የማንነት ፖለቲካ ያገበረው ፕሬስ በኢትዮጵያ

0
717

መገናኛ ብዙኀን በኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካ በፈጠረው ውስብስብ ማኅበረ-ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የማንነት ፖለቲካ ልክፍት ውስጥ ለምን ገቡ ሲሉ የሚጠይቁት ፍቃዱ ዓለሙ፣ ይህን መሠረት በማድረግ የመገናኛ ብዙኀን ባለቤቶች ሐሳብና ፍላጎት እንዴት በመገናኛ ብዙኀን እንደሚንጸባረቅ አንስተዋል። እንዴት መስተካከል ይችላል የሚለውም ላይ የመፍትሔ ሐሳብን አቅርበዋል።

መግቢያ
የአንድን አገር የፖለቲካ አስተዳደር ሥርዓት በአዎንታዊና በአሉታዊ ገልጠው የሚያሳዩን መገናኛ ብዙኀን ናቸው። ይህ ማለት ጤናማ የፖለቲካ ሥርዓት ባለበት አገር፤ ጤናማ የመገናኛ ብዙኀን ተቋማት ይፈጠራሉ። እጅግ ውስብስብ የፖለቲካ ሥርዓት በሰፈነበት አገር ደግሞ የመገናኛ ብዙኀኑ እጣ ፈንታ ረብ የለሽ ይሆናል።

ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የዘር ፖለቲካ ቀውስ ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት፣ መፈናቀል፣ ረሀብና ሞት ማቆሚያ የሌላቸው ክስተቶች ሆነው ቀጥለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ሥነ ምህዳሩና የመገናኛ ብዙኀን አካሄድ ጎታች እንጅ ተራማጅ መሆን አልቻሉም። ከአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት በኋላ የተፈጠሩ ኹነቶች ብሔር የወለዳቸው ግጭት ቀስቃሽ አጀንዳዎችን ሲያራምዱ በነበሩ መገናኛ ብዙኀን ጭምር ነው።

የሀጫሉን ሞት ተከትሎ የተፈጠረው ኹነት አንደኛው የሚያሳየን ጠርዝ ባለፉት ኹለት ዓመታት አዲስ የተመዘገቡና አልፎ አልፎ ነባር የምንላቸው መገናኛ ብዙኀን ውስጥ ዘልቆ የገባው የማንነት ፖለቲካ ነው። በፖለቲካው እንዳለመታደላችን ሁሉ መገናኛ ብዙኀኑም ችግርን ፈጠሪ እንጅ ቁስል አባሽ መሆን አልቻሉም።
ለዛሬ በኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካ በፈጠረው ውስብስብ ማኅበረ-ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መገናኛ ብዙኀን የማንነት ፖለቲካ ልክፍት (Identity politics) ቀውስ ውስጥ ለምን ገቡ የሚሉ ሐሳቦችን እናነሳለን። ልክ እንደ ፖለቲካው ሁሉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ለውጥ አይገመቴ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ በኢትዮጵያ ውስጥ ስር የሰደደ የማንነት ፖለቲካ ነው።

ወቅታዊ የመገናኛ ብዙኀን ሁኔታ
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ዓመታት በታየው አንጻራዊ ለውጥ (ሪፎርም) ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል መገናኛ ብዙኀን ተጠቃሽ ናቸው። የፕሬስ ነጻነት ዓይነተኛ መሻሻሎች አሳይቷል። በጋዜጠኝነት ሙያቸው ታስረው የነበሩ ተፈትተዋል፣ የአገልግሎት ሥርጭታቸውን በውጩ ዓለም አድርገው የነበሩ ልዩ ልዩ የዲያስፖራ መገናኛ ብዙኀን ኢትዮጵያ ገብተው አማራጭ ያሉትን ሐሳብ በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ በመንግሥት ጥሪ መሠረት ብዙዎች አገር ቤት እንዲገቡ መደረጉ ይታወሳል።
ይህን የሰላም አማራጭና የሐሳብ ሙግት ግን በአግባቡ አልተጠቀሙበትም። በተጨማሪም አንድ ወቅት ብልጭ ብሎ የጠፋው የሙያ ነጻነት (professional independency) የለውጡ አካል ነበር። በነበር ባይቀር ኖሮ ማለት ነው።

