ኢንጅነር ይልቃል አንድ ሳምንት ከጠበቃቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙ ተደርገዋል

0
863

የኢትዮጵያውያን አገር ዐቀፍ ንቅናቄ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ሐሙስ ምሽት 12 ገደማ ሰኔ 26/2012 ከመኖሪያ ቤታቸው በፌዴራል ፖሊስ አባላት ከተወሰዱ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በጠበቃቸው እና በቤተሰቦቻቸው እንዳይጠየቁ መደረጉን ጠበቃቸው አዲሱ ጌታነህ ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።
ኢንጅነር ይልቃል ሰኔ 26/2012 ሐሙስ ምሽት አራት ኪሎ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በፖሊስ መወሰዳቸውን ጠበቃቸው አዲሱ ጌታነህ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የኢንጅነር ይልቃል ጠበቃ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ኢንጅነሩ ለአንድ ሳምንት ከሌሎች እስረኞች በተለየ ሁኔታ የቤተሰቦቻቸውን ጥየቃ እና ከቤተሰቦቻቸው የሚመጡ ልብስና ምግብ እንዳይገባላቸው ተከልክለው መቆየታቸውን ጠበቃቸው ገልጸዋል።

የኢንጅነሩ ጠበቃ ለአዲስ ማለዳ እንደጠቆሙት በጣቢያው የታሠሩ እስረኞች ቤተሰቦች በቦታው ተገኝተው ለእስረኛ ቤተሰቦቻቸው ልብስና ምግብ ለማቀበል እንዲሁም ለመጠየቅ ቢሞክሩም እንዳልተፈቀደላቸው እና በፖሊስ ከአካባቢው ሲባረሩ እንደነበር አስታውሰዋል። በተቃራኒው እስረኛ ቤተሰባቸውን ሊጠይቁ ከተሰበሰቡ ሰዎች ውስጥ የጀዋር ቤተሰቦች በአደባባይ በፖሊስ “የጅዋር ቤተሰቦች ግቡ” ተብለው ለእነርሱ ብቻ ልዩ ጥየቃ እንደተፈቀደላቸው አዲሱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የኢንጅነሩ ቤተሰቦች እና ጠበቃ የይልቃልን እስር ሁኔታ አለማወቃቸው እና በአካል መጠየቅና እንደ ምግብና ልብስ የመሳሰሉ አስፈላጊ ነገሮችን መስጠት መከልከላቸው ስላሳሰባቸው ጠበቃቸው ጉዳዩን ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር) ማሳወቃቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የኢንጅነሩ ቤተሰቦች የኢንጅነሩን የእስር ሁኔታ ባለማወቃቸው እና ስጋት ውስጥ በመግባታቸው ለኮሚሽነሩ ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው እና ኮሚሽነሩ በቀረበላቸው ጥያቄ መሰረት ይልቃል ከሚገኙበት ማረሚያ ቤት በመገኘት የአንጅነሩን የእስር ሁኔታ በአካል አግኝተው ማረጋገጣቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ዳንኤል ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ኢንጅነሩ ያሉበት ሁኔታ መልካም መሆኑን ከራሳቸው ከኢንጅነሩ አንደበት ቢያረጋግጡም፣ ኮሚሽነሩ በቦታው እስከተገኙበት ሰዓት ድረስ ለኢንጅነሩ ልብስ፣ ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች እንዳልተሟሉላቸው ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም ለኢንጅነሩ የቤተሰብ ጥየቃ፣ ምግብና ልብስ እንዲፈቀድላቸው እና ከጠበቃቸው ጋር እንዲገናኙ እንደሚደረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግረው ለይልቃል አስፈላጊ ነገሮች ከቤተቦቻቸው እንዲቀበሉ እንዲደረግ መስማማታቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ በቦታው በመገኘት ባደረጉት ማግባባት ኢንጅነሩ በታሰሩ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሐምሌ 3/2012 የኢንጅነሩ ወንድም ኢንጅነሩን በአካል እንዳገኟቸው እና ምግብና ልብስ እንዳስገቡላቸው ጠበቃው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ነገር ግን ጠበቃቸው ኢንጅነሩን ማግኘት አለመቻላቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ዳንኤል እንደሚሉት በአገሪቱ የታወጀው አስቸኳይ አዋጅና ደንብ በኮቪድ-19 ምክንያት የእስረኞችን በቤተሰብ መጠየቅ እንደሚከልክል ገልጸው፣ የጤና ችግር ያለባቸው እስረኞች ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ከቤተሰቦቻቸው እንደሚገቡላቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገራቸውን ጠቁመዋል።

ኢንጅነር ይልቃል ሰኔ 26/2012 ሐሙስ ምሽት ከመኖሪያ ቤታቸው በፖሊስ ተይዘው በተወሰዱ በማግስቱ፣ መኖሪያ ቤታቸው ፍተሻ እንደተደረገበት ጠበቃቸው ተናግረዋል። ቤታቸው በተፈተሸበት ጊዜ በቤት ውስጥ የነበረች የቤት ሠራተኛ የኢንጅነሩ የፖለቲካ ድርጅት ማህተም እና ሌሎች ለድርጅቱ የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች በፌዴራል ፖሊስ አባለት መወሰዳቸውን እንዳረጋገጠችላቸው አዲሱ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

ኢንጅነሩ ቅዳሜ ሰኔ 27/2012 ፍርድ ቤት ቀርበው በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉበት እና የተከሰሱበትን ምክንያት መስማታቸውን ጠበቃቸው ተናግረዋል። ጠበቃው እንደሚሉት የኢንጅነሩ ክስ ብጥብጥ በማስነሳት ለሰው ሕይወት መጥፋት እና ለንብረት መውደም ምክንያት በሚል መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። ይልቃል በቀረበባቸው ክስ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው እንደተፈቀደ እና ለሐምሌ 11/2012 ቀጠሮ እንደተሰጣቸው አዲሱ አያይዘው አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here