መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳፍትሕ - ኮቪድ 19 እና ያለፉት ወራት

ፍትሕ – ኮቪድ 19 እና ያለፉት ወራት

የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን በተለያየ መልክ ሲያስጨንቅ የፍትሕ ጉዳይም አንዱ ነው። በአዘቦቱም ፍትሕ ትዘገያለች እየተባለች የምትወቀስ ስትሆን፤ በወረርሽኙ ምክንያት ደግሞ የተጀመሩ ክሶች ተቋርጠዋል፣ ሊጀመሩ የሚገባም ሳይጀመሩ ውለው አድረዋል። ወረርሽኙ በሌላው ዘርፍ እንደፈጠረው ሁሉ በዚህም ከፍተኛ ክፍተትን ሊፈጥር ችሏል።
የሕጻናትና የሴቶች ጉዳይም አንዱ ነው። በተለይም ከአንድ መቶ በላይ ሕጻናት፣ ሴቶችና ወንዶችም ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል የሚለው ጉዳይ የሕግና ፍትሕን ነገር ቀስቅሷል። በዚህ ላይ መረጃዎችና ቁጥሮችን በሚመለከት የተለያዩ ውዝግኖች ሲነሱም ቆይተዋል። ይህን በሚመለከት እንዲሁም ባለፉት ሦስትና አራት ወራት ስለደረሱ ጥቃቶች፣ መረጃዎችና መረጃዎችን ስለሚያቀብሉ ምንጮች እንዲሁም ስለተወሰኑ ውሳኔዎች የተለያዩ ባለሞያዎችንና የሚመለከታቸውን በማነጋገር፣ የቀደሙ በሚመለከታቸው የተሰጡ ሐሳቦችንም በማውሳት፣ የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

ክስተት ብቻ አይደለም!
በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ ልዩ ሥሙ ኮተቤ መሳለሚያ አካባቢ ነው። የ11 ዓመቷ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ጽናት (ሥሟ የተቀየረ) ታሪክ ከዚያ የተገኘ ነው። አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ግንቦት 29/2012 በወጣው 83ኛ ዕትሟ ይህን ታሪክ አጋርታ እንደነበር ይታወሳል። እነሆ ዳግም ልናወሳው ነው።
ጽናት በትምህርቷ ጎበዝ፣ የቤተቧን ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ በለጋ እድሜዋ ተደርታ በታዛዥነት የምትኖር፣ ለቤቱም ሦስተኛ ልጅ ናት። ታድያ የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በቤት ውስጥ እንድትውል ሲያስገድዳት፣ ለቤተሰቧም ሲታገሉት በቆዩት ኑሮ ላይ ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› እንዲሉ ፈተና የጨመረ ጉዳይ ነው። ሌላው ዱብ እዳ እስኪታከል።
እንዲህ ሆነ፣ ወላጆቿ ጠባብና አነስተኛ ከሆነ ጊቢያቸው አንድ ጥግ ላይ ከመውደቅ መለስ ያለች ክፍል ሠርተው ለኑሯቸው መደጎሚያ የሚሆን ኪራይ የሚያገኙበት አንድ በ30ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ ያለ ወንደ ላጤ ‹መምህር› አከራይተዋል። ይህ ግለሰብ ታዲያ በተደጋጋሚ ጽናትን አሳቻ ሰዓት አድብቶ በመያዝ ያልተገባ ስፍራዎች ላይ ይነካት ነበር። ጽናትም በልጅ አዕምሮዋ እና በለጋ ልቧ ፍራቻ እና ጥላቻ ለዚህ ግለሰብ ማሳደር ጀመረች።

የጊቢያቸው ተከራይ የሆነውን ይህን ሰው ስታይ ከርቀት በሩጫ ማምለጥ፣ ጊቢ ውስጥ በድንገት ስትመለከተው የምትገባበት መጥፋት እና አንዳንዴም ከወላጆቿ ወደ ተከራይ ቤት መልዕክት እንድታደርስ ስትታዘዝ በእምቢተኝነት መመለስ የጽናት ተግባራት ነበሩ። ሁኔታዋን ልብ ያለላት ግን የነበረ አይመስልም።
ቀናት እየተተካኩ ጊዜው ሄደ፣ በአንድ ቀን ግን ግለሰቡ ከውጭ ቆይቶ ወደ ቤቱ በሚገባበት ወቅት ጽናት እና ታላቅ እህቷን በቤት ውስጥ መኖራቸውን ተመለከተ። በዚህ ጊዜም በፍጥነት ወደ ተከራየው መኖሪያ ክፍል በመግባት በልብስ የተሞላ ላስቲክ ይዞ ወደ አከራዮቹ ቤት በመምጣት ለጽናት እህት የሚሠራው ሥራ ስላለው በአቅራቢያቸው ወዳለው ልብስ ሰፊ ጋር በመሔድ የታጠቡ ልብሶቹን እንድታስተኩስለት ይልካታል።

በዚህ ወቅት ታዲያ ጽናትን በግላጭ ያለ ገላጋይ ያገኘው መምህር፤ መምህርነቱ ሳያግደው፣ ልጅነቷ ሳያሳሳው፣ ሰውነትን ፍጹም ዘንግቶ ገና ሮጣ ያልጠገበችውን፣ አጥንቷ ያልጠነከረ አዳጊን በጠንካራ ጥፊ ራሷን እንድትስት ካደረገ በኋላ ለእንስሳዊ ፍላጎቱ የወሲብ ማርኪያ አደረጋት።
ከደረሰባት አቅል የሚያስት ጥፊ እና መደፈር ጉዳት ጋር ተደማምሮ ረጅም ሰዓት ራሷን ስታ ቆየችው ጽናት፣ ታላቅ እህቷ ከተላከችበት ስትመለስ ነው በደም አበላ ተውጣ መሬት ላይ ተዘርራ ያገኘቻት። በድንጋጤም ጩኸቷን አሰማች።

