የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የኮሮና ስርጭትን ለመግታት 5 ሺህ 456 ታራሚዎችን መፍታቱን አስታወቀ

0
563

የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በማረሚያ ቤቶች ሊከሰት የሚችል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመግታት በአገሪቱ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ 5 ሺህ 456 የህግ ታራሚዎችን በሁለት ዙሮች በይቅርታ መፍታቱን አስታውቋል። ይህም በማረሚያ ቤቶቹ ውስጥ ያለውን የታራሚዎች ቁጥር በግማሽ እንዲቀንስ እንዳደረገውም ተገልጿል።
ኮሚሽኑ በየማረሚያ ቤቶቹ የሚገኙ የህግ ታራሚዎቹን ከመፍታቱም በተጨማሪ የታራሚዎች ጭንቅንቅ በሚታይባቸው ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎችን ወደ ሌሎች አዳዲስ ማረሚያ ቤቶች በማዘዋወር የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚኝ የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ገረመው አያሌ ገልፀዋል። በዚህም መሰረት በመጀመሪያው ዙር አንድ ዓመት እና ከዛ በላይ የቀራቸው ታራሚዎች እንዲሁም በኹለተኛ ዙር ደግሞ ነብሰ ጡር እና አራስ እናት ታራሚዎች እንዲሁም ሶስት ዓመትና ከዛ በታች የቀራቸው ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ መደረጉ ታውቋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገራችን ስጋት ሆኖ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ምንም አይነት የበሽታው ምልክት በማረሚያ ቤቶች ያልተስተዋለ ሲሆን በየማረሚያ ቤቱ የሚገኙ የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች ወደስራ በሚገቡበት ወቅት የሙቀት ልየታ እንደሚደረግላቸው ተገልጿል። በተጨማሪም ከውጪ ወደማረሚያ ቤቶቹ የሚገቡ አዲስ ታራሚዎች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን በታራሚዎቹ ላይ የቫይረሱ ምልክት ቢታይ እንኳን የህክምና መስጫ ተቋማት መዘጋጀታቸውን እና ለጤና ባለሙያዎችን አስፈላጊው ስልጠና መሰጠቱም ታውቋል።
በሌላ በኩል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እና ለመቆጣጠር የሚያግዙ ቁሳቁሶች በማረሚያ ቤቶቹ ውስጥ እንዲመረቱ እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሸዋ ሮቢት፣ ዝዋይ እንዲሁም ድሬድዋ ማረሚያ ቤቶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች በመመረት ላይ እንደሚገኙም ታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here