ለዘመናዊ ችግር አሮጌ መፍትሔ

0
381

ከሰሞኑ በአዲስ አበባ እና አብዛኛው ኦሮሚያ ክልል ከተሞች ላይ ከተነሳው አለመረጋጋት እና መነሻውን በድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት ምክንያት ያደረገው ኹከት ከመንግስት የተሰጠው ግብረ መልስ እና ለማረጋጋት የተወሰደው እርምጃ ከዚህ ቀደሙ የተለዩ እንዳሆኑ በአመክንዮ የተቀመተበት ጉዳይ ሆኗል። በዚህ ጽሑፍም የደቡብ ምስራቅ እስያ የጉዞ ገጠመኞቹን ጸሐፊው አካቶ አሁን ካለው ነባራዊ አገራዊ ሁኔታ ጋር በማሰናሰልም ይዞ ቀርቧል።

የዓለም ታሪክ እንደሚያሳየን ወይም እየነገረ እንዳኖረን በየዘመናቱ የነበሩ ችግሮችን ዘመኑ በሚያዘው መፍትሔ ዕልባት እንዲያገኙ ማድረግ የተለመደ ጉዳይ ነው። ከኹለት ዓመታት በፊት ወደ ደቡብ ምሥራቅ እስያ አገር እና በርካቶች የኃጢአት ከተማ ብለው ወደሚጠሯት ታይላንድ አቅንቼ ነበር። እግረ መንገዴንም በፊሊፒንስ ዋና ከተማ ማኒላ የሦስት ቀናት ቆይታንም አድርጌ ከማኒላ ቅንጡ ከተማነት እስከ ፊሊፒንሳዊያን የአኗኗር እና የሕግ አከባበር እየተመለከትኩ ስደመም ነው ቆይታዬን ያጠናቀኩት።

እኔ ማኒላ በገባሁበት ወቅት ምክንያቱን በውል በማላውቀው መንገድ የማኒላ ቅንጡ አውራ ጎዳናዎች ለሰዓታት በዘለቀ ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲናጡ ነበር። ውብ ሕንጻዎቻቸው ግራ እና ቀኝ ተሰድረው በኩራት ሰልፈኛውን እንቅስቃሴ በአንክሮ የሚከታተሉ ይመስል ጸጥታ በዋጠው አኳኋን ነበር የሚታዩት።

ከአውሮፕላን ማረፊያ ወደማርፍበት ሆቴል የሚያደርሰኝ እስያዊው የአጭር ጊዜ ወዳጄ ታዲያ ስለሆነው ነገር በሚጎለዳደፈው እንግሊዘኛው ሲያጫውተኝ፣ ለቀናት የዘለቀ እንደነበር እና ግማሽ ቀን በሚዘልቀው የመጨረሻው ቀን የጎዳና ላይ አመጽ መገኘቴን ጠቅሶ፣ በቀደሙት ቀናት የነበረውን ውድመት እና ጉዳቶችንም በአጭር ቆይታዬ ነገረኝ። አያይዤም ከመንግሥት በኩል የተወሰደውን እርምጃም ጠየኩኝ። በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ግለሰቦች የመኖራቸውን እና የታሰበውን ያህል ጉዳት አለመድረሱንም አወጋኝ።

አሁን ዐይነ ሕሊናዬ ወደ አገር ቤት መሸምጠጥ ጀምሯል። ለመሆኑ የተጓደለ መሰረተ ልማትስ አለ ወይ ስል ጠየኩት። ምክንያቱም ኮሽ ባለ ቁጥር በኢትዮጵያ መብራት፣ ውሃ እና ኢንተርኔት አገልግሎት ደብዛቸው እንደሚጠፋ ስለማውቅ ነው። ጥያቄዬ ግራ የገባው አስጎብኝየ ‹‹ምን ማለትህ ነው? መሰረተ ልማትን በሚገባ ማዳረስኮ የመንግሥት ዋነኛ ተግባሩ ነው። ከተነሳው አለመረጋጋት ጋር ምንም የሚያገናኘው ጉዳይ የለም።›› ሲል መለሰልኝ።