ጽናት በጎረቤት እርዳታ ወደ ሕክምና ተቋም ተወስዳ ክሊኒክ አልጋ ላይ ነቃች። የሆነችውንም በጭንቀት፣ ድንጋጤ እና ሕመም ውስጥ ሆና በድንገት ተጠርተው እየተጣደፉ የሕክምና ተቋሙ ውስጥ ለተገኙት እናቷ ነገረቻቸው። ነገር ግን ጽናት መናገር የቻለችው በተከራዩ ሰው ከፍተኛ የሆነ ድብደባ እንደደረሰባት እንጂ የመደፈሯን ግን መናገር አልቻለችም። ይሁን እንጂ በጤና ባለሙያዎች ዘንድ ግልጽ ምልክቶች በማየታቸው በምርመራ መደፈሯን ለቤተሰቦቿ አረዷቸው።

ይህን ታሪክ አዲስ ማለዳ በባለታሪኳ ቤት ተገኝታ የሰማችና የተመለከተችው ነው። ይህም የሆነው በጽናት ላይ ጥቃቱ ከደረሰባት ከአንድ ወር በላይ ካለፈ በኋላ ነው። እናም የጽናት ጉዳት በዐይን የሚያስታውቅ ነው። የልጅነት ለዛዋ እና የፊት ጸዳሏ ደብዛው ጠፍቷል፣ የልቧ ስብራት ከውስጧ አልፎ ገጽታዋ ላይ በጉልህ ተጽፎ ይነበባል።
በጊዜው አዲስ ማለዳ እንዲህ ስትል ነበር ያሰፈረችው፣ ‹‹በእናቷ ጉያ ተቀምጣ ከበዛው እና ድምጽ አልባው እንባዋ ጋር እየታገለች በተወሰኑ ደቂቃዎች ውስጥ አንድ ቃል ትወረውርና ተጨማሪ ጥያቄ ለመጠየቅ ስንሞክር በዛው ቅጽበት ድንጋጤ ውስጥ ገብታ ዝም ትላለች። እንባዋ ግን አሁንም ይፈሳል፣ መቼም ማቆሚያ ያለው አይመስልም። ጉዳዩን በሕግ የተያዘ ቢሆንም ቅሉ ጉዳት አድርሷል የተባለው ግለሰብ ግን ከዛን ቀን በኋላ ጨርቄን ማቄን ሳይል ከተሰወረ እና ፖሊስም ግለሰቡን ማደን ከጀመረ ዋል አደር ብሏል።››
እናትም ‹‹ልጄን ቅስሟን እንደሰበረው የረገጠው ኹሉ ይጨልም፤ እኔ ፈጣሪን አምናለሁ ልጄን እንዲህ በቁሟ የገደላትን ሰው እንደሚበቀልልኝ አልጠራጠርም›› አሉ። እንባቸው ሳያባራ፣ በተሰበረ ልብና አቅም በተነጠቀ መንፈስ ሆነው።

ጽናት ከደረሰባት አካላዊ ጉዳት የተነሳ በትክክል መቀመጥ እንደሚቸግራትና ወደ መጸዳጃ ቤት ስትሄድም ሕመሟን ስለምትፈራ እንደምትጨነቅ ገልጻለች። ከዚህ በአካል ከሚሰማት ሕመም ባሻገር የተረጋጋ እንቅልፍ አትተኛም፣ ደርሶ ድንገት እንደመባነን ብላ መለስ ማለቷም የተለመደ ሆኗል። የደረሰባት ጥቃት የጽናትን ተስፋ ሊነካ ባይችልም፣ ዓለምን ልትጋፈጥና ልትሞግት በማትችልበት እድሜ እንቅፋት ሆኖ መትቷታል።

ፍትህ እንዴት ሰነበተች!
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዓለምን በብዙ መልኩ መፈተኑ በተደጋጋሚ የተባለ ጉዳይ ነው። በየዘርፉም ያሉ ባለሞያዎች ወረርሽኙ ስላስታጎለው መደበኛ ሥራዎች ብዙ የሚሉት አለ። ታድያ የፍትሕ ጉዳይም ከዚህ ወገን ሆኖ የሚቃኝ ነው። የፍትሕ አሰጣጥና የሕግ አፈጻጸም ባለፉት ሦስትና አራት ወራት ገደማ እንዴት ነበሩ?
እንቁ አስናቀ በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሴቶችና ሕጻናት ጉዳዮች ዳይሬክተር ናቸው። እንደ ማንኛውም ዘርፍ የፍትህ ጉዳይም ተጽእኖ ደርሶበታል ይላሉ። ይህ የሆነው ሰዎች እንደ ወትሮው ወጥቶ ለመመስከርና ጉዳያቸውንም ለመከታተል ይፈራሉና ነው። እንደ እንቁ ገለጻ በተለይ ቫይረሱ በኢትዮጵያ መገኘቱ የተረጋገጠበት ሰሞን፣ መጋቢትና ሚያዝያ ወር ላይ አስቸጋሪ ነበር። ያም በሥራው ላይ ተጽእኖ አሳድሯል።

