከላከል ብሎም የማጥቃት እርምጃ መውሰድ የሚጀምር ከሆነ የመንግሥትን ቅቡልነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባል። በመሰረቱ መንግሥት ከሕዝብ በሚሰበስበው ግብር እና ታክስ የሕዝብን ደኅነንነት ማረጋገጥ ካልቻለ የአገር ሕልውና አደጋ ውስጥ ይወድቃል። ይህ ጉዳይ በእጅጉ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ስትል አዲስ ማለዳ አጽንዖት ትሰጣለች።

በተለይ እንደ ድምፃዊ ሀጫሉ ያሉ ታወቂ ግለሰቦችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ አንድምታ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። የእነዚህን ታዋቂ ግለሰቦች እና ባለሥልጣናት ሕይወት ደኅንነት ዋስትና መስጠት ካልቻለ፣ ተርታ ለሚባለው የማኅበረሰብ ክፍልማ እንዴት አድርጎ ይችላል የሚል ትልቅ አንድምታ ያለው ጥያቄን ያስነሳል።

በርግጥ አደጋው ከደረሰ በኋላ በጥርጣሬ የተያዙ ሰዎች መኖራቸው ጥሩ ሆኖ ሳለ የፖለቲካ ጨዋታ አንዱ አካል እንዳይሆን መንግሥት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል፤ ተዓማኒነቱም በተግባርም መገለጽ ይኖርበታል። ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል ሙከራ አድርገዋል፤ ኤታማዦር ሹሙንም ገድለዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀርበዋል፤ ብይን ሲሰጥ ግን አላየንም። ለምን? የዚህን ጥያቄ መልስ መንግሥት ሊሰጥ ይገባል። አሊያም የዘገየ ፍትሕ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል የሚለውን ያረጋግጣል!

በተመሳሳይ ከድምፃዊ ሀጫሉ ግድያ እና ከሰሞሁ ኹከት እና ግርግር ጋር በተያያዘ ብዙ ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል። አንዳንዶቹም 48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደርጓል። ይህ መደረጉ በእውነቱ አዲስ ማለዳ ይበል የሚያሰኝ ነው ስትል ታበረታታለች። ነገር ግን የፍርድ ሒደቱ ያለምን ፖለቲካ ተጽዕኖ እና ጣልቃ ገብነት እንዲሁም በግልጽ ችሎት ፊት መካሔድ ይገባዋል ስትልም ታሳስባለች። የፍርድ ሒደቱን ለፖለቲካ ፍጆታ መዋል ፈጽሞ አይገባውም!

በሌላ በኩል በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ዴሞክራሲን በችሮታ ይሰጥ ይመስል የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ ሐሙስ፣ ሰኔ 25 በሰጡት መግለጫ በተለይ መገናኛ ብዙኀን በተመለከተ ትዕግሥታችን ተሟጣል የሚል አንድምታ ያለው ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል። መገናኛ ብዙኀንን በጅምላ የማሸማቀቂያ ማስጠንቀቂያ በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን ተገቢነት ይጎድለዋል ስትል አዲስ ማለዳ በአንክሮ ትገልፃለች።

በመሰረቱ መገናኛ ብዙኀንን የሚቆጣጠር ሕጋዊ አካል – የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን – ባለበት አገር፣ አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ማስጠንቀቂያ የሚሰጥበት ምክንያት አመክኗዊ አይደለም። ቅሬታ ካለ ለሚመለከተው አካል ማመልከት ካልሆነም በቂ መረጃ ይዞ መገናኛ ብዙኀኑን በፍርድ ቤት መክሰስ ሲገባ በአደባባይ ማስፈራራት ትላንት ኢትዮጵያ የነበረችበትን የመገናኛ ብዙኀን ጭቆናና አፈና መርሳት ተደርጎ ቢወሰድ ተገቢነት ይኖረዋል። በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ንግግሮች ወደ አምባገነንነት የመንደርድር አንድ ምልክት እንዳይሆኑ በጥንቃቄ ሊጠኑ ይገባቸዋል።
በመጨረሻም መንግሥት የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ዋስትና መስጠት ካልቻለ ሕዝብ በመንግሥት ላይ የሚኖረው መተማማን ከተሸረሸረ የአገሪቱን ደኅንነት አደጋ ላይ ከመጣሉም ባሻገር፤ ኀይል የሁሉም ነገር አማራጭ ወደ መሆን ይሔዳል። ይህም አገሪቱ ከዚህ ቀደም ወደ ነበረችበት አምባገነናዊ መንግሥት አሊያም የጎበዝ አለቆች አገር እንዳትሆን ያሰጋል። ስለሆነም መንግሥት ለሚወስዳቸው እያንዳንዱ እርምጃ ሕግን ብቻ መሰረት ያደረገ መሆን ይገባዋል። ሕግን በአግባቡ ማስፈጸም የሕዝብ ደኅነነት ዋስትና መሆኑ መታወቅ ይገባዋል ስትል አዲስ ማለዳ በአጽንዖት ታስታውሳለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here