በጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

0
774

የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል ከተከሰተው ኹከት ጋር በተያያዘ ከኹለት ሳምንት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ጅዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባ ላይ ፍርደ ቤት የ13 እና የ11 ቀናት ተጨማሪ የምርምራ ጊዜ ፈቀደ።
ፖሊስ በዋነኝነት ብሔርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ግጭት እንዲቀሰቀስ በማድረግ ተጠርጣሪዎቹ የነበራቸውን ሚና ጠቅሶ፣ በተለይም ጃዋር መሐመድ የአርቲስቱን አስከሬን ከቤተሰቦቹ ነጥቆ ወደ ኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በኃይል ለማስገባት መሞከራቸውን በመጥቀስ፣ በሁኔታው የአንድ ፖሊስ አባል ሞትና ሦስት ሰዎች ቁስለት መከሰቱን አስረድቷል። ይህ ሊሆን የቻለው ተጠርጣሪው በሰጡት ትዕዛዝ መሆኑን ፖሊስ አመላክቷል። በተጨማሪም የስልክ ልውውጥ በማድረግ የአመጽ ቅስቀሳ ሲደርግ እንደነበር በመግለጽ መርማሪ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ መረጃ ማሰባሰቡን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።
የተጠርጣሪውን የአመጽ ፅሪ በመቀበል የ81 ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና ጃዋር በሚመራው ቡድን ስር በቁጥጥር ስር የዋሉ የጦር መሣሪያዎች በሙሉ ሕገ ወጥ መሆናቸውን ፖሊስ ገልጿል። በተጨማሪም 14 የምርመራ ቡድን ተዋቅሮ ተጨማሪ ማጣራት እያደረገ እንደሚገኝ መርማሪ ፖሊስ ጠቁሟል። እንዲሁም ያልተያዙ ግብረ አበሮች መኖራቸውን ያመላከተው መርማሪ ፖሊስ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል።
ጃዋር መሐመድ በበኩላቸው ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ገልጸው፣ ጉዳዩ ድራማ ነው ሲሉ መናገራቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። ተጠርጣሪው አክለውም የሚበጀው ቁጭ ብሎ መነጋገር ነው ሲሉ ለፍርድ ቤቱ መግለጻቸውም ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here