ደረጄ ወዳጆ ለ30 ዓመታት በሕግ ሥራ ላይ ቆይተዋል። በፌዴራልና በክልል አማካሪና ጠበቃ በመሆን አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። አዲስ ማለዳ ከደረጄ ጋር ባደረገችው ቆይታም ይህን ጉዳይ አንስታ ነበር። ወረርሽኙና እርሱን ተከትሎ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፍትህ አሰጣጥና ሕግ ስርዓት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ ምንም ጥርጥር የለውም ይላሉ። በክርክር ላይ የነበሩና የተቋረጡ ጉዳዮች መኖራቸውን አያይዘው ጠቅሰዋል።

በግል ለሚሠሩ የሕግ ባለሞያዎችም ባለፉት ወራት ሥራ ላይ እንዳልነበሩ አውስተው፣ በአንድ በኩል ከድርጅት ጋር በሌላ በኩል ደግሞ ከግለሰቦች ጋር የተገናኘ ሥራ ያላቸው አሉ ብለዋል። ከተወሰኑ ጉዳዮች በቀር አብዛኞቹ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲቆዩ በመደረጋቸውም፣ በቀጠሮ ሲንከባለሉ የነበሩ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ጊዜ እንደጨመረ ነው የጠቀሱት።
ምንም እንኳ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ቢሆንም፣ ‹የዘገየ ፍትሕ የተከለከለ ፍትሕ ነው› የሚለውን የባህር ማዶውን ብሂል ያነሳሉ። አያይዘውም ‹‹አንዳንዴ ፈጣን ፍትሕ የሚፈልጉ ሰዎች ጉዳያቸውን ትተውና ተስፋ ቆርጠው እንደሞተ ነገር የሚያዩበት ጊዜ አለ። አንዳንዶችም ለችግር ተዳርገዋል። ንብረት ክፍፍል፣ በጋብቻና በውርስ የተነሳ ብዙ ጉዳይም አለ።›› ሲሉ ያስረዳሉ።
በጊዜ ሂደትና ርቀት ወራሽ መሆን የሚችል ሰው መብቱን የሚያጣበት ሁኔታም አለ ይላሉ። በይግባኝ ታስረው የተቀመጡ ጉዳዮችም እንደዛው በወረርሽኙ ምክንያት አፈጻጸም ሳይደርሱና ውሳኔ ሳያገኙ ቆይተዋል። ከኹለት የተለያዩ ሴቶች የወለደና ሕይወቱ ያለፈ ሰው የውርስ ጉዳይን በሚመለከት ይህን እንደምሳሌ ጠቅሰዋል።

‹‹ሕይወቱ ያለፈው ከኹለት ሴቶች የወለደ ሰው ነው። አንደኛዋ ትልቅ ሀብት ይዛ ስትንቀሳቀስ፣ ሌላዋ ከሰውየው የወለደችው ሴት ግን ልጆች ይዛ ለችግር ተጋልጣ ነው ያለችው። ለትምህርት ቤት ክፍያ እንኳ እጥታለች።›› በማለት እንደማሳያም ጠቅሰዋል።

ታድያ የፍትሕ መዘግየትና መጓተት ነገር በኮሮና ብቻ የሆነ ነው ወይ? አይደለም። እንቁ መረጃና ማስረጃ ከመሰብሰብና የክስ ሂደትን ከመከታተል ጀምሮ ለዚህ የተለያየ ምክንያት እንዳለ ሲጠቅሱ፣ ደረጄም በበኩላቸው ከኮሮና በፊትም ፍትሕ ይዘገይ እንደነበር ሳያነሱ አልቀሩም። ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው የሆነው።›› ባይ ናቸው። በተለይም የዳኛ ጥራትም ብዛትም አለመኖሩ፣ ሥራውም ብዙና አሰልቺ ከመሆኑም የተነሳ፣ ከክልል ሳይቀር በይግባኝና በሰበር የሚመጡ መዝገቦች በመኖራቸውም፣ በአግባቡ ለመሥራትና የቀረበላቸውን ፋይል በጥልቀት ለማየት እንኳ አይችሉም ሲሉም ያለውን ችግር ያስረዳሉ።

ስለሕጻናትና ሴቶች
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ዓለም ላይ መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል አንደኛውና ቀዳሚው የቤት ውስጥ ጥቃትን የሚመለከት ነበር። ይህም ጉዳይ በተመሳሳይ በኢትዮጵያም ተነስቷል። ምንም እንኳ በወረርሽኙ ምክንያት በኢትዮጵያ እንዲተገበር የተወሰነው የእንቅስቃሴ ገደብ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴዎችን የገታ ባይሆንም፣ በቤት ውስጥ አንዲውሉ ግድ የሆነባቸው ሰዎች በተገኙባቸው ቤቶች ግን የቤት ውስጥ ጥቃት ሊብስ እንደሚችል መገመትም ቀላል ነው።
አዲስ ማለዳም በሴቶች ላይ ላይ የሚሠሩ ባለሞያዎችን ስታናግር እነዚህ ችግሮች አሉ ሲሉ ማስረዳታቸውን በተለያየ ርዕስ ያወጣቻቸው ዘገባዎች ያስረዳሉ። ከላይ መግቢያ ላይ የተነሳው እውነተኛ ታሪክም አንዱ ማሳያ ነው።

