ያልተመለሱ ጥያቄዎች

0
1104

የታዋቂውን የሙዚቃ ሰው ሃጫሉ ሁንዴሳን አሳዛኝ እና አሰቃቂ ግድያን መነሻ በማድረግ በተለይ በመዲናችን እንዲሁም በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች፣ ዞኖች እና ወረዳዎች የተፈጠረው ስርዓት አልበኝነት፣ በመቶዎች ሕይወት ቀጥፏል፤ የአካል ጉዳትም አድርሷል። በርካታ የንብረት ውድመትም አስከትሏል፤ የግለሰብ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ ድርጅቶች ወድመዋል፣ በሰፊው ዝርፊያም ተካሒዷል። ጥቃቶቹ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ብሔርን መሰረት ያደረገ የሚመስል በሌሎች ቦታዎች ደግሞ የሃይማኖት ካርድ የተመዘዘበት መሆኑም ተስተውሏል። ኢትዮጵያዊው አብሮ የመኖር እሴት የት ገባ በሚያሰኝ መልኩ አሁንም ዜጎች ተወልደው ካደጉበት፣ ሀብት ንብረት ካፈሩበት ቀዬ እንዲፈናቀሉ መደረጉ በእጅጉ ያሰዝናል፤ አንገት ያስደፋል! እስካሁንም ድረስ አንዳንዶች በቤተ ክርስቲያን ሌሎች ደግሞ በትምህርት ተቋማት ውስጥ ተጠልለው ‘‘የመንግሥት ያለህ!’’ የሚል ጆሮ ዳባ ልበስ የተባለ የሚመስል ጩኸታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።
መጠነ ሰፊ የሆኑት እነዚህ ጥቃቶች የተፈጸሙት በተቀናጀ እና በተናበበ በሚመስል መልኩ በተመሳሳይ ቀናት መሆናቸው ሲሆን አገር የማፍረስ አካሔድ መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ ሆቴሎች፣ ፋብሪካዎች፣ ትምህርት ቤት፣ የአበባ እርሻዎች የጥቃቱ ኢላማዎች ነበሩ። ይህም ሆኖ ብዙዎች የዘገየ የሚሉትን መንግሥት እርምጃ ባይወሰድ ኖሮ የበለጠ እልቂት፣ የበለጠ ጥፋት ይደርስ ነበር ብለው ያምናሉ። ይሁንና ብዙዎች መልስ ያላገኙለትን ጥያቄዎች መጉረፋቸው አሁንም አላባራም። ለምን ሲሉም ማባሪያ የሌለው ጥያቄያቸውን እያዘነቡ ይገኛሉ።
ለመሆኑ መንግሥት ከወዴት ነበር ብለው ከሚጠይቁት ጀምሮ፣ በተለይ አሁን መንግሥት ጥፋቱን አድርሰዋል፣ አቀነባብረዋል፣ መርተዋል በሚል በአገር ማፍረስ ጠርጠሮ የያዛቸው ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ተነሱበት የተባሉትን አገርን የመማፍረስ፣ ሕዝብን እርስበርስ የማባላት ተልዕኮ ቀደም ብሎ ካወቀ የመከላከል እርምጃውንም ለምን ቀድሞ አልወሰደም ሲሉ ይሞግታሉ። ጅብ ከሔደ ውሻ ጮኸ ምን ሊፈይድ ሲሉ ደግመው ይጠይቃሉ፤ ‘ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ፣ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ’ በሚል መሳለቅ ጭምር ይሞግታሉ። ሌሎች ደግሞ መንግሥት እርምጃውን ያዘገየው ጥቃት አድራሾች ፍርድ ቤት ከሶ ሲያቆማቸው ማስረጃ ለማቅረብ እንዲያመቸውን ነው ሲሉም ተሳልቀዋል። የብዙዎች ጥያቄ ግን መንግሥት እስከ መቼ ድረስ ነው የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ቀዳሚ ሥራውን በበቂ ኹኔታ የሚወጣው ነው።
በርግጥ አንዳንዶች መንግሥት ለብሔር አክራሪ ኀይሎች የሰጠው መጠነ ሰፊ ታጋሽነት ዋጋ ቢያስከፍለውም፣ አክራሪ ብሔርተኞችን እርቃናቸውን አስቀርቷቸዋል ሲሉ ከነድክምቱ የመንግሥት አካሔድ ደግፈዋል። በርግጥ መንግሥት ብልሀት የተላበሰ የጥፋት መከላከል እና የመመከት ሥራ ባያካሒድ ኖሮ፣ ጥፋቱ አሁን ከደረሰው በብዙ እጥፍ ከመሆን አልፎ ምናልባትም አገር ማፍረሱ እውን ይሆን ነበር ሲሉም ያክለሉ።
የሆነው ሆኖ ቋሚ መንግሥት ባለበት፣ የጸጥታና ሰላም አስከባሪ አካላት ባሉበት እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ እና አስፈሪም አሳፋሪም ድርጊት መፈጸሙ ለብዙዎች ያልተፈታ እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here