የሆነ ሆኖ በአንድ ወቅት ብቻ የታየውን የፕሬስ ነጻነት እንዲቀጥል መንግሥትን ጨምሮ የትኛውም የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎችና የሚዲያ አመራሮች የተለየ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አልታየም። በእርግጥ እንደ አገር ከኹለት ዐሥርት ዓመታት በላይ የተፈጠረውን ውስብስብ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መስመር ለማስያዝ መንግሥት በሚያደረገው ሂደት እዛም እዚህም የተፈጠሩ ትልልቅ ኹነቶች ጊዜ አልሰጠው ይሆናል።

ይባስ ብሎ የማንነት ፖለቲካ እያራመዱ በተመሳሳይ የመገናኛ ብዙኀን ባለቤት የሆኑ ግለሰቦችና አመራሮች አገር ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብታ ሳለ፣ የራሳቸውንና የጥቂት ቡድኖችን ጥቅም በማስቀደም አገር የበለጠ እንድትተራመስ ዋና ተዋናይ ነበሩ። ይሄ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው።
ሌላው በክልል አስተዳደር ስር ያሉ የክልል መገናኛ ብዙኀን አንዲሁም አንዳንዴ የመንግሥት አቀንቃኝ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቆሜለታለሁ ለሚሉት ብሔር የጥላቻ አጀንዳዎችን በማቀበል ተጠምደው የነበሩ የፕሬስ ውጤቶች ዋና ዓላማቸው ተመሳሳይ ነበር። መገናኛ ብዙኅንን የሚመራው የብሮድካስት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በበኩሉ አልፎ አልፎ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ከመጻፍ የዘለለ ጠንከር ያለ እርምጃ ሲወስድ አልነበረም። የአርቲስት ሀጫሉን ሞት ተከትሎ የወሰደው እርምጃ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።

በማንነት የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ውስጥ
የወቅቱ የኢትዮጵያ አስቸጋሪና ፈታኝ በሽታ የሆነው የጥላቻ ትርክትን መሠረት ያደረገ የማንነት ፖለቲካ ርእዮተ ዓለም መገናኛ ብዙኀኑን የዚሁ በሽታ ተጠቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ቀደም ሲል ዋልታ ረገጥ ተብሎ የሚታማው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ውስጥ (politically polarized media) ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ አንዳንድ መገናኛ ብዙኀንና ጋዜጠኞች ጭልጥ ብለው ወደ ማንነት ፖለቲካ ውስጥ ገብተዋል።

እነዚህ የሚዲያ ባለቤቶችና ጋዜጠኞች ዋና ሥራቸው በልዩነት ላይ የተመሠረተ የማንነት ፖለቲካ ርእዮተ ዓለም አጀንዳ እየፈጠሩ በአገሪቱ የተወሳሰበውን የማኅበረ-ፖለቲካ ችግር የበለጠ እንዲወጠር ማድረግ ነበር። እንዲያውም የማንነት ፖለቲካ አራማጅ የሆኑት እነዚህ ግለሰቦች በሚመሩት ሚዲያ ራሳቸው አጀንዳ አምጭና በመረጡት ርእሰ ጉዳዩ ላይ ብቸኛ ተንታኝ በመሆን የፈለጉትን ዓላማ ሲያስፈጽሙ ቆይተዋል።