እንደሚታወቀው ሕግና ፍትሕ በግምትና በመላምት አይደለም የሚሠሩት። መረጃዎች፣ ማስረጃዎችና ምስክሮች ወዘተ የሚሉና እንዲሟሉ የሚጠየቁ የሂደት አካላት አሉ። ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተውና እንቁ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ እስከ ግንቦት 20/2012 ድረስ 94 የሚጠጉ መዝገቦች ፖሊስ ጋር ነበሩ። 29 መዝገቦችም ለፍርድ ቤት ቀርበዋል።
በፍርድ ቤት መደበኛ የሴቶችና ሕጻናትን ጉዳይ መታየት የጀመረው ሠኔ አንድ ነው፣ ከዛ በፊት ተረኛ ችሎት በሚል እየቀረቡ ይታዩ እንደነበር እንቁ አንስተዋል። ከሠኔ አንድ በኋላ ታድያ ስምንት መዝገቦች ውሳኔ ሲያገኙ፣ እነዚህም ወንጀሎቹ የተፈጸሙበት ጊዜ በኮቪድ 19 ወቅት ሳይሆን አስቀድሞ የደረሱና የክስ ሂደታቸውም ከወረርሽኙ መከሰት በፊት የተጀመረ ጉዳዮች ናቸው።
የኢፌዴሪ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የሕግ ክፍል ዳይሬክተር ደረጄ ተግይበሉ ከአዲስ ማለዳ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ በወረርሽኙ ምክንያት በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተነሳ የተለየ የተፈጠረ ተጽእኖ የለም። አያይዘው ታድያ ጥንዶችና የትዳር አጋሮች ቤት ውስጥ በመዋላቸው የሚፈጠሩና የተፈጠሩ ግጭቶች ቢኖሩም፣ በብዛት በመደበኛው ጊዜም የሚገጥሙ ችግሮች እንደገጠሙ ነው ያነሱት።

ከመጋቢት ጀምሮ የነበሩትን መዝገቦች በማንሳትም አነጻጽረው ሲያስቀምጡ፣ እንደውም ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከሰተ በተባለበት ሰሞን የተመዘገቡ ጉዳዮች መጠን አነስተኛ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል። ‹‹መረጃዎች ጥቃቶች መቀነሳቸውን እንጂ መጨመራቸውን አያሳዩም።›› በማለት ሲያነሱም፣ ትክክለኛ መረጃዎች ከየት ይገኛሉ የሚለው ላይ ማተኮር የተሻለ እንደሚሆን ሳይጠቅሱ አላለፉም። ‹ይህን ያህል ጥቃት ተፈጽሟል› ለማለትም ቢያንስ ከፖሊስ እየተጣሩ ያሉ፣ የፍርድ ቤት ክስ የተመሠረተባቸው ቢሆኑ የተሻለ ይሆናል ሲሉም ሐሳባቸውን አጋርተዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ጥናቶች አስፈላጊ መሆናቸው ግልጽ ነው። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ጥቃቶች በብዛት እንደተስተዋሉ የተለያዩ አገራት በግልጽ ያሳወቁ ሲሆን፣ በተለይም እርዳታ በመጠየቂያ የ‹ሆትላይን› ነጻ የስልክ መስመሮች የሚደርሱ ጥሪዎች መጨመር ለዚህ መረጃ ትልቅ ግብዓት መሆኑ ይጠቀሳል።

በኢትዮጵያም በአንድ ጎን እንደውም በወረርሽኙ ምክንያት ሰዎች ሰብሰብ በማለታቸው በአንጻሩ በሕጻናትና ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ደግሞ ጭርታን የሚፈልጉ በመሆናቸው፣ ጥቃቱ ቀንሶ ሊሆን ይችላል የሚል መላምት አለ። በተጓዳኝ ግን በር ሲዘጋ፣ በየጓዳው እነዚሁ ጥቃቶች ሊፈጸሙ የማይችሉበት ሁኔታ አይኖርም ብለው ስጋታቸውን የሚገልጹም አሉ። ይህንንም ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማንሳታቸው የሚታወስ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

የደረሰው ጉዳትና የደረሰን መረጃ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሠኔ 30/ 2012 የ2013 ዓመት በጀት በጸደቀበት እለት በቀረቡላቸው ጥያቄዎችና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምላሽና አስተያየታቸውን መስጠታቸው ይታወሳል። በዚህም ወቅት በሕጻናትና ሴቶች ላይ የሚደርሱና የደረሱ የተባሉ ጥቃቶችን፣ እነዚህም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት አገርሽተዋል የሚለውን በሚመለከት ሐሳባቸውን አካፍለዋል።
በንግግራቸው በቀዳሚነት የጠቀሱት በአባታቸው የተደፈሩ ሕጻናት ወንዶችና ሴቶች እንዳሉ የወጡ መረጃዎች፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ መተማመንን የሚሸረሽር እንደሆነ ነው። ‹‹በብዙ መንገድ ማኅበራዊ መስተጋብርን ያበላሻል። መጥፎ ባህል ነው። በሁሉም ኃይሎች መኮነንና መቀየር አለበት። በሃይማኖት ተቋማት፣ በሲቪክ ማኅበራትና በመንግሥት፣ በሁሉም ተቋማት ሊሠራበትና የባህል ለውጥ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው። ብዙ ነገር ያበላሻል። ክስተት ብቻ ሆኖ የሚቀር አይደለም።›› ብለዋልም።

አያይዘው ያነሱት ነጥብም ወዲህ ነው። የቤት ውስጥ ጥቃት በተለይም በሴቶችና በሕጻናት ላይ የሚደርሰው ከኮቪድ 19 መከሰት በኋላ ተባብሷል የሚለውን ጉዳይ፣ ‹‹በእውነት ላይ የተመሠረተ አይደለም።›› ሲሉ ገልጸውታል። ለዚህም ቁጥሮችን አጣቅሰው አስረድተዋል። አክለውም ምንም እንኳ የቀረቡት መረጃዎችም እንከን የለሽ ናቸው ባይባልም፣ መረጃዎችና ማስረጃዎች ከዐቃቤ ሕግ የሚመጡ ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።