በሺሕ የሚቆጠሩ ማይሎችን አቋርጨ የተገኘሁባት የደቡብ እስያዋ ዕንቁ ማኒላ፣ ትልቅ ነገር እያስተማረችኝ ነው። ልጓም ያላበጀሁለት አዕምሮዬ በሐሳብ ገስግሶ የኢትዮጵያን ጋራ እና ሸንተረር እያሰሰ አዲስ አበባ ላይ ከትሞ ከማኒላ ጋር ሊያወዳድር ይሞግታል። አሁንም ከታዳጊ አገራት ውስጥ የምትመደበው ፊሊፒንስ አመጽ ተነስቷል እና ኢንተርኔትን ዝጉ፣ መብራትም አታገኙም የሚል መንግሥት የላትም።

በከተማዋ በቆየሁባቸው ሦስት ቀናት ውስጥ ታዲያ በየተጓዝኩበት አገር አገሬን ይዤ ነው እና የምጓዘው ባየሁት እየተደንቅሁ ከአገሬ ጋር ሳወዳድር እና ሳበላልጥ ጉብኝቴን ራሴ ዳኛ ራሴ ፈራጅ ስሆን ነው የጨረስኩት። ከኹሉም ግን የገረመኝ የፊሊፒንስ መንግሥት በአደባባይ የሚቃወሙትን ቢችል በምክር ከፍ ካለም በአስለቃሽ ጭስ እንዲያው ከባሰ ለሰዓታት በቁጥጥር ስር አውሎ ኹለተኛ እንዳይለምድህ በሚል ወደ ቤቱ ይሸኘዋል እንጂ፣ በመሰረተ ልማት እና በተሻሻለው የመሰረታዊ ፍላጎት አንዱ በሆነው የኢንተርኔት አገልግሎት ሕዝብን አይቀጣም።

ከሦስት ቀናት በኋላ ወደ ታይላንድ ባንኮክ ተንቀሳቅሼ ከአግራሞት ወደ ሌላ አግራሞት ተሸጋገርኩ። ታይላንድ እና ፊሊፒንስ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ኹለት ትላልቅ ልዕለ ኃያላን ሲሳሳቡ አንገታቸውን ደፍተው በመሥራት ራሳቸውን ያቀኑ አገራት ናቸው። ባንኮክ አገሬው ሀብቱን የት ነው የሚያፈሰው በሚያስብል ደረጃ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ዜግነት ባላቸው ቱባ ቱጃሮች የተሞላች ድንቅ ከተማ ናት። ባንኮክ ያጋጠመኝ አስጎብኚ ታዲያ ቀላል እና ተግባቢ በመሆኑ ያሻኝን እየጠየኩ ሲመልስልኝ ደስ ያለውን ሲጠይቀኝ በደስታ ስመልስለት ነው የኹለት ሳምንት ቆይታችን የተጠናቀቀው።

በዚህ ወቅት ታዲያ አንድ ጥያቄ ከአስጎብኚዬ ደረሰኝ። በእርግጥ ጥያቄው መጀመሪያ ስንገናኝ ይቀርብልኛል ብዬ የጠበኩት ቢሆንም ዘግይቶ በመምጣቱ ለአፍታ ተገርሜ፣ ምላሼን በኩራት ሰጠኹት ‹‹ለመሆኑ ከየት አገር ነው የመጣኸው?›› የሚል ነበር። እኔ ታዲያ በኩራት እና በመጀነን ከምሥራቃዊ አፍሪካ ከጠያይሞች ምድር ጀግንነት አብሯቸው ከተወለደ እና ለጠላት መንበርከክን በታሪካቸው ከማያውቁት ኢትዮጵያ ከምትባል አንዲት ቅድስት ምድር የሚል ሰፊ ስብከት መሰል ምላሽ ሰጠሁ።

