የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ አባል በቁጥጥር ስር ዋሉ

0
521

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና በፓርቲው ውስጥ የሙያ ማኅበራት ተጠሪ ሒሩት ክፍሌ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታወቀ።
የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ፖሊስ ሰኔ 23/2012 በአዲስ አበባ ከተማ ተፈጥሮ የነበረውን ረብሻ እና ኹከት ሰዎችን በማደራጀት የንብረት ውድመት እንዲደርስ አድርገዋል በሚል ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው አስረድተዋል።

ናትናኤል አያይዘውም ሐምሌ 7/2012 ከረፋዱ 5 ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ባለው ጊዜ አዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ አስረድተዋል።

ሐምሌ 7/2012 በቁጥጥር ስር የዋሉት ሒሩት ክፍሌ፣ ሐምሌ 9/2012 ፍርድ ቤት መቅረባቸው ታውቋል። ሐምሌ 9/2012 በዋለው ችሎትም ፖሊስ 14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት ለፍርድ ቤት ያቀረበ ቢሆንም፣ ዐስር ቀናት ከፍርድ ቤቱ እንደተፈቀደላቸውም አዲስ ማለዳ ከፓርቲው ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ሐምሌ 7/2012 ተጠርጣሪዋ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት መኖሪያ ቤታቸው የተፈተሸ ሲሆን፣ በዚህም ሒደት ንብረትነቱ የተጠርጣሪዋ የሆኑ ሦስት ተንቀሳቃሽ የዕጅ ስልኮችን እና የተጠርጣሪዋ ልጅ ከሚሠራበት መሥሪያ ቤት የተሰጠው እና የሚገለገልበት ላፕቶፕ ኮምፕዩተር መወሰዱን ለማወቅ ተችሏል።

የተወሰዱት ዕቃዎች መኖራቸው እውን ሆኖ በዚሁ ጋር ተያይዞ ግን የፓርቲው ንብረት የሆኑ እና በተጠርጣሪዋ መኖሪያ ቤት ይገኙ የነበሩ ዕቃዎች አለመነካታቸውንም ፓርቲው ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ቀን አንስቶ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት የተከለከሉ ሲሆን፣ በተለይም ደግሞ ቤተሰብ ቅያሪ ልብስ ለማድረስ ተጠርጣሪዋ በቁጥጥር ስር በሚገኙበት አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቅጥር ጊቢ ውስጥ በሚሔዱበት ወቅት ኮቪድ 19 ወረርሽን ምክንያት በማድረግ ግንኙነት እንደተከለከሉ እና ከፓርቲው ጠበቃ ጋር ብቻ መገናኘታቸው አዲስ ማለዳ ከኢዜማ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ይሁን እንጂ ተጠርጣሪዋ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ቤተሰብ እንዳያገኛቸው ከመደረጋቸው ጋር ተያይዞ ልብስ ሳይቀይሩ ሐምሌ 7/2012 በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት ያደረጉትን ልብስ አድርገው እንደሚገኙ እና የኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ የወጣው ዕገዳ ግን በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ ሲተገበር አለመታየቱ እንዲሁም ልብስ ከቤተሰብ ሲገባላቸው መመልከታቸውንም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ከድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ ቁጥራቸው የበዛ ሰዎች ወደ አደባባይ በመውጣት ቁጣቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በተለይም ደግሞ ከተከሰተው አለመረጋጋት እና ሁከት ጋር ተያይዞ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ውድመት በንብረት ላይ ተከስቶ ማለፉም የሚታወስ ነው።

ከተከሰተው ኹከት እና የንብረት ውድመት እንዲሁም የሰው ሕይወት መጥፋት ጋር በተያያዘም ፖሊስ እጃቸው አለበት ብሎ የጠረጠራቸውን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንም በቁጥጥር ስር አውሏል።

በዚህም ረገድ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ከፍተኛ አመራር የሆኑት በቀለ ገርባ እና ቀደም ሲል አክቲቪስት በኋላም የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስን የተቀላቀለው ጃዋር መሐመድ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ ባላደራ ፓርቲ ባልደራስ ሊቀመንበር የሆነው እስክንድር ነጋ እና የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ስንታየሁ ቸኮል በቁጥጥር ስር ከዋሉት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በተመሳሳይም የኢትዮጵያውያን አገር ዐቀፍ ንቅናቄ ፓርቲ ሊመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነትም በሰኔ 23/2012 በአዲስ አበባ ከተማ በተከሰተው የሰው ሕይወት መጥፋት እና ንብረት መውደም ተጠርጥረው መታሰራቸውንም አዲስ ማለዳ በቀዳሚ ዕትሟ ማስነበቧ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here