ይህ ትክክል መሆኑን ባለሞያዎች ይናገራሉ። ጥቃቶች ወደ መንግሥት የሚደርሱበትና ‹ጥቃት› ተብለው እንዲጠቀሱ የሚያልፉበት ሂደት አለ። በዚህም ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችና ሕጻናት በቅድሚያ ወደ ሆስፒታል መሄዳቸው፣ በዛም የሕክምና አገልግሎት አግኝተው ለሕግ አካላት የደረሰባቸውን ማሳወቃቸው ይቀድማል። ፖሊስም ጉዳዩን ይዞ መረጃዎችንና ምስክሮችን የማሰባሰብ ሥራ ማከናወኑ፣ ይህን ሲያሟላም ጉዳዩ በዐቃቤ ሕግ ምልከታ ወደ ክስ የሚያመራ መሆኑ ተረጋግጦ ወደ ክስ ይገባል።

እንቁ በዚህ ላይ ሐሳባቸውን ሲያካፍሉ፣ መረጃዎች የሚገኙበት ሁኔታና ያሉበት ደረጃ ወሳኝነት እንዳላቸው ያነሳሉ። የአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ይፋ ያደረገውን መረጃ በሚመለከትም፣ ቢሮው ከየትኛው ወቅት ጀምሮ ያለውን መረጃ ይዞ እንደወጣ እርግጠኛ እንዳይደሉ ጠቅሰዋል።
ጊዜ ብቻም ሳይሆን መረጃዎች ሊገኙ የሚችሉበት ስፍራ ወሳኝ ነው። እንቁ እንዳሉት ከሕክምና ማእከላት እነዚህ መረጃዎች የሚገኙ ሲሆን፣ በተለይም ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችም ሆኑ ሕጻናት በዋነኝነት የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚሄዱባቸው የአንድ መስኮት አገልግሎት ሰጪዎች ቀዳሚ ምንጮች ናቸው። በእነዚህ ምኒልክ፣ ጥቁር አንበሳ፣ ጋንዲ እና ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታሎች ይህን አገልግሎት ሲሰጡ፣ ወደእነዚህ ተቋማት ብዙ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ይደርሳል።

ታድያ ሁሉም ጥቃት የደረሰባቸው ሆኖ ላይሆን ይችላል፣ አንዳንዶች አገልግሎቶችን ለማግኘትም ወደእነዚህ ስፍራዎች ‹ጥቃት ደርሶብናል› በሚል ይሄዳሉ። እዚህ ላይ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የሕግ ክፍል ዳይሬክተር ደረጄ እንደጠቀሱት ይህ የሚያጋጥም ጉዳይ ነው። እንዲህ ሲሉም ያስረዳሉ፣
‹‹አንዲት ሴት ተደፍሬአለሁ ብላ ሆስፒታል ከሄደች ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት አለባት። ከጤና አገልግሎት ውስጥ ደግሞ ኤች.አይ.ቪ. እንዲሁም እርግዝንና ከመከላከል አንጻር የሚሰጥ መድኃኒት አለ። በአስገድዶ መድፈር ሳይፈልጉ ከጸነሱም ሕጉ ጽንሱ እንዲቋረጥ ይፈቅዳል። እናም ይህን አገልግሎት ፈልገው መደፈርን እንደ ምክንያት አድርገው ጤና ጣቢያ የሚሄዱ አሉ። ያንን አገልግሎት ካገኙ በኋላም አድራሻ ይቀይራሉ። በፍቃደኝነት የተከናወነ፣ በጓደኝነት የተፈጠረ አንዳንዴም በወሲብ ንግድ ላይ ያሉ ሴቶች ችግር ሲገጥማቸው ይህን ሊያደርጉ ይችላሉ።››
የሕግ ባለሞያው ደረጄ በበኩላቸው በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ዐቃቤ ሕግ በእጁ ላይ ያለውን እንደሚናገርና በትክክልም መጠቀስ ያለበት ያ እንደሆነ አንስተዋል። ‹‹ይህን ጉዳይ ያነሱ የሕግ ባለሞያዎች እነርሱ ጋር የቀረበው መረጃ ዐቃቤ ሕግ ጋር ላይቀርብ ይችላል፣ ዐቃቤ ሕግ ደግሞ ከፖሊስ ነው የሚቀበለው። ምርመራውን በሚመለከት በቂ መረጃ ከማግኘት ጋር በተገናኘ ፖሊስ የሚጥለው ይኖራል።›› ሲሉ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በድምሩም ሁሉም በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ ባለሞያዎች እንደሚሉት፣ ወንጀሉን የሚያሳየውና ይህን ያህል ተብሎ የሚጠቀሰው ፖሊስ ጋር ሄዶ ምርመራ የተጀመረበት ጉዳይ ነው። ሕክምና ማእከልና ፖሊስ ጋር ግን በአንጻሩ ጥርጣሬም ያለው፣ ሙከራም የተደረገበት፣ እንዲሁም ከላይ እንደተጠቀሰው የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ብቻ የሚሄድ ሰው አለ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታድያ ጉዳዩን በሚመለከት ባነሱት ሐሳብ መቋጫ ላይ ‹‹ቁጥር ላይ መጨቃጨቅ ሳይሆን አንድም ሰው ቢሆን መጠቃት የለበትም ብለን በዚህ አቅጣጫ ነው መሠራት ያለበት።›› ብለዋል። ይህም ሲሆን በሴቶችና በሕጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት በአንድ ሰው ብቻ ቢጨምርም ዋጋ አለው ማለትም ነው።