እሱም ተደምሞ ሲያዳምጠኝ ከቆየ በኋላ ወደ አንድ ስፍራ ወሰደኝ። በርካታ የልብስ እና የጫማ መሸጫ መደብሮች ወዳሉበት ነው። ‹‹እዚህ ቦታ በምታየው ነገር እና ያስገረመህ ነገር ካለ ጠቁመኝ። እኔ ግን ገና ከወዲሁ የሚያስገርምህን አውቄዋለሁ›› ሲል ቀድሞ ድምዳሜ ላይ የደረሰው አስጎብኝዬ ወደ ስፍራው ወሰደኝ። በመንገዶች ግራ እና ቀኝ የተሰደሩት መደብሮችን እየገረመምኩ ዐይኔ ያረፈበትን ጫማ እና ልብስም ገብቼ ስጠይቅ ተመልሼ ስወጣ ብዙም ሳልጓዝ በቁሜ እየቃዠሁ ይሆን እንዴ ስል የተጠራጠርኩበትን ነገር ተመለከትኩ።

በኹለት ተከታታይ የጫማ እና ልብስ መደብሮች መስኮት እና በር ላይ ‹‹ኪሳችሁን ከሌባ ጠብቁ›› የሚል በጠራ አማርኛ የተጻፉ ማስጠንቀቂያዎችን ተመለከትኩ። ለአፍታ ፈዝዤ ከቆምኩኝ በኋላ የአስጎብኝዬ ‹‹እንደገመትኩት ነው። ይህ እንደሚያስደንቅህ ገምቼ ነበር›› ሲል ነቃሁ። በተንቀሳቃሽ ስልኬ ምስል ካስቀረሁ እና ከማስጠንቀቂያው አጠገብ ፎቶ ከተነሳሁ በኋላ የመደብሩ ባለቤቶች ሐበሾች መሆን አለባቸው በሚል ግምት ወደ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ሰላምታዬን አስቀድሜ ገባሁ።

‹‹እንደምን አላችሁ›› ብዬ ስገባ የተቀበለኝ ግን የሀበሻ ጠይም ቆንጆ መልክ ሳይሆን ታይላንዳዊት እንስት ነበረች። ከኢትዮጵያ እንደመጣሁ እና ከውጭ የተለጠፈውን ማስጠንቀቂያ አይቼ እንደገባሁ ነገርኳት። ልብን በሚያቀልጥ ትህትና ‹‹ምን መሰለህ አብዛኛው ደንበኞቻችን ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ይህንም ተከትሎ ወደዚህ መንደር ለግብይት ሲመጡ በሌቦች ቦርሳቸው ይሰረቃል ወይም የኪስ ቦርሳቸው ይወሰዳል። በመሆኑም በራሳችን ቋንቋ እና በእንግሊዘኛ የተለያዩ ማስታወቂያዎችን ብንለጥፍም መሰረቃቸው አልቀነሰም። ስለዚህ ለምን በራሳቸው ቋንቋ ጽፈን አንለጥፍም በሚል አስበን እንዲህ አደረግን።

ለሚገጥመን ችግርም በአንድ መፍትሔ ብቻ ሙጭጭ ከምንል በየደረስንበት የሚመጣን አዳዲስ ሐሳቦች በመጠቀም መፍትሔዎችን መፈለግ እኛ ታይላንዳዊያን የምንታወቅበት እና በደንብ የምንኮራበት ጉዳይ ጸባያችን ነው›› ስትል አፍ የሚያስከፍት ንግግሯን ቋጨች። ለምን ያህል ጊዜ ትንፋሼን ውጬ እና አፌን ከፍቼ እንደሰማኋት ባላውቅም፣ አስደማሚ ጉዳዮችን በሰው አገር ሲያይ ወደ አገር ቤት መሸምጠጥ የማይሰለቸው አዕምሮዬ ግን ገና ድሮ አገር ቤት ቀድሞ መንግሥትን እየሞገተ ነበር።

ከዚች አንዲት ብላቴና እንዲህ አይነት አስደማሚ ንግግር እንዴት የአንድ አገር መንግሥት ያንሳል? ዘመኑ የደረሰበትን ምጡቅ ሐሳብ እየተመረኮዘ እንዴት አዳዲስ መፍትሔ አያፈልቅም? እንዴት አዲስ ወይን በአሮጌ አቁማዳ እያስቀመጡ ወደ ፊት መራመድን ያስባሉ? ከአንዲት መደብር ውስጥ ያገኘሁት ጥበብ እንዴት አገር እንመራለን ካሉ የአገሬ ፖለቲከኞች ውስጥ ማግኘት ሳልችል ቀረሁ? የሚሉ እና ልጓም ያልተበጀላቸው ሐሳቦች ጭንቅላቴን ወጥረውኝ ለረጅም ሰዓት እንዳፈጠጥኩባት ቆሜ ኖሮ ‹‹ጌታዬ ደኅና ነዎት? ጤናዎ ታወከ እንዴ?›› የሚለው የባለ መደብሯ ጥያቄ ነበር ያናጠበኝ።

የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራትን የመንግሥታት እና ሕዝቡን ብልህነት እና ጠበብት በሚገባም ባይባል በደረስኩበት ኹሉ ስታዘብ እና ሳደንቅ ነበር ጊዜዬ ያለቀው። የጉብኝቴ ጊዜ ይለቅ እንጂ ለእኔ ግን የዘለዓለም ትዝታ እና የማይቋጭ ውድድር መድረክ በጭንቅላቴ ውስጥ ፈጥሬ ነበር የተመለስኩት። እስኪ ይታያችሁ! ትንሽ ኮሽ ባለ ቁጥር እንኳን ከዓለም በአኗኗር ዘይቤ ሰፈር የቀየረውን ወንድማችንን ማግኘት እኮ ህልም የሚሆንባት አገር ድንቋ የታሪክ ምድር ላይ ነው ያለነው።

ምን ይሄ ብቻ! ያኔ ኋላ ቀር አስተዳደር ነበር ሰብዓዊ መብትን ይረግጥ ነበር። ዘመኑን የሚመጥን አገዛዝን አላሟላም ብለን ገፍትረን ከወንበሩ ያስነሳነውን መንግሥት አካሔድ በመድገም አገርን በአንድ አዙሪት ውስጥ የመክተት አባዜ አሁንም እየተንጸባረቀ ነው። በቀደሙት ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ ዓመታት ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት የኢንተርኔት አገልግሎት ሲዘጋ በከፊልም ቢሆን የገመድ አልባ አገልግሎት ይሠራ ነበር። ነገር ግን ይህ ጉዳይ ትክክል አይደለም ያለው የአሁኑ አመራር ደግሞ ብጥብጡ አይሏል እና ኢንተርኔት ብትፈልጉ የሞባይል ብትሹ ገመድ አልባ ምንም አይነት አገልግሎት አታገኙም ብሎ ጭራሽ ለዘመናዊው ችግር ያረጀ ያፈጀ መፍትሔ ለማግኘት ሲዳክር ይስተዋላል።

የወረርሽኙን መከሰት ታሳቢ ተደርጎ አካላዊ ንክኪን ለማስቀረት በቤት ውስጥ ሆነን ሥራዎቻችንን እንድናከናውን ቢነገረንም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ የኢንተርኔት አገልግሎቱም በመንግሥት አኩራፊነት ይሁን መልካም እርምጃ ሳይታወቅ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። መታወቅ ያለበት ጉዳይ ሕግ አይከበር ወይም የዜጎች ደኅንነት አይረጋገጥ እያልኩኝ አይደለም። የምልም ሰው አይደለሁም። ፍትህ ሊሰፍን እና ሰላማዊ አገርን መፍጠር ትልቁ ዓላማችን ሆኖ ሳለ ሰላምን ለማስፈን እና ፍትህን ለማረጋገጥ የተሔደበት መንገድ ግን ሕዝብን መረጃ ማግኘት መብትን በመንፈግ ወይም እርስ በእርስ የመገናኘት እና የመነጋገር መብትን ደፍጥጦ መሆን የለበትም።

ዘመኑ እኮ ሰዎች ቤታቸው ተቀምጠው ንግዳቸውን እና ኑሯቸውን የሚመሩበት፣ መሮጥ ሳያስፈልጋቸው ኪሳቸው ውስጥ ባለው ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ጉዳያቸውን የሚፈጽሙበት ጊዜ ላይ ነን። ታዲያ እንዴት ነው ዘመናዊውን ችግር በአሮጌ መፍትሔ ለመፍታት መዘጋጀት? ምን ያህልስ ያስኬደናል?

ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here