አዲስ አበባ የሚገቡ ምርቶች በመቆማቸው የአትክልት ዋጋ ከዕጥፍ በላይ ጨመረ

0
562

ከተለያዩ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ከተሞች እና አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ ይገቡ የነበሩ የአትክልት ምርቶች በከፍተኛ መጠን በመቀነሳቸው በአዲስ አበባ ከተማ የአትክልት ዋጋ ከዕጥፍ በላይ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ታወቀ።

አንዳንድ ነጋዴዎች ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው ምርቶች ከሚመጡበት ስፍራ ላኪዎች ከሰሞኑ ግርግር ጋር በተያያዘ አድማ በማድረጋቸው መሆኑንም አስታውቀዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ከሻሸመኔ ይመጡ የነበሩ ምርቶች ወደ አዲስ አበባ እስከ ሐምሌ 15 ድረስ አይገቡም መባሉን ተከትሎ፣ የምርት እጥረት እየተከሰተ መሆኑን ነጋዴዎቹ ተናግረዋል።

ከዛ በተጨማሪ በአንዳንድ ገበያ ማእከል ሲገበያዩ የነበሩ ነዋሪዎችን አዲስ ማለዳ እንዳነጋገረቻቸው፣ ግርግሩን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ጭማሪ እየተስተዋለ መሆኑን እና ከዚህ ቀደም አንድ ኪሎ ሽንኩርት በ32 ብር ይገዙ የነበረውን አሁን በ50 ብር፣ የባሮ ሽንኩርት 40 ብር የነበረው 50 ብር፣ ፎሶሊያ 37 የነበረው በ50 ብር እንዲገዙ እየተገደዱ መሆኑን አስታውቀዋል። ከዛም በተጨማሪ 10 ብር የነበረው አንድ ኪሎ ድንች ደግሞ አንዳንድ አካባቢ እንደሌለ እና አንዳንድ ቦታ እስከ 20 ብር እየተሸጠ መሆኑን፣ ቆስጣ ከዚህ ቀደም 20 ብር ይሸጥ የነበረው 50 ብር መግባቱን ነጋዴዎቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ይህም የሆነበት ምክንያት ብለው ነጋዴዎቹ እንደሚናገሩት ከሆነ፣ አሁን አገሪቷ ግርግር ላይ ስለሆነች እና ምርቶች እንደ ከዚህ ቀደሙ እንደልብ ስለማይገባ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ እንደ ከዚህ ቀደሙ የነበሩ ምርቶች በገበያው ላይ እንደማይስተዋሉ እና ለአብነት ካሮት እና ቀይ ስር የመሳሰሉት ምርቶች አብዛኛውን ሱቆች ላይ እንደሌሉ አዲስ ማለዳ ታዝባለች።
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አልቃድር ሑሴን ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከሆነ፣ ምርቶቹ ላይ ዋጋ ለውጥ መኖሩን ታዝበናል። ነገር ግን የምርት እጥረት እንዳለ የምናውቀው ነገር የለም። ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሚሠራው የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዳንኤል ሙኤሳ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ሌሎች የመሠረታዊ ፍጆታዎች ሳይጨምር ነገር ግን የሽንኩርት የዋጋ ውድነት የተከሰተው የአቅርቦት እጥረት በመኖሩ ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በተያያዘም ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት የሽንኩርት እጥረት ሲኖር ከሱዳን ይመጣ የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን አሁን ያንን ማድረግ እንዳይቻል እንቅስቃሴ መገደቡ ምክንያት እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ዳንኤል ከሽንኩርት ውጪ የሆኑት ምርቶች ላይ የዋጋ ንረቱ የታየበት ምክንያት ሲያስረዱ ‹‹እኛ እንደታዘብነው ከሆነ ግርግሩን ምክንያት ያደረገ በመሆኑ እና አንዳንድ ነጋዴዎች የምርት መደበቅ ገና ለገና ሊጠፋ ይችላል በማለት እየቀነሱ የማውጣት እና ምርት የለም የማለት ነገር እንዳለ አይተናል።›› በማለት ለአዲስ ማላዳ አስረድተዋል።
ነገር ግን እነርሱን የመለየት ሥራ እየሠራን ነው ያሉት ዳንኤል፣ የዋጋ ንረቱ እንደማይዘልቅ እና በሳምንት ውስጥ ይስተካከላል ሲሉ ለአዲስ ማላዳ ተናግረዋል።
ምርቶች ይጠፋሉ በሚል ፍራቻም ኅብረተሰቡ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት በመነጋገር ከፍጆታ በላይ የሆኑ ምርቶችን በስፋት በመግዛቱም በምርቶች ላይ ያጋጠመው የዋጋ ጭማሪ እና የአቅርቦት እጥረት ምክንያት መሆኑንም አዲስ ማለዳ ለመታዘብ ችላለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here