‹እንኳንስ ዘንቦብሽ!…› መረጃ የመሰብሰብ ነገር!
የሕግና ፍትሕን ነገር ከኮሮና ቫይረስ ስጋት አንጻር አነሳን እንጂ፣ ለወትሮውም የሕግ ባለሞያዎች ፈተና ነው ብለው የሚያነሱት ጉዳይ ጥቃት በተለይም ጾታዊ የሆነ ጥቃት ከደረሰ በኋላ ክስ ለመመስረት የሚያስችልን በቂ መረጃ ከማሰባሰብ ጋር የሚገናኝ ነው።
ከላይ እንዳልነው ፖሊስ በቂ መረጃ ያላገኘባቸውን ጉዳዮች ወደ ዐቃቤ ሕግ አያስተላልፍም፣ መረጃ እስኪያገኝ ያቆያቸዋል አልያም ይተዋቸዋል፣ ይዘነጋሉም። ምንም እንኳ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም፣ ይህ መሆኑ በኢትዮጵያ ደርሰዋል ተብለው የተያዙ ጾታዊ የሆኑና በሴቶችና በሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ላይ ተጽእኖ አሳድሮ፣ ያልተሰሙና ያልተነገሩ ታሪኮችም እንደሚኖሩ ለመገመት የሚያስችል ክፍተት ነው።

በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክተር ወሰንየለሽ አድማሱ በአዲስ ማለዳ የ‹አንደበት› አምድ እንግዳ ሆነው በቀረቡ ጊዜ በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳባቸውን አካፍለው ነበር። የተነሳላቸው ጥያቄ አንድም በኮቪድ 19 መከሰት ጋር ተያይዞ የቤት ውስጥ ጥቃትን በሚመለከት ሕግ ምን ያህል ሊያግዝ ይችላል የሚል ሲሆን፣ እርሳቸውም ሲመልሱ አሉ፣
‹‹እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር የቤት ውስጥ ጥቃትን በተመለከተ ሁኔታው ከባድ ነው። ምክንያቱም በሚፈለገው ሰዓት ጥቆማ (ሪፖርት) አይደረግም። ማስረጃ ሳይጠፋ የፍትሕ አካላትና ጤና ተቋማት ምላሽ እንዲሰጡ ማድረግ ያስቸግራል።›› ሲሉ አስረድተዋል።

- ይከተሉን -Social Media

አያይዘውም የቤት ውስጥ ጥቃት አብዛኛው ፈጻሚዎች የቅርብ ሰዎች መሆናቸው ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች እንዳይወጡ ያደርጋል ብለዋል። ያም ብቻ አይደለም ይላሉ፣ ‹‹በጊዜውና በወቅቱ ካልተሰበሰበ በቀር የዲ.ኤን.ኤ ወይም ዘረመል ውጤት ጠፊ ነው፣ የተለያዩ ተፈላጊ ናሙናዎችም በተመሳሳይ ይጠፋሉ። ጥቃት የሚፈጸምባቸው ሴቶች ማቆያ ቦታ ከሌለ አድራሻቸው ይጠፋል። እናም ይህ ተደማምሮ በፍትሕ ምላሽ ለማግኘት ከባድ ያደርገዋል።››
ይህ የአዘቦቱ እውነት ሆኖ ሳለ፣ እንዲህ በወረርሽኝ ሰዓት የበለጠ የሕግና የፍትሕን ምላሽ ማግኘት ከባድ እንደሚሆን ጥርጥር አይኖርም።

በዚህ ላይ እንቁ ዕይታቸውን ሲያክሉ፣ ድርጊቱ አስቀድሞ ሲፈጸም በምስጢር መሆኑን ያስታውሳሉ። ከዛም ደግሞ ‹እንዲህ ሆንኩኝ› ብሎ በግልጽ ለመናገር አሳፋሪ ይሆናል። ‹‹የሚነገረውም ቆይቶና ዘግይቶ ነው። በ72 ሰዓታት ውስጥ መረጃ አደራጅቶ ለመከታተል ክፍተት ይፈጥራል። ከዛም ደግሞ ወደ ፖሊሲ ሲመጡ ያለውን ሂደት አብዛኛው ሰው አያውቀውም።›› ሲሉም ያሉትን ችግሮች ይገልጻሉ።

በቅድሚያ ጉዳዩ ፖሊስ ጋር ቀርቦ፣ መረጃዎች ሲሟሉ ወደ ፍርድ ቤት ያቀናል። ፍርድ ቤትም ቀጠሮ ይሰጥና ጉዳዩን መከታተል ይጀመራል። ይህን ሂደት ሳያውቅ የሚጀምር ሰው፣ ተከሳሽ መከላከያ ማስረጃ የማሰማት መብት እንዳለው ወዘተ የፍርድ ቤት ሂደቱን ካለማወቅ፣ አብዛኛው ሰው አመልክቶች ጉዳዩን ሳይከታተል ያቋርጣል።

‹‹ወዲያው ሪፖርት አለማድረግ አለ። ትክክለኛውን ቦታ አለማወቅም ሰውን እንዲንገላታ ያደርገዋል።›› ሲሉ ተያያዥ ችግሮችንም ጠቅሰዋል። እዚህ ላይ እንደ ምሳሌ ያነሱት፣ በሁሉም ክፍለ ከተማ ላይ ሴቶችና ሕጻናትን የሚያስተናግድ የተለየ ክፍል ቢኖርም፣ ይህን ሰው ስለማያውቅ የተሳሳተ ቦታ በመሄድ ‹‹እዚህ ነው! እዚያ ነው! የምትሄዱት›› በሚል በሚፈጠር መመላለስ፣ ሰው ያሰለቻል።
‹‹በእኛም በኩል አገልግሎቱን ማስተዋወቅ ላይ በደንብ መሥራት አለብን። አሁንም እሱን አቅደን እየሠራን ነው።›› ያሉት እንቁ፣ ቅድሚያ ጥቃት እንዳይፈጸም መከላከል ተገቢ ሥራ ሲሆን፣ ጥቃት ከተከሰተና ከሆነ በኋላ ‹‹በዚህ ቦታ መጥታችሁ አገልግሎት ማግኘት ትችላላችሁ።›› የሚለውን በማሳወቅ እየሠራን ነው ብለዋል። የሚወሰኑ ውሳኔዎችና ቅጣቶችም በተለያየ ምክንያት በበቂ ሁኔታ አናሳውቅም። በዚህም ላይ ማኅበራዊ ሚድያውን ከመጠቀም ጀምሮ እየሠራናቸው ያሉ ሥራዎች አሉ ሲሉም አብራርተዋል።

