ዲፕሎማቶች የአደጋ ስጋት ሊያድርባቸው እንደማይገባ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ

0
876

ባሳለፍነው ሳምንት የተከሰተውን የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ የተስተዋሉ ሁከት እና አለመረጋጋቶች በአሁኑ ወቅት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ በመመለሳቸው፤ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦች ስጋት ሊኖርባቸው እንደማይገባ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ አምባሳደሮች፣ የመንግስትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እና ገለፃ አድርጓል፡፡
በመግለጫውም የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በታዋቂው አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ መገደል ምክንያት ከባድና አሳዛኝ ጊዜያትን ማሳለፏል በመግለፅ ይህንንም የግድያ ሴራ ተከትሎ የተፈጠሩ ሁከት እና አለመረጋጋቶች በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ የሚባል ጉዳት ማስከተላቸውንም ገልፀዋል፡፡
ቢሆንም ግን በአሁኑ ወቅት አገሪቷ ወደቀደሞው ሰላም እና መረጋጋቷ በመመለሷ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ምንም አይነት ስጋት ሊያድርበት እንደማይገባ በመግለፅ አስፈላጊ የሆኑ ወቅታዊ መረጃዎችን መንግስት ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ በየጊዜው እንደሚያደርስ ገልፀው የተለመደው ትብብርና የአንድነት ስራም ሊቀጥል እንደሚገባ ቃል አቀባዩ አሳስበዋል፡፡
አምባሳደር ዲና በመግለፃው አያይዘውም በሀጫሉ ግድያም ሆነ ግድያውን ተከትሎ በተከሰቱ አለመረጋጋቶች ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ አካላት ህግን ባከበረ አካሄድ ጉዳያቸው እየታየ እንደሚገኝም ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ገልፀዋል፡፡
በመግለጫው ላይ የተሳተፉት የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባለትም በበኩላቸው በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው አደጋ የተሰማቸውን ከፍተኛ ሃዘን ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም ከኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ ጎን አገሮቻቸው እንደሚቆሙ ያረጋገጡት አባላቶቹ በአገሪቱ እየተከናወኑ የሚገኙ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን የመደገፍ ስራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here