መገናኛ ብዙኀን ችግሮችን በማጋለጥ የመፍትሄ አካል መሆን ሲገባቸው ችግር ፈጣሪ ሆነው ታይተዋል። በተለይ ያለፈው አንድ ዓመት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮች ባልሆነ መንገድ አጀንዳ እየተቀረጸላቸው ሕዝብን ከሕዝብ ሲያጋጩ፣ በየጊዜው ያልተገባ ዝግጅት ሲያስተላልፉ…..ዝም ተብለው ታይተዋል።

እዚች አገር ውስጥ ስንቱ በእርስ በርስ ግጭት፣ በጎርፍና በረሃብ እንደተፈናቀለ እየታወቀ አንድም ቀን እነዚህ ወገኖቻቸው ጉዳይ አሳስቧቸው የሚዲያ ሽፋን ሲሰጡ አልታየም። ከአገራዊ አንድነት ይልቅ….አሀዳዊ ሥርዓት፣ ከሚያግባቡን አጀንዳዎች ይልቅ በሚያነታርኩን ላይ ሆን ብሎ አጀንዳ መፍጠር፣ ሕዝቢ ሠርቶ የሚለወጥበትን ርእሰ ጉዳይ ትተው….ሥራ ፈት ሆኖ በሆነው ባልሆነው እንቶ ፈንቶ ጊዜውን እንዲያጠፋ ሲያደርጉት ነበር።

በማንነት የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም የተቃኙ መገናኛ ብዙኀን ሕግ እንዲከበር ሳይሆን ሥርዓት እንዳይሠፍን ይሠራሉ፣ ሰላም ሳይሆን ብጥብጥ እንዲነሳ አጀንዳ ይቀርጻሉ። ከዚህም በላይ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንዲነሳ በቀጥታ ሥርጭት አደገኛ የሆኑ አጀንዳዎችን ሲያስተላልፉ ምንም ቅር አይላቸውም። በተለይ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኀን የሌላ አገር ተቃዋሚ በሚመስል አኳኋን በገዛ አገራቸውና በገዛ ወገናቸው ላይ ያልሆነ አጀንዳ በመቅረጽ እርስ በእርስ ለማጋጨት ሲጥሩ እየታየ በምን መሥፈሪያ የሕዝብ ሚዲያ ተብለው ሊጠሩ እንደሚችሉ ይከብዳል። ጠላት እንኳ በሁሉም ነገር አይቃወምም። እነሱ ግን አንድም በጎ የሆነ ነገር ከስቱዲዮዋቸው ሲስተጋባ አልታየም።

በተጨማሪም በልዩነቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት፣ በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ላይ የተቃርኖ አጀንዳዎችን ማዘጋጀት፣ ጣቢያው ለቆመለት አካባቢ ብቻ ተቆርቋሪ መስሎ ያልሆነውን እንደሆነ አድርጎ መዘገብ፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሰብሳቢ በራሱ ጣቢያ በፈለገው ሰዓት ብቅ እያለ መግለጫ ሰጪ መሆን እና የመሳሰሉት አደገኛ አካሄዶች የአገሪቱን ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የሚዲያውን እድገት በአንድም በሌላም መንገድ እያቀጨጨ ለመሆኑ ማሳያዎች ናቸው።

መፍትሔ
የአንድ ሚዲያ ዋና እና መሠረታዊ ዓላማ ለሚወክለው አካባቢ ወይም ማኅበረሰብ እውነተኛ፣ ጠቃሚና አስፈላጊ መረጃዎችን በማቀበል ኅብረተሰቡ በማኀበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊና ወሳኝ አካል እንዲሆን ማስቻል ነው። ከዚህ በተቃራኒው በማንነት ርእዮተ ዓለም ቀውስ ውስጥ የመገናኛ ብዙኀን እድገትና ስፋት እየቀጨጬ ይሄዳል። ጠንካራ ሚዲያ የመፈጠር እድሉም በጣም ጠባብ ይሆናል።

መገናኛ ብዙኀን ገለልተኛ ባይሆኑ ነጻ መሆን አለባቸው። ነጻ መገናኛ ብዙኀን ቢያንስ ወቅታዊና ሚዛናዊ መረጃዎችን ለሕዝቡ ቶሎ ያደርሳሉ። ነጻ መገናኛ ብዙኀን በግልጽ የሚታዩ ችግሮችን ያለ ፍርሃት መተቸት ይችላሉ። ነጻ መገናኛ ብዙኀን በአገሪቱ እየታየ ስላለው የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ብልሹ አሠራር፣ እንዲሁም አገሪቱን በሙስና ስላነቀዟት ፖለቲከኞችና ግለሰቦች ቀደም ብሎ ፈልፍሎ በማውጣት ያጋልጣሉ።
ሆኖም እንዲህ ዓይነት መገናኛ ብዙኀን አገሪቱ ውስጥ እንዲኖር መመኘት ብቻ ነው ትርፉ። በመገናኛ ብዙኀን በኩል ቢሠራ ኖሮ መንግሥት አሁን ከገባበት ፈተና ለጊዜውም ቢሆን ማገገም ይችል ነበር።

‹የጥገኝት ሚዲያ ንድፈ ሐሳብ› (theory of media dependency) መሠረት ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በተፈጠረባቸው አገራት ከችግሩ ስፋት አንጻር ወደ ሽግግር ለማምራት በሚያደርጉት ሂደት ወቅት በየቦታው የሚሰሙ አሉባልታዎችን ለማጣራት እና እውነተኛ መረጃ ለማግኘት ሲሉ ዜጎች ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ መገናኛ ብዙኀን ያደርጋሉ ይላል። (the theory of media dependency posits that, as turmoil and periods of transitions exist, citizens are more likely to turn to the media as a source of reassurance and information, Loveless, 2008)

ይህ ማለት ዋናዎቹ የሕዝብ መገናኛ ብዙኀን ሪፎርም ውስጥ ባለች አገር ትኩረት አድርገው የሚሠሩት በአገሪቱ እሴቶች ላይ ስላለው አንድነት፣ መቻቻል እና ሰላም ይሆናል። በተጨማሪም ዴሞክራታይዜሽን ላይ፣ ወሳኝ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ ትልልቅ ውይይቶችን እያደረጉ ሕዝቡ እንዲሳተፍበትና እንዲወያይበት ያደርጋሉ።
አልፎ አልፎ በሚታዩ አመለካከቶች ላይ በመሥራት በሕዝቦች ዘንድ መግባባት እንዲፈጠር አጥብቀው ይሠራሉ። (The literature on political socialization in countries transitioning to democracy has focused on changes in individuals’ values, attitudes, and behaviors that emerge from their social locations (socio-economic status, Lipset, 1959)

በአጠቃለይ በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከመገናኛ ብዙኀን ጋር በተገናኛ የፓርላማ አባላት ላነሱላቸው ጥያቄዎች ‹‹የመንግሥትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙኀን ችግሩ ሚዲያው ውስጥ ያለው የሰው ኃይል በአቅምና በአፈጻጸም ደካማ መሆን ነው።›› ማለታቸው ይታወሳል።
ስለዚህ የመገናኛ ብዙኀን የሪፎርም ሥራ ‹በአመለካከት፣ በክህሎት፣ በአደረጃት፣ በአሠራር …የማስፈጸም አቅማቸውን› መሠረት ያደረገ መሆን እንዳለበት ሁሉም በየዘርፉ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል። በሌላ በኩል የተጀመረው የሚዲያ ፖሊሲ በፍጥነት ተጠናቆ የመገናኛ ብዙኀኑን አሠራር፣ አደራጃጀትና ለውጥ በተመለከተ ሰፋፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች መፍጠር አስፈላጊ ነው።
ፍቃዱ ዓለሙ ጋዜጠኛና የኮምዩኒኬሽንስ አማካሪ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው esmbefe@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here