ፖለቲካ ይቆየን!
እንግዳነሽ ቶላ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው። የአራት ሴት ልጆች እናት ሲሆኑ በየጊዜው የሴቶችንና ሕጻናትን ጉዳይ በሚመለከት የሚወጡ መረጃዎችንና የሚነሱ ጉዳዮችን በንቃት ይከታተላሉ። ‹‹በየጊዜው የምንሰማው ነገር አዳዲስና አሳሳቢ ነው። ስለዚህ በየጊዜው የሚሆነውን መከታተል እንዳለብኝ አምናለሁ። የሴት ልጆች እናት መሆኔም ጭንቀቴን ስለሚጨምረው የሚባለውን አዳምጣለሁ›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

እንደ እንግዳነሽ ዕይታ፣ የሴቶችና ሕጻናትን ጉዳይ የፖለቲከኞች ጨፈቃ ከሆነ፣ በአንድ ጎን ለውጥ ለማምጣት የሚረዳ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ያልሆነው ሆነ፣ የሆነው ደግሞ አልሆነም ብሎ መደበቅን ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አካፍለዋል። እናም የሠለጠነ የፖለቲከኞች ሙግትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ንግግር እስኪኖር ድረስ ጉዳዩ እንደወትሮው ከፖለቲካ አጀንዳነት ባይገባ ሲሉ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችና የሕጻናትን መብት በሚመለከት እንዲሁም እነዚህን ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዴት መጠበቅ እንደሚገባ በሕግና ፖሊሲ አማራጭ ሐሳብ እንዲያቀርቡ አጀንዳቸው ቢያደርጉት ጥሩ ነበር። አሁን ባለንበት የፖለቲካ ግንዛቤ ግን፣ ጭራሽ ማኅበራዊ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል። እነርሱ እርስ በእርስ ሲወራወሩ የሚወራወሩት ሐሳብን ሳይሆን የሰውን፣ የሴቶችና የሕጻናትን ሕይወት ነው።›› ሲሉም ሐሳባቸውን ገልጸዋል።

በሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የሕግ ክፍል ዳይሬክተር ደረጄ በበኩላቸው ጥቃቶችን በተመለከተ ከመከላከል አንጻር ብዙ ይሠራል በማለት ይጀምራሉ። የግንዛቤ ሥራ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ችግሩ ከገጠመ በኋላ ደግሞ ምላሽ ለመስጠት መረጃ የሚገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ብሔራዊ አስተባባሪ አካል አለ ሲሉ ያወሳሉ። በዚህም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ የአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ፣ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሰብሳቢነት በቅንጅት እየሠሩ መሆኑንም አንስተዋል።

- ይከተሉን -Social Media

አክለው እንዲህ አሉ፣ ‹‹የመረጃ አሰጣጥን በሚመለከት ምን ላይ ተመሥርተው ነው? መረጃዎቹስ ትክክለኛ ናቸው ወይ? ማን ነው መረጃ መስጠት ያለበት? ቸግሩ ተባብሷል አልተባባሰም? ወዘተ የሚለውን ለማየት ተሞክሯል። ትክክለኛ መረጃ ከማን ነው የሚሰጠው ከማን ነው ማወቅ ያለበት የሚለውን አይተናል።›› ሲሉም ብሔራዊ አስተባባሪው የደረሰበትን ደረጃ ገልጸዋል።
የሕግ ክፍሉ ዳይሬክተር በንግግራቸው ከዚህ በፊት የሚቀረቡ መረጃዎች ከጤና ተቋም የተወሰዱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በማኅበራዊ ሚድያ እንዲሁም በመደበኛ መገናኛ ብዙኀን ጭምር ሲነገሩ የነበሩት ከትክክለኛ ምንጭ ባለመወሰዳቸው ኅብረተሰቡን የማወዛገብ ሁኔታዎች ውስጥ ገብተዋል በማለት አስረድተዋል።

በተለይም በአባታቸው የተደፈሩ ልጆችን በሚመለከት፣ ከፖሊስ የተገኘ መረጃ እንዳሳየው በአባታቸው የተደፈሩ ኹለት ሕጻናት ሲሆኑ፣ ዘገባዎች ግን በጠቅላላው 101 ሕጻናት፣ ወንዶችና ሴቶች በሙሉ ወይም አብዛኞቹ በአባታቸው እንደተደፈሩ ሆኖ ነው የቀረበው በማለት የነበረውን ክፍተት አስረድተዋል።

ሆኖም ይህንንም መሠረት ያደረገ ማኅበራዊ ቀውስ የሚፈጥርና በእነዚህ በተጠቀሱ ጥቃቶች ላይ መሠረት ያደረገ ቅስቀሳ በተለያዩ ስፍራ ታይቷል። ደረጄ ተግይበሉ እንዳሉት፣ ፊልሞችም ሳይቀር ተሠርተው ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቀርበዋል። እነዚህም ሌላ ዓይነት መልዕክት ያላቸው፣ አገር በሕግ የተመራች አይደለችም የሚል ዓይነት ሐሳብ ይዘው ቅስቀሳ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል። ‹‹ያ የራሱ የፖለቲካ ፍላጎት ያለው ነው። ተልዕኮ ያላቸው አካላት ጭምር ያከናወኑት ነው የሚል ግምትም ተወስዷል።›› ሲሉም ጠቅሰዋል።

