የታሪካችን እጥፋት፡ የሕዳሴ ግድብ ሙሊት

0
442

ከመጋቢት ጀምሮ በኮሮና ወረርሽኝ አገራዊ ስጋት እና ከሰኔ 20ዎቹ ወዲህ ደግሞ በኹከት እና ብጥብጥ ስጥናት የከረመችው ኢትዮጵያ፣ አገራዊ ድብታ ውስጥ ከርማለች። የሕዳሴው ግድብም ድርድር ያዝ ለቀቅ እያለ ቢካሔድም ኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እየጨመረ መጥቷል፤ ዓለም ዐቀፍ ትኩረትም ስቧል።
እንግዲህ በዚህ ሁሉ መካከል ነው በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዓመት ሙሊት 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በመያዝ ሐምሌ 12/2012 በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቀ መሆኑን መንግሥት በይፋ ያስታወቀው። ይህም በጨፍጋጋው ክረምት በድብታ ውስጥ ለነበረው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ደስታ ፈንቅሎት እንዲወጣ፣ እንደመርግ የተጣበቀበትን ድብታም አላቆ እንዲወጣ ሰበብ ሆኖታል። አገራዊ አንድነትም በስፋት ተንጸባርቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በእንኳን ደስ አለን መልዕክታቸው ‘‘እኛ ኢትዮጵያውያን ዳግም ሀገር ተኮር ሥራ ሠርቶ እንዴት ማሳካት እንደሚቻል አውቀናል፤ ሠርቶ አንድ ምዕራፍ ላይ መድረስ የሚያስገኘውን ደስታ በድጋሚ ማጣጣም ጀምረናል። ይበልጥ የሚያስደስተው ማንም ባልተማመነብን ወቅት በራሳችን አቅም ላይ እምነት ኖሮን ማሳካት መቻላችን ነው’’ ብለዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው በትዊተር ገፃቸው ‘‘የድል ብስራት!” በሚል የብዙዎችን ቀልብ የሳበ የእንኳን ደስ አለን መልዕክታቸውን አስፍረዋል። ‘‘ዐባይ ወንዝ ነበር ተገርቶ ወንዝም ሀይቅም ሆነ። ከእንግዲህ በወንዝነቱ ይፈሳል። ሀይቅነቱ ኢትዮጵያ ለፈለገችው ልማት ሁሉ ለማዋል እጅ ሰጥቷል። እውነትም ዐባይ የኛ ሆነ።”

በመደበኛውም ይሁን በማኅበራዊ ትስስር መነጋገሪያ ርዕስ ዐባይ፣ ሕዳሴ ግድብ ሆኗል። አንድ የፌስቡክ ተጠቃሚ ‘‘The Power of ዐባይ የሞባይል ዳታ እስከማስለቀቅ’’ ሲል በስላቅ ደስታውን ገልጿል። ብዙዎች ከውጥኑ አሁን እስከ ተደረሰበት ደረጃ ላበረከቱ ላሏቸው መሪዎች እና ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል፤ እውቅናም ሰጥተዋል። ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ በመወጠንና በማስጠናት፣ ኮለኔል መንግሥቱን ለዘላቂ ልማት ጭምር አርባ ምንጭ የውሃ ኢንጅነሪንግ ኮሌጅን በማስገንባት፣ መለስ ዜናዊን የግድቡን ግንባታ በቁርጠኝነት በማስጀመር፣ ኀይለማሪያም ደሳለኝን የግድቡን ግንባታ በማስቀጠል፣ ዐቢይ አሕመድን ግንባታውን በማፋጠን እና አሁን ያለበት ደረጃ በማድረስ፣ ገዱን እና ኢንጅነር ስለሺ በቀለን በተደራደሪነታቸው እንዲሁም ኢንጅነር ስመኘውን በፕሮጀክቱ መሪነታቸው የምስጋናው ተጠቃሽ ተጋሪዎች ሆነዋል።

የግድቡን የውሃ ሙሌት ሒደት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት በይፋ አያረጋጋጥ ወይም አያስተባብል እንጂ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኀን የሳተላይት ምስል በማስደገፍ ዘገባዎችን መሥራት ከጀመሩ ሳምንት አልፏቸዋል።

የውሃ ሙሌቱ መሳካት በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጠረው ደስታና ፈንጠዝያና በግብፃውያን በኩል በተቃራኒው ድንጋጤንና ውዥምብር ፈጥሯል። አንዳንዶች እንዲያውም የጦርነት ነጋሪት እስከመጎሰም አድርሷቸዋል። በቴሌኮም፣ በመገናኛ ብዙኀን እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የተሰማሩ ግብፃዊው ቢሊየነር ናጊቡ ስዋሬስ ከ‘ዘ አፍሪካን አፍሪካን ሪፖርት’ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ ጦርነት እመርጣለው ሲሉ ተደምጠዋ።

ወጣም ወረደ የሕዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌትን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከግብፅ እና ሱዳን ጋር የምታካሒደው የሦስትዮሽ ድርድር እንደከዚህ ቀደሙ በተመሰሳይ መልክ (status quo) እንደማይቀጥል ብዙዎች በርግጠኝነት ይናገራሉ።

በቅርቡ ከአራት እና አምስት ወራት በኋላ ግድቡ ኹለት ተርባይኖች ኀይል የማመንጨት ሥራ የሚጀምሩ ሲሆን በኹለት ዓመት ውስጥም የግድቡ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ የተፈለገው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል። በመሆኑም ለብዙዎች ኢትዮጵያ አሁን የምትገኘው በወሳኝ የታሪክ እጥፋት ላይ መሆኑን አበክረው ይናገራሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here