የሴቶችንና የሕጻናትን ጉዳይ ዞር ብሎ ማየት፣ የፖለቲካ አጀንዳ ማድረግ አልያም ቢያንስ ለመብታቸው ለመከራከርና የተለያየ ሐሳብ አቅርቦ ለመሟገት ገዣ ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ የተባሉ ጠንካራ አቋም አሳይተው አያውቁም። በአንጻሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የታዩ መልካም ለውጦች የሴቶችን ጉዳይ የተሻለ ትኩረት እንዲያገኙ አድርገዋል ማለት ይቻላል።

ይህም የሕጻናትን የዛን ያህል ያስተዋለ አይደለም። ጉዳዩ ለምን የፖለቲካ መልክ ያዘ ብሎ መጠየቅ የዋህነት ሊሆን ይችላል፤ ፖለቲካ የሌለበት የለምና። ነገር ግን እንደ ሌላው የፖለቲካ ጉዳይ አንዱ ሌላውን የሚከስበት፣ ሌላው ለመሸፈን የሚጥርበት ጉዳይ እንዳይሆን፣ ከወዲሁ ጥንቃቄ ይፈልጋል፣ እንግዳነሽን ጨምሮ በጉዳዩ አስተያየት የሰጡ ባለሞያዎች የተናገሩት ሐሳብ ነው።

ምን ይደረግ?
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የቤት ውስጥ ጥቃትን፣ በተለይም ሴቶችና ሕጻናት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ሊያባብስ እንደሚችል የዓለም መገናኛ ብዙኀን ሁሉ ከሚመለከታቸው አካላት ያገኙትን ሐሳብ ወስደው ስጋቱን ለሕዝብ ሲያጋሩ ነበር። ያኔም ‹ምን ይደረግ?› የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ ሲነሳ ተሰምቷል። ወሰንየለሽም ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ስለወረርሽኝ በወጣው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰሞን ለሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 35 ማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያዎች ጋር ሊቀመጥ ይገባል ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለው ነበር።
ፍርድ ቤቶች በተዘጉበት ወቅትም የሴቶችና ሕጻናትን ጉዳይ የሚመለከት ልዩ ክፍል ሥራውን ማቆም እንደሌለበት ጠቅሰዋል። ጉዳዩን እንዲያ ብለው በድፍረት ያነሱትም፣ እንደሌሎች ገዳዮች ማስረጃ አቆይቶ፣ ወርና ኹለት ወር ምስክር አሰማለሁ የሚባልበት ጉዳይ ስላልሆነ ነው ብለዋል። ‹‹በመደበኛው የክርክር ሂደት እንኳ በጣም ማስረጃ ከሚባክንባቸውና እጅግ ከሚቆጩኝ የወንጀል ዓይነቶች አንደኛው ነው።›› ሲሉም ነው ያነሱት።

ፖሊስ ምርመራ ሥራውን እስካላቆመና 24 ሰዓታት እስከሠራ ድረስ፣ አሁን በሴቶችና ሕጻናት ጉዳዮ ዙሪያ ከሠኔ አንድ ጀምሮ ችሎቶች አገልግሎት መስጠታቸውም ተገቢ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።

ወሰንየለሽ እንዲህ አሉ፣ ‹‹አንዳንዱ ነገር እንዲህ ሲከሰት ከጾታ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን፣ ቀድመን እያነሳን ማሰብ ያስፈልጋል። ለዛ የሚሆን አሠራር ከስር ከስር እያመቻቸን የምንሄድ ካልሆነ፣ እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ሴቶችና ሕጻናት ግንባር ቀደም ተጎጂ መሆናቸው አይቀርም።›› ሲሉ ሐሳባቸውን ከወዲሁ አካፍለዋል።

የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ታድያ በኢትዮጵያ የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ በተለይም ከሕግና ፍትሕ ጋር በተገናኘ ምን አዲስ አቅጣጫ ያሳይ ይሆን ስትል አዲስ ማለዳ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕግ ክፍል ኃላፊ ደረጄ ጥያቄዋን አቅርባለች። እርሳቸውም መሥሪያ ቤቱ ይህን በሚመለከት ዓለማቀፍ ተሞክሮዎችንና የተደረጉ ጥናቶችን በመቃኘት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በተለይም በተለያዩ ክልሎች ያለእድሜ ጋብቻ እንዲሁም ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች በኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት የመጀመሪያ ሰሞን ሲከወኑ እንደነበርና ከወትሮውም በመጨመር መጠን ታይተዋል ብለዋል። በተወሰኑ ክልሎች ይህ ሲስተዋል፣ የቀረቡ ሪፖርቶችም እንዳሉ ነው ደረጄ ያወሱት።

መልእክታቸውን ሲያስተላልፉም ‹‹በተለይ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች መልዕክት ሲያስተላልፉ ጥንቃቄ ቢደረግ መልካም ነው። ሐሳባቸው በበጎ ቢሆንም የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያስከትል ስለሚችል ከሚመለከታቸው ጋር በቅንጅት ቢሠሩ። አሁን የጀመሯቸው ተጎጂዎችን የመደገፍ ሥራንም በዛው ቀጥለው ቢሠሩበት የተሻለ ይሆናል።›› ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች